Saturday, April 15, 2017

ትንሣኤን ስናከብር ልናስተውለው የሚገባን አቢይ ጉዳይ . . .


በዓለ ትንሣኤ በክርስትና ሕይወት ውስጥ ታላቅ ክብርና ግምት ከሚሰጣቸው በዓላት መካከል አንዱ ነው፡፡ የጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ በመንግሥተ ሠማያት በእግዚአብሔር ሐሳብ ከተሠራልን እረፍት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ የጌታችን ትንሣኤ ለእረፍታችን መነሻና ጅማሬ ስለሆነ የሚመጣውንና በሠማያት ተስፋ የምናደርገውን እረፍት የምንረዳበትና ለዚህም እረፍት በመንፈስ የምንዘጋጅበት ነው፡፡
በሰማያት ተሠርቶልናል የምንለው እረፍት ያለድካምና ያለመሞት በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ለዘለዓለም በሕይወት መኖራችንን ነው፡፡ አምላካችን አስቀድሞ ወደ ሠራልን እረፍት እንዳንደርስና እንዳንገባ ጠላት ዲያብሎስ ለሔዋን በመከራት ክፉ ምክር ወደ እረፍታችን የምንደርስበት መንገድ በሞት ተቋርጦ ነበር፡፡ ወደ እረፍታችን እንደርስ ዘንድ ደግሞ የሞት መሸነፍና መወገድ ግድ ሆነ፡፡ ሞት ከአዳም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ ሥጋዌ/መገለጥ ድረስ ሰዎችን ሁሉ ሥጋቸውን ወደ መቃብር፣ ነፍሳቸውን ደግሞ ወደ ሲኦል በማውረድ አስቀድሞ በአምላካችን ወደ ታሰበልንና ወደ ተሠራልን የመንግስቱ እረፍት እንዳንገባ እንቅፋት ሆኖ ቆየ፡፡ ሞት እያለ ወደ እረፍታችን መካን ልንደርስ ስለማንችል ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ተገልጦና በሥጋው የእኛን ሞት ሞቶ ብዙዎችን ሲያሸንፍ የነበረውን አሸናፊ በማሸነፍ በታላቅ ኃይልና ሥልጣን ከሞት በክብር ትንሣኤ ተነሳ፡፡ ከጌታችን ትንሣኤ በኋላ በክርስቶስ ትንሣኤ የምናምን ምእመናን የትንሣኤያችን በኩር በሆነው በጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥራና በማዳኑ በኩል ለእረፍታችን ወደ ሠራልን መንግስቱ መግባት ቻልን፡፡ በዚህም የተነሳ ክርስትናችን በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ላይ የተመሠረተ ሆነ፡፡ ሞቱ የኀጢአት ሥርየት አግኝተን ከእግዚአብሔር ጋር የታረቅንበት እንደሆነ ሁሉ፤ ትንሣኤውም ደግሞ እምነታችንና ተስፋችን ፍጹም እውነት መሆኑን የምንመሰክርበትና ወደ ዘለዓለም እረፍታችን የምንደርስበት መንገዳችን ሆኗል፡፡ ክርስቶስ የሙታን ሁሉ በኩር መባሉ ከእርሱ በፊት ሞትን አሸንፎ በገዛ ሥልጣኑ የተነሣ ስለሌለና በእግዚአብሔር ተአምራት የተነሡትም ሁሉ እንደገና ተመልሰው ወደ መቃብር  ስለወረዱ ብቻ ሳይሆን ከክርስቶስ መነሳት በኋላ በክርስቶስ የሚያምኑ ሁሉ የክርስቶስ ትንሣኤ ተካፋዮች ስለሚሆኑና ከእርሱ የተነሳ ከሞት የሚነሱ በመሆናቸውም ጭምር ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን የክርስቶስን ትንሣኤ በዓል የምታከብረው በታላቅ ጥንቃቄና በጥልቅ መንፈሳዊነት ውስጥ ሆና ነው፡፡ በጌታችን መከራና በማዳኑ ኃይል ያገኘነው ትንሳኤያችን በእግዚአብሔር ሐሳብ የተሠራ፣ በመንፈስ የምንረዳውና የምንደርስበት ታላቅ ምንፈሳዊነት ነው፡፡ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ተብሎ እንደተጻፈ በክርስትናችን ውስጥ የምንፈጽመው ማናቸውም ተግባር በእውነትና በመንፈስ የሚፈጸም ሊሆን ያስፈልጋል፡፡ ዮሐ 4፣24፡፡ ህልፈት የማይስማማው የዘለዓለም እረፍታችን መነሻው የክርስቶስ ትንሣኤ እንደመሆኑ መጠን ከሞት በኋላ የምንገባበት ዘለዓለማዊ እረፍታችንን በምድር ላይ በሕይወተ ሥጋ ሳለን እንድንረዳው፣እንድንናፍቀውና እንድንለማመደው፣ ለእርሱም የተገባን ሆነን በመንፈስ እንድንዘጋጅ በሰሙነ ትንሣኤ የምንፈጽማቸው የቤተ ክርስቲያናችን ሥርዐቶች ተሠርተውልናል፡፡ 
ከትንሣኤው በፊት ባሉት ሃምሳ አምስት ቀናት ውስጥ በጾም መቆየታችን በመንፈሳዊ ሐሳብ ውስጥ ሆነን ዘለዓለማዊውን እረፍት እንድናስብ ያደርገናል፤ ከዘወረደ እስከ ሆሣዕና ድረስ ያሉት ስምንቱም ሳምንታት የየራሳቸው ስያሜ ኖሯቸው ለየእንዳንዳቸው የተለየ ንባብና መዝሙር እንዲኖራቸው መደረጉ የጌታችንን ሥጋዌ፣ የፍቅሩን ፍለጋ፣ ሕይወትና መድኃኒት የሚሆን የቃሉን ትምህርት፣ ድንቅ ተአምራቱን . . . በማሰብና በመንፈስ በመረዳት በጾሙ መጨረሻ ላይ ወደምናገኘው የክርስቶስን ህማምና ሞት፣ ስለ ሰዎች ፍቅር የተቀበላቸውን መከራዎች ሁሉ ወደምናስብበት ሰሙነ ህማማት በመንፈሳዊነት እንድንደርስ ነው፡፡ ከሰሙነ ህማማቱ ቀጥሎ የምናገኘው ደግሞ ወደ እረፍታችን የምንደርስበትና የምንገባበት የክርስቶስ ትንሣኤ ይሆናል፡፡ 
የእረፍታችን መጀመሪያ የሆነውን የክርስቶስን ትንሣኤ ስናከብር ሥጋችንንና ነፍሳችንን ለዚህ ሰማያዊ ስጦታና መንፈሳዊ ዓለም ማዘጋጀት ይጠበቅብናል፡፡ የክርስቶስን ትንሣኤ በልዩ መንፈሳዊነት፣ በጠለቀ መረዳትና ተመስጦ ሆነን፤ በሰማያት ካሉ ቅዱሳኑና እነርሱንም ካከበረ ከመድኃኒታችን ህብረት ውስጥ ሆነን ልናከብር ስለሚገባን በምድርም ያለው ሥርዐት መንፈሳዊ ሆኖ ተሠርቶልናል፡፡ በሁሉም የጾሙ ሳምንታት በተለይም ደግሞ በሰሙነ ህማማት ወስጥ የምንደርስበት ከፍ ያለ መንፈሳዊነትና ተመስጦ ነገረ ትንሣኤውን በጥልቀት እንድንረዳውና ከጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መንፈሳዊ ህብረትና አንድነት እንዲኖረን ያግዘናል፡፡ የትንሣኤውን ነገር በመንፈስ ሆነን መረዳት ስንችል ደግሞ በትንሣኤው የሆነልንንና የተሠራልንን እረፍት፣ የተቀበልነውንም ጸጋ እናስባለን፤ በዚህም ውስጥ በምድር ላይ ሆነን ትንሣኤውን እያከበርን ከመንፈሳዊው ዓለምና ከሰማያዊው ህብረት ጋር አንድ መሆንና መተባበር እንችላለን፤ በክርስቶስ ትንሣኤ ያገኘነውን መጻኢ እረፍትና የክብሩንም መንግሥት አጥብቀን እንናፍቃለን፡፡
በጾማችንና በሌሎችም መንፈሳዊ ተግባሮቻችን የተሠሩልን ሥርዐቶች ሁሉ ዋናኛ ዓላማቸው እኛን ወደተሻለው መንፈሳዊ መረዳትና ከፍታ ማድረስ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ስለ ሕግ ሳይሆን ስለመንፈሳዊነትና ከፍ ስላለው የእግዚአብሔር እውቀትና መረዳት ስንል የተሠሩልንን መንፈሳዊ ሥርዐቶች እንፈጽማለን፡፡ በዓለ ትንሣኤ የክርስቶስን ማዳን፣ የፍቅሩንም ፍለጋ የምናስብበት እንደመሆኑ መጠን የክርስቶስን ሐሳብና ፈቃድ የምናገለግልበት፣ እንደቃሉ የምንመላለስበት እንጂ ከመንፈሳዊ ተግባር ርቀን ፈቃዳችንን የምናገለግልበትና ሥጋችንን ደስ የምናሰኝበት አይደለም፡፡ በምድር ላይ የምንኖረው ሕይወት የክርስቶስ እንደሆነ ስለምናምን ትንሣኤን ስናከብር ክርስቶስን በማሰብና እርሱንም በመፈለግ ደስ እንሰኛለን እንጂ በመብልና በመጠጥ እራሳችንን ደስ አናሰኝም፡፡
ከክርስቶስ ጋራ ተሰቅያለኹ፤ እኔም አኹን ሕያው ኾኜ አልኖርም፥ ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አኹንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ እራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው።ገላ 2፣20፡፡ ክርስትናችን ከክርስቶስ ጋር የተሰቀልንበት ነውና ክርስቶስን ደስ ከማሰኘት ዳግመኛ ሥጋን ደስ ወደ ማሰኘት ፈቀቅ አንልም፡፡ ይህ ሕይወታችን እኛ ሕያዋን ሆነን የምንኖርበት ሳይሆን ክርስቶስ በእኛ የሚኖርበት ነውና በዓለ ትንሣኤውን ክርስቶስ ደስ በሚሰኝባቸው ተግባራት እንጠመድበታለን እንጂ ከመንፈሳዊነት በራቀና ሥጋዊነት በተጫነው ሁኔታ አናከብረውም፡፡ የክርስቶስን ሥጋና ደም የምንቀበልበት እንጂ በዶሮና በበግ ሥጋ የምናሳልፈው ትንሣኤ የክርስቶስ ሊሆን አይችልም፡፡
እኛ ደግሞ ሸክምን ዅሉ ቶሎም የሚከበንን ኀጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስለ አለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጧልና። ዕብ 12፣1-2፡፡ ተብሎ እንደተጻፈ ጌታችንና መደኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለእረፍታችን መድከሙንና መከራን መታገሱን እያሰብን እኛም እንደ እርሱ ሁሉ በፊታችን ያለውን ነውር ሁሉ በመናቅና ሥጋችንን ደስ ከማሰኘት በመጠበቅ ከሁሉ የሚበልጠውን የትንሣኤውን ደስታና ብርሃን እንጠብቃለን እንጂ በመብልና በመጠጥ፣ በዘፈንና በጭፈራ እራሳችንን አናረክስም፡፡ ክርስቶስ መከራን የተቀበለው፣ የሞተው፣ ትንሣኤውንም የሰጠን ለመንፈሳዊ ሐሳብና አላማ እንጂ ለሥጋዊነትና ለዓለማዊነት አይደለም፡፡ ስለሆነም የጌታችንን ትንሣኤ የምናከብረው በመንፈሳዊነት እንጂ በዓለማዊነት አይደለም፣ በነፍስ ደስታ እንጂ በሥጋዊነት አይደለም፣ በዝማሬና ክርስቶስን በማመስገን እንጂ በዘፈንና በጭፈራ አይደለም፣ እራስን በመግዛት እንጂ ብዙ በመብላትና በመጠጣትም አይደለም፡፡
እንደ እግዚአብሔር ሐሳብና ፈቃድ በመንፈሳዊነት የሚደረግ በዓለ ትንሣኤና በዓለ ሃምሳ ይሁንልን!

ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ!