Wednesday, November 9, 2016

ኃያላን ለምን ይወድቃሉ? ብርቱዎችስ ለምን ይደክማሉ?



(ክፍል ሦስት)
በአገልግሎቱ ውስጥ ክርስቶስን መስበካቸውን ትተው ራሳቸውን ሲሰብኩ፡- የኦርቶዶክሳዊው አገልግሎት ፍጻሜ ክርስቶስን ማክበርና ነፍሳትን ሁሉ ወደ ክርስቶስ እንዲደርሱ ማገዝ ነው፡፡ “እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ያስፈልጋል” ማለት የማይችል አገልጋይ በአገልግሎቱ እግዚአብሔርን ማክበር ስለማይችል ፍጻሜው እንደ ጅማሬው በመንፈሳዊነትና በጸጋ የሚፈጸም ሊሆን አይችልም፡፡ ዮሐ 3፣30፡፡ ብዙ አገልጋዮች በአገልግሎቱ ታዋቂዎች ከመሆንና ብዙ ተከታዮችን ከማፍራት ባሻገር እግዚአብሔርን መፍራትን ገንዘብ ማድረግና በትህትና መመላለስ የሚሳናቸው ከክርስቶስ ይልቅ ራሳቸውን ስለሚሰብኩና ከሰዎች የሚሆን ክብርን ስለሚሹ ነው፡፡ የአገልጋዮች ዋነኛ አጀንዳ የክርስቶስ መሰበክና ለሰዎች ሁሉ መገለጥ ነው፡፡ ሰዎችን ሁሉ የክርስቶስና አካሉ የምትሆን የቤተ ክርስቲያን እንዲሆኑ መርዳትና ማገዝ እንጂ ለራሳቸው ተከታዮችንና ደጋፊዎችን ማብዛት የእውነተኛ አገልጋዮች መገለጫ አይደለም፡፡ በዚህ ዘመን የምንመለከተው እውነታ ግን አገልጋዮችን በመደገፍና በመከተል ብዙ ምእመናን ቤተ ክርስቲያንን ሲያውኩ ነው፡፡ ከአበው ሐዋርያት፣ ከቅዱሳንም ግን እንዲህ አልተማርንም፡፡ ከሐዋርያት መካከል ክርስቶስን ከመስበክ በቀር ራሱን የሰበከ ማን ነው? ከቅዱሳን አበውስ ስለራሳቸው ክብር ሲሉ የተጣሉና የተከራከሩ እነማን ናቸው? የራሳቸውንስ ክብር የፈለጉ ወዴት አሉ? ከዚህ ይልቅ ግን በሀሰት ሲከሷቸውና ሲያሳድዷቸው ሁሉ ስለጌታችን ፍቅርና ክብር ሲሉ ተሰደዋል፤ መከራንም ተቀብለዋል እንጂ ስለራሳቸው ሲከራከሩና ደጋፊዎችን በማብዛት ክብራቸውንና እውነተኝነታቸውን ለመግለጥ ሲደክሙ አላነበብንም፡፡ ዛሬ ላይ በቤተ ክርስቲያን እየሆነ ያለው ግን እንዲህ አይደለም፡፡ አገልጋዮቻችን ክብርንና ምስጋናን ከላይ ከእግዚአብሔር ሳይሆን ከዚህች ምድር ከሰዎች ዘንድ የሚሹ ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ ደጋፊዎችንና ተከታዮችን ለራሳቸው ስለሚያደርጉ የተለያዩ አገልጋዮችን በሚደግፉና በሚከተሉ መካከል ጸብና ክርክር ሲሆን በየጊዜው እንመለከታለን፡፡ በዚህ ውስጥስ የእግዚአብሔር ክብርና መንፈሳዊነት ስፍራቸው ወዴት አለ? በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የክርስቶስ ተከታዮች እንድንሆን እንጂ ሰዎችን እንድንከተል አልተጠራንም፡፡ ለመንፈስ ቅዱስ ምክርና አሠራር እንድንታዘዝ እንጂ የምንወዳቸውን ሰዎች ፈቃድ እንድንፈጽምና እንድንታዘዝ አልተጠራንም፡፡ በዚህም የተነሳ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ክርስቶስን ሳይሆን ራሳቸውን የሚገልጡ፤ ሰዎችን የክርስቶስ ተከታዮች ሳይሆን የራሳቸው ተከታዮች የሚያደርጉ ብዙ ብርቱዎችና ኃያላን አገልጋዮች እግዚአብሔር ስለሚያዝንባቸው ይወድቃሉ፣ የመንፈሳዊነት ምሳሌ ከመሆንም ይልቅ የጸብና የክርክር መንስኤዎች ይሆናሉ፡፡         
ሌሎችን ብቻ እንጂ ራሳቸውን ማገልገል ሲተዉ፡- አገልጋዮች ለሌሎች የሚፈጽሙት አገልግሎት ለራሳቸውም እንደሚያስፈልጋቸው መዘንጋት የለባቸውም፡፡ መምህርነታቸው ለሚያስተምሯቸው ምእመናን እንጂ በጌታ ፊት እነርሱም እንደሌሎቹ እኩል ተማሪዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ለማስተማር ብቻ ብለው ሳይሆን ለራሳቸውም ለመማር ብለው ሊያጠኑና ቅዱሳት መጻሕፍትንም ቁጭ ብለው ሊማሩ ያስፈልጋቸዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ነው የሚነግረን፡- “አንተ ግን አይሁዳዊ ብትባል በሕግም ብትደገፍ በእግዚአብሔርም ብትመካ፥ ፈቃዱንም ብታውቅ ከሕግም ተምረኽ የሚሻለውን ፈትነኽ ብትወድ፤ በሕግም የዕውቀትና የእውነት መልክ ስለ አለኽ፥ የዕውሮች መሪ፥ በጨለማም ላሉ ብርሃን፥ የሰነፎችም አስተማሪ፥ የሕፃናትም መምህር እንደ ኾንኽ በራስኽ ብትታመን፤ እንግዲህ አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስኽን አታስተምርምን አትስረቅ ብለኽ የምትሰብክ ትሰርቃለኽን አታመንዝር የምትል ታመነዝራለኽን ጣዖትን የምትጸየፍ ቤተ መቅደስን ትዘርፋለኽን በሕግ የምትመካ ሕግን በመተላለፍ እግዚአብሔርን ታሳፍራለኽን በእናንተ ሰበብ የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ መካከል ይሰደባልና፥ ተብሎ እንደ ተጻፈ፡፡” ሮሜ 2፣17-24፡፡ አገልጋይነት የሰነፎች መደበቂያ ዋሻ   አይደለም፡፡ አገልጋዮች ሌሎችን እንደሚያስተምሩት ሁሉ ተቀምጠው ራሳቸውም መማር ያስፈልጋቸዋል፡፡ መማር ያቆመ አገልጋይ በአገልግሎቱ መቀጠል ስለማይቻለው መውደቁ አይቀርም፡፡
አገልግሎቱን በመንፈሳዊነት ከመፈጸም ይልቅ እንደተግባረ ሥጋ ሲቆጥሩት፡- አገልግሎት መንፈሳዊ ነው፡፡ መንፈሳዊ ሳይሆኑ መንፈሳዊውን አገልግሎት የሚፈጽሙ ሁሉ በአገልግሎቱ ውስጥ ራሳቸውን መጥቀም ስለማይችሉ ከጊዜ በኋላ አወዳደቃቸው ታላቅና የከፋ ይሆናል፡፡ አገልግሎት የሚኖሩትና የሚታዘዙት መንፈሳዊነትም ጭምር ነው እንጂ ሥራ አይደለም፡፡ “የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር” 1ኛ ቆሮ 9፣9 ስለተባለና በአገልገሎቱ የተነሳ ገንዘብ ስለምናገኝ አገልግሎት ሥራ እንደሆነ ልናስብ አይገባም፡፡ መንፈሳዊ ሳንሆን ለማገልገል ከሞከርን አገልግሎቱንም፣ በአገልግሎቱ ውስጥ የምንቀበለውንም ገንዘብ አብረን እናጣዋለን፡፡ “እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል።” ዮሐ 4፣24፡፡ እንደተባለ መንፈሳዊውን የእግዚአብሔር አገልግሎት በመንፈስና በእውነት የማይፈጽሙ አገልጋዮች ፍጻሜያቸው ውድቀት ነው፡፡ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ሊሆን የተጠራው የአስቆሮቱ ይሁዳ የተጣለው የተሰጠውን መንፈሳዊ አገልግሎትና ከክርስቶስ የተቀበለውን አደራ በመንፈሳዊነት መጠበቅ ስላልቻለ ነው፡፡ እንዲህ ባይሆንማ ኖሮ ከክርስቶስ አፍ ከመማር የሚበልጥ ምን ዕድል ነበረ? ነገር ግን ከክርስቶስ የተማረውንና ያየውን በመንፈሳዊነት መጠበቅ ስላልቻለ ይሁዳ ፍጻሜው ክፉ ሊሆን ችሏል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደሚነግረንም በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ታላላቅና ኃያላን የነበሩ ሰዎች መንፈሳዊነታቸውን መጠበቅ ባለመቻላቸውና በመንፈስ ማገልገል ስለተሳናቸው አወዳደቃቸው እንደታላቅነታቸው እንዲሁ ታላቅ ሊሆን ችሏል፡፡ ስለሆነም በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ካህን የነበረው አርዮስ፣ ጳጳሳት የነበሩት ንስጥሮስና መቅዶንዮስም ሲወድቁና ሲጣሉ ተመልክተናል፡፡ ዛሬም በዘመናችን የሃይማኖት መምህራን የነበሩ ሰዎች ከኃይማኖት መንገድ ሲወጡና ሥጋዊነት ሲያሸንፋቸው እኛ ምስክሮች ነበርን፡፡ እግዚአብሔር የሚራራልን ለመንፈሳዊነታችን እንጂ ለታላቅነታችንና ለኃያልነታችን አይደለም፡፡ የቱንም ያህል በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ የሚታይ ድርሻና አስተዋጽዖ ቢኖረን መንፈሳዊ እስካልሆንንና ለእግዚአብሔር ሐሳብ እስካልታዘዝን ድረስ ከመውደቅ የሚታደገን አይኖርም፡፡
“የእግዚአብሔር ጸጋ ለማንም እንዳይጐድለው፥ ብዙዎቹም የሚረክሱበት አንድ መራራ ሥር ወደ ላይ በቅሎ እንዳያስጨንቅ፥ ሴሰኛም የሚኾን እንዳይገኝ፥ ወይም ስለ አንድ መብል በኵርነቱን እንደ ሸጠ እንደ ዔሳው ለዚህ ዓለም የሚመች ሰው እንዳይኾን ተጠንቀቁ። ከዚያ በኋላ እንኳ በረከቱን ሊወርስ በወደደ ጊዜ እንደ ተጣለ  ታውቃላችኹና፤ በእንባ ተግቶ ምንም ቢፈልገው ለንስሓ ስፍራ አላገኘምና።” ዕብ 12፣15-17፡፡ ዛሬ ብንቆምም ነገ ደግሞ ልንወድቅ እንችላለንና ጥንቃቄን ገንዘብ ልናደርግ ይገባናል፡፡ ኃይላችን ከእግዚአብሔር የተነሳ፣ በቤቱና በአገልግሎቱ ታማኞች አድርጎ ከቆጠረንና ዕድሉን ከሰጠን ከብዙ ምህረቱና ርህራኄው የተነሳ መሆኑን መዘንጋት አይገባም፡፡ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ ታላላቆችና ኃያላን ሆነን መገለጣችን በድካማችን ውስጥ ከሚሠራውና ከሚያግዘን ከክርስቶስ ጸጋ የተነሳ ነው፡፡ ይህንን መርሳት በጀመርንበት ጊዜ ግን እንወድቃለን፣ የሰልፍ እቃ ጦራችንም ይጠፋብናል፡፡ ‘‘ኃያላን እንዴት ወደቁ! የሰልፍም ዕቃ እንዴት ጠፋ!’’ 2ኛ ሳሙ 1፣27፡፡ ኃያላን ሆይ ከኃያልነታችን እንዳንወድቅ፣ የሰልፍ ዕቃ ጦራችንም እንዳይጠፋ መንፈሳውያን እንሁን! መንፈሳዊውን አገልገሎትም በመንፈስና በእውነት እንፈጽም፡፡
ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ!

መዳንና በጎ ምግባራት በመጀመሪያይቱ የቅዱስ ዮሐንስ መልዕክት



ምዕራፍ ሦስት (ክፍል ሁለት)
ቁ. 14-15 ‘‘ እኛ ግን ከሞት ወደ ሕይወት እንደተሻገርን እናውቃለን፣ ባልንጀራችንን እንወዳለንና፤ ባልንጀራውን የማይወድ ግን በጨለማ ይኖራል፡፡ ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳይ የሆነም ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት በእርሱ እንደማይኖር ታውቃላችሁ፡፡’’ ዳግመኛም ቅዱስ ዮሐንስ ከሞት ወደ ሕይወት መሸጋገራችን የሚታወቀው ወንድሞቻችንን በመውደዳችንና ለሰው ልጆች ባለን ፍቅር እንደሆነ ይነግረናል፡፡ ወንድሙን የሚጠላ ሰው የዘለዓለም ሕይወት በእርሱ ሊኖር እንደማይችል በማያሻማ ቃል ተቀምጦልናል፡፡ ከዚህ የምንማረው ክርስትናችን/የመዳን መንገዳችን ወንድሞቻችንን በመውደድም ጭምር የምንኖረው መሆኑን ነው፡፡ በእርግጥ መዳናችን በመስቀሉ ሥራ በሆነልንና በተቀበልነው ጸጋ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ የማዳን ሥራ ላይ ባለን እምነት ቢሆንም በበጎ ምግባራትም ሁሉ የምንታዘዘውና የምንፈጽመውም ጭምር እስከሆነ ድረስ ወንድሞቻችንን በመውደድ በድርጊት የሚገለጽ ተግባራዊ ሕይወት መሆኑን ሐዋርያው አስተምሮናል፡፡ በዚህም የተነሳ በየዕለቱ የምንፈጽመውና የምናድግበት እንጂ አንድ ጊዜ ሆኖልን ተቀብለነዋል ብለን ቸል የምንለው አይደለም፡፡ በክርስቶስ ቤዛነት ላይ ያለ እምነታችን የድኅነታችን መጀመሪያ ነው፡፡ የማያምን ሰው ወደ መዳን ሊደርስ  አይቻለውምና፡፡ እምነት ወደ ድኅነት የሚያደርስ መንገድ ቢሆንም ማመናችን ብቻውን ግን ለመዳናችን ዋስትና አይደለም፡፡ ስለሆነም እንዳመንን እንዲሁ ባመንንበት ነገር መጽናትና ለአዳነን አምላክ ፈቃድ መታዘዝና ቃሉንም መፈጸም እንዳለብን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ ‘‘በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ ከሚያደርግ በቀር አቤቱ! አቤቱ! የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግስተ ሰማያት የሚገባ አይደለም፡፡ በዚያች ቀን ብዙዎች አቤቱ! አቤቱ! በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን? በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን? በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል፡፡ ያን ጊዜ ከቶ አላውቃችሁም፤ አመጽን የምታደርጉ ሁላችሁ ከእኔ ራቁ እላቸዋለሁ፡፡’’ ማቴ 7፣21-23፡፡ እዚህ ላይ የተጠቀሱት ሰዎች የእምነት ሰዎች አልነበሩምን? በትክክል የእምነት ሰዎች ነበሩ፡፡ እንዲያውም በስሙ አምነው በስሙ ትንቢትን የተናገሩ፣ በስሙ አጋንንትን ያወጡ፣ በስሙ ብዙ ተአምራትን ያደረጉ ሰዎች ነበሩ፡፡ ታዲያ እንዴት ወደመንግስተ ሰማያት የማይገቡ ሊሆኑ ቻሉ? በምግባራቸውና በኑሮ ፍሬያቸው እግዚአብሔርን ደስ ስላላሰኙት ነው፡፡ ስለሆነም ለመዳን እምነት አስፈላጊ ቢሆንም በበጎ ምግባራትና በመንፈሳዊ ተጋድሎ መጽናትም የእምነትን ያህል አስፈላጊ ነው፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በእምነታችን ጸንተን በተግባር የተገለጠና በበጎ ምግባራት የተደገፈ ክርስትና ሊኖረን እንደሚያስፈልግ እንዲህ ሲል ጽፎልናል፡- ‘‘ ወንድሞቻችን ሆይ አባቶቻችን ሁሉ ደመና እንደጋረዳቸው ሁሉም በባህር መካከል አልፈው እንደ ሄዱ ልታውቁ እወዳለሁ፡፡ ሁሉንም ሙሴ በደመናና በባሕር አጠመቃቸው፡፡ ሁሉም ያንን መንፈሳዊ ምግብ ተመገቡ፡፡ ሁሉም ያንን መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፤ ይኸውም በኋላቸው ከሚሄደው ከመንፈሳዊ ዐለት የጠጡት ነው፤ ያም ዐለት ክርስቶስ ነበረ፡፡ እግዚአብሔር ግን ከእነርሱ በሁሉም ደስ አላለውም፤ ብዙዎቹ በምድረ በዳ ወድቀዋልና፡፡ እነርሱ እንደተመኙ እኛ ደግሞ ክፉ እንዳንመኝ እነርሱ ለእኛ ምሳሌ ሆኑልን፡፡ . . . እነርሱን ያገኛቸው ይህ ሁሉ ነገር በኋላ ዘመን  ለምንነሣው ለእኛ ትምህርትና ምክር ሊሆነን ምሳሌ ሊሆን ተጻፈ፡፡’’ 1ኛ ቆሮ 10፣1-11፡፡ እግዚአብሔር ከግብጽ ባወጣቸው በህዝቡ ደስ ያልተሰኘው ስለምን ነበር? ቃሉን ስላላመኑት ነበርን? ችግራቸው የእምነት አልነበረም፡፡ ስላመኑትማ በተአምራቱ ከግብጽ አውጥቶ ተስፋ ያደረገልንን ከነዓንን ያወርሰናል ብለው በእምነት ከግብጽ ወጥተዋል፡፡ በእምነት ቢወጡም በመንገዳቸው ለአምላካቸው ሐሳብ፣ ለቃሉና ለፈቃዱ ሊታዘዙ ስላልቻሉ እግዚአብሔር አምላካቸው ደስ አልተሰኘባቸውም፤ በዚህም የተነሳ ቃል የገባላቸውን ከነዓንን ሳያወርሳቸው ቀርቷል፡፡ ‘‘ እነርሱን ያገኛቸው ይህ ሁሉ ነገር በኋላ ዘመን  ለምንነሣው ለእኛ ትምህርትና ምክር ሊሆነን ምሳሌ ሊሆን ተጻፈ፡፡’’ እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ እኛም በክርስቶስ ደም በተዋጀንበት ቤዛነቱ መንግስቱን እንደምንወርስ እናምናለን፤ ስላመንን ብቻ ግን መንግስቱን ልንወርስ ስለማንችል ላመንነውና ቤዛነትን ላገኘንበት ለጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፈቃድ፣ ለቃሉም መታዘዝ እንዳለብን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ መታዘዝን እንቢ ካልን ግን እምነታችን ብቻውን መንግስቱን አያወርሰንም፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ ዝቅ ብሎ በቁ. 12 ላይ ‘‘አሁንም ያ ቆሜያለሁ ብሎ በራሱ የሚታመን ሰው እርሱ እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ’’ ያለው፡፡ በእርግጥ በክርስቶስ ላይ ያለን እምነት ነው የሚያቆመን፤ ነገር ግን ቆሜያለሁ ስንል ምናልባት ወድቀን እንዳንገኝ በእምነታችን ወስጥ ሆነን የምንፈጽመውን መታዘዝና የምናደርጋቸውን በጎ ምግባራት ማስተዋልና ራሳችንንም መፈተሽ ይጠበቅብናል፡፡ ያለ በጎ ምግባራት የምንኖረው ክርስትና የለንምና፡፡
በስሙ እናምን ዘንድ የጠራን አምላካችን የተወልን ምሳሌው በስሙ እንድናምን ብቻ ሳይሆን እርሱ እንዳደረገ እንድናደርግና ፍለጋውንም እንድንከተለው ነው፡፡ ‘‘ለዚህ ተጠርታቸኋልና ክርስቶስም እኮ ፍለጋውን ትከተሉ ዘንድ ምሳሌውን ሊተውላችሁ ስለእናንተ መከራን ተቀብሏል፡፡’’ 2ኛ ጴጥ 2፣21፡፡ ከዚህ የምንማረው ምንድን ነው? ክርስትና በክርስቶስ ማመን ብቻ ሳይሆን የክርስቶስን ፍለጋ መከተል፤ እርሱ እንደተመላለሰም መመላለስ መሆኑን ነው፡፡ ትክክለኛው የክርስትና ትምህርት ሰዎች ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ እንዲያምኑ ብቻ የሚያስተምር ሳይሆን ከክርስቶስ ኢየሱስ እንዳዩትና እንደተማሩት እንዲኖሩ የሚያስተምርም ነው፡፡ ‘‘ . . . ሥራችሁ ለክርስቶስ መንግስት እንደሚገባ ይሁን፡፡ . . . ይህንንም ጸጋ እግዚአብሔር ሰጥቷችኋል፤ ነገር ግን ስለእርሱ መከራ ልትቀበሉም ነው እንጂ ልታምኑበት ብቻ አይደለም፡፡’’             ፊል 1፣27-29፡፡ እውነተኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ይህ ነው፣ እንድናምን ብቻ ሳይሆን ባመንነው ጸንተን በሥራ እንድንታዘዝ፣ ኑሯችንና ሥራችን ሁሉ ለክርስቶስ መንግስት እንደሚገባ እንዲሆን፣ በስሙ እንድናምን ብቻ ሳይሆን ስለስሙ መከራን እንድንቀበል፡፡ የምንቀበለው መከራ የሚጀምረው ደግሞ ከገዛ ማንነታችን፣ ከራሳችን ፈቃድና ከሥጋችን ሐሳብ ነው፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳለን፡-‘‘ መንፈስ ይሻልና ሥጋ ግን ደካማ ነው፡፡’’ ማቴ 26፣41፡፡ ክርስትና ሥጋን ማሸነፍ፣ የመንፈስንም ፈቃድ መፈጸም ነው፡፡ ክርስትና ይህን ሁሉ የሚያካትት ሰፊ ትምህርት ነው እንጂ አንዱን ብቻ ነጥለን ወስደን ሌላውን የምንተወው አይደለም፡፡ ስለእምነት እንደምናስተምር ሁሉ ስለ በጎ ምግባራትም እናስተምራለን፤ ስለ እግዚአብሔር ጸጋ የምናስተምረውን ያህል ስለ ሰው ልጆች ድርሻና ሱታፌም እናስተምራለን፡፡
. . . ይቀጥላል . . .
ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ!

ጸሎተ ቡራኬ




  •         ልዩ ሦስት የምትሆን አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ሆይ የሚፋቀሩ የክርስቶስ ወገኖች የሚሆኑ ሕዝብህን በሰማያውያንና በምድራውያን በረከት ባርክ፡፡

  •        በእኛ ላይም የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ላክ፤ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንህንም ደጆች በምሕረትና በሃይማኖት እንዲከፈቱ አድርግልን፡፡ እስከ መጨረሻዪቱ  ሕቅታም ድረስ ልዩ ሦስትነትህን ማመንን ፈጽምልን፡፡
  •       ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ የታመሙ ወገኖችህን ጎብኝ፤ የሄዱትንና እንግዶች የሆኑትን አባቶቻችንና ወንድሞቻችንን መርተህ በሰላምና በጤና ወደ ቤታቸው መልሳቸው፡፡
  •       የሰማዩን ነፋስ ባርክ፡፡
  •       ዝናሙንም፤ በዚህች ዓመት የሚያፈራውን የምድሩን ፍሬ እንደ ቸርነትህ ባርክ፡፡ ዘወትር ተድላንና ደስታን አድርግ፡፡
  •       ሰላምህንም አጽናልን፤ ሁልጊዜ ለኛ በጎ ነገርን ሊያደርጉልን ጽኑዓን የሚሆኑ የነገሥታቱን ልቡና መልስ፡፡ በቅድስት ቤተ ክርስቲያንህ ሁል ጊዜ ለሚሰበሰቡ ለቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ፍቅርን ስጥ፡፡ ለሁሉም ለእያንዳንዱ በየስማቸው ኃያላን በሚሆኑ በነገሥታቱ ፊት ሰላምን አብዛላቸው፡፡
  •          አምላካችን ሆይ በቀናች ሃይማኖት ሆነው ያንቀላፉትንና ያረፉትን የአባቶቻችንንና የወንድሞቻችንን፤ የእህቶቻችንንም ነፍስ አሳርፍ፡፡
  •          አምላካችን ክርስቶስ በኢየሩሳሌም ሰማያዊት ዋጋቸውን ይከፍላቸው ዘንድ ዕጣንና ቁርባን ወይንና ሜሮን ዘይትም መጋረጃም የንባብ መጻሕፍቶችን የቤተ መቅደስንም ንዋያት በመስጠት የሚያገለግሉትንም ባርክ፡፡
  •        ይቅርታን ያገኙ ዘንድ ከእኛ ጋራ የተሰበሰቡትንም ሁሉ አምላካችን ክርስቶስ ሆይ ይቅር በላቸው፡፡ በሚያስፈራና በሚያስደነገጥ በመንበርህ ፊት ምጽዋት ያመጡትንም ሁሉ ተቀበላቸው፡፡
  •        የተጨነቀችዪቱን ነፍስ ሁሉ አሳርፍ፤ በሰንሰለት የታሠሩትን፤ በስደትና በምርኮ ያሉትንም፡፡ መሪር በሆነ አገዛዝ የተያዙትንም አምላካችን ሆይ በቸርነትህ አድናቸው፡፡
  •          መምህራችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ወደአንተ በምንማልድበት ጊዜ እንድናስባቸው ያዘዙንን ሁሉ በሰማያዊት መንግሥትህ አስባቸው፡፡ ኃጥእ ባርያህን እኔንም አስበኝ፡፡
  •         አቤቱ ሕዝብህን አድን ርስትህንም ባርክ፡፡ ጠብቃቸው እስከ ዘለዓለምም ከፍ ከፍ አድርጋቸው፡፡