ስለ ቤተ ክርስቲያናችን እንወቅ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በምድር ላይ የክርስቶስ መንግስት እንደራሴ፣ የመንግስቱ ወንጌል አገልጋይ፣
ለሰው ልጆች ሁሉ መዳን የምትሠራና የምትተጋ፣ የክርስቶስ አካሉ የምትሆን የተቀደሰች ጉባኤ ናት፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያን ራስ ሲሆን ቤተ ክርስቲያን ደግሞ የክርስቶስ አካሉ ናት፡፡ ቆላ 1፣18፡፡ እኛ ደግሞ የክርስቶስ የአካሉ
ብልቶች ነን፡፡ ኤፌ 5፣19፡፡ ስለሆነም ስለመዳን ስናስብ በዚህ ኅብረትና አንድነት ውስጥ ሆነን ነው፡፡ አካሉ ከምትሆን ቤተ ክርስቲያን
የተለዩ ብልቶች ራሷ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስም ስለሚለዩ መዳን አይቻላቸውም፡፡ ስለሆነም በቤተ ክርስቲያን ኅብረትና አንድነት
ውስጥ የሚኖረን ሱታፌ የመዳናችን መንገድ ነው፡፡ ራስ፣ አካልና የአካል ክፍሎች ተለያይተው መኖር እንደማይችሉ ሁሉ ያለ ክርስቶስ
ቤተ ክርስቲያን ልትኖር አትችልም፤ ያለቤተ ክርስቲያንም ምእመናን ሊኖሩ አይችሉም፡፡ በዚህም የተነሳ ስለ ሰው ልጆች መዳን ስናስብ
የሰው ልጆች በቤተ ክርስቲያን ምስጢራት ውስጥ የሚኖራቸው ሱታፌ ወሳኝ ነው የምንለው ስለዚህ ነው፡፡ የአካል ክፍሎች ብቻቸውን፣
ራሳቸውን ችለው በራሳቸው ሕይወት ሊኖራቸው እንደማይችል ሁሉ፣ የክርስቶስ አካሉ ከምትሆን ከተቀደሰችው ጉባኤ ከቤተ ክርስቲያን ኅብረትና
አንድነት የተለዩ ነፍሳትም መዳናቸውን መፈጸም አይቻላቸውም፡፡ እናም ስለቤተ ክርስቲያን የምናምነው እምነትና የምናውቀው እውቀት
በመዳን መንገድ ላይ ወሳኝ ነው፡፡
ስለ ቤተ ክርስቲያን ማውቅ ያለብን ምንድን ነው?
ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ደም የተዋጀች የራሱ የእግዚአብሔር ገንዘብ ናት፡፡ ሐዋ 2፣28፡፡ ትምህርቷ፣ ስብከቷና ፍለጋዋ
ሁሉ ከክርስቶስ ያየችውና የተማረችው ነው፡፡ የክርስቶስ ከሆነው በቀር የራሷ የምትለው አንዳችም ነገር የላትም፡፡ “የተጠራችሁለት
ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሏልና፡፡” 1ኛ ጴጥ 2 ፣21 ፡፡
ቤተ ክርስቲያን መምህሯ አንድ እርሱም ደግሞ ክርስቶስ ነው ማቴ 23፣8፡፡ “ከእኔ ተማሩ” ማቴ 11፣29 ተብለናልና ከክርስቶስ ያልተማርነው ማናቸውም አይነት እንግዳ
ትምህርት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተቀባይነት የለውም፡፡ የሰማይ መልአክ እንኳን ቢሆን ክርስቶስ ካሳየንና ካስተማረን ትምህርት የተለየ
እንግዳ ትምህርት ቢያሳየንና ቢያስተምረን ቤተ ክርስቲያን አትቀበለውም፡፡ “ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ
ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን” ተብሏልና እንደ ክርስቶስ ትምህርት ያለሆነ ትምህርት በቤተ ክርስቲያን
ስፍራ የለውም፡፡ ገላ 1፣8፡፡ ቤተ ክርስቲያን ለሚመጣ ሁሉ በክርስቶስም ትምህርት ለማይኖር ሰው አምላክ የለውም ብላ ታምናለች፡፡
2ኛ ዮሐ 1፣9፡፡ ስለሆነም ስለ ቤተ ክርስቲያን ልናወቀው የሚገባን መሰረታዊ ነገር ከክርስቶስ ያየችውንና የተማረችውን ትምህርት
ነው፡፡ ይህም ደግሞ ስለመዳን፣ ስለ ዘላለማዊ ሕይወት፣ ስለ ጽድቅና ፍርድ የምታምነውና የምታስተምረው ትምህርት ነው፡፡ “እንግዲያስ
እምነት ከመስማት ነው፥ መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው” ሮሜ 1፣ 17 ተብሎ ተጽፏልና ለማመን የእግዚአብሔርን ቃል መስማትና
መማር ያስፈልጋል፡፡
የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ለማወቅ ምን እናድርግ?
ሀ. የቤተ ክርስቲያንን
ትምህርት በመደበኛነት ጊዜ መድበን እንማር፡- በአሁኑ ጊዜ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት በመደበኛ ሁኔታ ጊዜ መድበው
የሚያስተምሩ የአብነት ትምህርት ቤቶች፣ የቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ ኮሌጆች፣ የተለያዩ ግቢ ጉባኤያት፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶችና
የሰርክ ጉባኤያት ስላሉ ጊዜ መድበን እንማር፡፡ ካልተማርን የእግዚአብሔር ሐሳቡና ምክሩ እንዴት ሊገባን ይችላል? ስለመዳንና ስለዘለዓለም
ሕይወትስ እንዴት ልንረዳ እንችላለን? ከመደበኛ ትምህርቶቹ በተጨማሪም የርቀት ትምህርት መርሐግብር ያላቸው መንፈሳዊ ኮሌጆችና ሰንበት
ትምህርት ቤቶችም ስላሉ በአካል መገኘትና መማር የማንችል ባለንበት ቦታ ሆነን በርቀት የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት መማር እንችላለን፡፡
እዚህ ጋር ሊጤን የሚያስፈልገው ጉዳይ ቢኖር ስንማር የሚያስተምሩን አካላት ትክክለኛ የቤተ ክርስቲያን መምህራን መሆናቸውንና ሕጋዊውን
የቤተ ክርስቲያን መዋቅር ተከትለው የሚሠሩ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅብናል፡፡ የቤተ ክርስቲያናችንን መምህራን የሚመስሉና ነን
የሚሉ፣ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያናችን የማታውቃቸው፣ የማታስተምረውን ትምህርት የሚያስተምሩ አካላት ስላሉ አስቀድሞ መጠንቀቁና ነገሮችን
በንቃት መከታታሉ ለሁሉም ነገር ጠቃሚ ነው፡፡ ለነፍሳችን ድኅነት ብለን ያደረግነው ምናልባት ለጥፋቷ እንዳይሆን መጠንቀቅ ያሻል፤
ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና፡፡ ኤፌ 5፣16
ለ. እንጸልይ፡- የጸሎት ሕይወት በመንፈሳዊ ሕይወታችን ለሚኖረን ሁሉን አቀፍ
እድገትና ለውጥ ጉልህ ድርሻ አለው፡፡ ስንጸልይ ምስጢር ይገለጥልናል፣ የራቀው ይቀርብልናል፣ የረቀቀው ይከሰትልናል፣ ወደ ቀናው
መንገድ ይመራናል፡፡ በአጠቃላይ የእግዚአብሔር ሐሳብና ምክር በሕይወታችን ውስጥ የተገለጠና የተረዳ ይሆንልናል፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔርን
በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር፥ ልመናና ጸሎት፣ ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ
መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ፡፡ ሰዎች ዅሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኀኒታችን
ፊት መልካምና ደስ የሚያሠኝ ይህ ነው።” 1ኛ ጢሞ 2፣1-4፡፡ የጸሎት ሕይወት የሌለው ሰው መቼም ቢሆን እውነትን ወደማወቅ ሊደርስ
አይችልም፡፡
ሐ. እናንብብ፡- መንፈሳውያት መጻሕፍት በእግዚአብሔር ፊት የምናድግባቸው መልካም መንገዶች ናቸው፡፡ የቤተ
ክርስቲያናችንንና የቅዱሳን አባቶቻችንን ትምህርት በደንብ ልናውቅና ልንረዳ የምንችለው በመንፈስ ቅዱስ የጻፏቸውን ቅዱሳት መጻሕፍቶቻቸውን
ማንበብ ስንችል ነው፡፡ “ከሕፃንነትህም ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን፥ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳን
መጻሕፍትን አውቀሃል፡፡” 2ኛ ጢሞ 3፣15 እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳውያት መጻሕፍት መዳን የሚገኝበትን ጥበብ የሚሰጡ ናቸው፡፡
መንፈሳውያት መጻሕፍት በስጋዊ ሐሳብና ፈቃድ የተጻፉ ሳይሆኑ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ምክርና ፈቃድ የተጻፉ ስለሆኑ ለመንፈሳዊ
ሕይወት እድገትና ለመዳን እጅግ ጠቃሚዎች ናቸው፡፡ “ይህን በመዠመሪያ ዕወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ዅሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም
አልተፈቀደም፤ ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።”
2ኛ ጴጥ 1፣2-21 ተብሎ እንደተጻፈ በቅዱሳት መጻሕፍት ያለው ሁሉ የመንፈስ ቅዱስ ምክርና ሐሳብ እንደሆነ እናምናለንና ለመንፈሳዊ
ሕይወታችንና ለመዳናችን የሚጠቅም መሆኑን እንቀበላለን፡፡ በተለይም በአሁኑ ወቅት በየሞባይሎቻችንና በየኮምፒውተሮቻችን ላይ ማንበብ
ስለምንችልና መጽሓፍትንም በለስላሳ ቅጂ (soft copy) በቀላሉ ማግኘት ስለምንችል በቀላሉ እውነቱን ወደ ማወቅ እንደርሳለን፡፡
መ. እንጠይቅ፡- ‘‘አባትህን ጠይቅ ያስታውቅህማል፤ ሽማግሌዎችህን ጠይቅ፥ ይነግሩህማል።’’
እንዲል መጠየቅ ስንችል እውነተኛውን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት መለየትና መረዳት እንችላለን፡፡ ዘዳ 32፣7፡፡ በእርግጥ የምንጠይቃቸው
ሰዎች እውነተኞች የቤተ ክርስቲያናችን አባቶችና መምህራን ከሆኑ ለሕይወታችን የሚረባንን፣ የሚበጀንንና መዳን የሚገኝበትን ጥበብ
እናገኝበታለን፡፡
ሠ. ትሕትናን ገንዘብ
እናድርግ፡- ‘‘በትሑታን ዘንድ ግን ጥበብ ትገኛለች።’’
እንዲል መጽሐፍ ትሑታን ስንሆን እግዚአብሔር አምላካችን ምስጢሩንና ጥበቡን ይገልጥልናል፡፡ ምሳ 11፣2፡፡ እግዚአብሔር የትሑታን
አምላክ ነውና ስለትሕትናችን ሲል ጸጋውን ያበዛልናል፣ ትዕቢተኞች ብንሆን ግን ጸጋው ትርቅብናለች፡፡ ‘‘በፌዘኞች እርሱ ያፌዛል፣
ለትሑታን ግን ሞገስን ይሰጣል፡፡’’ ተብሎ ተጽፏልና ምሳ 3፣34፡፡
ረ. በቤተ ክርስቲያን
አገልግሎት እንሳተፍ፡- ቤተክርስቲያናችን የአገልግሎት ቤት ናት፡፡ ማኅሌቱ፣ ሰአታቱ፣ ቅዳሴው፣ ጉባኤው፣ የሰበካ ጉባኤና
የሰንበት ትምህርት ቤት አገልግሎቱ፣ ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደቱ ሁሉ ለእኛ ስለሆነ በምንችለው መሳተፍ አለብን፡፡ ከመንፈሳዊ አገልግሎት
የተለየ ሰው በመንፈሳዊ ሕይወት ሊያድግ አይችልም፡፡ አገልግሎት ትልቅ ትምህርት ቤት ነውና ስናገለግል ብዙ እንማራለን፡፡ የተማርነውን
ስንተገብረው ይበልጥ ይዋሓደናል፡፡ የማወቅ ዓላማው ለመተግበር ስለሆነ አገልግሎት ወደ ማወቅና ወደማድረግም የሚያደርሰን መንገድ
ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ ከእርሱ ጋር አብረን የምንሠራ ነንና›› እንዳለ በእግዚአብሔር መንግሥት አብረን እንሥራ፣ የእግዚአብሔር
ስራ ለሌሎች ብቻ የምንተወው ሳይሆን እኛም የምናሳተፍበት የክርስትናችን ድርሻ ነው፡፡ (2ቆሮ 1፤24፣ቆላ 4፤11)፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አምላከ አበዊነ፡፡
Astemari new...yiketil !
ReplyDelete