Friday, May 13, 2016

መዳንና በጎ ምግባራት በመጀመሪያይቱ የቅዱስ ዮሐንስ መልዕክት




ምዕራፍ አንድ
ቁ. 1 ‘‘እግዚአብሔር ብርሃን ነው፣ ጨለማም በእርሱ ዘንድ ጥቂትስ እንኳ የለም’’
እግዚአብሔር ብርሃን ነውና ሁሉ በፊቱ የተገለጠና የተራቆተ ነው፤ የሚሰወረው አንዳችም ነገር የለም፡፡  እግዚአብሔር ብርሃን ነውና ጨለማ የተባለ ጥመትና ክፋት በእርሱ ዘንድ የሉም፡፡ እርሱ በጎ፣ ቅንና እውነተኛም ነው፡፡እርሱ ብርሃን ከሆነ ደግሞ እኛም በብርሃን/በቅድስና ሕይወት ልንመላለስ ያስፈልገናል፡፡
ቁ. 2፡፡ ‘‘እርሱ ብርሃን እንደሆነ በብርሃን ብንመላለስ እኛ እርስ በርሳችን አንድነት አለን፤ የኢየሱስ ክርስቶስም ደም ከኃጢአታችን ሁሉ ያነጻናል፡፡’’ ከክርስቶስ ጋር ህብረት እንዲኖረንና እርስ በርሳችንም በህብረቱ ውስጥ በሚሆንልን አንድነት ውስጥ ሱታፌ እንዲኖረን የምንፈልግ ከሆነ በብርሃን ልንመላለስ ያስፈልገናል፡፡ በብርሃን/በቅድስናና በበጎ ምግባራት ስንመላለስ ያን ጊዜ የጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአታችን ሁሉ ያነጻናል፡፡ ስላመንን ብቻ አይደለም በደሙ የምንነጻው፤ እንዳመንን ሁሉ እንዲሁ ደግሞ በብርሃን ልንመላለስ/ በጎ ምግባራትን ልናደርግ ያስፈልገናል፡፡ ብርሃን የተባለ ደግሞ ከኀጢአት የራቀ የተቀደሰ ሕይወታችን ነው፡፡ በጎ ሥራ በጌታችን ትምህርት ብርሃን ተብሎ ተጠርቷል፡- ‘‘መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን ያመሰግኑት ዘንድ እንዲሁ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ፡፡’’ ማቴ 5፣16፡፡ በክርስቶስ ነኝ የሚል እርሱ በብርሃን እንደሆነ በብርሃን ሊመላለስ ያስፈልገዋል፡፡ በብርሃን የማይኖር ከክርስቶስ ጋር ሊሆንና ህብረት ሊያደረግ አይቻለውም ‘‘በእርሱ እኖራለሁ የሚል እርሱ እንደ ተመላለሰ ራሱ ደግሞ ሊመላለስ ይገባዋል።’’  1ኛ ዮሐ 2፣6፡፡ ክርስቶስ ኢየሱስ አዳኛችንና ተቤዢያችን እንደሆነ ሁሉ የምንከተለው መንገዳችንና ፍለጋችንም ደግሞ ነው፡፡ ስለሆነም በዚህ መንገዳችን ላይ እንሔዳለን ፍለጋውንም እንከተላለን፡፡ ክርስቶስ መከራን የተቀበለው እርሱ ዋጋ ከፍሎልኛል ብለን እንድንሰንፍና ከበጎ ምግባራት እንድንርቅ ሳይሆን በኑሯችን ሁሉ እርሱን እንድንመስለውም ጭምር ነው፡፡ በማዳኑ ኃይልና በደሙ ቤዛነት የምናምነውን ያህል እርሱ እንደኖረ እኛም በቅድስና ልንኖርና ልንመስለውም ይገባናል፡፡
ክርስትና የሚያስተምረን በክርስቶስ ማመንን ብቻ ሳይሆን ክርስቶስን መምሰልንም ነው፡፡ ‘‘እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ፡፡’’ 1ኛ ቆሮ 11፣1፡፡ መጠራታችን በክርስቶስ ለማመን ብቻ አይደለም፤ የክርስቶስን ፍለጋ ልንከተልም ጭምር እንጂ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን ክርስቶስ የተወልን የምንከተለው ፍለጋ መኖሩን ነው፡፡ ‘‘የተጠራችኹለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችኹ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሏልና።’’ 1ኛ ጴጥ 2፣21፡፡ ክርስቶስን እንከተላለን የምንል ከሆነ በፍለጋው ውስጥ ልንመላለስ ይገባል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚነግረን ልንወጣ አንችልም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ በክርስቶስ ማመንን ብቻ ሳይሆን ክርስቶስ በምድር ላይ እንደኖረው ያለ የተቀደሰ ኑሮን ስለመኖርም ይነግረናል፡፡ ‘‘እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጧልና።’’ ዕብ 12፣1-2፡፡ ክርስትና እንዲህ ነው! ኀጢትን አስወግዶ የእምነታችን ራስና ፈጻሚ የሆነውን ኢየሱስን መመልከት፣ በክርስትናችን ውስጥ የሚገጥሙንን ጾሮችና መከራዎች መታገስ፣ ክርስቶስ ነውርን ሁሉ እንደናቀ ስለመዳናችንም የመስቀል ሞትን እንደታገሰ እኛም ከዚህ ዓለም የሆነውን ክፉ ምኞትና የኀጢአት ሥራ ሁሉ በመናቅ ከክርስቶስ ጋራ የምንኖረውን ሕይወት መናፈቅ ነው፡፡   
‘‘ዳሩ ግን፦እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ኹኑ ተብሎ ስለተጻፈ የጠራችኹ ቅዱስ እንደ ኾነ እናንተ ደግሞ በኑሯችኹ ዅሉ ቅዱሳን ኹኑ። ለሰው ፊትም ሳያደላ በያንዳንዱ ላይ እንደ ሥራው የሚፈርደውን አባት ብላችኹ ብትጠሩ በእንግድነታችኹ ዘመን በፍርሀት ኑሩ።’’ 1ጴጥ 1፣15-17፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን በክርስቶስ ኢየሱስ የተቀበልነውን ጸጋና በእምነት የሚሆን መዳንን ብቻ አይደለም፡፡ የጠራንን እስክንመስል ድረስ የሚፈለግብንን የቅድስና ሕይወትም ጭምር እንጂ፡፡ እንደ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ ለሚነግረን ሁሉ እንታዘዛለን እንጂ የሚመቸንንና የምንፈልገውን ብቻ መርጠን አንከተልም፡፡ መዳናችን በጸጋው እንደሆነ እናምናለን፡፡ በጸጋውም እንደዳንን እንደምናምነው ሁሉ በጎ ምግባራት ለመዳን እንደሚያስፈልጉም መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናልና ይህንንም እናምናለን፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን በማመናችንና ባለማመናችን ላይ እንደሚፈርደው ሁሉ በበጎ ሥራችንና በክፉው ሥራችንም ላይ እንደሚፈርድ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡
ሰዎች በመዳን ትምህርት ውስጥ በጎ ምግባራትን የሚቃወሙት ለምንድን ነው ብለን ስንጠይቅ ምክንያቱ አምልኳቸው በእግዚአብሔር ፊት ንጹህ ስላልሆነና ራሳቸውንም በዓለም ከሚገኝ እድፍ መጠበቅ ስለማይችሉ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ ‘‘ንጹሕ የኾነ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው፤ ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ፥ በዓለምም ከሚገኝ እድፍ ሰውነቱን መጠበቅ ነው።’’ ያዕ 1፣27፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን እንግዲህ እንዲህ ነው! በእግዚአብሔር ፊት ንጹሕ የኾነ፣ ነውርም የሌለበት አምልኮ ከበጎ ምግባራት ያልራቀ፣ ሰውነትንም ከዓለም እድፍ የሚያርቅና የሚጠብቅ ነው እንጂ ክርስቶስ ስለ ኀጢአቴ ሞቷል እያሉ በጎውን ላለማድረግ የሚሰንፉበትና ሰበብ የሚፈልጉበት አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለጸጋ፣ እምነትና በጎ ምግባራት የሚያስተምረን በእኩል ሁኔታ ነው፡፡ አንደኛው ከአንደኛው እንደሚበልጥና እንደሚሻል አይነግረንም፡፡ ሦስቱም ግን ለመዳን እንደሚያስፈልጉ ይነግረናል፡፡ ስለሆነም ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችን ያለ ልዩነት ስለጸጋ፣ ስለእምነትና ስለበጎ ምግባራት በእኩል ታስተምራለች እንጂ ከዚህኛው ይኼኛው ስለሚሻል ይህንን አብልጣችሁ ያዙ የሚል ትምህርት የላትም፡፡ ‘‘ቃሉ የታመነ ነው። እግዚአብሔርንም የሚያምኑት በመልካም ሥራ በጥንቃቄ እንዲጸኑ፥ እነዚህን አስረግጠህ እንድትናገር እፈቅዳለሁ።’’ ቲቶ 3፣8 እንደተባለ የተጻፈውን በእኩል ተቀብለን እናምናለን እንጂ የገዛ ሐሳባችንን ለማቆም አንሞክርም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን እንዲህ ነው፡- ‘‘ሰው በእምነት ብቻ ሳይኾን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችኹ፡፡’’ ያዕ 2፣24፡፡ ቃሉን ልንሽረው ስለማንችል ቤተ ክርስቲያናችን በእግዚአብሔር ርህራሄ፣ በክርስቶስ መታዘዝ አንዲሁ በነጻ በጸጋው የተደረገልንን መዳናችንን፣ ከጸጋው የተነሳም በጸጋው ላይ በሚኖረን እምነትና መደገፍ፣ ጸጋውን በማመናችንም በመታዘዝ የምንፈጽማቸውን በጎ ምግባራትና የተቀደሰ ሕይወት የመዳን ትምህርቶች ናቸው ብላ ታስለምረናለች እንጂ ጸጋውን፣ ወይም እምነትን አሊያም በጎ ምግባራትን አስበልጣችሁ ያዙ የሚል ትምህርት የላትም፡፡ 
‘‘ብርሃን ወደ ዓለም መጥቷልና፤ ሰውም ሥራው ክፉ ስለሆነ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን መርጧልና፡፡ ሥራው ክፉ የሆነ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፤ ክፉም ስለሆነ ሥራው እንዳይገለጥበት ወደ ብርሃን አይመጣም፡፡ እውነትን የሚሠራ ግን ሥራው ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል፤ ስለ እግዚአብሔር ብሎ ይሠራልና፡፡’’ ዮሐ 3፣19-21፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለሙ ሁሉ ብርሃን ሆኖ በምድር ላይ ተገልጧል፡፡ ሥራቸው በጎ የሆነና በጽድቅ የሚመላለሱ ብርሃን ወደሚሆን አምላካችን ይቀርባሉ፣ ክፉውን የሚያደርጉ ግን በጨለማ ናቸውና ብርሃን ወደሚሆን አምላካችን ሊመጡ አይወዱም፡፡ ጨለማ የተባለ ክፉ ስራቸው ብርሃን በሚሆን በጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲገለጥ አይሹምና፡፡ ያለበጎ ምግባራት የሚሆን በክርስቶስ ኢየሱስ ያለ እምነት ሊኖር አይችልም፡፡ በክርስቶስ የሚያምን ሰው በጎ ምግባራትንም ገንዘብ ያደርጋል፡፡ ‘‘ቃሉን የምታደርጉ ኹኑ እንጂ ራሳችኹን እያሳታችኹ የምትሰሙ ብቻ አትኹኑ፡፡’’ ያዕ 1፣22፡፡ እንግዲህ ቃሉን የምንሰማው ለማመን ነው፤ እምነት ደግሞ ከመስማት ነው ሮሜ 10፣17፡፡ ማመን ደግሞ ለማድረግ ነው፡፡ ቃሉን ሰምቶ የሚያምን ነገር ግን እንደቃሉ የማያደርግና የማይኖር እራሱን ያስታልና፡፡ ‘‘ነገር ግን፥ ነጻ የሚያወጣውን ፍጹሙን ሕግ ተመልክቶ የሚጸናበት፥ ሥራንም የሚሠራ እንጂ ሰምቶ የሚረሳ ያልኾነው፥ በሥራው የተባረከ ይኾናል።’’ መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን እንዲህ ነው፤ ስለ እምነትብቻ አይደለም፣ ስለ በጎ ምግባራትም ብቻ አይደለም፤ ስለ ሁለቱም እንጂ፡፡ ያዕ 1፣25፡፡
በጎ ምግባራት በመዳናችን ወስጥ ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው ከዚህ ምዕራፍ እንማራለን፡፡ የተቀደሰ ሕይወት ያለው ሰው ሥራው በብርሃን የተገለጠ ነውና ብርሃን ወደሚሆን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይደርሳል፤ ክፉ ሥራን የሚያደርጉ ግን በጨለማ ናቸውና ብርሃን ወደሚሆን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መድረስ አይቻላቸውም፡፡

No comments:

Post a Comment