እለቱ አርብ ነው፡፡ አምሽቼ ነበር ወደ ቤት የገባሁት፡፡ቤት ወስጥ ማንም ስላልነበረ መኝታ ቤቴ ገብቼ ጋደም ብያለሁ፡፡
‘‘ እሺ አቤል ክላስ አለቀ ?’’ ታላቅ ወንድሜ ነበር፤
የመኝታ ቤቴን በር ቀስ ብሎ ከፍቶ እየገባ፡፡
‘‘እንዴት አመሸህ አልዓዛር?’’
‘‘አለሁ ይመስገን፡፡ እማዬ የለችም እንዴ?’’
‘‘ ለቅሶ ቤት ልታማሽ ሄዳለች አለች ስምረት ’’
‘‘ቆይተሀል እንዴ ከመጣህ?’’
‘‘%ረ ገና መግባቴ ነው ’’
‘‘ታዲያ ምነው አመሸህ?’’
‘‘ግቢ ጉባኤ ስብሰባ ነበረኝ’’
‘‘ምን ነበር አጀንዳው ?’’ አልጋዬ ጫፍ ለይ ተቀመጠ፡፡ሁልጊዜም ስለ ግቢ ጉባኤ ከተነሳ የሆነ የሚለኝ ነገር እንደሚኖር
እርግጠኛ ነኝ፡፡ እራሱን ምሳሌ እያደረገ የሚነግረኝ ነገሮች ስለራሴ ብዙ እንዳስብ ያደርጉኛል፡፡
‘‘ስለ አባላት ጉዳይ ነበር የተወያየነው’’
‘‘ስለ አባላት ምን?’’
‘‘በአገልግሎት ስለመበርታትና ኃላፊነትን
ስለመወጣት ’’
‘‘እና ምን ድምዳሜ ላይ ደረሳችሁ?’’
‘‘ብዙ ነገሮችን አንስተን ተወያይተናል፡፡ በመጨረሻ ግን በአገልግሎት መበርታት እንዳለብንና ኃላፊነታችንን በፈሪሀ
እግዚአብሔር መወጣት እንዳለብን ተስማምተን ተለያየን፡፡ ’’
‘‘እየውልህ አቤል ከማንኛውም አይነት አገልግሎት በፊት ሊታሰብበትና ሊቀድምም የሚገባው ጉዳይ የአገልጋዮች መንፈሳዊነት
ነው፡፡’’ ምን ለማለት እንደፈለገ ስላልገባኝ አይኖቼ አፈጠጡበት፡፡እንዴት አድርጎ እነደሚያብራራልኝ እያሰበ ነው መሰለኝ ጥቂት
ፋታ ወሰደ፡፡
‘‘መንፈሳዊ አገልግሎት የሚጀምረው መንፈሳዊ ከመሆን ነው፡፡ መንፈሳዊ ሳይሆኑ ማገልገል የጉልበት ስራ ከመስራት በምን
ሊለይ ይችላል?’’ አለኝ፡፡ በርግጥ እውነቱን እኮ ነው ስል አሰብኩኝ፡፡ በሦስት አመታት የግቢ ቆይታዬ የነበረኝን የአገልጋይነት
ሕይወት በጥልቀት ማሰላሰል ጀመረኩ፡፡ በደስታ ከሰራሁባቸው ቀናት ይልቅ እዳይቀር ያህል ብቻ፤ በድካምና በመሰላቸት የሰራሁባቸው
ቀናት ይበልጣሉ፡፡ ችግሮችን የፈታሁባቸው መንገዶች ከመንፈሳዊነታቸው ይልቅ ስጋዊነታቸው ያይላል፡፡
‘‘ምን መሰለህ አቤል ምንም እንኳን የምንጓዝበት የሕይወት መስመር አንድ አይነት ቢሆንም፤ አረማመዳችን ግን የግድ
መለያየት አለበት፡፡ ከእኔ የተሻለ መንፈሳዊ ህይወት ቢኖርህ ደስታዬ ነው፡፡ እኔም ግቢ እያለሁ በመንፈሳዊ አገልግሎት ውስጥ በንቃት
እሳተፍ ነበር፡፡ ዛሬ ግን እኔም ሆንኩኝ ጓደኞቼ አይደለም ከአገልግሎት ሕይወት ከቤተ ክርስቲያንም ሕይወት እጅግ ብዙ እርቀናል፡፡’’
‘‘እንዴት ታደርገኝ ይሆን? ’’ ትል ነበር አያቴ፡፡ ዛሬ ከሆንኩት ይልቅ ነገ የምሆነው ይበልጥ አሳሰበኝ፡፡ በርግጥ
ታላቅ ወንድሜ የሚለኝ ነገር ሁሉ በሕይወቴ በተጨባጭ እየሆነ ያለ ነገር ነበር፡፡ ከአገልግሎቱ መንፈሳዊነት ይልቅ የአገልግሎቱ መቅረት
ወይም አለመቅረት ይበልጥ ያሳስበኛል፤ በአገልግሎቱ ከሚጠቀሙት ሰዎች ይልቅ ስለአገልግሎቱ ድምቀትና የሰዎች ቁጥር ይበልጥ እጨነቃለሁ፡፡
‘‘ስማ አቤል አንድ ነገር ልጠይቅህ ?’’
‘‘ይቻላል’’
‘‘የእግዚአብሔር ትልቁ ጉዳይ አገልግሎቱ ነው ወይስ የሚገለገሉት ነፍሳት ’’
‘‘ሁለቱም ይመስለኛል’’
‘‘አይምሰልህ እግዚአብሔር አገልግሎትን የሠጠን ሰዎች ሁሉ እርሱን ወደማወቅ እንዲደርሱና የዘለዓለምን ሕይወት እንዲወርሱ
ነው፡፡ ለሰው ልጆች ሁሉ መዳንና መንፈሳዊ እድገት የማይተጋ አገልግሎት እግዚአብሔር ደስ አይሰኝበትም፡፡ ሰዎችና መላእክት የተፈጠሩት
እግዚአብሔርን እንዲያገለግሉና ክብሩን እንዲወርሱ እኮ ነው፡፡’’
‘‘እና ምን መሆን አለበት እያልከኝ ነው?’’
‘‘መሆን ያለበትማ ከአገልግሎቱ ይበልጥ በአገልግለሎቱ ውስጥ ስለሚኖርህ መንፈሳዊነትና በአገለግሎቱ ስለሚጠቀሙት ሰዎች
ነፍስ የበለጠ ተጠንቀቅ፡፡’’
‘‘የምር ግን ብዙ አገልግሎትና ብዙ አገልጋዮች ባሉበት ዘመን የአገልግሎቱ ፍሬ ለምን ጥቂት ሆነ? የሚደከመውንስ
ያህል ለምን ለውጥ አይታይም? ’’
‘‘ምክንያቱ ግልፅ ነው አገልጋዮቹ መንፈሳዊነት ይጎድላቸዋል፡፡ ከሰዎች ነፍስ ይልቅ አገልግሎቱን ያሰቀድማሉ፡፡ ልክ
ጌታ በመዋዕለ ስጋዌው እንደገሰፃቸው ፈሪሳውያን ከወጭቱ ውስጥ ይልቅ ለውጪው ይበልጥ ይጠነቀቃሉ፡፡መንፈሳዊ ሳልሆን ያገለገልኩባቸው ብዙ አመታት ዛሬ ላይ እንዴት ይቆጩኛል መሰለህ፡፡ ለዚህም
ነው ዛሬ ከትዝታው ባለፈ በድርጊት የሚገለጥ አንዳች ነገር ሊተርፍልኝ ያልቻለው፡፡’’
ታላቅ ወንድሜን በጣም እወደዋልሁ፣ የእርሱ ደግሞ ከእኔም ይለያል፤ ይበልጥ ይወደኛል፡፡ ከማንም በተሻለ ለስሜቴ ቅርብ
ነው፡፡ ጥቂት ተናግሬ አብዝቶ ይረዳልኛል፡፡ እኔም ብሆን ልረዳው እሞክራለሁ፡፡ ለዚህም ሳይሆን አይቀርም መንፈሳዊ ሆኖ ስለማገልገል
እያወራን በጥልቅ መገናዘብ ውስጥ ገብተን የምንተያየው፡፡ ሊለኝ የፈለገው ገብቶኛል፡፡ ከቃላቱም በላይ በወንድምነቱ ውስጥ ያለው
እውነተኛ ስሜት ነገሮችን ይበልጥ እንድረዳቸው ያደርገኛል፡፡ …………. በመካከላችን ዝምታ ሰፈነ፡፡ሁለታችንም ግን ለየራሳችን በውስጣችን
እያወራን ነበር፡፡ ውስጥን ዘልቆ የሚያይ ያህል በጥልቅ ስሜት አተኩሮ ተመለከተኝ፡፡ ሊለኝ የፈለገው ግን ገብቶኝ ነበር፡፡
እጁን ወደ ራስጌዬ ልኮ መፅሐፍ ቅዱስ አነሳ፡፡ ‘‘እንካ እስኪ ይህንን አንብብ’’ የማነበውን በጣቱ እያመለከተኝ፡-
የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት ነበር ለሮሜ ሰዎች የጻፈላቸው ምዕራፍ 2 ከቁጥር 07-@4 በጥልቅ መገረም ውስጥ ሆኜ እንዲህ አነበብኩት
፡-
‘‘አንተ ግን አይሁዳዊ ብትባል በህግም ብትደገፍ ፣ በእግዚአብሔርም ብትመካ፣ ፈቃዱንም ብታውቅ ከህግም ተምረህ የሚሻለውን ፈትነህ ብትወድ በህግም የእውቀትና የእውነት መልክ
ስላለህ፣ የእውሮች መሪ፣ በጨለማም ላሉ ብርሀን፣ የሰነፎችም አስተማሪ፣ የሕፃናትም መምህር እነደሆንህ በራስህ ብትታመን ፤ እንግዲህ
አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርምን? አትስረቅ ብለህ የምትሰብክ ትሰርቃለህን? አታመንዝር የምትል ታመነዝራለህን?
ጣዖትን የምትጸየፍ ቤተ መቅደስን ትዘርፋለህን? በህግ የምትመካ ህግን በመተላለፍ እግዚአብሔርን ታሳፍራለህን? በእናንተ ሰበብ የእግዚአብሔር
ስም በአህዛብ መካከል ይሰደባልና ተብሎ እንደተፃፈ፡፡ ’’
ከዚህ በኋላ ለረጅም ጊዜ ምንም አልተነጋገርንም፡፡ ሁለታችንም በየራሳችን ጥልቅ ስሜት ውስጥ ሰጥመን ነበር፡፡ ከራሳችን
ጋር ለየራሳችን እያወራን ብዙ አሰላሰልን፤ እማዬ ከለቅሶ ቤት ተመልሳ ከየሄድንበት እረጅም የሀሳብ መንገድ እስክትመልሰን ድረስ፡፡
‘‘ውይ አቤልዬ መጥተሀል እንዴ?’’ ሁለታችንም ተነስተን ቆምን፡፡
‘‘እስኪ ና ሳመኝ ጌታዬ’’
የእናቴ ነገር ሁሌም ይገርመኛል፡፡ ባገኘችኝ ቁጥር እንደ አዲስ ትናፍቀኛለች፡፡ ለአንድ ቀን አዳር ተለያይተን የአመታት
ናፍቆት ያህል እንቅ አድርጋ ትስመኛለች፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቴክኖሎጂ ኢኒስቲቲዩት የሶስተኛ አመት የኤሌክትሪካል ምሕንድስና
ተማሪ ነኝ፡፡ በየሳምንቱ አርብ ማታ ወደ ቤቴ እየመጣሁ ከእናቴና ከወንድሜ ጋር እሁድና ቅዳሜን አሳልፋለሁ፡፡ አባቴና እናቴ አብረው
አይደለም የሚኖሩት፡፡ ለምን እንደተለያዩ አናውቅም፤ እናታችንንም ምክንያቱን አልጠየቅናትም ፡፡ አባታችን እናታችንን አይረዳትም፡፡
ወጪያችንን በሙሉ እናታችን ብቻዋን ትሸፍናለች፡፡ አሁን እንኳን ታላቅ ወንድሜ አልዓዛር ስራ ስለያዘ በወጪ ያግዛታል፡፡ አባታችን
አልፎ አልፎ እየመጣ ይጠይቀናል፡፡ እናታችን አንድም ቀን ስለአባታችን ክፉ ተናግራ አታውቅም፡፡ ስምረት እኔንና አልዓዛርን ያሳደገችን
ሞግዚታችን ናት፡፡ የማታ ትምህርት እየተማረች ዘጠነኛ ክፍል ደርሳለች፡፡ ከእናታችን ጋር የእህትማማቾች ያህል ይግባባሉ፡፡
‘‘አልዓዛርዬ አንተስ ለምን ይቅርብህ ና እስኪ
ልሳምህ፡፡ ከአንተም ጋር ቢሆን አብረን አልዋልን’’ ብላ በስስትና በናፍቆት እቅፍ አድርጋ ሳመችው፡፡
‘‘እማዬ ዛሬ ለራት ምን ሰርተሽ ጠበቅሽኝ?’’
አልኳት፡፡
‘‘ያቺን የምትወዳትን ድፍን ምስር በቅመም
አሳምሬ ሰርቼልሀለሁ፡፡ እራት ይቅረብ አይደል?’’ እራት ልታቀርብ ወጥታ ሔደች፡፡
እናታችን ሲበዛ የፍቅር ሰው ናት፡፡ ለሌሎች ደስታ ስትል የኔ የምትለውን ሁሉ የምትተው፣ ማንንም ስለድካሙ የማትወቅስ፣
የበጎ ነገር ሁሉ ምሳሌያችን ናት፡፡ እንዲያውም አልዓዛር ‘‘ፍቅር የሚሰጥ መሆኑን የተማርኩት ከእናቴ ነው፡፡’’ ይላል፡፡ እውነቱን
ነው ከእናታችን ያገኘነው ፍቅር ብዙዎችን እስክንወድበት ድረስ በዝቶልን ተመልክቻለሁ፡፡
‘‘ ስማ አቤል ’’
‘‘አቤት አልዓዛር ’’
‘‘ለእኔ ሃይማኖትን ማን እዳስተማረኝ ታውቃልህ?’’
አልመለስኩለትም ነበር፡፡ የሚለኝን ለመስማት ጓጉቼ ዝምታን መረጥሁ፡፡
‘‘ ማን ይመስልሃል ?’’
‘‘ለመጀመሪያ ጊዜ ቃለ እግዚአብሔርን ያስተማሩህ
ሰዎች ናቸዋ፡፡’’ እራሱን በአሉታ ነቀነቀ፡፡ ማን ሊሆን ይችላል ብዬ አሰብኩ፡፡
‘‘ለእኔ ሃይማኖትን ያስተማረችኝ እናቴ ናት’’
‘‘አልገባኝም ’’
‘‘ እስኪ ተመልከት እማዬ አንድም ቀን ስታማርር
ሰምተሃት ታውቃለህ? አታውቅም፡፡ በነገር ሁሉ እግዚአብሔርን ታመሰግናለች፡፡ ይህ ማለት ግን ምንም ችግር ገጥሟት አያውቅም ማለት
አይደለም፡፡ እኛን ስታሳድግ ብዙ ልትቸገር ትችላለች፡፡ ስለአባታችንም ቢሆን አንድም ቀን ክፉ ስታወራ ሰምተን አናውቅም፡፡ እኔና
አንተ ከተማርነው የሃይማኖት ትምህርትና እማዬ ከተማረችው የትኛው በደንብ የተጠናና የተደራጀ ይመስልሃል?’’ ጥልቅ በሆነ ስሜት
ለደቂቃዎች ያህል ተመለከተኝ፡፡ እኔም ብሆን ለመልስ አልቸኮልኩም፤ የእናቴን ክርስቲያናዊ ሕይወት ከእኛ ከልጆቿ ክርስቲያናዊ ሕይወት
ጋር እያወዳደርኩ ነበር፡፡ በእርግጥ እናታችን የእኛን ያህል በደንብ የተደራጀ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት የተማረችበትን ጊዜ አላስታውስም
ሆኖም ከእኛ ይልቅ እርሷ በተግባር የተገለጠና የሚታይ ክርስቲያናዊ ሕይወት አላት፡፡ መልሴ ስለዘገየበት የጥያቄውን መልስ ከነማብራሪያው
እንዲህ ሲል ቀጠለ ፡-
‘‘አየህ አቤል ስለሃይማኖት ትምህርት ከሆነ እማዬ ከእኛ ጋር ሊነፃፀር የሚችል ትምህርት የላትም፤ የእኛን ያህል
የቤተ ክርስቲያናችንን ትምህርት በደንብ በተደራጀ መልኩ አልተማረችም፤ ሆኖም ግን ከእኛ ጋር ሊነፃፀር በማይችል መልኩ በተግባር
የተገለጠ ክርስቲያናዊ ሕይወት አላት፡፡ የበደሏትን ሳይቀር ትወዳለች፣ሁልጊዜ ለበጎ ነገር ትተጋለች፣ የተቸገሩትን ትረዳለች፣ ባወቀችው
ለመኖር ትጥራለች፣ ዘወትር በጸሎት ትተጋለች፣ ለችግሮቿ ሁሉ እግዚአብሔር መፍትሄ እንዳለው ታምናለች፣ እርሱንም ብቻ በትዕግስት
ትጠብቃለች፣ በሀዘኗም ሆነ በደስታዋ እግዚአብሔርን ታመሰግናለች….. ስለሆነም ከእኔና ከአንተ ይልቅ እማዬ ክርስቲያን ነች፡፡ እኔና
አንተስ? ልንኖረው የሚገባንን ህይወት ታሳቢ ባደረገ መልኩ ስርዐተ ትምህርት ተቀርጾልን በተደራጀ መልኩ በግቢ ጉባኤ ውስጥ ቃለ
እግዚአብሔር ተምረናል፣ ብዙ መንፈሳዊ መፃህፍትን አንብበናል፣ ስለቤተ ክርስቲያን ሕይወት ብዙ ተምረናል ግን ደግሞ በተማርነው ልክ
አንኖርም፣ ከመማር ባሻገር የተማርነውን ለመተግበርና በኑሯችን ለመግለጥ አንጥርም … ስለሆነም አይደለም የተማርነውን ያህል የእማዬን
ያህል እንኳን ክርስቲያኖች መሆን አልቻልንም፡፡’’
እውነቱን ነው፡፡ ከማወቅ ባለፈ በተግባር የተገለጠ ክርስትና እንዲኖረኝ አልተጋሁም፡፡ በመማሬና በማወቄ ውስጥ ያመጣሁትን
ብልጫ ፈለግሁት፣ በእርግጠም አንዳችም ብልጫ አልነበረኝም፡፡ አስከ ዛሬ ድረስ ብዙ ስለመማር እንጂ በተማርሁትና በተረዳሁት በጥቂቱ
እንኳን ለመኖር አለማሰቤ በጣም ቆጨኝ፡፡
‘‘ምን መሰለህ የምንማረውና የምናውቀው እንደተማርነው ለማድረግና ለመኖር ካለሆነ በመማርና ባለመማር መካከል ልዩነቱ
ምን ላይ ነው? ቅዱስ ጴጥሮስም ‘የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን
ተቀብሏል’ ያለው ይህንን ነው፡፡ 1ኛ
ጴጥ 2፣21፡፡ ክርስቶስ የተወልን ፍለጋ ደግሞ አውቀን ብቻ የምንተወው ሳይሆን እንዳወቅነውና እንደተረዳነው መጠን በተግባር የምንታዘዘውና
የምንኖረው ነው፡፡’’
‘‘በምትለው ነገር እኮ ሙሉ በሙሉ እስማማለሁ፤ ግን ችግሩ የቱ ጋር እንዳለ ነው ማወቅ የምፈልገው፡፡ ከእውቀት ባለፈ
በተግባር የተገለጠ ሕይወት እንዳይኖረን ያደረገን ችግር የቱ ጋር እንዳለ እንድታሳየኝ እፈልጋለሁ፡፡’’
‘‘ በእርግጥ ችግሩ አንድ ቦታ ብቻ ስለማይሆን በአጭሩ እንዲህ ነው ብሎ መመለስ አይቻል ይሆናል፡፡ ሆኖም በተግባር
ለተገለጠ ክርስትና ተገቢውን ትኩረት አለመስጠታችንና ከልጅነታችን አንስቶ ቀስ በቀስ እያደግንበትና እየተለማመድነው እንድንመጣ አለመደረጋችን
ለዛሬ ችግራችን አስተዋፅዖ ሊኖራቸው እንደሚችል ግን አስባለሁ፡፡’’
…….. ይቀጥላል ……