Friday, January 15, 2016

ጸሎት ለመንፈሳዊ ሕይወት ዕድገት



ጸሎት ለመንፈሳዊ ሕይወት ዕድገት
ጸሎት ምንድን ነው? ጸሎት ጸለየ ከሚለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም መለመን፣ መማጸን የሚለውን ትርጉም ይሰጠናል፡፡ ጸሎት ሰው ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብበትና የሚነጋገርበት  መንፈሳዊ መንገድ ነው፡፡ ጸሎትስ ሰው ከልዑል እግዚአብሔር ጋር የሚነጋገራት ነገር ናት፡፡ ፈጽሞ እያመሰገነ ጌትነቱን አውቆ በደሉን አምኖ እርሱን ደስ የሚያሰኝበትንም ሽቶ የሚነጋገራት ነገር ናት (ፍትሕ መንፈሳዊ አን 14 ቁ 528)፡፡ ጸሎት በእግዚአብሔር ፊት እንድንቆምና ከአምላካችን ጋር እንድንነጋገር የሚያስችለን ታላቅ መንፈሳዊነት ነው፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት ‘‘አቤቱ፥ ፊትህን እሻለሁ ልቤ አንተን አለ።’’  እንዳለ ጸሎት ዘወትር የእግዚአብሔርን ፊት መሻት ነው፡፡ መዝ 27፣8፡፡ ስንጸልይ ከአምላካችን ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር እንችላለን፤ ይህም ንግግራችን ለሕይወታችን ምሪትን የምንቀበልበት ነው፡፡ ጸሎት ወደ እግዚአብሔር የሚያደርስ መንገድ ነው፡፡ ዘወትር የሚጸልይ ሰው ወደ እግዚአብሔር ሳይደርስ አይቀርም፡፡ ‘‘በጥዋት ጸሎቴ ወደ ፊትህ ትደርሳለች።’’ እንዳለ ቅዱስ ዳዊት እግዚአብሔርን የምትሻ ነፍስ ዕለቱን በእግዚአብሔር ፊት በመሆንና ከእርሱም ጋር በመነጋገር ትጀምረዋለች፡፡ መዝ 88፣13፡፡ ጸሎት የሰው ልጆች  ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኙበት ድልድይም ነው፡፡ ከስጋዊ ሃሳብና ድካም ርቀን ወደ እግዚአብሔር ለመድረስ በመንፈስ የምንሻገርበት መንፈሳዊ የመሸጋገሪያ ድልድይ ነው፡፡  ልክ ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ እንዳያው መሰላል ከምድር አስከ ሰማይ የሚደርስ መወጣጫም ነው፡፡ በምድር ላይ ሳለን በመንፈስ ከፍ በማለት ወደ ሰማይ የምንደርስበትና በአምላካችን ፊት የምንሆንበት፣ ከእግዚአብሔር የሆነውን ሰማያዊ ሃሳብ የምንቀበልበት የመወጣጫ መሰላል ነው፡፡ ጸሎት የቃላት ንግግር ብቻ ሳይሆን በጠለቀ መረዳትና በታላቅ ተመስጦ ውስጥ ሆነን ነፍሳቸንን፣ ሐሳባችንንና ስሜታችንን ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት የምናደርግበት መንፈሳዊ ተግባር ነው፡፡ 
ምንም እንኳን ጸሎት ወደ እግዚአብሔር የሚያደርስ መንገድ ቢሆንም ሁሉም ጸሎት ወደ እግዚአብሔር ያደርሳል/ያቀርባል ማለት አይደለም ፡፡ ጸሎት ወደ እግዚአብሔር ሊያደርስና  ኃይል ሊኖረው የሚችለው እንደፈቃዱ ሆነን ስንለምንና በፈሪሀ እግዚአብሔር መጸለይ ስንችል ብቻ ነው፡፡ ‘‘የጻድቅ ሰው ጸሎት በስራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች፡፡’’ ያዕ 5፣16 ተብሎ እንደተጻፈ ኃይል የሚፈጸምበት ጸሎት የጻድቅ ሰው ጸሎት ነው፣ የክፉዎችን ጸሎት ግን አምላካችን ይጸየፋል፡፡ ‘‘እግዚአብሔር ከኅጥኣን ይርቃል የጻድቃንን ጸሎት ግን ይሰማል፡፡’’ እንዲል ምሳ 15፣29፡፡
ለጸሎት በቆምንበት ቅጽበት ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት መቆማችንን እናስባለን፡፡ ‘‘በፊቱ የቆምሁት የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር’’ 1ኛ ነገ 17፣1 እንዳለ ነቢየ እግዚአብሔር ኤልያስ ጸሎት  በእግዚአብሔር ፊት የምንቆምበት እርግጠኛ ሐሳብ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ፊት መቆማችንን ሳናስብና ሳናምን ለጸሎት በፊቱ አንቆምምና፡፡ ጸሎት ከውስጣችን የሚመነጭ  የነፍሳችንና የልባችን መቃተት እንጂ የቃላት ንባብና ድግግሞሽ አይደለም፡፡ ጸሎት በመንፈስ የምንረዳው እንጂ በቃላት ውበት የምንገልጸውና የምናስረዳው ተራ ድርጊት አይደለም፡፡ ማስመሰል በሌለበት እውነተኛ ስሜት ውስጥ ሆነን፣ በተመስጦ፣ በማስተዋልና በመረዳት፣ በተሰቀለ ኅሊና፣ በተሰበረ መንፈስ፣ ስለኃጢአቱ በተጸጸተ ልብ ወደ አምላካችን የምንጠጋበት መጠጋትና ከፈጣሪያችን ጋር የምንነጋገርበት መነጋገር ስለሆነ  ጸሎት በተግባር የሚገለፅ ታላቅ መንፈሳዊነት እንጂ ተራ የቃላት ስብስብ አይደለም፡፡ ጸሎት በመንፈስና በነፍስ ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር ነውና በዝምታ ውስጥ ሆነን እንኳን በህሊናችንና በሃሳባችን ወደ እግዚአብሔር ደርሰን ልንነጋገር እንችላለን፡፡ ጸሎት እግዚአብሔርን መናፈቅም ነውና ወደ እግዚአብሔር ለመድረስ የምንቸኩልበትና የምንናፍቅበት የነፍስ መሻት ነው፡፡ ‘‘ዋላ ወደ ውኃ ምንጭ እንደሚናፍቅ፥ አቤቱ፥ እንዲሁ ነፍሴ ወደ አንተ ትናፍቃለች።’’ መዝ 42፣1፡፡ ጸሎት ወደ ሕይወት ውኃ ምንጭ እግዚአብሔር ለመድረስ የምንጠማው መጠማት ነውና ከነፍሳችንና ከመንፈሳችን የሚወጣ ጥልቅ ስሜት እንጂ ቃላትና ንግግር ብቻ አይደለም፡፡
     ‘‘አምላኬ፥ አምላኬ፥ ወዳንተ እገሠግሣለኹ፤ ነፍሴ አንተን ተጠማች፥ ሥጋዬ አንተን እንዴት ናፈቀች’’ እንዳለ ቅዱስ ዳዊት ጸሎት ስራ ወይም ልንፈፅመው የሚገባ አስገዳጅ ሕግ ሳይሆን ወደንና ፈቅደን የመንፈፅመው የነፍሳችንና የስጋችን የእግዚአብሔር ናፍቆትና በፊቱ ለመሆን የምናደርገው መጓጓት ነው፡፡ የሚጸልይ ሰው አምላኩንና በአጠገቡ ያለውን ወንድሙን የሚወድ ነው፡፡ ያለፍቅር የሚጸልይ ሰው ወደ እግዚአብሔር መድረስ ስለማይችል ጸሎቱ መጽናናትንና የልብ እረፍትን አያመጣለትም፡፡ እግዚአብሔር የአፋችንን ንግግርና የቃላቱን ማማር ሳይሆን በልባችን ውስጥ ያለውን በጎ ሃሳብ ነው የሚሻው፡፡ ለዚህም ነው ‘‘ይህ ህዝብ በአፉ ወደ እኔ ይቀርባል፣ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው’’ ሲል የተናገረው፡፡  ኢሳ 29፣13፡፡   ስለዚህ  ጸሎታችንን  በፍቅር የሚደረግ፣ የወንድምን በደል ይቅር የሚልና የሚታገስ ሊሆን ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር የእጁ ስራ የሆኑ ፍጥረቱን ሁሉ የሚወድና የሚቀበል ስለሆነ ወንድምን በሚጠላ ልብ የምንጸልየው ጸሎት እግዚአብሔርን ደስ አያሰኝም፡፡ ብዙ በደላችንን የተወልን ጌታ እኛም የወንድሞቻችንን በደል እንድንተውላቸው ይፈልጋል፡፡ ስለሆነም በተሰበረ መንፈስና በትሑት ሰብዕና፣ ስለድካሙ በሚያዝንና በሚጸጸት ማንነት፣ ወንድሙን በሚወድና ይቅር በሚል ልቡና ውስጥ ሆነን መጸለይ ካልቻልን ጸሎታችን በፊቱ ሊወደድልን አይችልም፡፡ ስለዚህም ነገር እግዚአብሔር አምላካችን እንደህ ሲል ተናግሮናል፡- ‘‘እጃችሁን ወደ እኔ ብትዘረጉ ዐይኔን ከእናንተ እሰውራለሁ ልመናንም ብታበዙ አልሰማችሁም፡፡ እጆቻችሁ በደም ተሞልተዋል ፡፡’’  ኢሳ 1፣15፡፡ ጸሎት ሁሉን በሚችል ጌታ ፊት ከድካማችን እንዲያበረታንና ከኃጢአታችን ሁሉ እንዲያነጻን ነፍሳችንን በፊቱ የምናፈስበት ማፍሰስ ነው፡፡ ‘‘ልመናዬን በፊቱ አፈሳለኹ’’ እንዳለ ቅዱስ ዳዊት የነፍሳችንንና የስጋችንን ሁሉ መሻት፣ ጭንቀትና መረበሽ ሁሉ በፊቱ የምናፈስበትና የምናርፍበት ታላቅ እረፍት ነው፡፡ ጸሎት በእግዚአብሔር ፊት ድካማችንን የምናምንበትና ምሕረቱን የምንለምንበት የይቅርታና የንስሓ ልመናም ነው፡፡ ይህም እውነቱን በፊቱ በመግለጥ እርቅንና ይቅርታን የምንቀበልት የትሑታን መንገድ ነው፡፡ እራሱን በማጽደቁ አንዳች ሳይቀበል ወደቤቱ እንደተመለሰው ፈሪሳዊ ሳይሆን ጥፋቱንና ድካሙን በማመን አምላኩን እንደለመነውና ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ ብሎ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳመሰገነው እንደቀራጩ ሰው ለጸሎት በቆምንበት ቅጽበት ሁሉ በፊቱ መበደላችንንና ሕጉን መተላለፋችንን መርሳት አይገባንም፡፡ሉቃ 18፡13፡፡ ከዚህ ይልቅ ግን እንዲህ ልንል ያስፈልገናል፡- ‘‘አቤቱ፥ እንደ ቸርነትኽ መጠን ማረኝ፤ እንደ ምሕረትኽም ብዛት መተላለፌን ደምስስ። ከበደሌ ፈጽሞ እጠበኝ፥ ከኀጢአቴም አንጻኝ፤ እኔ መተላለፌን ዐውቃለኹና፥ ኀጢአቴም ዅልጊዜ በፊቴ ነውና። አንተን ብቻ በደልኹ፥ በፊትኽም ክፋትን አደረግኹ፥ በነገርኽም ትጸድቅ ዘንድ በፍርድኽም ንጹሕ ትኾን ዘንድ። እነሆ፥ በዐመፃ ተፀነስኹ፥ እናቴም በኀጢአት ወለደችኝ። እንሆ፥ እውነትን ወደድኽ፤ የማይታይ ስውር ጥበብን አስታወቅኸኝ። በሂሶጵ ርጨኝ፥ እነጻማለኹ፤ እጠበኝ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እኾናለኹ፡፡’’ መዝ 50፣1-7፡፡
በእንዲህ ያለ መረዳትና ተመስጦ የምንጸልየው ጸሎት እጅግ ታላቅ የሆነ ኃይልን ያደርጋል፡፡ ያዕ 5፣16፡፡ በመንፈሳዊ ሃሳብና መረዳት የሚደረግ ጸሎት ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ስለሚያደርስ የጠላትን ኃይልና ተግዳሮት ሁሉ ለማሸነፍ ያስችላል፡፡ እንዲህ ባለ ሁኔታ የሚደረግን ጸሎት አጋንንት ክፉኛ ይፈሩታል፡፡
 ይቀጥላል …


ወጣትነትና ክርስትና



ወጣትነትና ክርስትና
ክርስትና  በእድሜ፣ በጾታ  እንዲሁም  በትምህርት  ደረጃ  የሚወሰን  ሳይሆን  በየትኛውም  ሁኔታ  ውስጥ ሆነን  የምንመራበት  ሕይወት  ነው፡፡  ‘‘በጊዜውም አለጊዜውም ጽና’’ እንዲል፡፡ 2  ጢሞ  42  ፡፡ በስጋችንና በነፍሳችን፣ በሃሳባችንና በድርጊታችን፣ በመውጣትና መግባታችን፣ በኑሯችን ሁሉ እግዚአብሔርን የምንፈልግበትና ከእርሱም ጋር ኅብረት የምናደርግበት የተቀደሰ ሕይወት ነው፡፡ ‘‘ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ በብርሃን ብንመላለስ ለእያንዳንዳችን ኅብረት አለን’’ ተብሎ እንደተጻፈ ክርስትናችን በብርሃን እየኖርንና እየተመላለስን ከአምላካችን ጋር  ኅብረት የምናደርግበትም ነው፡፡ 1ኛ ዮሐ 1፣7፡፡ ወጣትነት  በሰው ልጆች አጠቃላይ ሕይወትና በክርስቲያናዊ ኑሮ ውስጥ ትልቅ  ድርሻ  አለው፤  ምክንቱም  የወጣትነት ዘመን ቢሰሩ የማይደክሙበት፣ ቢሮጡ የሚቀድሙበት፣   ሲያረጁ  ሚጦሩበትን  ሀብትንብረት የሚያፈሩበት የእድሜ ክልል በመሆኑ ነው፤ ስለሆነም በክርስትና ሕይወት ውሥጥ ስንኖር ጉዟችን ሁሉ የተሳካ፣ በማስተዋል የሚደረግና እግዚአብሔርንም ደስ የሚያሰኝ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ወጣትነታችን ስጋችንንም ሆነ ነፍሳችንን የምንቀድስበት ሕይወት እንዲሆን ጥረት ማድረግ የሁላችንም ድርሻ ነው፡፡ ‘‘ማንም ሊሠራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለች፡፡’’ እንደተባለ ወጣትነታችን የማንሰራበት ወቅት ከመድረሱ በፊት ያለ የስራ ክፍለ ጊዜ ነው፡፡ ዮሐ 9፣4፡፡ ‘‘የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ ደስ አያሰኙም የምትላቸውም ዓመታት ሳይደርሱ’’ የተባልነውም ወጣትነታችን የጉብዝናችን ወራት ስለሆነ ነፍሳችንንና ስጋችንን ሊጠቅም የሚችል በጎ ስራ እንድንሰራበት ነው፡፡ መክ 12፣1፡፡
የወጣትነት ሕይወት ፈተናዎች
     1.ትእቢት
የወጣትነት  ጊዜ ስጋችን ብርቱና ንቁ የሚሆንበት ወቅት ስለሆነ ብዙውን ጊዜ ሁሉን ነገር ያደረግነውና ማድረግ የምንችለው፣ ሁሉም  ነገር በጥረታችንና በእጃችን ብርታት ብቻ እንደሆነ ልናስብ እንችላለን፡፡ ሁሉም ነገር የራሳችን  ድካም ፣ የስራችን፣ የእውቀታችንና የጥንካሬያችን ውጤት እንደሆነ  እናስባለን፡፡ ይህም በእግዚአብሔር ላይ የሚኖረን መደገፍ እንዲቀንስ ስለሚያደርግ በመንፈሳዊ ሕይወታችን እንድንዝልና ከእግዚአብሔር ኅብረት እንድንርቅ የሚያደርግ የዲያብሎስ ውጊያ ነው፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ ሲል የመከረን፡- ‘‘በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችኹ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤ በዓለም ያሉት ወንድሞቻችኹ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችኹ በእምነት ጸንታችኹ ተቃወሙት።’’ 1ኛ ጴጥ 5፣8፡፡ በእግዚአብሔር አለመደገፍና ሁሉን ለራስ አቅም መተው ክርስትናችንን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ የሚመራ ታላቅ ውጊያ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ሰው እጁና ብርታቱ ብቻውን የሚፈለገውን ውጤት እንደሚያመጣ አያስብም፤ ከዚህ ይልቅ ሁልጊዜም ይህን ቃል ያስባል፡- ‘‘በልብኽም፦ ጕልበቴ የእጄም ብርታት ይህን ሀብት አመጣልኝ እንዳትል። ነገር ግን፥ ዛሬ እንደ ኾነ ለአባቶችኽ የማለውን ቃል ኪዳን ያጸና ዘንድ፥ ሀብት ለማከማቸት እርሱ ጕልበት ሰጥቶኻልና፥ አምላክኽን እግዚአብሔርን ዐስብ።’’ ዘዳ 8፣17-18፡፡ ስለሆነም አንድ ክርስቲያናዊ ወጣት ከእግዚአብሔር በቀር ሌላ ተስፋ የሚያደርገው፣ የሚደገፍበትና የሚታመንበት ኃይል ሊኖረው አይገባም፡፡
   2. ችኩልነት
ችኩልነት  ላው  የወጣቶች  የክርስትና ሕይወት ፈተና  ወይም  እንቅፋት  ሲሆን  ነገሮችን ተረጋግቶ ባለማሰብና ባለማስተዋል ወደተግባር  እንድንገባ የሚገፋን ኃይል ነው፡፡ ሁሉም ነገር እኛ በምንፈልገው ልክ፣ መጠንና ፍጥነት ሆኖ ካላየን የምንልበት የጥድፊያ ሕግ ነው፡፡ ይህም ደግሞ ከእውነቱ ዓለም ሕግ ጋር ስለሚጣረስ ባሰብነው ልክ ሆኖ ሳናገኘው ስንቀር ተስፋ እንድንቆርጥ፣ ለሕይወት ያለን ግምት እንዲቀንስ፣ ደስተኞች እንዳንሆን፣ ከእውነታው ጋር እንድንጣላና በእግዚአብሔርም ላይ ያለን መደገፍ እንዲቀንስ ያደርገናል፡፡ እንደ ክርስቲያን ልናደርገው የሚገባን ነገር ቢኖር ሁሉም የሚሆንበትና የሚከናወንበት የራሱ የሆነ የጊዜ ዑደት እንዳለው ተረድተን የድርሻችንን እየተወጣን ሌላውን ለጊዜ ጌታ ለእግዚአብሔር መተውና እርሱንም መጠበቅ ነው፡፡ መቸኮላችን ባለን ነገር እንዳናመሰግንና ደስተኞች እንዳንሆን ስለሚያደርገን ቁጡዎችና ተረጋግተን ማስተዋል የማንችል እንድንሆን ያደርገናል፡፡ ‘‘በነፍስኽ ለቍጣ ችኵል አትኹን ቍጣ በሰነፍ ብብት ያርፋልና።’’ መክ 79፡፡

   3.  አለማስተዋል
ነገሮችን ተረጋግቶ ማስተዋል መቻል የበሳል ክርስቲያን መገለጫ ነው፡፡ ገንዘብ  በሃያ  አመት  ሌብ  በአርባ  አመት  የሚባለውም ብዙ ጊዜ ወጣትነት ከማስተዋልና ከመረጋጋት ሕይወት ሲርቅ ስለሚታይ ነው፡፡ ነገሮችን ተረጋግቶ ማስተዋል አለመቻል በመንፈሳዊ ሕይወታችንም ሆነ በተግባረ ስጋችን መጠቀም ያለብንን ያህል እንዳንጠቀም፣ ከእግዚአብሔርም ጸጋንና በረከትን እንዳንቀበል እንቅፋት ይሆንብናል፡፡ ማስተዋል ካልቻልን ምን ማድረግና ምን አለማድረግ እንዳለብን መለየት ያቅተናል፣ ስለሆነም ሕይወታችን የእግዚአብሔር ሃሳብና ምክር ያልተገለጠበት፣ ከእግዚአብሔር ሃሳብ በእጅጉ የራቀ፣ ከዘላለማዊ መንግስቱም በአፍኣ/ውጪ ይሆናል፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ኀይል አለ፤ ለርሱ ምክርና ማስተዋል አለው።” ተብሎ እንደተጻፈ ከእግዚአብሔር የሆነውን ይህን ጥበብ፣ ኀይል፣ ምክርና ማስተዋል ገንዘብ ለማድረግ መጣር ሕይወታችንን የተቃና ያደርግልናል፡፡ ኢዮ 12፣13፡፡ በምድር ላይ የምንኖረው ሕይወታችን ዝም ብለን በአጋጣሚ የምንኖረው ሳይሆን በእግዚአብሔር ዘላለማዊ ሃሳብና ምክር የሆነም ስለሆነ ራሳችንን ለዚህ ዘላለማዊ ፈቃድና ሃሳብ በማስገዛት እርሱን ደስ ለማሰኘት የምንጥርበት፣ በማስተዋልና በጥበብ የምንኖረው ሊሆን ያስፈልጋል፡፡ በጌታችንና በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ዕውቀት እደጉ ስለተባልን ክርስትናችን ከክርስቶስ የሆነውን ጸጋ፣ ዕውቀትና ማስተዋል በመፈለግ የምናድግበት ሕይወት ነው፡፡   2 ጴጥ 318፡፡
   4. ለዘመናዊነት ያለን የተዛባ ዕይታ
ዘመናዊነት በጣም ብዙ የሚጠቅሙ ነገሮች አንዳሉት የሚካድ አይደለም፡፡ ዘመናዊነት የጥበብ መንፈሳዊና ጥበብ ስጋዊ ውጤት በመሆኑ ብዙዎቹ በዘመናዊነት ውስጥ የተፈጠሩ የቴክኖሎጂ ግኝቶች የሰውን ልጅ  የቀን  ተቀን  ስራዎችን  በማገዝና በማቀላጠፍ ረገድ ትልቅ አስተዋጽዖ አላቸው፡፡ ጥብብ የእግዚአብሔር ስጦታ በመሆኑ የዘመን ግኝቶች ለበጎ ተግባራት እስከዋሉና እግዚአብሔርን በመፍራት እስከተጠቀምንባቸው ድረስ ምንም ጉዳት አይኖራቸውም፡፡ ስለሆነም “ሃይማኖት  አንደ  አባቶቻችን  ጥበብ  እንደጊዜያችን እንላለን፡፡ የዘመን ግኝቶችን ለእግዚአብሔር አገልግሎትና ለሰው ልጆች ሁሉ ጥቅም፣ ለፍቅርና ለበጎ ስራ መጠቀም የክርስቲያኖች ሁሉ ኃላፊነት ነው፡፡ “ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ”  የተባልነው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶችን በእግዚአብሔር ፍርሐትና በመንፈሳዊ ጥበብ እንድንጠቀምባቸውም ነው፡፡ ኤፌ 5፣6፡፡ ዘመንን መዋጀት ማለት በዘመን ለውጥ ውስጥ በለውጡ ተጽዕኖ ውስጥ ሳንሆን የእግዚአብሔርን ሃሳብና ፈቃዱንም ማገልገል መቻል ማለት ነው፡፡
ዘመናዊነት ካመጠቸው ግኝቶች መካከል ማህበራዊ ሚዲያዎች በወጣቶች ሕይወት ውስጥ ያላቸውን ተጽዕኖ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ብንመለከት ፌስቡክና መሰል ማኅበራዊ ሚዲያዎች ዓለማችንን የአንድ መንደር ያህል ማቀራረብ የቻሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች/ግኝቶች ናቸው፡፡ በተለያዩ የምድራችን ክፍሎች ወስጥ የሚገኙ ሰዎች ርቀት ሳይገድባቸውና ሳይወስናቸው ከአንደኛው  የዓለማችን ጫፍ ወደሌላኛው የዓለማችን ጫፍ  እነዚህን የመገናኛ መረቦች ተጠቅመው  መልእክቶችንና  መረጃዎችን ይለዋወጣሉ፣ ሃሳቦቻቸውን ያስተላልፋሉ፡፡ ነገር  ግን  እነዚህን  ቴክኖሎጂ ውጤቶች ሁሉም ወጣቶች ለበጎ ነገርና ሰዎችን ሁሉ ሊጠቅሙ በሚችሉበት ሁኔታ ይጠቀሙባቸዋል ማለት አይደለም፡፡ የማይረባ ቧልትን ለማስተላለፍ፣ ከሩካቤ ጋር የተገናኙ ምስሎችንና ፊልሞችን ለማሳየት፣ የማኅበረሰብን ጤናማ ግንኙነቶችና እሴቶቻችን የሚፃረሩ ሃሳቦችን ለማስተላለፍ፣ ዘረኝነትንና መለያየትን ለማስረጽ የሚጠቀሙባቸው ወጣቶች ቁጥር ትንሽ የሚባል አይደለም፡፡  እንግዲህ ማንም ራሱን ከነዚህ ቢያነጻ፥ ለክብር የሚኾን የተቀደሰም ለጌታውም የሚጠቅም ለበጎም ሥራ ዅሉ የተዘጋጀ ዕቃ ይኾናል።” ተብሎ እንደተጻፈ የእግዚአብሔር የሆኑ ወጣቶች ራሳቸውን ለወደዳቸውና ለሞተላቸው ጌታ አሳልፈው የሰጡ ስለሆኑ የሚያደርጉት ማናቸውም ነገር የእግዚአብሔር ክብር የሚገለጥበትና በዙሪያቸው ያሉ ሰዎችንም የክርስቶስን ፍቅር ወደማወቅ የሚያደርስ ነው፡፡ 2ኛጢሞ221፡፡ “በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችኹ ቁሙ እንደ ገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ።” ስለተባልን ማኅበራዊ ሚዲያዎች ግንኙነቶቻችንን የሚያሳልጡና የሚያግዙ እንጂ ሱስ ሆነውብን ለክርስቶስ ያለንን የተቀደሰ ሕይወት የሚያሳጡን ሊሆኑ አይገባም፡፡ ገላ 51፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያዎች በራሳቸው ኃጢአት ባይሆኑም በአጠቃቀማችን ላይ በምንፈጥራቸው ስህተቶች ለኃጢአቶቻችን ምክንያት ሊሆኑ ግን ይችላሉ፡፡ “ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ ሁሉ ግን አይጠቅምም። ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ በእኔ ላይ ግን አንድ ነገር እንኳ አይሰለጥንብኝም” ተብሎ እንደተጻፈ ይህ የምንኖረው የምድር ኑሯችን የእኛ ሳይሆን ለክርስቶስ ብለን የምንኖረው ስለሆነ ሁሉን ለክርስቶስ እንቀድሳለን እንጂ ለዓለሙና ለክፋቱ አንሸነፍም፡፡ 1ኛ ቆሮ 6፣12፡፡ ራሱን ለእግዚአብሔር እንደሚቀድስና ክርስቶስን ደስ ለማሰኘት እንደሚጥር ሰው ክርስቲያኖች ሁሉን ለጌታ ክብር ያውሉታል እንጂ በክፋቱ አይተባበሩም፡፡ “እንግዲህ የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትሆኑ ወይም ማናቸውን ነገር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” 1ኛ ቆሮ 10፣31 ስለተባልን ክርስቲያን ወጣቶች ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ሰላምን ለማውራት፣ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ለመጎብኘትና ፍቅርን ለማብዛት፣ የክርስቶስን በጎነት ለማውራት፣ የእግዚአብሔርን መንግስት በሰው ልጆች ሁሉ ፊት ለማስፋት ልንዋጃቸው ያስፈልገናል፡፡  
    5. ቸልተኝነት
በምድር ላይ ስንኖር የእግዚአብሔርን ፈቃድና ሃሳብ እየፈጸምን እንደሆነ እናምናለን፡፡ የምድር ላይ ኑሯችን በአጋጣሚ፣ ዝም ብለን፤ በዘፈቀደ የምንኖረው ሳይሆን እግዚአብሔር ከዘመናት አስቀድሞ ያዘጋጀልንን በጎ ሃሳቡንና ፈቃዱን የምንኖርበትም ነው፡፡ በወጣትነት ሕይወታችን ውስጥ ስሜታችንን የሚይዙና ትኩረታችንንም የሚስቡ ብዙ ጉዳች ቢኖሩም ከእግአብሔር ጋር የምንኖረውን ክርስቲያናዊ ኑሯችንንና በፊቱም የምናድግበትን ጸጋ ተጠንቅቀን የምንይዘው እንጂ ቸል የምንለው አይደለም፡፡ ስለሆነም እያንዳንዱ የእለት ተእለት እንቅስቃሴያችን በጥንቃቄና በማስተዋል የምናደርገውና የምንፈጽመው እንጂ ቸል የምንለው ተራ ጉዳይ አይደለም፡፡ በሚያልፈው ምድራዊ ኑሯችን ወስጥ ለማያለፈው፤ ለሚበልጠውና ለማይፈጸመው ዘላለማዊ ሕይወት ራሳችንን እንደምናዘጋጅበት አንስተውም፡፡ “ትሄዱ ዘንድ ምድሪቱንም ለመውረስ ትገቡ ዘንድ ቸል አትበሉ።” ተብለናልና ለመንፈሳዊ ሕይወታችን የሚጠቅሙንን ማናቸውንም አይነት በጎ ምግባራትና መንፈሳዊ ተግባራት ሁሉ ቸል ልንል አይገባንም፡፡ ከዛሬ ድካማችንና አለመቻላችን ባሻገር በክርስቶስ ጸጋና ምሕረት የምንቀበለውን ሕይወት በተስፋና በትዕግስት እንጠብቃለን እንጂ ባለማመንና ተስፋ በመቁረጥ ራሳችንን አናደክምም፡፡ ነገር ግን፥ የኀይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳይኾን ይህ መዝገብ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን፤ በዅሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቈርጥም፤ እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም፤ እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም፤ የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ዅል ጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን። የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሚሞት ሥጋችን ይገለጥ ዘንድ እኛ ሕያዋን የኾን ከኢየሱስ የተነሣ ዘወትር ለሞት አልፈን እንሰጣለንና። ስለዚህ፥ ሞቱ በእኛ፥ ሕይወቱም በእናንተ ይሠራል።” 2ኛ ቆሮ 4፣7-12፡፡  
    ምን እናድርግ ?
በምድር ላይ የምንኖው ይህ ሕይወታችን የእኛ ሳይሆን የክርስቶስ መሆኑን ተረድተን ወጣትነታችንን ለፈቃዱና ለሐሳቡ እንቀድስ፡፡ ክርስቲያናዊ ሕይወታችንም በአንድ ጊዜ የምንደርስበትና የምንፈጽመው ሳይሆን የእግዚአብሔርን ጸጋ አጋዥ በማድረግ ቀስ በቀስ የምናድግበትና የምንጠነክርበት ረጅም ሒደት በመሆኑ ለዚህ የተቀደሰ ሕይወት በየእለቱ ራሳችንን አናለማምድ፡፡ “ስለዚህም ምክንያት ትጋትን ዅሉ እያሳያችኹ በእምነታችኹ በጎነትን ጨምሩ፥ በበጎነትም ዕውቀትን፥ በዕውቀትም ራስን መግዛት፥ ራስንም በመግዛት መጽናትን፥ በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል፥ እግዚአብሔርንም በመምሰል የወንድማማችን መዋደድ፥ በወንድማማችም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ። እነዚህ ነገሮች ለእናንተ ኾነው ቢበዙ፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዕውቀት ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች እንዳትኾኑ ያደርጓችዃልና፤ እነዚህ ነገሮች የሌሉት ዕውር ነውና፥ በቅርብም ያለውን ብቻ ያያል፥ የቀደመውንም ኀጢአቱን መንጻት ረስቷል። ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ መጠራታችኹንና መመረጣችኹን ታጸኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ፤ እነዚህን ብታደርጉ ከቶ አትሰናከሉምና። 2ኛ ጴጥ 1፣5-10::