የሰንበት ትምህርት ቤቶች ታሪክ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከክርስትናው ጅማሬ አንስቶ
ምእመናንን በአገልግሎት ማሳተፍ ከጀመረችበት ጊዜና ሰዓት ጀምሮ ለብዙ ዘመናት ሁሉንም ያሳተፈና ያማከለ እንቅስቃሴ ከማድረግ አንጻር
እንደዚሁም ሁሉንም የእምነቱን ተከታዮች በየደረጃቸው፣ በየእድሜያቸውና በየግንዛቤ መጠናቸው በመያዝ አስፈላጊውን ትምህርትና አገልግሎት
ከመስጠት አንጻር ሰፊ ክፍተት ነበረባት፡፡ በዚህም መሰረት የነገ
የቤተክርስቲያን ተረካቢ የሆኑትን ወጣቶች በተቀናጀ እንቅስቃሴ
ከማሳተፍ አንጻር የነበረውን ክፍተት በመገንዘብ
ራሳቸውን እንደቤተ ክርስቲያን አካል በመቁጠርና ቤተ ክርስቲያናቸውን ለማገልገል በራሳቸው ተነሳሽነት ሃይማኖታዊ ትምህርትን ለመከታተል
በሚል በ1936 ዓ.ም በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ትምህርት ቤት የሥላሴ ማኅበር በሚል ስያሜ ወንድ ወጣቶች ብቻ የሚሳተፉበት ማኅበር መሰረቱ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላም የቅድስት
ሥላሴ ካቴድራል አስተዳደር ሴት ወጣቶችም ልክ እንደ ወንዶቹ የራሳቸውን
ማኅበር መመስረት እንደሚያስፈልጋቸው በመገንዘቡና ሴቶች እህቶቻችንም የቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርት እየገባቸው ሲመጣ ልክ እንደወንዶቹ
በመሰባሰብ መንፈሳዊ መዝሙሮችን ማጥናትና ከቅዳሴም በኋላ ዝማሬዎችን
ማቅረብ ጀመሩ፡፡ይህም ተግባራቸው የቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት አባቶችንና አገልጋዮችን ደስ በማሰኘቱ ማኅበሩን ለማጠናከርና ለመደገፍ
አስችሏቸዋል፡፡ በዋናነትም የነዚህ ማኅበራት መመስረት የሚከተሉትን ዓላማዎች ታሳቢ ያደረገ ነበር፡-
·
የቤተ
ክርስቲያንን ዶግማና ቀኖና ማስተማር
·
ሰብአዊ
ተግባራትንና አገልግሎቶችን መፈጸም
·
ኦርሮዶክሳዊ
ባህልንና አኗኗርን ማስጠበቅ
·
ወጣት
ሴቶች ያለምንም ፍርሀት ለማህበረሰቡ አገልገሎት እንዲሰጡና እንዲያስተምሩ ማስቻል
በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ
ቤተ ክርስቲያን የተጀመረው የሴት መዘምራን ወጣቶች መጠናከርና መበረታታት በሌሎች አቢያተ ክርስቲያናትም ለነበሩ ወጣቶች ትልቅ መነሳሳትን
በመፍጠሩ የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም መንፈሳዊ አገልግሎት የተፈሪ መኮንንና የእቴጌ መነን ትምህርት ቤት ተማሪዎችን አነሳሳቸው፡፡
በዚህም ምክንያት በየሳምንቱ እሁድ በቁጥር በዛ የሚሉ ወጣቶች በየቤተክርስቲያኑ እየተሰባሰቡ መንፈሳዊ ትምህርት ይማማሩ ጀመር፡፡
ግማሾቹም ለቤተክርስቲያን የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን መስጠት ጀመሩ፡፡ የኦርቶዶክሳውያን ወጣቶቹ ኅብረትና አንድነት እየተጠናከረ ሲመጣ
በተለያዩ የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች በጋራ በመሆን ሰንበት ትምህርት ቤት እንዲመሰረት ጥያቄ ማቅረብ
ስለጀመሩ በ1936 ዓ.ም የተምሮ ማስተማር ማኅበር በምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም ተመሰረተ፡፡ ከዚህ በማስከተል የወጣት ማኅበራቱ
ወደ ታዕካ ነገስት በዐታ ለማርያም፣ መንበረ መንግስት ግቢ ቅዱስ
ገብርኤል፣ መናገሻ ገነተ ጽጌ ቅ/ጊዮርጊስና ወደ ሌሎች ታላላቅ አድባራት
ተስፋፋ፡፡ በዚህ አግባብ እስከ 1974ዓ.ም የሴት ወጣቶች እና የወንድ
ወጣቶች ማህበር አድማሱን እያሰፋና እየተጠናከረ ቀጠለ፡፡ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል አስተዳዳሪ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ የሰንበት ትምህርት ቤቶችን አላማ በመቀበል ሰንበት
ትምህርት ቤቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግላቸው፣ ቀጣይነት እንዲኖራቸውም ተገቢ ትኩረት እንደሚቸራቸው
ገለጹ፡፡ ምንም እንኳን የነዚህ ማኅበራት መመስረት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ብቻ የተወሰነ ቢሆንም ቀስ በቀስ ከቤተክርስቲያኗ
አስተዳደር ጋር ሊያግባባና ሊያገናኝ የሚችል አደረጃጀት በመዘርጋት ወጣቶቹ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ሊኖራቸው
የሚገባውን ሱታፌ ማሳደግ በማስፈለጉ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ጽ/ቤት በሚል የጋራ አንድነት ተመሰረተ፡፡ የዚህ የጋራ ጽ/ቤት ዋና
አላማ የህጻናትንና ወጣቶችን መንፈሳዊ ትምህርትና አገልግሎት በተወሰኑ መንገዶች ማገዝና ማስተባበር ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ከ1965
ዓ.ም ጀምሮ የሰንት ትምህርት ቤቶች ጽ/ቤት የወጣቶች ጉዳይ ክፍል የሚል እድገት ተሰጠው፡፡ በ1966ዓ.ም ደግሞ የወጣት መንፈሳውያን
ኅብረት ጠቅላላ ጉባኤውን በደርግ ዘመን ከነበረው ለውጥ በኋላ ማካሄድ ቻለ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የእነዚህ ወጣቶች መንፈሳውያን ማኅበር በዚያን ሰዓት ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረግ ጀመረ፡፡ የዚህ
ጠቅላላ ጉባኤ መመስረት አሁን ያለው የሰንበት ትምህርት ቤቶች አደረጃጀት
ህጋዊ እውቅና አግኝቶ መቀጠል እንዲችል ትልቅ አስተዋጽኦ በማድረግ ከ 1970-1974 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በመላ ኢትዮጵያ ለመስፋፋት ችሏል፡፡ ከየካቲት 1974 ዓ.ም ጀምሮ
ቅዱስ ሲኖዶስ የወጣቶች ጉዳይ የሚለውን ስም በማስቀረት ሰንበት ትምህርት ቤት የሚል ስም እንዲሰጠው አደረገ፡፡ ከዚያን ጊዜ አንስቶ
ቅዱስ ሲኖዶስ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያን በማቋቋም ዛሬ ላለው የሰንበት ትምህርት ቤቶች አደረጃጀት መሰረቱን ጥሏል፡፡
የሰንበት ትምህርት ቤቶች አስፈላጊነት
አሁን ባለው የቤተ ክርስቲያናችን ነባራዊ ሁኔታ ሰንበት ትምህርት ቤቶችና ሌሎች የአገልግሎት ማኅበራት በቤተ ክርስቲያኒቱ
ሁለንተናዊ አገልግሎትና እድገት ወስጥ እያበረከቱት ያለው አስተዋጽዖ እጅግ ታላቅ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ እነዚህን ማኅበራትና
አደረጃጀቶች በአግባቡ በመቆጣጠር ወጥ የሆነ መዋቅራዊ አሰራር እንዲኖራቸው በማስቻል አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ማድረግ ብትችልና
ምቹ የአገልግሎት ዐውድ ብትፈጥርላቸው ለቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚያበረክቱት አስተዋጽዖ እጅግ
ሰፊ መሆን ይችል ነበር፡፡ አሁን ባለው የቤተ ክርስቲያኒቱ ተጨባጭ ሁኔታ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ያላቸው አስፈላጊነት ይህን ይመስላል፡-
1.
የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደራዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖያዊና መዋቅራዊ ክፍተት በመሙላት ረገድ ታላቅ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡
የቤተክርስቲያናችን አስተዳደር
ዘመኑን የዋጀና የተጠናከረ አለመሆኑ፣ የፋይናንስ ስርዐቱም ያልተማከለ መሆኑ አሁን በቤተ ክርስቲያኒቱ ወስጥ ለሚታዩት ችግሮች፣ ለአቢያተ ክርስቲያናት መዘጋት፣ ለአብነት ትምህር ቤቶች መዳከምና ለምእመናን
መነጠቅና መወሰድ ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ በዚህ ረገድ ሰንበት ትምህርት ቤቶች በቤተ ክርስቲያኒቱ የሚስተዋሉትን ክፍተቶች በሚችሉት
አቅም ለመሙላትና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠት ረገድ እያደረጉት ያለው አስተዋጽዖ ከፍተኛ ነው፡፡ ለምሳሌም ያህል የአብነት
ትምህርት ቤቶችን ለማገዝ የመማሪያ መጻሕፍትን፣ አልባሳትንና ሌሎች የመገልገያ ቁሳቁሶችን በማሟላት ረገድ እያደረጉት ያለው አስተዋፅዖ
ከፍተኛ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ በሚያስፈልጋት ማናቸውም ዓይነት ድጋፍ ምእመናንን በማስተባበር እያደረጉ ያሉት አገልግሎት የቤተ
ክርስቲያኒቱን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ድርሻ ከማጉላትና ከማሳደግ አኳያ ትልቅ አስተዋጽዖ በማበርከት ላይ ነው፡፡ በተጨማሪም ገዳማትና
አድባራት የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ በሚፈልጉበት ጊዜ ቀድመው በመገኘት ረገድ ሰንበት ትምህርት ቤቶችን የሚቀድም አካል የለም፡፡ ለምሳሌ ያክል በ
2004 ዓ.ም በዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም እና በአሰቦት ቅድስት ሥላሴ ገዳም ተከስቶ በነበረው የእሳት ቃጠሎ እሳቱን
ለማጥፋትና ገዳማቱን ከውድመት ለመታደግ ባደረጉት ርብርብና የአካባቢውን ህዝብ በማስተባበር የሰሩት ድርሻ በምንም ሊተካ የማይችል
ነው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን በየአቢያተ ክርስቲያናቱ ችግኞችን በመትከል የአበው ቅዱሳንን አሰረ ፍኖት ለመከተል እያደረጉት ያለው አሰተዋጽዖ
የሚያስመሰግናቸው ነው፡፡
በተጨማሪም
ሰንበት ትምህርት ቤቶች ለአቢያተ ክርስቲያናት ነፃ የጉልበት፣ የእውቀት፣ የሙያና የማማከር አገልግሎትን በመፈጸም የሚያደርጉት አስተዋጽዖም
ታላቅ ነው፡፡ ምእመናንን በማስተባበር ችግረኞችን ለመርዳትና የቤተ ክርስቲያንን ማኅበራዊ አገልግሎት ለማሳደግ እያበረከቱት ያለው
ድርሻ ጉልህ ነው፡፡ ህጻናትንና ወጣቶችን በስነ ምግባር በማነፅ፣ ኦርቶዶክሳዊውን ትምህርት በማስፋፋትና ለኦርቶዶክሳዊው ኑሮ አርአያ
በመሆን ሰንበት ትምህርት ቤቶች እየፈጸሙት ያለው አገልግሎት የሚያስመሰግንና ሊበረታታ የሚገባው ነው፡፡
2.
የወንጌል ተደራሽነትን ለማስፋት ሰንበት ትምህርት ቤቶች ትልቅ አስተዋጽዖ አላቸው፡፡
ሰንበት
ትምህርት ቤቶች በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ በሚሰጡ ማናቸውም ዓይነት ትምህርቶች ውስጥ በዝግጅትና በማስተማር እያደረጉት ያለው ተሳትፎ
ለቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርት መስፋፋት፣ መጠናከርና ለተደራሽነቱም ያለው በጎ አስተዋጽዖ በምንም ሊተካ የማይችል ነው፡፡ የአውደ
ምህረት ትምህርቶችን፣ ተከታታይ የኮርስ ትምህርቶችንና የርቀት ትምህርቶችን በመቅረፅ፣ በመምራትና በማስፈጸም ደረጃ እያበረከቱት
ያለው ድርሻ ለእቅበተ እምነትና ለምእመናን መጠበቅ ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡ ኦርቶዶክሳዊውን አስተምህሮ በማስፋፋትና በማጠናከር፣
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በማዘጋጀትና በመምራት፣ እርስ በርሳቸው በመማማር፣ ህፃናትን፣ ወጣቶችንና ጎልማሶችን በማስተማር ለክርስቶስ
ወንጌል መዳረስና ለመንግስቱ መስፋት ሐዋርያዊ ተልዕኳቸውን እየተወጡ ይገኛሉ፡፡
3.
ሰንበት ትምህርት ቤቶች በጋራ በመሰባሰባቸው በቤተክርቲያን ውስጥ ለሚካሄዱ አገልግሎቶች ውጤታማነት ትልቅ አስተጽኦ
ያደርጋሉ፡፡
የሰንበት
ትምህርት ቤት ወጣቶች በኅብረት ሆነው ለአገልግሎት መሰባሰባቸው አንድ ሰው በግለሰብ ደረጃ ከሚሰራው ስራና ሊያበረክተው ከሚችለው
አስተዋጽዖ በተሻለ ደረጃ የሚታይ ለውጥ ለማስመዝገብና የቤተ ክርስቲያኒቱን ሐዋርያዊ አገልግሎት ለመደገፍ ምቹ ሁኔታና ዕድልን ይፈጥራል፡፡
ስራዎችን በዕቅድ፣ በተደራጀና በተጠናከረ መልኩ ለማከናወን፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ባለው አሰራር ውስጥ ሆኖ ሊቆጠርና ሊለካ የሚችል
ስራን ለመስራትና ለውጥ ሊያመጣ የሚችል አገልግሎትን ለመፈጸም ሰንበት ትምህርት ቤቶች ምቹ መድረኮች ናቸው፡፡
4. ሰንበት ትምህርት ቤቶች የእግዚአብሔርን ብዙ የጸጋ
ስጦታዎች ለመጠቀም ትልቅ እድል ይሰጣሉ፡፡
ሰንበት
ትምህርት ቤቶች የነገዋ ቤተ ክርስቲያን ተረካቢ ወጣቶች በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች እንዲሳተፉ እድል በመስጠትና ወጣቶች ያላቸውን
ተሰጥኦ ለይተው በየዘርፉ ቤተ ክርስቲያንንና ምእመናንን እንዲያገለግሉ በማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ ሁሉም ሰው እንደተሰጠውና
እንደበዛለት ጸጋ መጠን የክርስቶስ ወንጌልና የመንግስቱ ሰራተኛ እንዲሆን በማስቻልና ቤተ ክርስቲያንን በልዩ ልዩ የሙያ ዘርፎች
ማገልገል እንዲቻል ሰንበት ትምህርት ቤቶች ምቹ የስራ አካባቢዎች ናቸው፡፡
5.
ሰንበት ትምህርት ቤቶች በቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ አገልግሎት ውስጥ ዝግጁነትን ከማሳደግ አንጻር ትልቅ ድርሻ
አላቸው፡፡
የቤተ
ክርስቲያንን አገልግሎቶች ተደራሽነት ለማሳደግና ለነገው የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት አስፈላጊውን ዝግጅት ለማድረግ፣ ወቅቱ የሚጠይቀውን
ተጨባጭ ሁኔታ ለመገንዘብና ወቅቱ በሚፈልገው መልኩ የቤተ ክርስቲያናችንን አገልግሎቶች ለመቃኘት፣ ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ ጊዜያት
ብዙ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች በሚያጋጥሟት ወቅት እነዚህን አደጋዎችና ችግሮች እንደዚሁም አፍራሽ እንቅስቃሴዎች ለመግታት ለቤተ ክርስቲያን
አባቶች በቂ መረጃዎችን በማሰባሰብ በቀላሉና በአጭር ጊዜ ውስጥ ለአባቶች በመስጠት ቤተ ክርስቲያን አፋጣኝ እርምጅ እንድትወስድ
ጉልህ ድርሻ አላቸው፡፡
በአጠቃላይ
ከላይ እንደተመለከትነው ሰንበት ትምህርት ቤቶች በቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት ሱታፌ ውስጥ ይህንን ያክል አስፈላጊ ከሆኑ በቀጣይ
በቤተክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ ውጤታማ አሰራር እንዲኖር ማድረግ
እንዲችሉ ሰንበት ትምህርት ቤቶችን በምን አግባብ ብንደግፋቸው ከዚህ በተሻለና በተጠናከረ መልኩ የቤተ ክርስቲያንን ሁሉን አቀፍ
አገልግሎት ማገዝና ማጠናከር ይችላሉ የሚለውን ቀጥለን እንመለከታለን፡፡
ይትባረክ አምላከ አበዊነ!
ይቀጥላል …
No comments:
Post a Comment