Tuesday, March 29, 2016

ሰንበት ትምህርት ቤቶቻችንን እንዴት እንደግፋቸው? (ክፍል ሁለት)




ሰንበት ትምህርት ቤቶችን አስመልክቶ በክፍል አንድ አቅርበነው በነበረው ዝግጅታችን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት ውስጥ የሰንበት ትምህርት ቤቶችን አስፈላጊነት ለመዳሰስ ሞክረን ነበር፡፡ ለዛሬ ደግሞ በምን አግባብ ብንደግፋቸው በቤተ ክርስቲያናችን አገልግሎት ውስጥ አሁን ካለው አገልግሎት የተሻለና ውጤታማ የሆነ አሰራር እንዲኖር  ማድረግ እና በተጠናከረ መልኩ የቤተ ክርስቲያንን ሁሉን አቀፍ አገልግሎት  ማገዝና ማጠናከር ይችላሉ? የሚለውን ለማየት እንሞክራለን፡-
     1.    ማዕከላዊነቱን የጠበቀና የተጠና የሰንበት ትምህርት ቤቶች ስርዐተ ትምህርት እንዲኖር መሥራት፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሁለት ሺህ ዓመታት ውስጥ የዳበረ ክርስቲያናዊ ትምህርትና ባህል ያላት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ይህንን የዳበረ ክርስቲያናዊ ትምህርትና ባህል ለተተኪ ትውልዶች ለማውረስና ቀጣይነቱን ለማስቀጠል ሰንበት ትምህርት ቤቶች ምቹ የመማሪያ አካባቢዎች ናቸው፡፡ በሰንበት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚሰጡት ትምህርቶች የነገዋን ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ታሳቢ ያደረጉ፣ የተጠኑ ሆነው አሁን ያለውን ማኅበራዊና አካባቢያዊ ተጽዕኖ ከግምት ውስጥ ማስገባት ካልቻሉ፣ ችግር ፈቺና ጥያቄዎችን መመለስ የሚችሉ ካልሆኑ ነገ የምትኖረን ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን አሁን ያላትን መልክ ልትይዝ አትችልም፡፡ ነገሮችን በልማድና ባጋጣሚ የምናደርግባቸው ጊዜያት አልፈዋል፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤቶቻችን የእውቀት ማእከል ሆነው፣ ለሚነሱ ማናቸውም አይነት ጥያቄዎች መልስ መስጠት የሚችሉበትን አቅም ዛሬውኑ ካልገነባንላቸው በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ስነ ልቦናዊና ሌሎች አካባቢያዊ ተጽዕኖዎች ስር ስለሚወድቁ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አጋር ከመሆን ይልቅ ጥቅም አልባ ስብስቦች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
የግብጽ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ላይ በዕቅድ ላይ የተመሰረተ ስራ መስራቷ ዛሬ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ለግብጽ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት መጠናከርና ለወንጌል መስፋፋት ጉልህ ድርሻ ማበርከት ችለዋል፡፡ የእኛም ሰንበት ትምህርት ቤቶች በዓላትን ከማድመቅ ያለፈ ድርሻ እንዲኖራቸው ማዕከላዊነቱን የጠበቀና የተጠና የሰንበት ትምህርት ቤቶች ስርዐተ ትምህርት እንዲኖረን በማድረግ የሰንበት ትምህርት ቤቶችን ድርሻ ማሳደግ ለነገ የማንለው የቤት ሥራችን ሊሆን ያስፈልጋል፡፡ የአብነት ትምህርት ቤቶቻችን እየተዳከሙ በመጡበት አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ሰንበት ትምህርት ቤቶች አማራጭ የአብነት ትምህርት ቤቶች ሆነው ማገልገል የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ካልቻልንና የሰንበት ትምህርት ቤቶች ስርዐተ ትምህርት በአብነት ትምህርቱ ውስጥ የሚሰጡትን የተወሰኑትን የቤተ ክርስቲኒቱን ትምህርቶች እንዲያካትቱ ማድረግ ካልተቻለ ነገ የምንከፍለው ዋጋ ከፍተኛ መሆኑ አይቀርም፡፡
ለዚህ ሁሉ ግን ከላይ እስኪመጣ እጅና እግርን አጣጥፎ መቀመጥ አግባብ አይደለም፡፡ በአሁኑ ወቅት የራሳቸውን ሥርዐተ ትምህርት በመቅረጽ የተሻለ አገልግሎት እየፈጸሙ ያሉ ሰንበት ትምህርት ቤቶች በመኖራቸው ከነዚህ የተሻለ ተሞክሮ ካላቸው ሰንበት ትምህርት ቤቶች ልምድ በመውሰድ የተሻሉ ተሞክሮዎችን በማስፋት አገልግሎታቸውን ማጠናከር እንጂ፡፡
     2.   ሰንበት ትምህርት ቤቶችን በበቂ ሁኔታ በበጀት መደገፍ፡፡
ሰንበት ትምህርት ቤቶቻችን አሁን እየሰጡት ያለውን አገልግሎት የሚፈጽሙት ያለምንም የበጀት ድጋፍ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤቶች በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕጋዊ መዋቅር ስር ያሉ ሕጋዊ ተቋማት ቢሆኑም ሥራዎቻቸውን የሚያከናውኑበትና ወጪዎቻቸውን የሚሸፍኑበት ቋሚ የበጀት ድጋፍ የላቸውም፡፡ ከዚህ ይልቅ በአባላቱ የገንዘብ አስተዋፅዖና በጎ ፈቃደኝነት ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው፡፡ እንዲህ ያለው አሠራር ዘላቂነት ሊኖረው ስለማይችልና አገልግሎቱንም ስለሚያቀጭጨው ሰንበት ትምህርት ቤቶቻችን አገልግሎታቸውን በተቀላጠፈ ሁኔታ መፈጸም የሚያስችላቸው በቂ የሆነ የበጀት ድጋፍ ሊደረግላቸው ያስፈልጋል፡፡ ያለበቂ የበጀት ድጋፍ ይህን ያህል አገልግሎት መፈጸም ከቻሉ፤ በበጀት መደገፍና መታገዝ ቢችሉ ከዚህ የበለጠና የተሻለ አገልግሎት ለመፈጸም መቻላቸው እሙን ነው፡፡ 
      3.   ሰንበት ትምህርት ቤቶች ለአገልግሎት ምቹ የሆኑ አዳራሾች፣ ቢሮዎችና ቤተ መጽሐፍቶች እንዲሟሉላቸው ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ ማድረግ፡፡
ሰንበት ትምህርት ቤቶቻችን አሁን ባሉበት ሁኔታ የሚፈጽሟቸው የተለያዩ አግልግሎቶች እንዳሏቸው ሁሉ እነዚህን አገልግሎቶች የሚፈጽሙባቸው ምቹ የስብከተ ወንጌል አዳራሾች፣ ቢሮዎች፣ ወንበሮችና ጠረጴዛዎች  ያስፍልጓቸዋል፡፡ በበጎ ፈቃዳቸውና በግል ተነሳሽነታቸው ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥተው እናገልግል ካሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸትና አስፈላጊውን እገዛ ማድረግ የሁላችንም የቤተ ክርስቲያኒቱ ባለድርሻ አካላት ግዴታ ነው፡፡ በሰንበት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩት ወጣቶች የእኛው ወንድሞችና እህቶች እንደመሆናቸው መጠን የሚያስፈልጓቸውን ግብአቶች ማሟላት አገልግሎቱ ለሚመለከተን ክርስቲያኖች ሁሉ ግዴታ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን ትምህርትና አገልግሎት እንዲያድግና እንዲጠናከር የምንፈልግ ሁሉ ሰንበት ትምህርት ቤቶቻችንን መደገፍና ማገዝ ይጠበቅብናል፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤቶቻችን የእኛ ናቸው፣ በሚያሰፈልጋቸው ሁሉ ልንረዳችውና ልናግዛቸው የምንችለውም እኛ ራሳችን ነን፡፡ እኛ የሚጠበቅብንን ድርሻ መወጣት ሳንችል እንዲህ ቢሆን ኖሮ ብሎ ማሰቡና መመኘቱ ምንም ፍሬ አይኖረውም፡፡ በትልልቅ ከተሞቻችን ውስጥ የሚገኙ ታላላቅ አድባራት ሳይቀሩ ለሰንበት ትምህርት ቤቶቻቸው ምቹ የሆኑ የአገልግሎት ቢሮዎችንና አዳራሾችን መገንባት ያልቻሉት የገንዘብ እጥረት ስላለባቸው ሳይሆን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ድርሻና አስተዋጽዖ ስላልተገለጠላቸው ነው፡፡ የሰፋችና የተጠናከረች አንዲት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን ነገ ላይ ማየት የምንፈልግ ከሆነ ዛሬ ላይ ሰንበት ትምህርት ቤቶቻችን ላይ በእቅድና በጥናት ላይ ተመስርተን መስራት ይጠበቅብናል፡፡ ይህንን ማድረግ ካልቻልን ጊዜው ይቀድመንና ነገሮች ከእኛ ፈቃድና ቁጥጥር ውጪ ሆነው ነገሮችን ለማረምና ለማስተካከል ብዙ ርቀት መጓዝ ይጠይቀናል፡፡
    4.   ሰንበት ትምህርት ቤቶች በገቢ ራሳቸውን የሚችሉበትንና አገልግሎቱን የሚደግፉበትን ሁኔታ መፍጠር፡፡
የሰንበት ትምህርት ቤቶችን አገልግሎት ከዚህ በተሻለ ሁኔታ ማሳደግ እንዲቻል የተጠናከረ የገንዘብ አቅም መፍጠር ለነገ ወሳኝ ነው፡፡ ጊዜው እየተለወጠ፣ የቴክኖሎጂው እድገት እየፈጠነ፣ የሰው ልጆች ማኅበራዊና ስነ ልቦናዊ ቀውስ እየሰፋ፣ የሉላዊነት (Globalization) ተጽዕኖ እየበረታ በመጣበት በዚህ ዘመን ሰንበት ትምህርት ቤቶቻችን ወቅቱን የጠበቀና ዘመኑን የሚዋጅ አገልግሎት መስጠት ካልቻሉ በትውልዱ ስለሚቀደሙ ከመከተል ባለፈ የመሪነት ሚና ሊኖራቸው አይችልም፡፡ ሁሉን በአገልግሎቷ መድረስ የምትችል፣ ለችግሮች አፋጣኝ ምላሽ ያላት፣ አገልግሎቷ ሁሉን አቀፍ የሆነ፣ የተጠናከረች ቤተ ክርስቲያን እንድትኖረን ዛሬ የሰንበት ትምህርት ቤቶቻችንን የገንዘብ አቅም ማሳደግና ማጠናከር ይጠበቅብናል፡፡ በምናወጣው የገንዘብ መጠን ልክ ተጽዕኖ መፍጠርና ውጤት ማስመዝገብ መቻላችንን መርሳት የለብንም፡፡ ነገሮች ልክ እንደዛሬውና እንደትናንቱ ሁሉ ነገም እንዲሁ ይቀጥላሉ የሚል ሞኝነት ሊኖረን አያስፈልግም፡፡ አገልግሎቱ የሚቀላጠፍበትንና ያለብዙ ድካም ብዙዎችን መድረስ የሚቻልበትን ሁኔታ ለመፍጠር ጠንካራ የሆነ የገንዘብ አቅም መፍጠር ወቅቱ የሚጠይቀው ግዴታ ሆኗል፡፡ በጥቂት በጎ አድራጊዎች የገንዘብ አስተዋጽዖ ላይ የተንጠለጠለ የሰንበት ትምህርት ቤት አገልግሎት ብዙዎችን መድረስና ተጽዕኖ መፍጠር አይቻለውም፡፡ ለወንጌል መዳረስና ለሰዎች ሁሉ መዳን የምናስብ ሁሉ በእቅዶቻችን ውስጥ ሰንበት ትምህርት ቤቶቻችንን አስገብተን ስለምናደርግላቸው አስተዋጽዖና ስለምናበረክተው ድርሻም ማሰብ ይጠበቅብናል፡፡ የቤተ ክርስቲያናችንን ሥራ የምንሰራው እኛ እንደመሆናችን መጠን ሰንበት ትምህርት ቤቶቻችንን ልናስብላቸውና ልንቆረቆርላቸው ያስፈልገናል፡፡ በመሆኑም የተለያዩ የልማት ተቋማትን በማቋቋም የገቢ ማስገኛ ሥራዎችን በመለየትና በመተግበር እንዲሁም የአባላትን እና ተባባሪ አባላትን ድርሻ ከፍ በማድረግ ራሳቸውን እንዲችሉ በቂ የገቢ ምንጭ ያላቸው እንዲሆኑ ማድረግ አለብን፡፡
ማጠቃለያ
ሰንበት ትምህርት ቤቶች ልዩ ልዩ እውቀት፣ ልምድና ክህሎት ያላቸው ወጣቶች የተሰባሰቡባቸው የቤተ ክርስቲያናችን እምቅ ሀብቶች ናቸው፡፡ የቤተ ክርስቲያናችንን ነገዋን የምንናፍቅና የተሻለ እንዲሆን የምንመኝ ሁሉ በምንችለው አቅም ሰንበት ትምህርት ቤቶቻችንን መደገፍና ማጠናከር ይጠበቅብናል፡፡ የምንችል በሰንበት ትምህርት ቤቶች መደበኛ መዋቅር ውስጥ ታቅፈን ማገልገል አለብን፣ ይህን ማድረግ የማንችል ደግሞ በገንዘባችን፣ በእውቀታችንና በልምዳችን ከሰንበት ትምህርት ቤቶቻችን ጋር አብረን መስራት አለብን፡፡ የሚፈለገውን ያህል ሳንረዳቸውና ሳናግዛቸው ሰንበት ትምህርት ቤቶቻችን ለኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን መጠበቅና መጠናከር እስካሁን እያየናቸው ያሉትን በጎ አስተዋጽኦዎች ማድረግ ከቻሉ፤ በተጠናና በተቀናጀ መልኩ ብናግዛቸውና ብንረዳቸው ምድርን ሁሉ ክርስቲያን ለማድረግ የሚያስችል አቅም አላቸው፡፡ ምንም ማድረግና ማገዝ ሳንችል እንዲሆን የምንመኘውን መጠበቅ ብቻውን ምንም ለውጥ አያመጣም፡፡ ሁላችንም የምንችለውን አስተዋጽዖ ማድረግ መጀመር አለብን፡፡ የነገዋ ቤተ ክርስቲያናችን ጥንካሬ በዛሬዎቹ ሰንበት ትምህርት ቤቶቻችን ላይ የተመሰረተ መሆኑን ልንዘነጋ አይገባንም፡፡ እያንዳንዱን ምእመን ሊደርስ የሚችል አሰራርና መዋቅር እንዲኖረን ከፈለግን ሰንበት ትምህርት ቤቶቻችን ላይ የተጠናከረ ሥራ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤቶቻችን የእኛ ናቸው፣ የማንም አይደሉም፡፡ እኛ ካልረዳናቸውና ካልደገፍናቸው ማንም ሊረዳቸውና ሊደግፋቸው ስለማይችል በምንችለው አቅምና ጉልበት ሰንበት ትምህርት ቤቶቻችን የሚጠናከሩበትን መንገድ እንፈልግ፣ ከዚያም ቢያንስ አንድ በተግባር የተገለጠ ድጋፍ እናድርግ፡፡ ያን ጊዜ የቤተ ክርስቲያናችን ነገዋ ብሩህ ሆኖ እናያለን፡፡
ይትባረክ አምላከ አበዊነ!

No comments:

Post a Comment