Thursday, January 14, 2016

ታላቅ ወንድሜ (ክፍል ሁለት)


ታላቅ ወንድሜ (ክፍል ሁለት)

‘‘እናንተ ልጆች ጨዋታችሁን አልጨረሳችሁም እንዴ? እራት ቀርቧል ኑ ቅረቡ፡፡’’ እማዬ ናት ራታችንን ለማቅረብ ተፍ ተፍ እያለች፡፡
‘‘እሺ እማዬ’’ ሁለታችንም ለእራት ተነሳን፡፡
‘‘ አልዓዛር በል የማዕድ ጸሎታችንን አድርስና ባረክልና?’’ ሁለታችንንም አተኩራ እየተመለከተችን ለጸሎት ተዘጋጀች፤ ስምረትም ጸሎቱ ከመጀመሩ በፊት መጥታ ተቀመጠች፡፡
‘‘እሺ እማዬ’’
ሁልጊዜ እንደዚህ ነው፡፡ ነፍስ ካወቅንበት ጊዜ አንስቶ ሳንጸልይ የበላንበት ጊዜ ትዝ አይለኝም፡፡ ጸሎት በቤታችን ውስጥ ትልቅ ስፍራ አለው፡፡ እንዴት እንደሆነ ባላውቅም ከልጅነታችን ጀምሮ እናታችን የጸሎት ሕይወትን አስለምዳናለች፡፡ በጸሎት ጊዜ ልዩነት የለም ሁሉም ይሳተፋል፡፡ ካህናት ከተጋበዙ ማዕዱን ይባርካሉ፤ ባዘቦቱ ቀን ደግሞ አልዓዛር፤አልዓዛር ሳይኖር ደግሞ እኔ እባርካለሁ፡፡ የቤታችን ስርዓት እንዲህ ነው፤ እናታችን ያስተማረችን፡፡
የአልዓዛር ጸሎት ሁልጊዜ ወስጤን ይነካዋል፤ ለነፍሴ ቶሎ ይሰማታል፡፡ ወንድሜ እግዚአብሔር ስላደረገልን በጎነት፣ ቤታችንን ስለባረከበት ብዙ በረከቱ፣ ቤተሰባችንን ስለረዳበት ቸርነቱ ሲያመሰግን መስማት ከእግዚአብሔር ጋር የሆንኩኝ ያህል እንዲሰማኝ ያደርገኛል፡፡ ሁልጊዜም እንደምናደርገው በአልዓዛር መሪነት የማዕድ ጸሎታችንን ሁላችንም በጋራ አድርሰን እራታችንን መመገብ ጀመርን፡፡
በጸሎታችን ውስጥ የእማዬ አሜን ጎልቶ ይሰማኛል፡፡ ሁልጊዜ ደግሞ የሚገርመኝ ነገር ቢኖር ብዙ ጊዜ አሜን የምትለው በእንባ ጭምር ነው፡፡ ለምን እንደሆነ ሳስብ በጣም እገረማለሁ፤ ምናልባት እኛን ብቻዋን ያለአባት ስታሳድገን እግዚአብሔር ምንኛ እንዳገዛትና እንደረዳት ስለምታስብ ይሆን ብዬ አስባለሁ፡፡ የእናቴ መንፈሳዊነት ይበልጥ እግዚብሔርን እንድወድውና በእርሱም እንድደገፍ ያደርገኛል፡፡ እማዬ የበጎ ነገር ሁሉ ምሳሌዬ ናት፡፡ ማንንም ስትነቅፍና በማንም ላይ ስትፈርድ ሰምቼያት አላውቅም፡፡ የሰዎችን አትፈልግም፤ የራሷን ግን ለሌሎች ትተዋለች፡፡ ከምስጋና በቀር ምሬቷን አላስተዋልኩም፡፡ እኔንና ወንድሜን ብቻዋን ስታሳድገን ብዙ ጊዜ ገንዘብ ይቸግራት እንደነበረ አስታውሳለሁ ነገር ግን አንድም ቀን ስለችግር  ለማንም ስታወራ አልሰማኋትም፤ እግዚብሔርን ከማመስገን ግን አቋርጣ አታውቅም፡፡
‘‘ አቤልዬ የቤተ ክርስቲያን ትምህርትህን ከምን አደረስከው? ’’ የእናቴ የተለመደ ጥያቄ ነው፡፡
‘‘ እየታገልኩ ነው እንግዲህ፡፡’’
‘‘ታዲያ መቼ ነው ዲቁና የምትቀበለው?’’
‘‘ያው እግዚአብሔር የፈቀደ ዕለት ነዋ፡፡’’
‘‘መቼም ከምርቃትህ ቀን የበለጠ ዲቁናህን የምትቀበል ቀን ነው ደስ ሚለኝ’’
‘‘እንዴ ለምን?’’ ታላቄ በመገረም ጠየቃት፡፡
‘‘ለምን እንደሆነ እኔ ብቻ ነኝ የማውቀው፡፡’’
‘‘ እማዬ ደግሞ ከመቼ ወዲህ ነው ለእኛ የማትነግሪን ለብቻሽ የምታውቂው ነገር የኖረሽ?’’ ታላቄ ትንሽ ፈርጠም ብሎ ጠየቃት፡፡
‘‘አንተ ሞኝ ከነገርኳችሁ ይልቅ ያልነገርኳችሁ ነገር እኮ ነው የሚበልጠው፡፡’’
‘‘ይህን ማመን ይከብደናል፡፡ አይደል አቤል?’’ መስማማቴን ጭንቅላቴን በማወዛወዝ ገለፅኩለት፡፡
‘‘ሁሉን ለእናንተ ነግሬ ከአምላኬ ጋር ምን ላወራ ነው?’’
‘‘ከአምላክ ጋር አወራለሁ እያልሽን ነው እማ?’’ በመገረም አፈጠጥኩባት፡፡
‘‘ አይ አቤልዬ እግዚአብሔር እኮ ለምትሻው ነፍስ እጅግ ቅርብ ነው፡፡’’ ማመን አቃተኝ፡፡ እናቴ አትሮንስ ዘርግታ የምትሰብከኝ እስኪመስለኝ ድረስ፡፡
‘‘ አንቺ ግን ስለ እግዚአብሔር ይህን ያህል ያስተማረሽ ማን ነው?’’
‘‘መጀመሪያ እርሱ ራሱ፣ ከዚያም የገዛ ኑሮዬ፡፡ የምነግረውን ሲያደምጠኝ፣ የማማክረውን ሰምቶ ምላሽ ሲሰጠኝ፣ በችግሬ ሲረዳኝ፣ በሀዘኔ ሲያፅናናኝ፣ ስለእናንተ የጸለይኩትን ጸሎቴን ሰምቶ እንደለመንኩት ሲያደርግልኝ ሳይ፣ በእድሜ ጠብቆኝ እንዲህ አድጋችሁ ሲያሳየኝ … ይህ ሁሉ ስለእግዚአብሔር የተማርኩበት ትምህርት ቤቴ ነበር፡፡’’
እዩልኝ እንግዲህ እናቴን፡፡ በሁሉ እግዚአብሔርን የምታስብ፣ ሁሉን ከእርሱ የምትጠብቅ፣ በሁሉምና ስለሁሉም እርሱን የምታከብርና የምታመሰግን፣ በኑሮዋ እግዚአብሔርን የተሰበከች፣ እንደተሰበከችውም ደግሞ የምታደርግ የተግባር ክርስቲያን ናት፡፡ የልጆቿ የወንጌል ሰባኪና የሃይማኖት መምህር፣ እንዲህ አድረጉ ሳትል ማድረግን በኑሮዋ የምታሳይ፣ እራሷን ምሳሌ አድርጋ በማቅረብ ሌሎችን ወደማድረግና ወደተግባር የምታደርስ የተግባር ሰው!
‘‘እማይዬ እኔን ግን ስለእግዚአብሔር የሰበክሽኝ አንቺ ነሽ፡፡’’ ታላቄ ነበር፡፡
‘‘እንዴት ብዬ አልዓዛርዬ?’’
‘‘ ለእግዚአብሔር በምትጠነቀቂበት ክርስቲያናዊ ኑሮሽ ውስጥ ነዋ፡፡’’
‘‘ አይ ልጄ እኔ እኮ በእኔ ብቻ ሳይሆን በእናንተም የምቆጭባቸው ብዙ ጉዳዮች አሉኝ፡፡’’
‘‘በምንድን ነው ደግሞ የምትቆጪው?’’
‘‘የእኔን ተዉትና የእናንተን ብነግራችሁ ሰንበት ትምህርት ቤት እንድትማሩ አለማድረጌ እንዴት ይቆጨኛል መሰላችሁ! ይኼ የዩኒቨርስቲ መንፈሳዊ ትምህርት ቤታችሁን ማን ነበር የምትሉት አቤልዬ?’’
‘‘ግቢ ጉባኤ’’
‘‘አዎ ግቢ ጉባኤ፡፡ እርሱ ባይኖርማ ኖሮ እንዴት የባሰ እቆጭ ነበር፡፡ ቢያንስ ስለሰንበት ትምህርት ቤት ያለብኝን ቁጭት እወጣበታለሁ፡፡’’
‘‘ ቆይ ግን አንቺ ስለሰንበት ትምህርት ቤት ምን የምታወቂው ነገር ኖሮ ነው ይህን ያህል የሚቆጭሽ?’’
‘‘እንዴት ነው የማላውቀው፡፡ ለቤተ ክርስቲያን የሚሰሩትን ስራ እያየን አይደል እንዴ! ወጣትነታቸውን ለእግዚብሔር አገልግሎት የሰጡ ወጣቶችን ከማየት የበለጠ ምን ታላቅ ነገር ይኖራል፡፡ ለጸሎት ሲተጉ፣ ለቤተ ክርስቲያን ጥብቅና ሲቆሙ፣ የክፉዎችን ሴራ ተከታትለው ሲያጋልጡ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሲያጠኑና ሲያስተምሩ እያየናቸው ነው፡፡ ይህንን ደግሞ የሚያደርጉት በራሳቸው ተነሳሽነትና በበጎ ፈቃዳቸው ነው፡፡ ከዚህ የበለጠ ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅም ምን አገልግሎት አለ?’’
‘‘አይ እማዬ ሰንበት ትምህርት ቤትን ይህን ያህል የምትወጂ ከሆነ ታዲያ አንቺስ ለምን ሰንበት ትምህርት አትማሪም?’’
‘‘ አይ እኔማ አረጅባቸዋለሁ፡፡ በእነርሱ ፍጥነት መራመድ ስለሚያዳግተኝ አጉል ስራቸውን ወደኋላ እጎትትባቸዋለሁ፡፡ ከዚህ ይልቅ ለኔ ብጤ አሮጊቶችና ሽማግሌዎች የሚሆን የሰንበት ትምህርት ቤት በተጀመረና እኔም በተራዳሁኝ፡፡’’
‘‘በምን ልትራጂ ትችያለሽ?’’
‘‘በምችለው ነዋ! መዝሙር ሲዘመር እልል ብልስ፣ ቤተ መቅደሱን ባጸዳስ፣ ጸዲቅ ጋግሬ ብወስድስ፣ መፅሐፍ ቅዱስ ሲያጠኑ ቁጭ ብዬ ባደምጥስ፣ ስለበጎ ስራቸው ባመሰግናቸውና ብመርቃቸውስ፣ ስለመጽናታቸው ብጸልይላቸውስ ….’’
እኔና ታላቄ እናታችን የምትለውን ማመን አቅቶን በመደነቅ እርስ በርሳችን ተፋጠጥን፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ቅርብ ነን ብለን የምናስበው እኛ እንኳን  ይህን ያህል ስለ ሰንበት ትምህርት ቤት አገልግሎት አስበን ስለማናውቅ ራሳችንን ታዘብነው፡፡
‘‘ለመሆኑ ግን አንቺ ብቻ ነሽ እንዳንቺ ያሉ ሌሎች ሰዎችም ስለ ሰንበት ትምህርት ቤት እንዲህ ያስባሉ?’’ የታላቄ ጥያቄ ነበር፡፡
‘‘ የቤተ ክርስቲያን ጓደኞቼ ብዙዎቹ ስለ ሰንበት ትምህርት ቤት ያስባሉ፡፡ ሲጠፉ ራሱ ልጆቻችን የት ሄዱ ነው የሚሉት፡፡ ያለ እናንተ ያለወጣቶቹ የነገዋ ቤተ ክርስቲያን እኮ የለችም፡፡ ሰንበት ተማሪዎቻችን የተለየ ጉባኤ አድርገው ከጠሩን ማናችንም ብንሆን አንቀርም፡፡ ሁላችንም ነን የምንታደምላቸው፡፡’’
‘‘እና የሰንበት ትምህርት ቤት አግልግሎት ይህን ያህል አስፈላጊ ነው እያልሽን ነው?’’
‘‘ታዲያስ! ወጣት የያዘው ነገር ምኑ ነው የማያስፈልገውና የማያምረው? የንግስ በአዓሎቻችን እንኳን በእነርሱ አይደል እንዴ ደምቀው የሚውሉት፡፡ ብዙ ሳንረዳቸውና ሳናግዛቸው ይህን ያህል መስራት ከቻሉ ብንረዳቸውና ብናግዛቸውማ ዓለሙን ሁሉ ክርስቲያን ለማድረግ አያንሱም ነበር፡፡ ብቻ ምን ዋጋ አለው የሚፈለገውን ያህል አልደገፍናቸውም፡፡’’
‘‘%ረ እማዬ! ይህን ያህል የሰንበት ትምህርት ቤቶች ድርሻ ገብቶሻል ማለት ነው ?’’
‘‘ እንዴት አይገባኝም! ቤተ ክርስቲያናችንን ለማፍረስ የሚያሴሩትን የውጭና የውስጥ አርበኞች እግር በእግር እየተከታተሉ የሚያሳውቁን ሰንበት ተማሪዎቻችን አይደሉ እንዴ ?’’
     ይቀጥላል …



No comments:

Post a Comment