Monday, February 15, 2016

መዳንና ቤዛነት በኦርቶዶክስ አስተምህሮ




   ኦርቶዶክሳዊ የሆነው ክርስቲያናዊ ሕይወት በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ኅብረትና አንድነት ውስጥ የሚሆን፣ የመጽሐፍ ቅዱስን መሰረታዊ ትምህርት የሚቀበል፣ ከእግዚአብሔርና ከቅዱሳኑ አንድነት ያልተለየ፣ በመንፈስና በእውነት የሚኖሩት ሕይወት ነው፡፡ ይህም ደግሞ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃሉና በስራው ያሳየን፣ ከክርስቶስ የተማሩ ሐዋርያትና ሐዋርያውያን አበው የሰበኩት፣ ከቅዱሳን አገልጋዮቹ የተቀበልነውና የወረስነው ሕይወት ነው፡፡ ‘‘ለቅዱሳን አንድጊዜ ፈጽሞ ስለተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርዃችኹ እጽፍላችኹ ዘንድ ግድ ኾነብኝ፡፡’’ (ይሁዳ ቁ 3) እንደተባለ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀመዛሙርቱ ያስተማራቸውና ያሳያቸው፣ በብዙ አመታት የትውልድ ቅብብሎሽ አንዳች ሳይጨመርበትና ሳይቀነስበት ከእኛ ዘንድ የደረሰ ነው፡፡ ‘‘የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለኹና፤ እነርሱም ተቀበሉት’’ ብሏልና ዮሐ 17፣8:: ሐዋርያት ያሳዩንና ያስተማሩን ሁሉም ከጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበሉት ነው፤ ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ ‘‘ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠኹትን እኔ ከጌታ ተቀብያለኹና’’ ሲል ያስተማረን፡፡ 1ኛቆሮ 11፣23፡፡ ስለሆነም ኦርቶዶክሳዊው ክርስትና የወደድነውን የምናደርግበት ሳይሆን ከክርስቶስ የተማሩ ቅዱሳን አባቶቻችን ያሳዩንን የምንከተልበትና ባስተማሩን ትምህርት የምንጸናበት ሕይወት ነው፡፡
የኦርቶዶክሳዊ ክርስትና መሰረታዊ አላማ የእያንዳንዱ ፍጥረታዊ ሰው መዳን፣ የክርስቶስ አካሉ በምትሆን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆኖ የክርስቶስ የአካሉ ክፍል መሆን፣ የቅድስና ሕይወትን ገንዘብ ማድረግና ዘላለማዊውን ሕይወት መውረስ ነው፡፡ ይህም የምስራቹ ወንጌል ነው፤ መሲህ ክርስቶስ ዓለሙን ሁሉ የዋጀበትና በሞቱ ሞታችንን አጥፍቶ በትንሳኤው የመዳናችንን መንገድ ያበጀበት፡፡
ኦርቶዶክሳዊ መዳን
አንደ ኦርቶዶክሳዊ የመዳን ትምህርት ከሆነ መዳን የምንለው ሰዎች ሁሉ ከጥፋት ርኩሰት ተለይተው በየእለቱ እግዚአብሔርን ወደመምስል የሚያድጉበት የማይቋረጥ ቀጣይነት ያለው ሒደት ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የመዳን ሕይወት ክርስቶስን የመምሰል ሕይወት ስለሆነ በመለኮታዊ ባሕርይ ውስጥ የሚኖረን ሱታፌ ነው፡፡ ይህም ደግሞ በክርስቶስ ስጋዌ የተቀበልነው ጸጋ ነው፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስም አምላክ ሰው ስለሆነ ሰው አምላክ መሆን ችሏል ያለው ለዚህ ነው፡፡ የክርስቶስ ስጋዌ ሰዎች በእርሱ ጸጋ ክርስቶስን በመምሰል የሚያድጉበትን ዕድል ፈጥሯል፡፡  ‘‘ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኗልና ’’ ዕብ 8፣29 እንዲል ያንን መልክ እንመስለው ዘንድ የክርስቶስ ቤዛነት/ የመስቀሉ ስራ የተገባን አድርጎናልና በየእለቱ ይህን መልክ ወደመምሰል እናድግ ዘንድ እግዚአብሔር ባበዛልን በጸጋው መጠን እንተጋለን፡፡ ከክርስቶስ ጋር ባለን ኅብረትና አካሉ በምትሆን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚኖረን ሱታፌ ክርስቶስን እየመሰልነው እንመጣለን፡፡
መዳን በምድር ላይ የምንኖረውን ሕይወት ብቻ የሚመለከት ሳይሆን ቀጣይነት ያለውን ዘላለማዊ ሕይወት የምንጀምርበትና በጀመርነው ዘላለማዊ ሕይወት ውስጥ ዛሬ በምድር ላይ ነገም ደግሞ በእግዚአብሔር መንግስት ለዘላለም የምንኖርበትም ነው፡፡ ይህም ሕይወት ሦስት ደረጃዎችን የያዘ ሲሆን እነርሱም ንፅህና(ከኃጢአት መንፃት/መለየት)፣ አብርሆት (በእግዚአብሔር ሀብትና ጸጋ ማደግ)፣ ክርስቶስን መምሰል ናቸው፡፡ ስለሆነም መዳን ከኃጢአት መለየት/መንጻት ብቻ ሳይሆን በመለኮታዊ ኃይል፣ ምስጢር፣ ጸጋና ጥበብ በመሞላት ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ወደማድረግ የምናድግበትና የመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች የምንሆንበትም ነው፡፡ ‘‘ስለ ክፉ ምኞት በዓለም ካለው ጥፋት አምልጣችኹ ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች በተስፋ ቃል እንድትኾኑ፥ በእነዚያ ክብርና በጎነት የተከበረና እጅግ ታላቅ የኾነ ተስፋን ሰጠን፡፡’’ 1ኛ ጴጥ 1፣4
   መዳን በክርስቶስ በጸጋው ስጦታ የሚደረግልንና እኛም ደግሞ በክርስቶስ ሆነን የምንፈፅመው ቀጣይነት ያለው የማይቋረጥ ሒደት ነው፡፡ መዳን ዝም ብለን ከእግዚአብሔር የምንቀበለው ነፃ ስጦታ ብቻ ሳይሆን ከእኛ የሆነውን ድርሻ የምንፈፅምበትም ሱታፌያችንን የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡ ይህም ደግሞ በቅጽበት የሚፈጸም ሳይሆን በእምነታችን፣ በበጎ ምግባራችንና መታዘዛችን ውስጥ የሚፈጸም ረጅም ሒደት ነው፡፡ በመዳን ውስጥ የሰው ልጅ ሱታፌ ባይኖር ኖሮ ዓለሙ ሁሉ በቅጽበት በዳነ ነበር፡፡ ስለሆነም መዳን የምንቀበለው ብቻ ሳይሆን የምንፈልገውም ነው፤ የሰው ልጅ ከአምላክ ጋር በኅብረት የሚያደርገው ሱታፌም ነው፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር የሰውን ነፃ ፈቃድ ያከብራልና! ሁላችንም ወደንና ፈቅደን እንጂ ሳንፈልግ ተገደን እንድንድን አያደርገንም፡፡ ስለሆነም የንስሓ ሕይወትና በምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን የሚኖረን ሱታፌ ከእግዚአብሔር ጋር የምንሆንባቸውና ከእርሱም ጋር ኅብረት የምናደርግባቸው መንገዶች ናቸው፡፡  እንግዲህ መዳን ስንል ይህንን ኅብረትና አንድነት ጭምር ነው፡፡
   ክርስቲያኖች ከእግዚአብሔር ጋር በሚኖራቸው ኅብረት የመለኮታዊ ባህርይ ተካፋዮች ይሆናሉ፡፡ 1ኛ ጴጥ 1፣4 ይህ ሲባል ግን ከሥላሴ ሦስትነት ውስጥ ይጨመራሉ ማለት አይደለም፡፡ ክርስቶስን በመምሰል ውስጥ የሚኖረን መንፈሳዊ እድገት በመለኮታዊ ኃይልና ጸጋ እንድንሞላ ስለሚያደርገን የእግዚአብሔር የሀብቱ ማደሪዎች እንሆናለን፡፡ ይህም ከአምላክ ጋር ኅብረት አንዲኖረን ስለሚያስችለን እዚህ ደረጃ ላይ የደረሱ ቅዱሳን ሰዎች በጸጋ አምላክነትን ገንዘብ ያደርጋሉ፡፡ ስለሆነም አንደአምላካቸው ሁሉ ብዙ ድንቆችንና ተአምራትን የሚያደርጉ ይሆናሉ፡፡ ‘‘እውነት እውነት እላችዃለኹ፥ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፤ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል፡፡’’ ዮሐ 14፣12፡፡ በመዳን መንገድ ውስጥ  የምንደርስበት መንፈሳዊ የእድገት ደረጃ ደግሞ ክርስቶስ ያደረገውን ድንቅ ተአምር አስከማድረግ ብቻ ሳይሆን እርሱ ካደረገው የሚበልጥ ነገርን ማድረግ እስከምንችልበት ጸጋ ድረስ የሚደርስ ነው፡፡ ‘‘እግዚአብሔር መንፈሱን ሰፍሮ አይሰጥምና፡፡’’ ዮሐ 3፣34፡፡ መዳን በጸጋ የእግዚአብሔር ልጆች የምንሆንበት መንገድ እንደመሆኑ መጠን የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችን ደግሞ የእግዚአብሔር ገንዘብ የሆነውን ሁሉ የምንወርስበት ነው፡፡ ‘‘ልጅም ከሆንህ ደግሞ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሽ ነህ’’ ይላልና፡፡ ገላ 4፣7
   ኦርቶዶክሳውያን ያልሆኑ ‘‘አቢያተ ክርስቲያናት’’ ኃጢአትን፣ ጸጋንና መዳንን የሚረዱበት መንገድ ህግንና ቅጣትን መሰረት ባደረገ መልኩ ስለሆነ የአዳምን ጥፋትና የክርስቶስን ማዳን የሚረዱበት መንገድ አዳም በማጥፋቱ ተቀጥቷል፣ ከዚያም ደግሞ ክርስቶስ የጥፋቱን ዋጋ ስለከፈለለት ይህንን ዋጋ ከማመን ባለፈ ሌላ የሚፈለግ የሰው ልጅ ድርሻ የለም ብለው ነው፡፡ የተከፈለለትን ዋጋ ማመኑ ብቻውን ለመዳን በቂ ነው ብለው ምናሉ፡፡ በእርግጥ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ነፃ ፈቃድን ሰጥቶታል ሰውም ይህንን ነፃ ፈቃዱን ተጠቅሞ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ አፍርሷልና መቀጣት ይገባው ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ጸጋ ደግሞ በይቅርታው ውስጥ ያለ ከኃጢአት ባርነትና ከቅጣት ሁሉ ነፃ የሚያወጣ ነውና ኦርቶዶክሳውያን አቢያተ ክርስቲያናት ይህንን ጉዳይ የሚመለከቱበት መንገድ ከዚህ የተለየ ነው፡፡ እንደ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ የሰው ልጅ የተፈጠረው በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት እንዲያደርግ ነው፡፡ ይህም ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖረን እውነተኛ ኅብረትና አንድነት ነው፡፡ የአዳም በደል ውጤቱ ከዚህ ኅብረትና አንድነት መለየት ሆኗል፡፡ ይህም የሰው ልጅ በመጀመሪያ ሲፈጠር የነበረውን እግዚአብሔርን የሚመስልበትን መልኩን አሳጥቶታል፡፡ ስለዚህ መዳን በህግ የተደረገ ይቅርታ ሳይሆን የሰው ልጅ ወደ ቀደመ ክብሩና መልኩ የተመለሰበት በክርስቶስ ኢየሱስ የተቀበልነው የእግዚአብሔር ጸጋ ሲሆን በተቀበልነው በዚህ ጸጋ ውስጥም የምናድግበት ሱታፌና ረጅም ሒደት ነው፡፡ ይህም የሰው ልጅና የመለኮት ኅብረት እንደገና የተመለሰበትና ሰው አምላኩን ወደመምሰል የደረሰበት ጸጋ ነው፡፡ ይህን ስንል ግን የሰው ልጅ አምላክነትን የባህርይ ገንዘቡ አደረገ ማለት ሳይሆን በመለኮታዊ ኑሮ ውስጥ ሱታፌ ማድረግ ቻለ ማለታችን ነው፡፡ ስለሆነም የክርስቶስ የማዳኑ ስራ የአዳም በደል የተቀጣበትና የእግዚአብሔር ፍርድ የተፈፀመበት ብቻ ሳሆን የአዳም የቀደመ መልኩ የታደሰበት እኛም በየቀኑ እግዚአብሔርን ወደመምሰል የምናድግበትና በክርስቶስ ሕይወት ውስጥ ሱታፌ የምናደርግበትም ጭምር እንጂ አንድ ጊዜ ተዋጅቻለሁና ከማመን የዘለለ ሌላ የሚጠበቅብኝ ነገር የለም በማለት ወደ ክርስቶስ የሚያቀርቡንን በጎ ምግባራትና መንፈሳዊ የትሩፋት ስራዎችን የምንተውበት አይደለም፡፡ የመዳናችንን መንገድ ያበጀልንና የሰራልን ራሱ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ይኸውም ደግሞ በራሱ ፈቃድ ያለሰው ልጆች አስተዋፅኦ የተፈጸመልን የጸጋው ነጻ ስጦታ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን የጸጋው ስጦታ በሕይወታችን ውስጥ እንዲሰራና እንዲገለጥ ከእኛ የሚጠበቅ ምንም ድርሻ የለም ማለት አይደለም፡፡ በመጀመሪያ የክርስቶስን መድኃኒትነትና በጸጋው የበዛልንን ስጦታውን ማመን ይጠበቅብናል፡፡ በእርግጥ እምነት ከእኛ የሚፈለግ የሰው ልጆች ድርሻ ቢሆንም በመዳን ውስጥ ብቸኛው ግን አይደለም፡፡ ‘‘ሰው በስራ እንደሚጸድቅ በእምነት ብቻም እንዳይደለ’’ እናውቃለንና እንደምናምን ሁሉ እንዲሁ ደግሞ በጎ ምግባራትንም እናደርጋለን፡፡ ያዕ 2፣24፡፡
ቤዛነት
   ቤዛነት የምንለው ደግሞ ስለ ሰው ልጅ መተላለፍና በደል ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ ጻድቅ ሲሆን የዓለሙን ሁሉ ኃጢአት ተሸክሞ የመተላለፋችንን እዳ የከፈለበትና ስለመተላለፋችን ሊሆንብን የሚገባውን የእግዚአብሔርን ፍርድና ቅጣት የፈጸመበት መንገድ ነው፡፡ እርሱ  አንዳችም በደል ሳይኖርበት ስለዓለሙ ሁሉ መዳን ሲል ኃጢአተኛ ሆኖ ተቆጥሯል፡፡ ‘‘በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሟል፤ እኛ ግን እንደ ተመታ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ እንደ ተቸገረም ቈጠርነው። እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ’’ እንዲል ኢሳ 53፣4-5፡፡ በክርስቶስ ስጋዌ ሰው አምላክ አንደሆነ ሁሉ/ ክርስቶስ በሰውና በአምላክ መካከል የሆነ መካከለኛ ስለሆነ፣ ሰውም አምላክም መሆን ስለቻለ/ በደሙ ቤዛነት የዓለሙን ሁሉ ኃጢአት ተሸክሞ የዓለሙን ሁሉ ቅጣት ተቀብሏል፡፡ እንደሰውነቱ የሰው ልጆችን ኃጢአት ተሸክሞ ለእኛ ስላለው ፍቅር ኃጢአተኛ ሆኖ ተቆጥሮልናል፤ እንደ አምላክነቱ ደግሞ በአዳም መተላለፍና ኃጢአተኝነት ላይ ፈርዷል፡፡ በዚህም የተነሳ ቀድሞ ወደነበረን እግዚአብሔርን ወደምንመስልበት መልክ መልሶናል፡፡ የክርስቶስ ቤዛነት ለዓለሙ ሁለ የተፈፀመና የሰው ልጆችን ሁሉ ስለቀደመው መተላለፍና መተዳደፍ እንዳይጠየቁ የሚያደርግና ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖረንን ኅብረትና አንድነት የሚመልስ ነው፡፡ ቤዛነቱም አዲሱን ሰው አዳምን ወደቀደመው መልኩ የመለሰበት፣ መለኮታዊውን ፍርድ የፈፀመበት፣ የአዳምን መተላለፍ የቀጣበትና የሰውን ልጅ ከእግዚአብሔር ጋር ያስታረቀበት የራሱ የእግዚአብሔር የሰውን ልጅ የዋጀበትና ገንዘብ ያደረገበት ጥበቡ ነው፡፡ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ሁሉ ኃጢአት በራሱ ላይ አድርጎ ስለዓለሙ ሁሉ ተላልፎ እንደተሰጠ ሁሉ፣ አሁን ደግሞ በክርስቶስ ሕይወት ውስጥ ዓለሙ ሁሉ ይኖራል፡፡ ምክንያቱም ቤዛነቱ ያስገኘልን ሕይወት ለራሳችን የምንኖረው ሳይሆን ክርስቶስ በእኛ ውስጥ ሆኖ የሚኖረው ሕይወት ነውና፡፡ ‘‘እኔም አኹን ሕያው ኾኜ አልኖርም፥ ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አኹንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው።’’ ገላ 2፣20
   ስለሆነም የተፈፀመልን ቤዛነት መዳናችንን የምንፈፅምበትና እግዚአብሔርን ወደመምሰል የምንደርስበት መንገድ እንጂ በእምነት ብቻ እንጸድቅበታለን ብለን የምንሰንፍበት ምክንያት አይደለም፡፡ ይህም ደግሞ የራሳችንን ፈቃድና ሃሳብ ሕያው የምናደርግበት ሳይሆን ሃሳባችንንና ፈቃዳችንን እየተውን የክርስቶስን ፈቃድና ሃሳብ የምንፈፅምበት ነው፡፡ ይህም ደግሞ አምነናል ብቻ ብለን የምንተወው ሳይሆን ደማችንን እሰከማፍሰስ ደርሰን የምንጋደልበትም ነው፡፡ ‘‘ከኀጢአት ጋራ እየተጋደላችኹ ገና ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችኹም ’’ ይላልና መፅሐፉ ዕብ 12፣4 ፡፡
                                                 ይትባረክ አምላከ አበዊነ!


4 comments:

  1. You are doing good. Keep going. we are following you do not be late to write.

    ReplyDelete
  2. I am really happy with your work. Keep it up!!!!

    ReplyDelete
  3. ያባቶቸን እርስት አልሰጥም

    ReplyDelete
  4. ቃለ ሕይወት ያሰማልን በጣም ጥሩ ትምህርት ነው ቀጥሉበት

    ReplyDelete