ቅዳሴ ቄርሎስ
(ክፍል ሁለት)
ይህን ንጹሕ ቅዱስ መስዋዕት በፊትህ እናቀርባለን፤ ስለ አቤልና ስለ ሴት፤ ስለ ሄኖክ፤ ስለ መልከ ጼዴቅም፡፡ ስለአብርሃም፣
ስለ ይስሐቅና ስለ ያዕቆብ፤ ስለ ሙሴና ስለአሮን፤ ስለ ነቢያትም ሁሉ፡፡
ስለ ስምዖን ጴጥሮስ፤ ስለ ዮሐንስ መጥምቅም፤ ስለ ሐዋርያትም ሁሉ፡፡
ስለ ዳዊትና ሕዝቅያስ፤ ስለ ኢዮስያስና ስለ ንጉስ ቆስጠንጢኖስ፤ በቀናች ሃይማኖት ስለሞቱት ነገሥታት ሁሉ፡፡
ስለ ኤጲስ ቆጶሳት፤ ስለ ቀሳውስትና ስለ ዲያቆናት፤ ስለ ንፍቀ ዲያቆናትና ስለ አናጉንስጢሳውያን፤
ስለ ወራዙትና ስለ ደናግልም ሁሉ፡፡
መንፈስ ቅዱስ በላይዋ ስላደረባትና የሕይወት መንፈስ ስለ ተፈጸመላት ነፍስ፡፡ በምትወደው በልጅህና በወዳጅህ፤ በጌታችን
በኢየሱስ ክርስቶስ አምሳል ስለ ተቀረጸች መልክ ሁሉ፡፡
ይህ ቁርባን ስለ ተደረገላቸው፤ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንህ ስላገቧቸውና ደገኛ ቅዱስ ወደሚሆን
ወደ መሠውያህ ፊት ስላቀረቧቸው ቅዱሳንም ሁሉ፡፡
በቀናች ሃይማኖት በምድር ላይ ሁሉ ስለሚኖሩ ስለ መንገደኞችና ስለ ስደተኞችም ሁሉ፤ ከዚህ ዓለም የወጡ፡፡
በምትወደው በልጅህና በወዳጅህ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስም ስላመኑ አፍና አንደበት ሁሉ፡፡
ከርሱ ጋራ ክብር ያለው ሥውር ከሚሆን ከመንፈስ ቅዱስም ጋራ፤ ለዘለዓለሙ፡፡
ለእነርሱም ለሁሉም፤ ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ቤተ ክርስቲያንህ ትሰግድልሃለች፣ ሙሽራህም ከፍ ከፍ ታደርግሃለች፡፡ በልዑላን ጥቅም፤ በሱራፌል ቅዳሴና በኪሩቤል ውዳሴ፤
በመላእክትም ምስጋና፤ በትጉሃን ልመና፤ በቅዱሳንም ፍጹምነት፡፡
በአዳም ንጽሕና፤ በኖኅም መሥዋዕት፤ በአብርሃም እንግዳ ተቀባይነት፤ በይስሐቅ ቸርነት፤ በያዕቆብ
መገለጽ፡፡
በዮሴፍ እስራት፤ በኢዮብ ትዕግሥት፤ በሙሴም የዋህነት፤ በኤልያስም ምስጋና፡፡
በሐዋርያትም ማፍቀር፤ በቅዱሳንም ልመና፤ በተሰደዱ ሰዎች ድካም፤ ባልበደሉ ሰዎች ጽድቅ፤ ንጽሕናን
ባገኙ ሰዎች ትሕትና፡፡
በንጹሓን ገድል፤ ከምግብ በተለዩ ሰዎች ትህርምት፤ ፍጹማን ስለሆኑ ቅዱሳን ጽድቅ ፡፡
በምድር ዳርቻ ርቀት፤ በባሕር አዝዋሪ ጥልቅነት፤ በመባርቅት ብልጭታ፤ በደመናትም መውጣት ፡፡
በመላእክት ምስጋና፤ በቅዱሳንም ምስጋና፤ በትጉሃን ንጽሕና በልዑላንም መስማማት፤ በመንፈሳውያን ብርሃን ፡፡
በካህናት ቀኝ፤ በሰማዕታት መሞት፤ በምዕመናንም ደም፤ በብርሃናውያን መላእክትም ገናንነት ፡፡
በልጅህ መመታት (ተጸፍኦ)፤ በአንድ ልጅህ ሕማማት፤ ሁሉን በያዘ ሥልጣንህም ፡፡
ወደ ጌታችንና ወደ መድኃኒታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ አባት በምታርግ ጸሎት ፡፡
እርሱን በሚያሲዙባት በዚያች ሌሊት ፡፡
ክቡራትና ብፁዓት በሚሆኑ እድፍ በሌለባቸው እጆቹ ኅብስቱን ያዘ፤ ወደ አንተ ወደ አባቱ ወደ
ሰማይ አቅንቶ አየ፡፡
አመሰገነ ባረከ ቆረሰ ፡፡ አላቸውም ንሡ ብሉ ይህ ኅብስት “እማሬ” ኃጢአት በሚሠረይ ገንዘብ ለዓለሙ ሁሉ ቤዛ ስለእናንተ የሚፈተት ሥጋዬ ነው፡፡
ዳግመኛም ራታቸውን ከበሉ በኋላ ጽዋውን ይዞ አመሰገነ፤ ባረከ፤ አከበረም፡፡ ደቀመዛሙርቱንም
አላቸው ንሡ ጠጡ ይህ ጽዋ፤ “እማሬ” ኃጢአትን ለማስተሥረይ ስለእናንተ የሚፈስና ለዓለሙ ሁሉ ቤዛ የሚሰጥ ሐዲስ ሥርዓት የሚሆን ደሜ ነው፡፡
የሚነድ የእሳት ሰይፍ ሜሎስ (መንፈስ ቅዱስ) ይገለጽ፤ ሰማየ ሰማያትም በቸርነትህ ይከፈት፤ በፈቃድህም ሕያውና ቅዱስ
መንፈስህ ይላክ፤ ይውረድ፤ ይምጣም። በዚህም ኅብስትና ጽዋ ላይ ይረፍ፤ ይባርከው፤ ይቀድሰውም፤ ከአንድ ልጅህ ከጌታችንና ከአምላካችን ከመድኃኒታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ደም ጋራ አንድ ይሆን ዘንድ። ለሚቀርቡት የበደል ማስተሥረያ፤ ለሚቀበሉትም የኃጢአት ይቅርታ ይሆን ዘንድ ።
በቀናች ሃይማኖት አንድ ሆነው ከእርሱ ለሚቀበሉ ሰዎች ሁሉ ለይቅርታና ለምሕረት፤ ለደኅንነትና ለረድኤት፤ ለነፍስና ለሥጋ ሕይወት ይሁንላቸው፡፡ ለበደል ማስተሥረያ፤ ለኃጢአት ይቅርታ፤ ለትንሣኤ ሙታንና ለሐዲስም ሕይወት ይሁንላቸው፤ ለዘለዓለሙ።
ዳግመኛም ሁሉን የሚይዝ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አባት እግዚአብሔርን እንማልዳለን።
አቤቱ የመንፈስ ቅዱስን መውረድ እየተመኘን ዐይኖቻችንን ወደአንተ እንሰቅላለን። በአብራከ ልቡናችንም እንሰግድልሃለን፤ የኅሊናችንንና የመንፈሳችንን ራስ እናዋርድልሃለን ።
አቤቱ በቅድስናህ ቀድሰን፤ በምሕረትህም አንጻን፤ ቅዱስ ምስጢርህንም ለመቀበል የተገባንና አንድ የሆን አድርገን ።
በቅዱስ መሠውያህ በፊትህ ያኖርነው ይህ የእሳት
ፍሕም የሚከሰን አይሁን። የፈተትነው ይህ የአምልኮ ኅብስት ለበቀል አይሁንብን፤ ነፍሳችንንና ሥጋችንን ስላላነጻን ።
የሚያቃጥል እሳትን ለመብላት፤ የጋለ ፍሕምንም ለመዋጥ ከንፈርን መክፈት የሚያስፈራ ነው። ነፍስ ውስጥዋን ከሽንገላ ካላነጻች ።
በድንኳኑ ውስጥ የንጹሕ ሙሽራን መሠዋቱን ማየት
የሚያስፈራ ነው ።
ሕያው የሚሆን የአምላክን
ልጅ በሰማያዊ አባቱ ፊት መሠዋቱን ማየት የሚያስፈራ ነው ።
የመለኮትን ብልጭታ መቅረብ፤ የጌትነት ብርሃንንም
(መብረቅ)መንካት የሚያስፈራ ነው ።
ለመያዙ ራሳችንን እናንጻ፤ ለመቀበሉ ነፍሳችንን እንቀድስ፤ ንጹሕ መግዝዐ ላህም ሆኖ ይሠዋ ዘንድ ለወደደ
አብ ምስጋና ይገባዋል እንበል ።
ለወልድም ምስጋና ይገባዋል፤ ይኸውም ንጹሕ የሚሆን መግዝዐ ላህም ነው፡፡ ይህን ኅብስት ንጹሕ የሚሆን የመግዝዐ ላህም ሥጋ ላደረገው
ለመንፈስ ቅዱስም ምስጋና ይገባዋል ።
ሦስት ስም አንድ እግዚአብሔር
ነው፤ ሦስት ገጽ አንድ መልክ፤ ሦስት አካል አንድ ባሕርይ ነው ።
በትጉሃን መላእክት አፍ መመስገን ይገባዋል፤
በነቢያትና በሐዋርያትም አፍ መመስገን፤ ቅዱስ
መባል ይገባዋል፤ ከዛሬ
ጀምሮ እስከ ዘለዓለሙ፤ እስከ ሁለተኛ ጉባኤ ድረስ ።
አብ ከልጁ ጋራ፤ ከመንፈስ ቅዱስም ጋራ፤ ከሰዓትና ከዕለት፤ ከአውራኅና ከዓመታት አስቀድሞ የነበረ ነው ።
በአነዋወር ለአንዱ ከሁለተኛው፤ ለሁለተኛውም ከሦስተኛው መቅደም የለም። የመባርቅት ፍጥነታቸው
ምን ያህል ነው። የንሥር ክንፎች ፍጥነት ምን ያህል ነው።
ባለመለያት አንድ ናቸው፤ ባለመቀላቀልም አንድ ናቸው፤ በሦስትነት ይኖራሉ፤ ባንድነት የተያያዙ
ናቸው፤ በአካል የተካከሉ ናቸው፤ በብርሃንና በፀዳል የተመሳሰሉ ናቸው ፡፡
አብ ልጁን ዓለም ሳይፈጠር የወለደው በሥራ ሊረዳው አይደለም፡፡ የመንፈስ ቅዱስም ባሕርይ የተገኘ ብልሃትና ሥራ ለማወጣጣት
አይደለም፡፡
ከእግዚአብሔር አብ ብቻ መወለዱን እንናገር፤ ያን ጊዜ እናት አልነበረችውም፤ የፍጡራን አነዋወር
ገና አልታየም ነበርና፤ ዳግመኛም ምድራዊ አባት ሳይኖረው የአምላክ ልጅ ብቻውን ከዳዊት ልጅ ከድንግል ብቻ መወለዱን እንናገር፤
እናውራ ፡፡
በዘር ለመወለድ አባት ስላልነበረው የሰውነት ሥራ አልጎደለበትም፤ ከድንግል ብቻ ፈጽሞ ሰው ሆነ እንጂ፡፡
ከአዳም ጎን አጥንት በተፈጠረች ጊዜ እናት ስላልነበረቻት ሔዋን የሴቶች ባሕርይ እንዳልጎደለባት፤
እንዲሁ የአዳምን አባት በሥጋ በወለደችው ጊዜ የማርያም ማኅተመ ድንግልናዋ
አልጎደለም ፡፡
አዳምን የጎኑ አጥንት በተነቀለ ጊዜ እንዳላሳመመው
እንደዚሁ የገሊላ ወገን የምትሆን የአምላክን እናት ሕማመ ወሊድ አላገኛትም ።
እንዲህ እናምናለን፤ እንዲህም እንታመናለን፤ ይህ የምንፈትተው ኅብስት ከዕብራውያን ልጅ
የነሣው የክርስቶስ ሥጋ እንደ ሆነ ።
ዳግመኛም ይህ ጽዋ የእግዚአብሔር በግ ከሚሆን
የፈሰሰ ደመ መለኮት እንደሆነ እናምናለን፤ ዳግመኛም ይህ ትእምርተ መስቀል በሕማማቱ ጊዜ የተዘረጋ የክርስቶስ የመስቀሉ ምሳሌ እንደ
ሆነ እናምናለን ።
ደምን የተረጨች ልብስን
ለለበሰ ለእርሱ በመሠዊያው
ፊት እንሰግዳለን፤ ደምን ለተረጨች ለዚያችም ልብስ ለዘለዓለሙ ።
ያን ጊዜ ከዚህ ከማይጠፋ ምሥጢር የተቀበልን
የእኛ አፋችን ደስታን ተመላ፤ አንደበታችንም
ደስ አለው ።
አቤቱ ዓይን ያላየውን፤ ጆሮ ያልሰማውን፤ በሰው ልቦናም ያልታሰበውን ቅዱስ ስምህን ለሚወዱ
ሰዎች ያዘጋጅህ አምላክ ምን ትደነቅ። በቅድስት ቤተ ክርስቲያንህ ላለን ለታናናሾች ሕፃናት ለእኛ ገለጽህ፤ አብ ሆይ ይህ ፈቃድህ
በፊትህ የሆነው አምላካችን እግዚአብሔር አንተ ይቅር ባይ ስለ ሆንህ ነውና።
ለአንተም እስከ አርያም ድረስ ምስጋናን፣ ክብርንም ለአብና ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስም እናቀርባለን
ዛሬም፣ ዘወትርም፤ ለዘለዓለሙ ።
የጠራኸንንና የቀደስኸንን
እኛን አቤቱ በአጠራርህ ዐድለን፤ በፍቅርህ ጠብቀን፤ በምስጋናህም አጽናን ።
ከክፉ ነገር ሁሉ ጠብቀን፤ በዘለዓለም መንግሥትህ በልጅህ በክርስቶስ በቀኝህ አድነን፡፡ በእርሱ ያለ ክብር፣ ጽንዕ ለአንተ ይገባል፤ ከእርሱ ጋራ፣ ከመንፈስ ቅዱስም ጋራ፤ ዛሬም ዘወትርም፤ ለዘለዓለሙ ።
No comments:
Post a Comment