Tuesday, January 31, 2017

ትምህርተ ንስሓ (ክፍል አንድ)




ትምህርተ ንስሓ (ክፍል አንድ)

ንስሓ፦ ነስሓ/ተጸጸተ ከሚለው የግዕዝ ግስ/ቃል የተገኘ ሲሆን፤ በሠሩት ኃጢአት መጸጸት፣ ማዘን፣ ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ መወሰን ማለት ነው። በአንቀጸ ንስሓ እንደተገለጸው ንስሓ መናዘዝ፣ ኑዛዜ ማደረግ፣ ወይም ኃጢአትን ለአበ ነፍስ (ለካህን) መናገርና ራስን መግለጥ ነው፡፡ በትንቢተ ሕዝቅኤል ላይ ኃጢአተኛውም ከሠራው ኃጢአት ቢመለስ ፍርድንና ቅን ነገርንም ቢያደርግ ነፍሱን ይጠብቃል፡፡ አስቦ ከሠራው በደል ሁሉ ተመልሷልና ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም በማለት የሰፈረው ቃል የንስሓ ሕይወትን ምንነት በጉልህ ያስገነዝባል (ሕዝ.18.27-29)፡፡ በዚሁ መጽሐፍ በምዕራፍ 33 ቁጥር 16 ላይ የሠራው ኃጢአት ሁሉ አይታሰብበትም ይላል፤ ስለሆነም በኀጢአታችን ስንናዘዝና ንስሓ ስንገባ እግዚአብሔር ይተውልናል፣ ይቅርም ይለናል፤ ባልተናዘዝንበትና ንስሓ በልገባንበት ኀጢአት ግን እግዚአብሔር አምላካችን ያዝንብናል፣ ስላለመናዘዛችንም ይቀጣናል፡፡ ንስሓ ለተጠመቁ ሰዎች ከጥምቀት በኋላ የተሰጠች ሀብት ናት። በጥምቀት ከእግዚአብሔር ከምትገኝ ልጅነት ቀጥላ ያለች ሁለተኛ ማዕረግ ናት፡፡ በጥምቀት የእግዚአብሔር ልጆች ሆነን እንደምንወለድ ሁሉ በኃጢአትና በበደል የምናጣትን ልጅነታችንን በንስሓ መልሰን እናገኛታለንና ከጥምቀት በኋላ የእግዚአብሔርን ልጅነት የምታስገኝ ሁለተኛ መዐርግ ትባላለች፡፡ ንስሓ በሃይማኖት ገንዘብ የምናደርጋት የመንግሥተ ሰማያት መግዣ ናት፤ በንስሓ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንወርሳታለንና። ንስሐ ለሚሿት ሰዎች የተከፈተች የይቅርታ በር ስትሆን ከፈጣሪ ወደሚገኝ ቸርነትና በጎነት እንገባባታለን/እንቀርብባታለን፡፡

ምሥጢረ ንስሓ ማለት አንድ ሰው ከጥምቀት በኋላ የፈጸመውን ጥፋት አውቆ ሁለተኛ ጥፋቱን ላለመድገም ወስኖ በእግዚአብሔርና በካህኑ ፊት ተንበርክኮ ከልቡ ተጸጽቶ ኃጢአቱን በመናዘዝ ከኃጢአቱ እስራት የሚፈታበትና ከእግዚአብሔር ይቅርታን የሚያገኝበት ታላቅ የይቅርታ ምሥጢር ነው። ምሥጢር መባሉም በአይናችን በምናየውና በምናስተውለው የንስሓ ሥርዐት መንፈሳዊና ረቂቅ የሚሆን ሥርየተ ኀጢአትን/የኀጢአት ይቅርታን ስለምንቀበልበት ነው፡፡ ንስሐ ከእግዚአብሔር የሚሰጥ እግዚአብሔርን የሚያስወድድ፤ ከንጹህ ልብ የሚመነጭ ጸጋ ነው። እግዚአብሔር አምላካችን ሐዳጌ በቀል/ኀጢአትን ቅር የሚል መሆኑን የምንረዳበት መንገድ ስለሆነ በፊት ከነበረው ሕይወታችን በተሻለና በበለጠ ሁኔታ በንስሓ ወደ እግዚአብሔር እንቀርባለን፤ ፍቅሩንም እያሰብን የበለጠ እንወደዋለን፡፡ ሕዝ 36፡25-27፡፡ ንስሓ ከኃጢአት እንቅልፍ መንቃት ሲሆን (ሮሜ 13፡11) ሰዎች ስለ ኃጢአታቸው ተጸጽተው ከእግዚአብሔር ጋር እንዳይታረቁና ወደሚወዳቸውና ወደሚቀበላቸው አምላክ እንዳይመለሱ በብርቱ በሚጥረው ሰይጣን ላይ የተገኘ ድልም ነው። መዝሙር 123፣ 6-7፡፡ ንስሓ ከኃጢአትና ከዲያብሎስ ባርነት ነጻ በመውጣት (ዮሐ 8፣34-36) ወደ መንፈሳዊ ሕይወት ተመልሶ (ኤፌሶን 5፣14) ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅና (2ኛቆሮ 6፣19) ወደ እግዚአብሔር መቅረብና መመለስ ነው። (ሚል 3፣7)፡፡

የምሥጢረ ንስሓ አመሠራረት
ምሥጢረ ንስሓን የመሠረተ ራሱ ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ለሰው ልጆች ሁሉ የሚራራና የሚያዝን መፍቀሬ ሰብእ ክርስቶስ የእኛን ኃጢአት ሁሉ በሰውነቱ ተሸክሞ በሕማምና በሞቱ አንድ ጊዜ አድኖናል፤ በዚህም የተነሳ ልጅነታችን ተመልሶልናልና ዳግመኛ የእግዚአብሔር ልጆች የምንሆንበት ዕድል ተሰጥቶናል፤ ይህንንም ጸጋ በምሥጢረ ጥምቀት አግኝተነዋል። ከዚህ በኋላ ለምንፈጽመው በደል ማስተሥረያ እንዲሆነን ለሐዋርያትና በእነርሱ እግር ለተተኩት ካህናት ሥልጣንን በመስጠት ምሥጢረ ንስሐን መሥርቶልናል። ኃጢአትን የማስተስረይ ሥልጣን የእግዚአብሔር ብቻ ሲሆን ለእኛ ጥቅምና ደህንነት ሲል ለቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ለጴጥሮስና ለሐዋርያት ተከታዮች የክህነትን አገልግሎት ሰጥቷል። ቅዱስ ጴጥሮስ ስለእውነተኛ እምነቱ ከመሰከረ በኋላ ሥልጣነ ክህነትን ማለትም የመንግሥተ ሰማያትን ቁልፍ ክርስቶስ ሰጥቶታል። እንዲህም ብሎታል የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፤ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል ማቴ 16፣19፡፡  እንደዚሁም ይህን ሥልጣን ለሌሎች ሐዋርያትም ሰጥቷቸዋል። ማቴ 18፣18፡፡ ከትንሣኤው በኋላም ለሦስተኛ ጊዜ ኃጢአትን የማስተስረይ ሥልጣን ሰጥቷቸዋል። አብ እኔን እንደላከኝ እኔም ደግሞ እልካችኋለሁ አላቸው። ይህንንም ብሎ እፍ አለባቸውና መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል አላቸው። 20፣21-23፡፡ ስለዚህ ኃጢአትን የማስተሥረይ ሥልጣን ለእነሱ የተሰጠ ስለሆነ በሐዋርያት እግር ለተተኩ ለቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ካህናት ኃጢአትን መናዘዝ ይገባል።

የንስሐ ዓላማ በራሳችን ድካም የሠራነውን በደል ዕገሌ አሳስቶኝ እያሉ ሌላውን ሰው ስለ እኛ ስህተት ተጠያቂ ማድረግ ሳይሆን፣ አንደበታችንን ከሳሽ፣ ህሊናችንን ምስክር፣ አድርገን በመጨከን ራሳችንን በእግዚአብሔር ፊት መክሰስ ነው። ከሰዎች ተሸሽገን የበደልነውን በደልና የፈጸምነውን ኀጢአት ካህኑን ምስክር አድርገን በእግዚአብሔር ዳኝነት ፊት መቅረብ ነው፡፡ ከሰዎች ተሸሽገን የበደልነውን በደል በካህኑ ፊት በምንናገር ጊዜ ነፍሳችን ስለምታፍርና ስለምትሸማቀቅ ምህረቱ ብዙ የሚሆን አምላካችን እግዚአብሔር ይህንን የልባችንን መመለስ አይቶ የሠራነውን በደል ሁሉ እንዳልተሠራ አድርጎ ያነጻናል ። በደልንና መተላለፍን በንስሓ ይቅር ማለት የእግዚአብሔር የቸርነት ሥራ ነውና በካህኑ ፊት ማፈሯንና መሸማቀቋን ለነፍሳችን እንደቅጣት ይቆጥርላትና ሥርየትን/የኃጢአት ይቅርታን ይሰጣታል፡፡  

ኃጢአትን ለመምህረ ንስሓ መናገርን ወይም መናዘዝን እንደ ስሕተት የሚቆጥሩና ሌላ ወኪል ምን ያስፈልጋል፣ እኔ ራሴ በቀጥታ ለእግዚአብሔር አልነግረውምን? . . . ብለው የሚከራከሩ ሰዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ሐሳባቸው ከቅዱሳት መጻሕፍት ቃል ውጭ ስለሆነ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም። ኀጢአቱን የሚሰውር አይለማም፤ የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምሕረትን ያገኛል። ምሳ 28፣13 ተብሎ እንደተጻፈ ኀጢአትን መናዘዝ ተገቢ ክርስቲያናዊ ተግባር ነው፡፡  በሌላም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እርስ በርሳችሁ በኀጢአታችሁ ተናዘዙ ተብለን ስለታዘዝን ኀጢአታችንን ለመምህረ ንስሓችን እየተናዘዝን ሥርዐተ ንስሓን እንፈጽማለን፡፡ ያዕ 5፣16፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ የንስሓ ጥምቀትን በሚያጠምቅበት ጊዜም ሕዝቡ ሁሉ ከመጠመቃቸው በፊት ኀጢአታቸውን ይናዘዙ አንደነበረም ከመጽሐፍ ቅዱስ እናነባለን፡፡ ማቴ 3፣6፤ ማር 1፤5፡፡

ንስሓ እንዴት ይፈጸማል?

እንግዲህ ንስሓ ገብተን፣ የኃጢአትን ሥርየት አግኝተን፣ ከሰውና ከእግዚአብሔር ጋር ታርቀን በጽድቅ ጎዳና ለመራመድና በደኅንነት ጸጋ ለመኖር እንድንችል ቢያንስ ሦስት ነገሮችን መፈጸም አለብን። የመጀመሪያው የንስሓ ኀዘን ወይም እውነተኛና ልባዊ ጸጸት ሲሆን ይኸውም ስለክፉ ሥራችንና ስለመተላለፋችን የምንጸጸትበትና በደላችንን የምናምንበት ነው፡፡ መበደላችንንና መተላለፋችንን ሳናምንና ጥፋተኛነታችንን ሳንቀበል ወደሚቀጥለው የንስሓ ሥርዐት ልንደርስ አንችልምና፡፡ ሁለተኛው ኑዛዜ ሲሆን የበደልነውን በደልና ክፉ ሥራችንን ሁሉ ካህኑን ምስክር አድርገን በእግዚአብሔር ዳኝነት ፊት የምንናዘዝበትና ራሳችንን ጥፋተኛ አድርገን የምናቀርብበት መንገድ ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ስለኃጢአታችን የሚሰጠንን የንስሓ ቅጣት የሚመለክት ሲሆን የሚሰጠንን ቀኖና/ሥርዓት መፈጸምና ከዚህ በኋላ በካህኑ በኩል የምናገኘው የፍትሐት/ከኃጢአት እስራት የመፈታት/ ጸጋ ነው። እግዚአብሔር ኀጢአታችንን ይቅር እንደሚለንና ምህረትን እንደምንቀበል ማመናችን የተሰጠንን ቀኖና በመንፈሳዊ ታማኝነትና በእምነት በመፈጸማችን ይታወቃል፡፡

ንስሐ የሚገባ ሰው በመጀመሪያ ኀጢአቱን እያስታወሰ፣ ሰውና ፈጣሪውን መበደሉን እያሰበ የሚያደርገው ኀዘን ወደ ንስሐ የሚወስድ እውነተኛ ኀዘን ስለሆነ ኀዘኑን እግዚአብሔር ይቆጥርለታል። የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፣ መጽናናትን ያገኛሉና ማቴ 5፣4 የተባለው የራሳቸውንና የሌላውን ኃጢአት እያሰቡ የሚያዝኑትን ተነሳሒያን ይመለክታል። ስለእውነተኛው ኀዘን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደሚከተለው ያስተምረናል፡- አሁን ግን ስለ እርሷ በብዙ ደስ ይለኛል፡፡ ደስታዬም ስለአዘናችሁ አይደለም ንስሓ ልትገቡ ስላዘናችሁ እንጂ፤ ከእናንተ አንዱ ስንኳ እንዳይጠፋ ስለእግዚአብሔር ብላችሁ አዝናችኋልና፡፡ ስለእግዚአብሔር ተብሎ የሚደረግ ኀዘን የዘለዓለም ሕይወትን የሚያሰጥ ንስሓ ነው፡፡ 2ኛ ቆሮ 7፣9-10፡፡ እንግዲህ ከዚህም በኋላ ተነሳሒው እውነተኛውን ኀዘን ከእንባ ጋር አድርጎ በንጹህ ልቦናና ጸሎት ለእግዚአብሔር በማቅረብ እንደገና ላለመበደል መወሰን ይኖርበታል። ውሳኔውንም ለመፈጸም የሚያስችለውን የመንፈስ ቅዱስን ረድኤት ለማግኘት ሁልጊዜ ተግቶ መጸለይ አለበት።

ከዚህ ቀጥሎ ተነሳሒው ኃጢአቱን ሥልጣነ ክህነት ላለው ካህን ይናዘዛል። ኑዛዜ ማድረግ በቅዱሳት መጻሕፍት የታዘዘ ነው። ከእነዚህ ነገሮች በአንዲቱ በደለኛ ቢሆን፥ የሠራውን ኀጢአት ይናዘዛል። ስለሠራው ኀጢአት ለእግዚአብሔር የበደልን መስዋዕት ያመጣል፤ … ካህኑ ስለኀጢአቱ ያስተሠርይለታል። … እርሱም ይቅር ይባላል።ዘሌ 5፣5-10፡፡ የኀጢአትን ሥርየት ለማግኘት ለካህን መናዘዝ እንደሚገባ መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚያስተምረን ኃጢአታችንን ለአናዛዡ ካህን ከበደሉ ዓይነትና ሁኔታ ጋር ማስረዳት ይገባናል። ስንናዘዝም ከእንባና ከጸጸት ጋር ሆነን ከካህኑ ጋር አብሮ እግዚአብሔር እንደሚሰማን አምነን በእውነት መናገር ያስፈልገናል። በሽታውን የሰወረ መድኃኒት አያገኝም እንዲሉ ለነፍስ ቁስል ሐኪም ለሆነው ለካህኑ ኀጢአታችንን ከሰወርን ለነፍስ የሚሆነውን ፈውስ ለማግኘት አንችልም። ኀጢአቱን የሚሰውር አይለማም፤ የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምሕረትን ያገኛል። ምሳ 28፣13 ተብሎ ተጽፏልና ከቂምና ከበቀል በመራቅ፣ የበደልነውን እየካስን፣ የበደለንን ደግሞ ይቅር እያልን ብንናዘዝና የሰማዩን አባታችንን በጸሎት ብንጠይቀው ምሕረትና ፈውስን፤ ለኀጢአታችንም ሥርየትንና ይቅርታን ይሰጠናል። ነገር ግን እኛ ማንንም አልበደልንም ኃጢአትም የለብንም ብንል እግዚአብሔርን ሐሰተኛ ማድረጋችን ስለሆነ እንጠንቀቅ። ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ እንዳለው ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፣ እውነትም በኛ ውስጥ የለም። በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው። ኃጢአትን አላደረግንም ብንል ሐሰተኛ እናደርገዋለን ቃሉም በኛ ውስጥ የለም። 1ኛ ዮሐ 1፣8-10፡፡

ምንጭ፡-
1) መጽሐፍ ቅዱስ
2) የንስሓ ሕይወት - በዲ/ን እሸቱ ታደሰ
3) የንስሓ በር - በመ/ር ተስፋሁን ነጋስህ
4) ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት - በሊቀ ጉባዔ አባ አበራ በቀለ


ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ!

 . . . ይቀጥላል . . .


No comments:

Post a Comment