መጀመሪያይቱ የቅዱስ
ዮሐንስ መልዕክት ምዕራፍ አራት
(መዳንና
በጎ ምግባራት በመጀመሪያይቱ የቅዱስ ዮሐንስ መልዕክት)
ቁ. 4 “ልጆች ሆይ እናንተ ግን ከእግዚአብሔር ናችሁ፣ ክፉውንም አሸንፋችሁታል፡፡” ከእግዚአብሔር የሆኑ ሁሉ ክፉውን ያሸንፋሉ፤ ክፉውን ማሸነፍ የምንከተለው የክርስቶስ ፍለጋ
ነውና፡፡ “በዓለም ግን መከራን ትቀበላላችሁ፤ ነገር ግን ጽኑ፤ እኔ ዓለሙን ድል ነስቼዋለሁና፡፡” ዮሐ 16፣33፡፡ ተብሎ እንደተጻፈ ጽኑ የተባልንበት ይህ መጽናት እንዴት ያለ
ነው? መጠራታችን ክርስቶስ ለኖረው ሕይወት ነው፣ የክርስቶስ ሕይወቱ ደግሞ በዘመነ ሥጋዌው በምድር ላይ የተመላለሰው የተቀደሰ መመላለሱ
ነው፡፡ “እኔ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርኹኽ” ዮሐ 17፣4 ተብሎ እንደተጻፈ የክርስቶስን
ፍለጋ እንከተላለን ስንል እርሱ የአባቱን ፈቃድ እንደፈጸመ እኛም እስከሞት የወደደንን የአምላካችንን ፈቃድ እንከተላለን እንፈጽማለንም
ማለታችን ነው፡፡ ከእርሱ ፈቃድ የተለየ ፈቃድ ካለን እንዴት የእርሱ ልንሆን እንችላለን? መጠራታችን በስሙ ልናምን ብቻ
ሳይሆን በስሙ መከራንም ልንቀበል ነውና ክርስትና በስሙ ማመን ብቻ ሳይሆን በስሙ መጋደልና መከራ መቀበልም ነው፡፡ ፊልጵ 1፣29፡፡
ስለሆነም እውነተኛው የክርስትና አስተምህሮ በክርስቶስ ስም ስለማመን እንደሚያስተምረው ሁሉ ለክርስቶስ መኖርን፣ ለእርሱ ብሎ ማድረግንና
መጋደልንም ያስተምራል፡፡
“የእምነታችንንም
ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን እንከተለው እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሶ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጧልና፡፡
በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ ከኃጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን እስኪ አስቡት፡፡ ገና አልጸናችሁምና፣ ደማችሁን
ለማፍሰስ እስክትደርሱ ኀጢአትን ተጋደሏት፣ አሸንፏትም፡፡” ዕብ
12፣2-4፡፡ ክርስቶስ የናቀው ነውር ምንድን ነው? በጎውን ማድረግ የመዳን መንገድ ባይሆን ኖሮ ክርስቶስ በምድር ላይ ለሠላሳ ሦስት
ዓመታት መመላለስ ሳያስፈልገው ደሙን ብቻ ሊያፈስልን ይቻለው ነበር፡፡ በእነዚህ ሁሉ አመታት ግን ያሳየንና የተወልን የምንከተለው
ፍለጋ አለን፡፡ ክርስትና በክርስቶስ ደም፣ በቤዛነቱ ማመን እንደሆነ ሁሉ የክርስቶስ ፍለጋውን መከተልም ነው፡፡ በክርስቶስ ባለን
እምነት ለማደግ የምንተጋውን ያህል እንዲሁ ደግሞ ፍለጋውን ለመከተልና በተግባር የተፈተነውን ክርስትና ለመኖርና ለማድረግም እንተጋለን፤
በክርስቶስ እናምናለን የምንል ከሆነ የእምነታችን ራስና ፈጻሚ የሆነውን እርሱን መከተልና እርሱ እንደተመላለሰም ልንመላለስ ያስፈልገናልና፡፡
“እንመላለስበት
እግዚአብሔር አስቀድሞ ላዘጋጀው በጎ ሥራ በኢየሱስ ክርስቶስ የፈጠረን ፍጥረቱ ነንና፡፡” ኤፌ 2፣10፡፡እንግዲህ ምን እንላለን? እግዚአብሔር የፈጠረን በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ
እንድናምን ብቻ ሳይሆን እንመላለስበት ዘንድ አስቀድሞ ላዘጋጀው በጎ ሥራውም ጭምር ስለሆነ በስሙ እንደምናምን ሁሉ ስለ ስሙ ብለን
በጎውን ማድረግና በተቀደሱ ተግባራት መመላለስንም አንተውም፡፡ ይህን ብቻ አድረጉ (እምነትን ብቻ) የሚል የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት
የለምና! እውነተኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የሚነግረንና የሚያስተምረን “በበጎ ሥራ
ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ፣ እግዚአብሔርንም በማወቅ እያደጋችሁ በሁሉ ደስ ታሰኙት ዘንድ፡፡ በፍጹም ኃይል፣ በክብሩ ጽናት፣ በፍጹም ትዕግስት፣
በተስፋና በደስታም ጸንታችሁ፡፡” ብሎ ነው፡፡ ቆላ 1፣10-11፡፡
በእምነት እንድንጸና፣ በክርስቶስ ላይ ባለን እምነት እንድንደገፍ እንደሚነግረን ሁሉ በበጎ ሥራ፣ በፍጹም ትዕግስትና በተስፋ እንድንጸናም
ይነግረናል፡፡ በፍጹም ትዕግስት የተባልነው ክርስትና አንድ ጊዜ አምነን የምንተወው ብቻ ሳይሆን በእምነታችን ውስጥ የምንታዘዘው
በድርጊት የሚገለጥ ሕይወትና የምንታገሰው መከራም ጭምር ስለሆነ ነው፡፡
ቁ. 7-8 “ወንድሞቻችን ሆይ እርስበርሳችን እንፋቀር፤ ፍቅር እግዚአብሔር ነውና፤ የሚፋቀርም
ሁሉ እርሱ ከእግዚአብሔር ተወለደ፤ እግዚአብሔርንም ያውቀዋል፡፡ ወንድሙን የማያፈቅር እግዚአብሔርን አያውቅም፤ እግዚአብሔር ፍቅር
ነውና፡፡” ክርስትና እምነት ብቻ ሳይሆን በእምነት ውስጥ
የሚሆን በተግባር የሚገለጥ በጎ ምግባርም ነውና በእምነት የእግዚአብሔር ልጆች ሆነን እንደምንወለደው ሁሉ በበጎ ምግባራትና በተቀደሰ
ክርስቲያናዊ ኑሯችንም ከእግዚአብሔር እንወለዳለን፡፡ በዮሐንስ ወንጌል ላይ ደግሞ እንዲህ ተጽፏል፡- “ለተቀበሉት ሁሉ በስሙ ለሚያምኑ የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑ ሥልጣንን ሰጣቸው፡፡” ዮሐ 1፣12፡፡ በእምነታችን የእግዚአብሔር ልጆች እንደምንሆን ሁሉ በበጎ ምግባራችንም
የእግዚአብሔር ልጆች እንሆናለን፡፡ ስለሆነም በክርስትናችን ውስጥ ለበጎ ምግባራት ያለን ቦታ ለእምነት ከሚኖረን ቦታ እንዲያንስ
አንፈቅድም፡፡ በእምነት ለማደግ የምንተጋውን ያህል በበጎ ምግባራት ለማደግም እንዲሁ ደግሞ በእጅጉ እንተጋለን፡፡ ከቅዱስ መጽሐፍና
ከቅዱሳን አባቶቻችን እንዲህ ተምረናልና! “ግን እላችኋለሁ
ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ የሚረግሟችሁን መርቁ፣ ለሚጠሏችሁ መልካም አድርጉ፤ ስለሚበድሏችሁና ስለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ፡፡ በሰማያት ላለው
አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ፡፡” ማቴ 5፣44-45፡፡ ይህ ከሆነ የእግዚአብሔር ልጆች
የምንሆነው በእምነታችን ብቻ ሳይሆን በበጎ ምግባራችንም ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህም በእምነታችን ብቻ ወይም በበጎ ምግባራችንም
ብቻ አንድንም ማለት ነው፡፡ ታዲያ እውነተኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የትኛው ነው?
እውነተኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ስለመዳን የሚነግረን መዳናችንን እግዚአብሔር
በራሱ በነጻ እንደሰጠን ይህም ደግሞ ጸጋው እንደሆነ፤ ይህም በነጻ የሆነልንን ጸጋውን ደግሞ ልናምን እንደሚያስፈልገን ነው፡፡ ጸጋው
በዓለሙ ሁሉ በሙላት መሆኑና መደረጉ ብቻውን ዓለሙ ይህንን ጸጋ እስካላመነና እስካልተቀበለ ድረስ ሊድን አይቻለውምና ይህንን ጸጋ
ማመን ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ጸጋ ከታመንን በኋለ ደግሞ እንዳመንን እንዲሁ ደግሞ ጸጋውን በሥራችን የምንታዘዝ ልንሆን ያስፈልገናል፡፡
ጸጋው በእምነት አድኖናል ብለን በጎውን ከማድረግ ብንሰንፍ ጸጋው ብቻውን ሊያድነን አይችልምና፡፡ “ወንድሞቻችን አሁንም በሥጋችን ሳለን በሥጋ ፈቃድ እንኖር ዘንድ አይገባም፡፡
እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞታላችሁ፤ ነገር ግን በመንፈሳዊ ሥራ
የሥጋችሁን
ፈቃድ ብትገድሉ ለዘለዓለም በሕይወት ትኖራለችሁ፡፡ በእግዚአብሔር መንፈስ የሚሠሩ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው፡፡”ሮሜ 8፣12-14፡፡ እንግዲህ መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን እንዲህ ነው! ስለ ጸጋ፣ ስለ እምነትና ስለ በጎ ምግባራት
ይነግረናል፡፡ በጸጋ ስለ መዳን፣ በእምነት ስለ መዳንና በበጎ ምግባራት ስለ መዳንም ይነግረናል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ግን አንደኛውን
ብቻ ነጥሎ መዳን በጸጋ ብቻ፣ ወይም በእምነት ብቻ፣ ወይም በበጎ ምግባራት ብቻ ነው ብሎ ግን አይነግረንም፡፡ በዚህም የተነሳ ኦርቶዶክሳዊት
ቤተ ክርስቲያናችን መዳን በጸጋው፣ በጸጋው ላይ ባለን እምነትና ከእምነታችን የተነሳ በምናደርጋቸው በጎ ምግባራት እንደሆነ ታስተምራለች፡፡
ቁ 16-17 “እኛስ የእግዚአብሔር ፍቅር ከእኛ ጋር እንዳለ አውቀን አምነናል፤ እግዚአብሔር
ፍቅር ነው፤ በፍቅር የሚኖርም ከእግዚአብሔር ጋር በፍቅር ይኖራል፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ይኖራል፡፡ በዚህም በፍርድ ቀን በእርሱ
ዘንድ መወደድን እናገኝ ዘንድ ከእኛ ጋር ያለችው የእግዚአብሔር ፍቅር ትፈጸማለች፡፡” እግዚአብሔር እርሱ ራሱ አስቀድሞ
እንደወደደንና ስለመዳናችን አንድ ልጁን ቤዛ አድርጎ እንደሰጠልን እናምናለን፡፡ በዚህ እምነታችንም ደግሞ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘትና
ልጆቹም ለመሆን ስንል ወንድሞቻችንን እንወዳለን፡፡ ክርስቶስ የሁሉ ራስ ነውና፤ እኛም ሁላችን ደግሞ ራስ የሚሆን የክርስቶስ የአካሉ
ብልቶች ነንና፡፡ በአካሉ ወስጥ ያለውን አንደኛውን ብልት ወንድማችንን ብንጠላ ራስ ወደሚሆነው ክርስቶስ ልንደርስ አንችልምና ወንድሞቻችንን
ሁሉ እንወዳለን፡፡ እናምናለን፤ ባመንነው ደግሞ ጸንተን ላመንነው እንታዘዛለን፤ ባመንነው እንኖራለን እንዳመንን እንዲሁ ደግሞ እናደርጋለን፡፡
ከዚህ የወጣ ሁሉ ከክርስትና የወጣ ነው፡፡ ክርስትና ጸጋ ብቻ፣ ወይም እምነት ብቻ፣ ወይም በጎ ምግባራት ብቻ አይደለምና፡፡ ክርስትና
ጸጋ፣ እምነትና በጎ ምግባራት በአንድ ላይ ነው እንጂ፡፡
ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ!
. . . ይቀጥላል . . .