Friday, May 13, 2016

መዳንና በጎ ምግባራት በመጀመሪያይቱ የቅዱስ ዮሐንስ መልዕክት




ምዕራፍ አንድ
ቁ. 1 ‘‘እግዚአብሔር ብርሃን ነው፣ ጨለማም በእርሱ ዘንድ ጥቂትስ እንኳ የለም’’
እግዚአብሔር ብርሃን ነውና ሁሉ በፊቱ የተገለጠና የተራቆተ ነው፤ የሚሰወረው አንዳችም ነገር የለም፡፡  እግዚአብሔር ብርሃን ነውና ጨለማ የተባለ ጥመትና ክፋት በእርሱ ዘንድ የሉም፡፡ እርሱ በጎ፣ ቅንና እውነተኛም ነው፡፡እርሱ ብርሃን ከሆነ ደግሞ እኛም በብርሃን/በቅድስና ሕይወት ልንመላለስ ያስፈልገናል፡፡
ቁ. 2፡፡ ‘‘እርሱ ብርሃን እንደሆነ በብርሃን ብንመላለስ እኛ እርስ በርሳችን አንድነት አለን፤ የኢየሱስ ክርስቶስም ደም ከኃጢአታችን ሁሉ ያነጻናል፡፡’’ ከክርስቶስ ጋር ህብረት እንዲኖረንና እርስ በርሳችንም በህብረቱ ውስጥ በሚሆንልን አንድነት ውስጥ ሱታፌ እንዲኖረን የምንፈልግ ከሆነ በብርሃን ልንመላለስ ያስፈልገናል፡፡ በብርሃን/በቅድስናና በበጎ ምግባራት ስንመላለስ ያን ጊዜ የጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአታችን ሁሉ ያነጻናል፡፡ ስላመንን ብቻ አይደለም በደሙ የምንነጻው፤ እንዳመንን ሁሉ እንዲሁ ደግሞ በብርሃን ልንመላለስ/ በጎ ምግባራትን ልናደርግ ያስፈልገናል፡፡ ብርሃን የተባለ ደግሞ ከኀጢአት የራቀ የተቀደሰ ሕይወታችን ነው፡፡ በጎ ሥራ በጌታችን ትምህርት ብርሃን ተብሎ ተጠርቷል፡- ‘‘መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን ያመሰግኑት ዘንድ እንዲሁ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ፡፡’’ ማቴ 5፣16፡፡ በክርስቶስ ነኝ የሚል እርሱ በብርሃን እንደሆነ በብርሃን ሊመላለስ ያስፈልገዋል፡፡ በብርሃን የማይኖር ከክርስቶስ ጋር ሊሆንና ህብረት ሊያደረግ አይቻለውም ‘‘በእርሱ እኖራለሁ የሚል እርሱ እንደ ተመላለሰ ራሱ ደግሞ ሊመላለስ ይገባዋል።’’  1ኛ ዮሐ 2፣6፡፡ ክርስቶስ ኢየሱስ አዳኛችንና ተቤዢያችን እንደሆነ ሁሉ የምንከተለው መንገዳችንና ፍለጋችንም ደግሞ ነው፡፡ ስለሆነም በዚህ መንገዳችን ላይ እንሔዳለን ፍለጋውንም እንከተላለን፡፡ ክርስቶስ መከራን የተቀበለው እርሱ ዋጋ ከፍሎልኛል ብለን እንድንሰንፍና ከበጎ ምግባራት እንድንርቅ ሳይሆን በኑሯችን ሁሉ እርሱን እንድንመስለውም ጭምር ነው፡፡ በማዳኑ ኃይልና በደሙ ቤዛነት የምናምነውን ያህል እርሱ እንደኖረ እኛም በቅድስና ልንኖርና ልንመስለውም ይገባናል፡፡
ክርስትና የሚያስተምረን በክርስቶስ ማመንን ብቻ ሳይሆን ክርስቶስን መምሰልንም ነው፡፡ ‘‘እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ፡፡’’ 1ኛ ቆሮ 11፣1፡፡ መጠራታችን በክርስቶስ ለማመን ብቻ አይደለም፤ የክርስቶስን ፍለጋ ልንከተልም ጭምር እንጂ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን ክርስቶስ የተወልን የምንከተለው ፍለጋ መኖሩን ነው፡፡ ‘‘የተጠራችኹለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችኹ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሏልና።’’ 1ኛ ጴጥ 2፣21፡፡ ክርስቶስን እንከተላለን የምንል ከሆነ በፍለጋው ውስጥ ልንመላለስ ይገባል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚነግረን ልንወጣ አንችልም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ በክርስቶስ ማመንን ብቻ ሳይሆን ክርስቶስ በምድር ላይ እንደኖረው ያለ የተቀደሰ ኑሮን ስለመኖርም ይነግረናል፡፡ ‘‘እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጧልና።’’ ዕብ 12፣1-2፡፡ ክርስትና እንዲህ ነው! ኀጢትን አስወግዶ የእምነታችን ራስና ፈጻሚ የሆነውን ኢየሱስን መመልከት፣ በክርስትናችን ውስጥ የሚገጥሙንን ጾሮችና መከራዎች መታገስ፣ ክርስቶስ ነውርን ሁሉ እንደናቀ ስለመዳናችንም የመስቀል ሞትን እንደታገሰ እኛም ከዚህ ዓለም የሆነውን ክፉ ምኞትና የኀጢአት ሥራ ሁሉ በመናቅ ከክርስቶስ ጋራ የምንኖረውን ሕይወት መናፈቅ ነው፡፡   
‘‘ዳሩ ግን፦እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ኹኑ ተብሎ ስለተጻፈ የጠራችኹ ቅዱስ እንደ ኾነ እናንተ ደግሞ በኑሯችኹ ዅሉ ቅዱሳን ኹኑ። ለሰው ፊትም ሳያደላ በያንዳንዱ ላይ እንደ ሥራው የሚፈርደውን አባት ብላችኹ ብትጠሩ በእንግድነታችኹ ዘመን በፍርሀት ኑሩ።’’ 1ጴጥ 1፣15-17፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን በክርስቶስ ኢየሱስ የተቀበልነውን ጸጋና በእምነት የሚሆን መዳንን ብቻ አይደለም፡፡ የጠራንን እስክንመስል ድረስ የሚፈለግብንን የቅድስና ሕይወትም ጭምር እንጂ፡፡ እንደ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ ለሚነግረን ሁሉ እንታዘዛለን እንጂ የሚመቸንንና የምንፈልገውን ብቻ መርጠን አንከተልም፡፡ መዳናችን በጸጋው እንደሆነ እናምናለን፡፡ በጸጋውም እንደዳንን እንደምናምነው ሁሉ በጎ ምግባራት ለመዳን እንደሚያስፈልጉም መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናልና ይህንንም እናምናለን፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን በማመናችንና ባለማመናችን ላይ እንደሚፈርደው ሁሉ በበጎ ሥራችንና በክፉው ሥራችንም ላይ እንደሚፈርድ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡
ሰዎች በመዳን ትምህርት ውስጥ በጎ ምግባራትን የሚቃወሙት ለምንድን ነው ብለን ስንጠይቅ ምክንያቱ አምልኳቸው በእግዚአብሔር ፊት ንጹህ ስላልሆነና ራሳቸውንም በዓለም ከሚገኝ እድፍ መጠበቅ ስለማይችሉ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ ‘‘ንጹሕ የኾነ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው፤ ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ፥ በዓለምም ከሚገኝ እድፍ ሰውነቱን መጠበቅ ነው።’’ ያዕ 1፣27፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን እንግዲህ እንዲህ ነው! በእግዚአብሔር ፊት ንጹሕ የኾነ፣ ነውርም የሌለበት አምልኮ ከበጎ ምግባራት ያልራቀ፣ ሰውነትንም ከዓለም እድፍ የሚያርቅና የሚጠብቅ ነው እንጂ ክርስቶስ ስለ ኀጢአቴ ሞቷል እያሉ በጎውን ላለማድረግ የሚሰንፉበትና ሰበብ የሚፈልጉበት አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለጸጋ፣ እምነትና በጎ ምግባራት የሚያስተምረን በእኩል ሁኔታ ነው፡፡ አንደኛው ከአንደኛው እንደሚበልጥና እንደሚሻል አይነግረንም፡፡ ሦስቱም ግን ለመዳን እንደሚያስፈልጉ ይነግረናል፡፡ ስለሆነም ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችን ያለ ልዩነት ስለጸጋ፣ ስለእምነትና ስለበጎ ምግባራት በእኩል ታስተምራለች እንጂ ከዚህኛው ይኼኛው ስለሚሻል ይህንን አብልጣችሁ ያዙ የሚል ትምህርት የላትም፡፡ ‘‘ቃሉ የታመነ ነው። እግዚአብሔርንም የሚያምኑት በመልካም ሥራ በጥንቃቄ እንዲጸኑ፥ እነዚህን አስረግጠህ እንድትናገር እፈቅዳለሁ።’’ ቲቶ 3፣8 እንደተባለ የተጻፈውን በእኩል ተቀብለን እናምናለን እንጂ የገዛ ሐሳባችንን ለማቆም አንሞክርም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን እንዲህ ነው፡- ‘‘ሰው በእምነት ብቻ ሳይኾን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችኹ፡፡’’ ያዕ 2፣24፡፡ ቃሉን ልንሽረው ስለማንችል ቤተ ክርስቲያናችን በእግዚአብሔር ርህራሄ፣ በክርስቶስ መታዘዝ አንዲሁ በነጻ በጸጋው የተደረገልንን መዳናችንን፣ ከጸጋው የተነሳም በጸጋው ላይ በሚኖረን እምነትና መደገፍ፣ ጸጋውን በማመናችንም በመታዘዝ የምንፈጽማቸውን በጎ ምግባራትና የተቀደሰ ሕይወት የመዳን ትምህርቶች ናቸው ብላ ታስለምረናለች እንጂ ጸጋውን፣ ወይም እምነትን አሊያም በጎ ምግባራትን አስበልጣችሁ ያዙ የሚል ትምህርት የላትም፡፡ 
‘‘ብርሃን ወደ ዓለም መጥቷልና፤ ሰውም ሥራው ክፉ ስለሆነ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን መርጧልና፡፡ ሥራው ክፉ የሆነ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፤ ክፉም ስለሆነ ሥራው እንዳይገለጥበት ወደ ብርሃን አይመጣም፡፡ እውነትን የሚሠራ ግን ሥራው ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል፤ ስለ እግዚአብሔር ብሎ ይሠራልና፡፡’’ ዮሐ 3፣19-21፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለሙ ሁሉ ብርሃን ሆኖ በምድር ላይ ተገልጧል፡፡ ሥራቸው በጎ የሆነና በጽድቅ የሚመላለሱ ብርሃን ወደሚሆን አምላካችን ይቀርባሉ፣ ክፉውን የሚያደርጉ ግን በጨለማ ናቸውና ብርሃን ወደሚሆን አምላካችን ሊመጡ አይወዱም፡፡ ጨለማ የተባለ ክፉ ስራቸው ብርሃን በሚሆን በጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲገለጥ አይሹምና፡፡ ያለበጎ ምግባራት የሚሆን በክርስቶስ ኢየሱስ ያለ እምነት ሊኖር አይችልም፡፡ በክርስቶስ የሚያምን ሰው በጎ ምግባራትንም ገንዘብ ያደርጋል፡፡ ‘‘ቃሉን የምታደርጉ ኹኑ እንጂ ራሳችኹን እያሳታችኹ የምትሰሙ ብቻ አትኹኑ፡፡’’ ያዕ 1፣22፡፡ እንግዲህ ቃሉን የምንሰማው ለማመን ነው፤ እምነት ደግሞ ከመስማት ነው ሮሜ 10፣17፡፡ ማመን ደግሞ ለማድረግ ነው፡፡ ቃሉን ሰምቶ የሚያምን ነገር ግን እንደቃሉ የማያደርግና የማይኖር እራሱን ያስታልና፡፡ ‘‘ነገር ግን፥ ነጻ የሚያወጣውን ፍጹሙን ሕግ ተመልክቶ የሚጸናበት፥ ሥራንም የሚሠራ እንጂ ሰምቶ የሚረሳ ያልኾነው፥ በሥራው የተባረከ ይኾናል።’’ መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን እንዲህ ነው፤ ስለ እምነትብቻ አይደለም፣ ስለ በጎ ምግባራትም ብቻ አይደለም፤ ስለ ሁለቱም እንጂ፡፡ ያዕ 1፣25፡፡
በጎ ምግባራት በመዳናችን ወስጥ ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው ከዚህ ምዕራፍ እንማራለን፡፡ የተቀደሰ ሕይወት ያለው ሰው ሥራው በብርሃን የተገለጠ ነውና ብርሃን ወደሚሆን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይደርሳል፤ ክፉ ሥራን የሚያደርጉ ግን በጨለማ ናቸውና ብርሃን ወደሚሆን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መድረስ አይቻላቸውም፡፡

የልጅነት ወዳጄ




አንድ ዕለት ነው የቅርቤ ናቸው ከምላቸው ወዳጆቼ ጋር ሆኜ እየተጫወትን ነበር፡፡ ብዙ እያወራን ነው፤ ሳቅና ሁካታ በዝቷል፤ አንዱን እናነሳለን፣ ሌላውን መልሰን እንጥላለን፤ ከድሮ እስከ ዘንድሮ የማናነሳው ጉዳይ አልነበረም፡፡ በመሐል ግን በምን ምክንያት እንደሆነ ባላውቅም ድንገት ቅር አለኝ፡፡ የቅሬታዬን መነሻ ለመፈለግ ስዳክር ሳላውቀው ብዙ ነገሮችን በጥልቀት አሰብሁ፤ የረሳኋቸውን ሁሉ አስታወስሁ፡፡ ‘ቅሬታዬ ከምን የመነጨ ነው?’ ስል ራሴን ጠየቅሁኝና  ቅሬታዬ በወዳጆቼ መሐል ሆኜ እያለሁ ብቸኛ እንደሆንኩኝ ማሰቤ እንደሆነ ተረዳሁ፡፡ በእርግጥም ከወዳጆቼ ዘንድ የነበረው አካሌ እንጂ መንፈሴና ስሜቴ አብሯቸው አልነበረም፡፡ ‘ምክንያቱን አውቀው ይሆን?’ ብዬ ስል ብዙ ነገሮች በአእምሮዬ ውስጥ አንድ በአንድ ይከሰቱ ጀመር፡፡
ከልጅነቴ ዓመታት አንስቶ እስከአሁን ጊዜ ድረስ ወዳጆቼ የነበሩትንና አሁንም ወዳጆቼ ናቸው የምላቸውን ሰዎች ሁሉ አሰብኋቸው፡፡ በኀዘኔም ይሁን በደስታዬ ጊዜ የነበረንን የአብሮነት ቆይታ፤ አብረን ያሳለፍናቸውን ገጠመኞች ሁሉ  ተራ በተራ በጥልቀት ተመለከትኋቸው፡፡ ለካስ ብዙ ጓደኞች ነበሩኝ፤ ብዙ ወዳጆችም አግኝቼ ነበር’ አልሁ ለራሴ፡፡ በጣም ልጅ እያለሁ በጣም የምወዳቸው የነበሩት የሰፈር አብሮ አደግ ጓደኞቼን አስታውስሁ፡፡ ጥሩ የልጅነት ፍቅር ነበረን፡፡ ትምህርት ቤት ከመግባታችን በፊት ሰፈር ውስጥ አብረን ነበር የምንውለው፡፡ ትምህርት ከጀመርንም በኋላ አብረን ወደ ምህርት ቤት እንሄዳለን፤ አብረን እንመለሳለን፡፡ ስንጫወት፣ ለደብረ ታቦር ጅራፍ ስንገምድ፤ ለፍልሰታ ሙልሙል ዳቦ ይዘን ስናስቀድስ …....ብቻ ብዙ ነገራችን አንድ ላይ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ሁሉ  ነገር የለም፡፡ ሁላችንም በያለንበት የየራሳችንን ኑሮ በዝምታ ውስጥ እንኖራለን እንጂ እንደ ትናንቱ አብረን ምንሆንበትና የትናንት ትዝታችንን የምናስብበትና የምንዘክርበት ገጠመኝ አልቀረልንም፡፡ በሆነ ገጠመኝ ስንገናኝ እንኳን የትናንት ቀረቤታችንን በማያሳይ የርቀት ሰላምታ እንዲሁ ለወጉ ብቻ ሰላም ተባብለን እናልፋለን፡፡ የሚገርም ነው! ከልጅነት ጓደኞቼና ከአብሮ አደጎቼ  መካከል ዛሬ ድረስ አብሮኝ የዘለቀ አንድ ሰው እንኳን የለም ኖሯል!፡፡
የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁኝ የነበሩት ጓደኞቼስ? አዎ - እነ ይልቃል፣ ዘሪሁን፣ አስቻለዉ . . . ዛሬ የት ይሆን ያሉት? በጣም እንዋድድ ነበር እኮ! ታድያ ለምንድን ነው ዛሬም ድረስ ወዳጅነታችን ሊዘልቅ ያልቻለው? በአንድ ወቅት በጣም የጠበቀ ወዳጅነት ነበረን - ዛሬ ግን የለም፡፡ ትዝ ያሉኝ ራሱ ድንገት ዛሬ ነው እንጂ ከረሳኋቸው ቆይቷል፡፡ ምናልባት እነርሱም ረስተውኝ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ነገር በጥልቀት አሰብኩኝ፡፡ ብዙ ያጣኋቸው ወዳጆች እንዳሉኝ ተሰማኝ፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁኝስ? አቤት! ያንጊዜማ ብዙ ጓደኞች ነበሩኝ፡፡ እንዲያውም ይሄ ጊዜ ሰንበት ትምህርት ቤት መማር የጀመርኩበትም ጌዜ ነበር እኮ፡፡ ሰጠኝ፣በላይነህ፣አበባ፣መሰለ፣ ዕግሰ፣ሰላማዊት . . . አረ በጣም ብዙ ናቸው፡፡ ግን የት ይሆን ያሉት? ተገናኝተን አናውቅም እኮ፡፡ በአንድ ወቅት ግን በጣም እንቀራረብ ነበር፤ የሕይወታችንን ክፉና በጎ ገጠመኞች አብረን ተጋርተናል፤ በአንዱ ደስታ ደስ ብሎን በሌላው ሀዘን ደግሞ ተከፍተናል፡፡ ዛሬ ግን ይህ ሁሉ የለም፡፡ ትዝውን ብቻ አስቀርቶልን አልፏል፡፡ ሁላችንም በያለንበት አዲስ ወዳጅና አዲስ ጓደኛ አበጅተናል፡፡ ትናንትን የምንዘክርበት ምንም ቋሚ ነገር አልተውንም፡፡
ከሁሉም ይልቅ ደግሞ የሰንበት ምህርት ቤት ጓደኞቼ በጣም ብዙ ነበሩ፡፡ አሁን ድረስ የማልረሳው ብዙ በጎ ትዝታ አለኝ፡፡ በአገልግሎት ውስጥ የነበረን ቅንነት፤ እርስ በርሳችን የነበረን ሀዘኔታ፤ ስንለያይ የነበረን ናፍቆት፤ አንዱ ለሌላው የነበረው በጎነት . . . ብቻ ብዙ የማይረሱ ገጠመኞች አሉኝ፡፡ እነ
ፀሀይቤዛዊትእቴነሽአበሩግርማተመስገንመድሃኔአሸናፊሳምሶንክብረትሞገስመልካሙፍቅሩተስፉ
. . . አረ በጣም ብዙ ነበሩ፡፡ እኒያ የጌታ ባሪያዎች፣ በጎውን ለማድረግ ይተጉ የነበሩት፤ ስለ ክርስቶስ ፍቅር የሚቃጠሉት፤ ስለ አገልግሎቱ የሚቀኑት የዋኀን ወንድሞቼና እህቶቼ ዛሬ ላይ አንዴት ሆነው ይሆን? ምን ላይስ ደርሰው ይሆን? . . . አቤት! ጊዜው ግን አንዴት ነው የሚሮጠው! ከእነዚህ ሁሉ ጋር የነበረን መልካም ወዳጅነት ዛሬ በጊዜና በቦታ ተገድቦ ከትዝታው በቀር የተረፈልኝ ምንም እንደሌለ ሳስብ ግን በጣም ይቆጨኛል፡፡

በኮሌጅ ቆይታዬ፤ በግቢ ጉባኤ ተሳትፎዬ፤ ከግቢ ከውጣሁኝ በኋላም በሥራ ዓለም ያገኘኋቸውና የተዋወቅኋቸው፤ ብዙ በጎ ነገሮችን የተጋራኋቸው ወዳጆቼ . . .  አንድ በአንድ በኅሊናዬ ውስጥ እየተከሰቱልኝ አየኋቸው፡፡ የተረሳሳነውን፤ ያለበቂ ምክንያት የተራራቅነውን፤ በቀላል ነገር የተቀያየምነውን፤ ከተቀያየምንም በኋላ የተፈላለግነውንና የታረቅነውን፤ አሁን ድረስ የምንጠያየቀውን . . . ብቻ ምን አለፋችሁ ሁሉንም ተራ በተራ አሰብኩት . . . አንዱን ከሌላኛው እያስከትልኩ አውጠነጠንኩት፡፡ ስለ ጓደኝነት የነበረኝን ስሜት፤ መረዳቴን፤ አቋሜንና፤ ፍልስፍናዬን በጥልቀት አሰብኩት፡፡ ጓደኛ ስለማበጀት፤ ወዳጅ ስለማፍራት የከፈልኩትን ዋጋ፤ የደክምኩትንም ድካም ሁሉ አሰላሰልኩት፤ ጓደኞቼንና ወዳጆቼን ለእኔም የነበራቸውን ምላሽ ዞሬ አየሁ፡፡ በዚህ ሁሉ መሐል ታዲያ ወደኋላ የሚጎትተኝ አንድ ስሜት እንዳለ ተሰማኝ፡፡ አዎን በእርግጥ የሆነ ቅሬታ በውስጤ አለ፡፡ ግን ምን ይሆን? በውስጤ ስለቀረው ቅሬታ በጥልቀት ሳስብ ከእነዚህ ሁሉ ወዳጆቼ ሁሉ መሐል ከቁም ነገር ያልቆጠርሁትና ቦታ ያልሰጠሁት ወዳጄ ድንገት ተከሰትልኝ፡፡ የሚገርም ነው! ግን እንዴት ረሳሁት? ከመቼ ጀምሮስ ነበር የምንተዋወቀው?
በጣም ዘግይቼ ያስታወስኩት ይህ ወዳጄ የምንተዋወቀው ከልጅነቴ ጊዜ አንስቶ ነው፡፡ ምናልባትም ስለ አብሮ አደጎቼ ከማስታወሴም በፊት እርሱን ነበር ማስታወስ  የነበረብኝ፡፡ በሚገርም ሁኔታ ዛሬም ድረስ ወዳጅነታችን እንዳለ ነው፡፡ በእርግጥ እኔ እንኳን አብሮነታችን ብዙ ጊዜ እንዲቋረጥ አድርጌ ነበር፡፡ እርሱ ግን ያለሁበት ድረስ ፈልጎኝ ይመጣና ይታረቀኛል፡፡ በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ውስጥ ስንት ጊዜ መሰላችሁ የተነጫነጭኩበት? እርሱ ግን ተከፍቶብኝ አያውቅም፡፡ ከማውቃቸው ወዳጆቼ ሁሉ በፊት መጀመሪያ የማውቀው እርሱን ስለሆነ የልጅነት ወዳጄ ነው፡፡ ዛሬም ድረስ ደግሞ በወዳጅነቱ እንደታመነልኝ ነው፡፡ እኔ ግን ከብዙ ወዳጆቼ መሐል ለእርሱ ያለኝ ቦታ የመጨረሻው ነው፡፡ ይህን ሁሉ ቢያውቅም እርሱ ግን ወዳጅነቱን እንዳጣው አላደረገም፡፡ ስለ እርሱ አለማሰቤ ወረተኛነቴን ያሰታውሰኛል፡፡ ከእርሱ በኋላ ባወቅኋቸው ጓደኞቼ ስንት ጊዜ መሰላችሁ ያስቀናሁት፡፡ ከሌሎች ጋር እያለሁ አንድም ቀን አስታውሼውና ትዝ ብሎኝ አያውቅም ነበር፡፡ ስሜቴን፣ ፈቃዴንና ጊዜዬን ሁሉ አንድም ሳላስቀር ለሌሎች እየሰጠሁ ለእርሱ የምተወው እንጥፍጣፊ ፍቅር፣ አብሮነት፣ ጊዜና ቦታ አልነበረኝም፡፡
አዎን - በጣም የምወዳቸው፤ የምናፍቃቸውና የምሳሳላቸው ብዙ ወዳጆች ነበሩኝ፡፡ ከእነዚህ ሁሉ ውስጥ ግን አንድስ እንኳን የልጅነት ወዳጄን ያህል የሚረዳኝና የሚጠነቀቅልኝ አልነበረም፡፡ እኔም በትዝታዬ ውስጥ የልጅነት ወዳጄን አላኖርኩትም ነበር፡፡ ይባስ ብሎ ከሌሎች ጋር በተጋጨሁና  ውስጤ በተጎዳብኝ ሰዓት ጉዳቴንና ኀዘኔን ይዤ የምሄደው ወደ እርሱ ነበር፤ ግን ምንም አይለኝም፡፡ ብሶቴን ሰምቶ፤ ጉዳቴን ተመልክቶ፤ ስሜቴን ተረድቶ ደስ ያሰኝና ይመልሰኛል፡፡ ከእርሱ ይልቅ ሌሎችን እንደምወድ እያወቀ እርሱ ግን አብልጦ ይወደኛል፤ በተውኩትና በረሳሁት ጊዜ ሁሉ ያስበኛል፤ ይጠነቀቅልኛልም፡፡
የሚወዱትን ሲያጡ፤ የሚናፍቁት ሲርቅ ልብ እንዴት ይጎዳ መሰላችሁ! በወዳጆቼና በቅርቤ ሰዎች ብዙ ተጎድቻለሁ፤ የሌሎችን ጓደኝነት አተርፍ ዘንድ ለዓመታት ደክሜ ብዙ ዋጋ ከፍያለሁ፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ለእኔ የቀረልኝና ያተረፍኩት የልብ ኀዘን ብቻ ነው፡፡ የብዙ ዓመታት ትርፌ ምንም ነው! ይህን ሳስብ በጣም እቆጫለሁ፡፡ ጊዜዬ፣ ስሜቴ፣ ልፋቴ፣ ድካሜ፣ ሌሎችን ለማትረፍ ያደረኩት ጥረቴ . . . ብዙ ነገሮችን እንዳጣሁና እንደከሰርኩ ይሰማኛል፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን የቀረልኝ አንድ ጥቅም፤  አለኝ የምለው ብቸኛ ትርፍ፤ የልጅነት ወዳጄ ብቻ መሆኑን ሳስብ ደግሞ ይበልጥ የቆጨኛል፡፡ ለሌሎች ከከፈልሁት ዋጋ፤ ከደከምሁት ድካም፤ ከሰጠሁት ቦታ . . . ከእነዚህ ሁሉ ነገሮች ወስጥ ለእርሱ ያደረግሁት አንዳች ነገር አለመኖሩ ይጸጽተኛል፡፡ ከደስታዬ ጊዜ ይልቅ በሀዘኔ፤ ከማግኘቴም ወራት ይልቅ በማጣቴ፤ ከአብሮነቴም ይልቅ በብቸኝነቴ ጊዜ ብቻ ለምን ትዝ እንደሚለኝና እንደማስታውሰው ሳስብ በራሴ አፍራለሁ፡፡ ይህን ሁሉ እያወቀ ሳይተወኝ መቅረቱ ደግሞ እንደ እግር እሳት ያቃጥለኛል፡፡ ምን ያህል እንዳስጠበቅሁት፣ ለዓመታት ቸል እንዳልሁት፣ አንዳስመረርሁትም ሳስብ ሰውነቴን እጠላዋለሁ፣ አለማስተዋሌንም እረግማለሁ፡፡
የተጣላኋቸውን ጓደኞቼን ሳስታውሳቸው፤ የተጣላንበትንና  እስከ መጨረሻ እርግፍ  አድረጌ ወዳጅነታቸውን የተውሁበትን ምክንያት ሳስብ ወረተኛነቴን የታገሰው ወዳጄ በትዝብት ሲያየኝ እመለከተዋልሁ፡፡ በምክንያት ከሆነማ እኔን ለመተው፤ ከእኔም ጋር ለመጠላት ብዙ አሳማኝ ምክንያቶች እያለው የወደደኝና ከነብዙ ድካሜና ጉድለቴ የተቀበለኝ የልጅነቴ ወዳጅ ገና ከበፊቱ ይተወኝ እንደነበር አስባለሁ፡፡ እርሱ ግን ፍቅር ከምክንያት በላይ መሆኑን አስተማረኝ፤ የወዳጅነት ልኩን፣ የበጎነትንም ጥጉን አሳየኝ፡፡ ከልጅነት እስከ እውቀት እኔ ሌሎችን የምተውበትንና የምጠላበንት ምክንያት ስፈልግ የኖርኩትን ያህል እርሱ ግን ደግሞ እኔን የሚያውቀኝ እንዴት አድረጎ እንደሆነ ሳስብ ሐፍረት ይሰማኛል፡፡ በእርግጥ እኔን ከሚያውቅበት ከልጅነቴ ወራት አንስቶ አንድም ቀን በበጎነት አያውቀኝም፡፡ ከእርሱ ጋር የነበረኝ አብሮነት ሁሉ በቅሬታ፤ በማስቀናት፤ ሌሎችን በመክሰስና በመንቀፍ፤ ብሶትን በማውራት . . . የተደረገ ነበር፡፡ በእነዚህ ሁሉ የአብሮነታችን ዓመታት ወስጥ ለእርሱ ብዬ ያደረግሁት የማስታውሰው አንድም በጎነት የለም፡፡ ይህም ሁሉ ሆኖ ግን እኔ እርሱን የማውቀውና የማስታውሰው በበጎነት ብቻ ነው፡፡ ስሜቴን ሲረዳኝ፤ ጥፋቴን ይቅር ሲለኝ፤ ስህተቴን ሲያርመኝ፣ በገዛ ጥፋቴ ተቆጥቼ ሳኮርፈው እርሱ ግን ሲለማመጠኝ፣ በተውኩት ጊዜ ሁሉ መመለሴን መጠበቁንና መናፈቁን፤ ክፉ አመሌን መቻሉን፤ ድካሜን መታገሱንና መራራቱን . . .  ይህን ብቻ ነው የማስታውሰው፤ እኔ እርሱን እንዲህ ነው የማውቀው፡፡
ከዚያን ጊዜ አንስቶ፤ ይህን ያህል ዓመታት የታመነልኝን ወዳጄን የሚገባውን ቦታና ክብር ሳልሰጠው ኖሬያለሁ፡፡ ለሌሎች ካደረግሁት ከብዙው መልካምነት መሐል ጥቂትስ እንኳን በጎነት ነፍጌዋለሁ፤ ከሁሉ ላስቀድመውና ላስበልጠው ሲገባኝ ለዓመታት ረስቼዋለሁ፡፡ ለዚህም ነው ከሌሎች ጋር የነበረኝ አብሮነት የምጠብቀውንና የምጓጓለትን ያህል ያልሆነው፡፡ ዛሬ ግን ከማንም ይልቅ አስበዋለሁ፤ እወደዋለሁ፤ በጣምም እሳሳለታለሁ፡፡ የሚገባኝን ሳይሆን የማይገባኝን ሊያደርግልኝ መሻቱ፤ ለቅጣት የተገባሁኝ ሆኜ ሳለሁ ይቅር ሊለኝ መፍቀዱ፤ ለብዙ ዓመታት እኔን በትግስት መጠበቁ፤ መቻሉ፤ ሊነቅፈኝና ሊወቅሰኝ አለመፍቀዱ፣ ትናንት እንደሚወደኝ ሁሉ ዛሬም በእውነተኛ ፍቅድ ሊወደኝ አለመድከሙ፣ እርሱን በተውኩባቸው ዓመታት ሁሉ ስለ እኔ ማሰቡን አለመተዉ፣ ከብዙ ጥፋቴ ይልቅ ለእኔ ያለውን ፍቅር ብቻ ማሰቡ፤ እውነተኛነቱ፣ ቅንነትና በጎነቱ . . . ከቅጣት ሁሉ የሚበልጥ ቅጣት ሆኖብኝ ውስጤን ጸጸት ሞልቶታል፡፡ ስለክፋቴ የተቀበልኩት በጎነቱ ይበልጥ እንድናፍቀው አድርጎኛል፡፡ መቀጣት ሲኖርብኝ ምህረቱን መቀበሌ ከቅጣት ሁሉ በልጦብኛል፡፡ ፍቅሩ ነው የቀጣኝ እኔን፣ ፍቅሩ . . . ብዙ ፍቅሩ፣ የበረታው መውደዱ . . .  ቃላት የማይገልጹት በጎነቱ፣ ኀዘኔታውና ርኅራሄው  . . . በድካሜ ወስጥ የሆነው መቀበሉና መራራቱ . . . አዎን ይህ ነው የእኔ ቅጣት፣ ይህ ነው በየዕለቱ የምታመመው የዘለዓለም ህመሜ!
ዘመናችሁን ሙሉ ስለምታውቋቸው ሰዎች ስታስቡ የሚሰማችሁ ስሜትና የሚታሰባችሁ ሐሳብ ምን ይሆን? ሌሎችን መታገሳችሁ፤ ሌሎች እናንተን መበደላቸው፤ እናንተ ሌሎችን መጠበቃችሁ፤ ሌሎች ለይቅርታ መስነፋቸው፤ እናንተ ስለጓደኝነት የሰራችሁትና የከፈላችሁት ዋጋ፤ የደከማችሁትም ድካም፤ የሌሎች የቸልተኝነት አጸፋ . . .  ይታሰባችሁና ትዝ ይላችሁ ይሆናል፡፡ እኔም በወዳጆቼ መሐል ቁጭ ብዬ ብቸኝነት በተሰማኝ ሰዓት በመጀመሪያ ያሰብኩትና ትዝ ያለኝ ይሄው ነበር፡፡ የተውኩትን፤ በሌሎች የለወጥሁትንና ያስቀናሁትን፤ ትኩረትና ቦታ የነፈግሁትን ከልጅነቴ ወራት አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ አብሮነቱን ያልነፈገኝን የልጅነት ወዳጄን ባስታወስኩት ቅጽበት ግን የይቅርታው፣ የትዕግስቱና መመለሴን የመጠበቁ ውጤት መሆኔን ተረድቻለሁ፡፡ የማይገባኝን የተቀበልሁ፤ ከበጎነቱ የምመጸወት ደኃ መሆኔን አምኛለሁ፡፡
ለወዳጆቻችሁ ዋጋ እንደከፈላችሁ፤ ለከፈላችሁትዋጋ ተቃራኒውን እንደተቀበላችሁ፤ በሌሎች እንደተተዋችሁና እንደተረሳችሁ፤ እንደተበደላችሁና ቸል እንደተባላችሁ . . . ታስባላችሁ ይሆን? እኔ እንደዚያ ነበር ሳስብ የነበረው፡፡ ለዚህም ነበር ወዳጆቼ በምላቸው ሰዎች መሐል ሆኜ ብቸኝነት የተሰማኝ፡፡ እውነታው ግን ከዚህ ይለያል፡፡ በብዙ ድካሜና ስንፍናዬ ውስጥ፤ ባለማስተዋሌና በሞኝነቴ ውስጥ፤ በወረተኛነቴና በግዴለሽነቴ ውስጥ . . . የታመነልኝንና የወደደኝን፤ የጠበቀኝንና የታገሰኝን፤ ያልነቀፈኝንና ያልተወኘን . . . የልጅነቴን ወዳጅ እንዳገኘሁት ሁሉ ምናልባት እናንተም  በጥልቀት መረዳት ውሰጥ ሆናችሁ ብትፈልጉት ታገኙታላችሁና የልጅነት ወዳጃችሁን ፈልጉት፡፡ ዛሬ በእኔ ዘንድ ስለ ጓደኝነት ቅሬታ የለም፤ ቅያሜና ፈራጅነትም የለም፤ ሌሎችን መንቀፍና ስህተትን የሚፈልግ  ዐይንም የለም፡፡ ከዚህ ይልቅ ግን እግዚአብሔርን የሚሻ፤ እርሱንም የሚናፍቅ፤ ስለ እርሱም ሲል ሌሎችን  የሚታገስና ይቅር የሚል ልብ፤ የሌሎችንም በደል የማይመለከት ዐይን፤ በሌሎችም የማይፈርድ ኅሊና ከእኔ ዘንድ ቀርቷል፡፡ ለምን ብትሉኝ ከልጅነቴ አንስቶ እስከዛሬ ድረስ በበጎነት ብቻ የማውቀው እውነተኛው ወዳጄ፤ የልጅነቴ ወዳጅ ያልኩት፣ እስከ ሞት ድረስ ደርሶ የፈለገኝና መድኃኒት የሆነልኝ ኢሱስ ክርስቶስ፤ እርሱም የበጎነቴና የመልካምነቴ ሁሉ አባት ታላቁ እግዚአብሔር ሆኖ ካገኘሁኝ በኋላ ከሐሳቤ ስለነቃሁ!! ዛሬ ለእርሱ ነው የምኖረው! ለእርሱ ብቻ፡፡ ዛሬ እርሱን ነው የምናፍቀው! እርሱን ብቻ! ዛሬ እርሱን ብቻ ነው የምፈልገው! እርሱን ብቻ! እርሱ ከሐሳቤ በላይ ነው፣ ከመረዳቴና ከቃሎቼ የመግለጽ ችሎታ ሁሉ በላይ፡፡ እርሱን ብቻ ሳስብ ውዬ አድራለሁ፡፡ ከእርሱ የተነሳ ለመኖር እጓጓለሁ፣ ስለፍቅሩ ስል ብቻ ነገን ላይ እናፍቃለሁ፡፡ ስላልጠገብሁት፣ በየቀኑም ስለምናፍቀው በጣም እጓጓለሁ፣ ዝም ብዬ እጓጓለሁ . . . አምላኬን ዝም ብዬ እናፍቀዋለሁ!!! ዝም ብዬ . . .