Sunday, June 19, 2016

መዳንና በጎ ምግባራት በመጀመሪያይቱ የቅዱስ ዮሐንስ መልዕክት




ምዕራፍ ሁለት
ቁ. 9-10 ‘‘በብርሃን ውስጥ አለሁ የሚል ወንድሙን የሚጠላ ገና እስካሁን በጨለማ ውስጥ አለ፡፡ ወንድሙን የሚወድ ግን በብርሃን ይኖራል’’ የክርስትና ሃይማኖት ማሰሪያው ፍቅር ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ በፍቅር የሚሰራ እምነት እንጂ መገረዝ ወይም አለመገረዝ አይጠቅምም (ገላ. 5፡6) እንዳለ ወንድምን መውደድ አንድ ሰው በብርሃን ስለመኖሩ ማረጋገጫ ሆኗል፡፡ ወንድሙን የሚጠላ ከእግዚአብሔር ሊሆን አይችልምና፡፡
በጎ ምግባራት በመዳን ሕይወት ውስጥ ታላቅ ድርሻ አላቸው፡፡ በብርሃን እንድንሆንና ከእግዚአብሔር ጋር ህብረት እንዲኖረን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ልንወድ ያስፈልገናል፡፡ ወንድሞቻችንን እየጠላን በብርሃን ልንሆንና ከእግዚአብሔርም ጋር ህብረት ሊኖረን አይችልም፡፡ ወንድሞቻችንን ስንወድ ግን ከጨለማ ሥራ ስለምንለይ በብርሃን መሆን ይቻለናል፤ በዚህም ደግሞ ከአምላካችን ከእግዚአብሔር ጋር ህብረትና አንድነት ይኖረናል፡፡
‘‘በዚህም የእግዚአብሔር ልጆችና የሰይጣን ልጆች ይታወቃሉ፤ ጽድቅንም የማይሠራ ሁሉ ከእግዚአብሔር የተወለደ አይደለም፤ ወንድሙንም የማይወድ እንዲሁ ነው፡፡’’ 1ኛ ዮሐ 3፣10፡፡ ጽድቅ በእምነት ብቻ ሳይሆን በጎውን በማድረግና በመሥራትም ነው፡፡ ጽድቅን የማያደርግና ወንድሙን የማይወድ ሁሉ የሰይጣን ልጅ ነው፤ በእግዚአብሔር ማመኑ ብቻውን የእግዚአብሔር ልጅ ሊያደረገው አይችልምና፡፡ አጋንንትም ያምናሉ ይንቀጠቀጡማል ነገር ግን የእግዚአብሔር ልጆች አይባሉም (ያዕ 2፡19)፡፡ ጽድቅ በጎውን በማድረግና ወንድሞቻችንን በመውደድ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይነገረናል፡፡ ክርስትና የማድረግ ሕይወት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፉልን ብዙዎቹ ትምህርቶች በተግባር የምንታዘዛቸው ናቸው፡፡ እነዚህም ደግሞ ባነበብናቸው ቁጥር ጽድቅን ማድረግ ስለሚያስችሉን ጽድቅን በመሥራት የእግዚአብሔር ልጆች መሆን እንደምንችል ይነግሩናል፡፡ ጌታችን በወንጌል ‘‘እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው ሕይወትም ነው።’’ እንዳለን ቃሉ መንፈስም ነውና በሕይወታችን ውስጥ ይሠራል፤ በጎ ማድረግንም ያስተምረናል፡፡ ዮሐ 6፣63፡፡ ‘‘ከአፌ የሚወጣ ቃሌ እንዲሁ ይሆናል፤ የምሻውን ያደርጋል የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም፡፡’’ እንዲል ቃሉን ስናምንና ልንታዘዘው ስንፈቅድ ብቻ በእኛ ውስጥ ይሠራል፤ በዚህም ጊዜ በሥራ የሚገለጥና የሚታይ እምነት ይኖረናል፡፡ ኢሳ 55፣11፡፡
ቁ. 28-29 ‘‘አሁንም ልጆቼ ሆይ፣ በሚገለጥበት ጊዜ መወደድን እናገኝ ዘንድ፣ በሚመጣበትም ጊዜ ከእርሱ የተነሳ እናዳናፍር በእርሱ ጸንታችሁ ኑሩ፡፡ እርሱ ጻድቅ እንደሆነ ብታውቁ ጽድቅን የሚያደርግ ሁሉ ከእርሱ እንደተወለደ እወቁ፡፡’’ በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ ለተቀበሉትና በስሙ ለሚያምኑት ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን እንደሰጣቸው ይነግረናል፡፡ ዮሐ 1፣12፡፡ በእምነት ብቻ ሳይሆን ጽድቅን/በጎ ምግባራትን በማድረግም ከእግዚአብሔር እንደምንወለድና የእግዚአብሔር ልጆች እንደምንሆንም ደግሞ ይነግረናል፡፡ ጽድቅን የማያደረግ ሁሉ ከእግዚአብሔር አልተወለደምና፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ስለምን ይሆን እዚህ ላይ ስለእምነት ሳያነሳ ጽድቅን ስለማድረግ ብቻ የጻፈልን? ምክንያቱም በጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከማመን ባሻገር እርሱ እንደተመላለሰ እኛም ደግሞ በጽድቅ መመላለስና ጽድቅን ማድረግ ስለሚያስፈልገንም ነው፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጻድቅ መሆኑን የማወቃችን ጥቅሙ ጽድቅን ለማድረግ ነው፡፡ ‘‘ለዚህ ተጠርታችኋልና፤ ክርስቶስም እኮ ፍለጋውን ትከተሉ ዘንድ ምሳሌውን ሊተውላችሁ ስለእናንተ መከራን ተቀብሏል፡፡’’ 1ኛ ጴጥ 2፣21፡፡ ክርስትና ይህ ነው በጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ብቻ ሳይሆን የእርሱን ፍለጋም መከተል፡፡ ስላመንን ብቻ እንድናለን ብለን ፍለጋውን ከመከተል ፈቀቅ ብንል ልንድን አንችልም፡፡ የምንከተለው ፍለጋ ደግሞ እርሱ በምድር ላይ እንደተመላለሰና እንዳሳየን በጽድቅ ሕይወትና ከኀጢአት በመራቅ የሚደረግ መመላለስ ነው፡፡ በክርስቶስ ማመኑን ወድደን ክርስቶስ የኖረውን የተቀደሰ ሕይወት ልንተውና ልንጥል አይቻለንም፡፡ የትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ይህን አይደግፍም፡፡ በክርስቶስ ካመንን በኋላ እርሱ ጾሞ እንዳሳየን አንዲሁ ደግሞ እንጾማለን፣ መጸለይን እንዳሳየን እንዲሁ እኛ ደግሞ እንጸልያለን፣  በገዳመ ቆሮንቶስና በጌቴ ሴማኒ የአትክልት ስፍራ በመንፈሳዊ ተጋድሎ (በጸሎት፣ በሰጊድና በቁመት) መቆየትን እንዳስተማረን እንዲሁ እኛ ደግሞ እናደርጋለን፡፡ መቼም ክርስቶስ የጾመውና የጸለየው ለኃጢአታችን ሥርየት ነው ካላልን በቀር፡፡ የኃጢአታችን ስርየትማ በደሙ መፍሰስ ብቻ ነው የተደረገው፤ መጾሙና መጸለዩ ግን እኛ እንጾምና እንጸልይ ዘንድ አርአያ ሊሆንልን ነው፡፡ በደሙ ከሆነልን ሥርየት የተነሳ የምንኖረው አዲስ ሕይወት የምንጠብቀውና ወደ ክርስቶስ የምናድግበት፤ ወደ ክብሩም ሙላት የምንደረስበት መንገድ ሲሆን ይኽውም ክርስቲያናዊው ምግባር፣ የተቀደሰውና በድርጊት የተገለጠው ኑሯችን ነው፡፡ እርሱ እንዳደረገ ስናደርግና እርሱ እንደተመላለሰ መመላለስ ስንችል ያን ጊዜ ወደ ክርስቶስ እንደርሳለን፤ ወደ መዳንም እንገባለን፡፡
 

የቅዱስ ዲዮስቆሮስ ቅዳሴ




ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የጌታን ስጋና ደም የምታከብርባቸው  አሥራ ዐራት ቅዳሴያት አሏት፡፡ ከእነዚህ ምስጋናዎች መካከል ለዛሬው የቅዱስ ዲዮስቆሮስን የቁርባን ምስጋና እንደሚከተለው ይዘንላችሁ ቀርበላል፡፡  ጸሎቱና በረከቱ ከሁላችን ጋራ ይኑር ለዘለዓለሙ አሜን።
ቅዱስ ዲዮስቆሮስ በቅዳሴው ስለ ሀልዎተ እግዚአብሔር እንደዚህ ይላል፡-
እግዚአብሔር ከዓለም በፊት እስከ ዘለዓለምም ድረስ፤ እግዚአብሔር በሦስትነቱ አለ፣ እግዚአብሔር በመለኮቱ፣ እግዚአብሔር በመንግስቱ አለ ።
ከጎሕና ከጽባሕ በፊት፣ ከመዓልትና ከሌሊት በፊት፣ መላእክት ሳይፈጠሩ እግዚአብሔር በመንግስቱ አለ ።
ሰማያት ሳይዘረጉ፣ የየብስም ፊት ሳይታይ፣ ሐመልማላት ሳይበቅሉ እግዚአብሔር በመንግስቱ ነበረ ፡፡
ከፀሓይና ከጨረቃ፣ ከከዋክብትም በፊት፣ ከብርሃናትም መመላለስ በፊት እግዚአብሔር በመንግስቱ ነበረ ፡፡
ከሚንቀሳቀሱ እንስሳት በፊት፣ ከሚበሩም አዕዋፍ በፊት፣ ከባሕር አራዊት በፊት እግዚአብሔር በመንግስቱ ነበረ ፡፡
አዳምን በርሱ አምሳልና አርኣያ ሳይፈጥረው፣ ትእዛዛቱንም ሳያፈርስ እግዚአብሔር በመንግስቱ ነበረ ፡፡
ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ  ምስጋና ይገባል፤ ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለምም ፡፡
ስለ ጌታችን ወደዚህ ዓለም መምጣት፣ ከቅድስት ድንግል ማርያም ስለመወለዱ፣ ስለ አስተዳደጉ፣ ስለ አስተማረው ትምህርት፣ በገዳመ ቆሮንቶስ ስለመጾሙ፣ ስለእኛ ስለተቀበለው መከራ፣ በሞቱ ሞታችንን ድል ስለመንሳቱ፣ ስለትንሣኤው እንዲሁም ስለ ዕርገቱና ዳግም ምፅአቱ  ደግሞ እንዲህ ብሏል፡-
ሰማይ ይስማ ምድርም ታድምጥ የምድር መሠረቶችም ይደንግጡ ፡፡
በአባቱ ፈቃድ ወረደ፣ በማርያም ዘንድ እንግዳ ሆነ፣ እግዚአብሔር በንጹሕ ድንግልናዋ ተወለደ ፡፡
በእንስሳት በረት ተጨመረ፣ የንጉሡንም እጅ መንሻ ተቀበለ፣  ከእናቱ ጡቶች ምግብን እየለመነ እንደ ሕፃናት አለቀሰ ፡፡
በግልጥ ተመላለሰ፣ እንደ ሰውም ታየ፣ በየጥቂቱ አደገ፣ በሠላሳ ዘመን በዮርዳኖስ ተጠመቀ ።
እንደሰው ሆኖ ለመጾም በገዳም አደረ፣  ከዲያብሎስ ዘንድ ተፈተነ፣ የጨለማን መኳንንት በአምላክነቱ ኃይል ሻረ ።
ሰውን የፈጠረ እርሱ እጁን ለሕማም ዘረጋ፣  አዳምን ከኀጢአት ቀንበር ነጻ ያድርገው ዘንድ፡፡
ወዳንተ ወደ አባቱ ወደ ሰማይ አቅንቶ አየ፣ አመሰገነ፣ ባረከ፣ ቆረሰም። ንጹሓን ቅዱሳን ወገኖቹ ለሆኑ ደቀ መዛሙርቱ  ለሐዋርያት ሰጣቸው፤ ይህ ኅብስት ለኀጢአት ማስተሥረያ ስለናንተ የሚፈተት ሥጋዬ ነው ንሡ ብሉ አላቸው ።
ዳግመኛም ውኃውን ከወይን ጋራ ቀላቅሎ አመሰገነ፣ ባረከ፣ አከበረ ፡፡ ንጹሓን፣ ቅዱሳን ወገኖቹ ለሆኑ ደቀ መዛሙርቱ ለሐዋርያት ሰጣቸው ይህ ጽዋ  ለብዙ ሰዎች ቤዛ ስለናንተ የሚፈስ ደሜ ነው ንሡ ጠጡ አላቸው ፡፡ 
አይሁድ ያዙት፣ የመላእክት ሠራዊት በመፍራትና በመንቀጥቀጥ የሚቆሙለት እርሱን በዐደባባይ አቆሙት ፡፡
በእንጨት ላይ ሰቅለው በቀኖት ቸነከሩት፣ ራሱንም በዘንግ መቱት፣ ጎኑን በጦር ወጉት፣ ለጉበኞች እስራኤል ካንድ ድንጋይ ያጠጣቸውን ለጥሙ ከከርቤ ጋራ የተቀላቀለ ሐሞትን አጠጡት ፡፡
የማይሞት እርሱ ሞተ፤ ሞትን ይሽረው ዘንድ ሞተ፤ ሙታንን ያድናቸው ዘንድ ሞተ፤ በቃል ኪዳን ተስፋውን እንደ ነገራቸው ፡፡
ከእንጨት አወረዱት፣ በበፍታም ገንዘው በአዲስ መቃብር ቀበሩት ፡፡
በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፣ የተሰበሰቡ ደቀመዛሙርቱ ወዳሉበትም ገባ፣ በጽርሐ ጽዮንም ታያቸው፣ በአርባኛውም ቀን ወደ ሰማይ ባረገ ጊዜ የአብን ተስፋ ደጅ ጥኑ ብሎ አዘዛቸው ፡፡
በአምሳውም ቀን በእሳት አምሳል መንፈስ ቅዱስን ሰደደላቸው፣ በአገሩ ሁሉ ቋንቋ ተናገሩ፣ እንደነርሱም ወደዚህ ኅብስትና ጽዋ ያንን ቅዱስ መንፈስህን ላክ፡፡ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋና ደም ያደርገው ዘንድ ለዘለዓለሙ፡፡  አንተ ሥጋዬን የበላ ደሜንም የጠጣ ከእኔ ጋራ ይኖራል እኔም ከርሱ ጋራ እኖራለሁ እንዳልህ፡፡
ለሕይወትና ለዘለዓለም ከኃጢአት ለማንጻት ይሆናቸው ዘንድ ለወገኖችህ ሁሉ አንድ አድርገህ ስጥ ፡፡
የአንተ በሚሆን በመንፈስ ቅዱስ አንድ እንሆን ዘንድ መሆንን ስጠን፤ በዚህም ጵርስፎራ (ኅብስት) አድነን ለዓለሙ ሁሉ በምትሆን በአንተ ለዘለዓለሙ ሕያዋን እንሆን ዘንድ ፡፡
የእግዚአብሔር ስሙ ምስጉን ነው፣ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣውም ምስጉን ነው፣ የጌትነቱ ስም ይመስገን ይሁን ይሁን የተመሰገነ ይሁን ፡፡
በሌላም በኩል ስለ ምሥጢረ ቁርባንንም በሰፊው ይነግረናል። ሥጋውና ደሙ ከምሥጢረ ሥጋዌ ጋር ያለውን ግንኙነት፤ ለመዳን ምሥጢራቱን መፈጸም እንዳለብን፤ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስም አምላክነት፣ ንጉሥ መሆኑን፣ የሁሉ ገዢ መሆኑንና መሃሪነቱን እንደሚከተለው ይነግረናል፡-
በግዕ ይምጣ በዓይናችን እንድናየው፣ በእጃችንም እንድናርደው በርሱ ደስ ይለን ዘንድ፡፡ ሥጋው ከዚህ ኅብስት ጋራ አንድ ይሁን፤ ደሙም በዚህ ጽዋ ይቀዳ ፡፡
ከኛ ወገን ላንዱ ይህን ኅብስት በሚበላበት ጊዜ ያለ ደምና ያለ መንፈስ ሥጋን ብቻ የሚበላ፤ ይህንንም ጽዋ በሚጠጣበት ጊዜ ከኛ ወገን ላንዱ ያለ ሥጋና ያለ መንፈስ ደምን ብቻ የሚጠጣ አይምሰለው፣ ሥጋና ደም መንፈስም አንድ ናቸው እንጂ መለኮቱ ከትስብእቱ (ከሰውነቱ) ጋራ አንድ እንደሆነ ለዘለዓለሙ ፡፡
ዳግመኛም ሁሉን የሚይዝ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አባት እግዚአብሔርን እንማልዳለን፤ ልመናችንን አልናቀምና አልተቆጣምና፣ ይቅርታውንም ከኛ አላራቀምና አምላካችን እግዚአብሔር ይቅር ባይ ስለሆነ ፡፡
አዎን አቤቱ የሁሉ አምላክ ነህ፡፡
አዎን አቤቱ የሁሉ ንጉሥ ነህ ፡፡
አዎን አቤቱ ሁሉን የያዝህ ነህ ፡፡
አዎን አቤቱ ሁሉን የምትገዛ ነህ ፡፡
አዎን አቤቱ ሁሉን የምታድን ነህ ፡፡
አዎን አቤቱ በእውነት የሁሉ ገዢ ነህ ፡፡
አዎን አቤቱ የሁሉ መድኃኒት ነህ ፡፡
አዎን አቤቱ ሁሉን የምትጠብቅ ነህ ፡፡
አዎን አቤቱ ሁሉን የምትመግብ ነህ ፡፡
የልጅህን ሥጋ ከኛ ሥጋ ጋራ አንድ እንዳደረግህ፤ ያንተን መሢሕ ደምም ከኛ ደም ጋራ አንድ እንዳደረግህ እንዲሁ አንተን መፍራትን በልቦናችን፤ በጎ አምልኮትህንም በኅሊናችን ጨምር ፡፡
ሥጋውያን የምንሆን እኛ ግን የሥጋን ሕግ እናስባለን፤ የሥጋንም ሥራ እንሠራለን፤ በሥጋ መንገድም እንሄዳለን፡፡ አንተ ግን የመንፈስን ሥራ አስተምረን፤ የመንፈስንም ሕግ አስረዳን፤ የመንፈስንም መንገድ ምራን ፡፡
እኛን ኃጥአንን  ብትምረን ያን ጊዜ መሐሪ ትባላለህና፡፡ ጻድቃንን ግን ከሥራቸው የተነሣ ትምራቸዋለህ፣ እንደ ጽድቃቸውም ትሰጣቸዋለህ ፡፡
የቀደመ በደላችንን አታስብብን፤ አቤቱ ይቅርታህ ፈጥኖ ይደረግልን ፡፡
ወደ አንተ እንጮሃለን፤ ወደ አንተ እናለቅሳለን፤ ወደ አንተ እንማልዳለን ለዘለዓለሙ ፡፡
አንብሮ ዕድ/ ካህኑ ሊባርክ ከመውጣቱ በፊት

ለዘለዓለሙ የማይጠፋ የሕይወት ብርሃን እግዚአብሔር ወንዶቹንና ሴቶቹን ባሮችህን ተመልከታቸው፡፡ ስምህን መፍራትን በልቡናቸው ዝራ፤ በበረከት ያፈሩ ዘንድ፤ ሥጋህና ደምህ ከተሰጣቸውም ጋራ ቁጠራቸው ፡፡
እጅህም በላያቸው የሚያድር ይሁን፤ እራሳቸውን በፊትህ ዝቅ ዝቅ ባደረጉ በወገኖችህ ላይ በወንዶቹና በሴቶቹ በሽማግሎዎቹና በሕፃናቱ፤ በደናግልና በመነኮሳቱ በባልቴቶችና አባት እናት በሞተባቸው ላይ ፡፡
እኛንም ከዚያ ጨምር፤ ሠውርና እርዳ፣ አጽና፣ በመላእክትህ አለቆችም ኃይል አበርታ፡፡ ከክፉ ሥራ ሁሉ አርቀን፤ በበጎውም ሥራ ሁሉ አንድ አድርግ ፡፡
በአንድ ልጅህ በእርሱ ያለ ክብርና ጽንዕ ላንተ ይገባል፤ ከርሱ ጋራ ከመንፈስ ቅዱስም ጋራ፤ ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን ፡፡