Saturday, April 15, 2017

ትንሣኤን ስናከብር ልናስተውለው የሚገባን አቢይ ጉዳይ . . .


በዓለ ትንሣኤ በክርስትና ሕይወት ውስጥ ታላቅ ክብርና ግምት ከሚሰጣቸው በዓላት መካከል አንዱ ነው፡፡ የጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ በመንግሥተ ሠማያት በእግዚአብሔር ሐሳብ ከተሠራልን እረፍት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ የጌታችን ትንሣኤ ለእረፍታችን መነሻና ጅማሬ ስለሆነ የሚመጣውንና በሠማያት ተስፋ የምናደርገውን እረፍት የምንረዳበትና ለዚህም እረፍት በመንፈስ የምንዘጋጅበት ነው፡፡
በሰማያት ተሠርቶልናል የምንለው እረፍት ያለድካምና ያለመሞት በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ለዘለዓለም በሕይወት መኖራችንን ነው፡፡ አምላካችን አስቀድሞ ወደ ሠራልን እረፍት እንዳንደርስና እንዳንገባ ጠላት ዲያብሎስ ለሔዋን በመከራት ክፉ ምክር ወደ እረፍታችን የምንደርስበት መንገድ በሞት ተቋርጦ ነበር፡፡ ወደ እረፍታችን እንደርስ ዘንድ ደግሞ የሞት መሸነፍና መወገድ ግድ ሆነ፡፡ ሞት ከአዳም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ ሥጋዌ/መገለጥ ድረስ ሰዎችን ሁሉ ሥጋቸውን ወደ መቃብር፣ ነፍሳቸውን ደግሞ ወደ ሲኦል በማውረድ አስቀድሞ በአምላካችን ወደ ታሰበልንና ወደ ተሠራልን የመንግስቱ እረፍት እንዳንገባ እንቅፋት ሆኖ ቆየ፡፡ ሞት እያለ ወደ እረፍታችን መካን ልንደርስ ስለማንችል ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ተገልጦና በሥጋው የእኛን ሞት ሞቶ ብዙዎችን ሲያሸንፍ የነበረውን አሸናፊ በማሸነፍ በታላቅ ኃይልና ሥልጣን ከሞት በክብር ትንሣኤ ተነሳ፡፡ ከጌታችን ትንሣኤ በኋላ በክርስቶስ ትንሣኤ የምናምን ምእመናን የትንሣኤያችን በኩር በሆነው በጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥራና በማዳኑ በኩል ለእረፍታችን ወደ ሠራልን መንግስቱ መግባት ቻልን፡፡ በዚህም የተነሳ ክርስትናችን በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ላይ የተመሠረተ ሆነ፡፡ ሞቱ የኀጢአት ሥርየት አግኝተን ከእግዚአብሔር ጋር የታረቅንበት እንደሆነ ሁሉ፤ ትንሣኤውም ደግሞ እምነታችንና ተስፋችን ፍጹም እውነት መሆኑን የምንመሰክርበትና ወደ ዘለዓለም እረፍታችን የምንደርስበት መንገዳችን ሆኗል፡፡ ክርስቶስ የሙታን ሁሉ በኩር መባሉ ከእርሱ በፊት ሞትን አሸንፎ በገዛ ሥልጣኑ የተነሣ ስለሌለና በእግዚአብሔር ተአምራት የተነሡትም ሁሉ እንደገና ተመልሰው ወደ መቃብር  ስለወረዱ ብቻ ሳይሆን ከክርስቶስ መነሳት በኋላ በክርስቶስ የሚያምኑ ሁሉ የክርስቶስ ትንሣኤ ተካፋዮች ስለሚሆኑና ከእርሱ የተነሳ ከሞት የሚነሱ በመሆናቸውም ጭምር ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን የክርስቶስን ትንሣኤ በዓል የምታከብረው በታላቅ ጥንቃቄና በጥልቅ መንፈሳዊነት ውስጥ ሆና ነው፡፡ በጌታችን መከራና በማዳኑ ኃይል ያገኘነው ትንሳኤያችን በእግዚአብሔር ሐሳብ የተሠራ፣ በመንፈስ የምንረዳውና የምንደርስበት ታላቅ ምንፈሳዊነት ነው፡፡ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ተብሎ እንደተጻፈ በክርስትናችን ውስጥ የምንፈጽመው ማናቸውም ተግባር በእውነትና በመንፈስ የሚፈጸም ሊሆን ያስፈልጋል፡፡ ዮሐ 4፣24፡፡ ህልፈት የማይስማማው የዘለዓለም እረፍታችን መነሻው የክርስቶስ ትንሣኤ እንደመሆኑ መጠን ከሞት በኋላ የምንገባበት ዘለዓለማዊ እረፍታችንን በምድር ላይ በሕይወተ ሥጋ ሳለን እንድንረዳው፣እንድንናፍቀውና እንድንለማመደው፣ ለእርሱም የተገባን ሆነን በመንፈስ እንድንዘጋጅ በሰሙነ ትንሣኤ የምንፈጽማቸው የቤተ ክርስቲያናችን ሥርዐቶች ተሠርተውልናል፡፡ 
ከትንሣኤው በፊት ባሉት ሃምሳ አምስት ቀናት ውስጥ በጾም መቆየታችን በመንፈሳዊ ሐሳብ ውስጥ ሆነን ዘለዓለማዊውን እረፍት እንድናስብ ያደርገናል፤ ከዘወረደ እስከ ሆሣዕና ድረስ ያሉት ስምንቱም ሳምንታት የየራሳቸው ስያሜ ኖሯቸው ለየእንዳንዳቸው የተለየ ንባብና መዝሙር እንዲኖራቸው መደረጉ የጌታችንን ሥጋዌ፣ የፍቅሩን ፍለጋ፣ ሕይወትና መድኃኒት የሚሆን የቃሉን ትምህርት፣ ድንቅ ተአምራቱን . . . በማሰብና በመንፈስ በመረዳት በጾሙ መጨረሻ ላይ ወደምናገኘው የክርስቶስን ህማምና ሞት፣ ስለ ሰዎች ፍቅር የተቀበላቸውን መከራዎች ሁሉ ወደምናስብበት ሰሙነ ህማማት በመንፈሳዊነት እንድንደርስ ነው፡፡ ከሰሙነ ህማማቱ ቀጥሎ የምናገኘው ደግሞ ወደ እረፍታችን የምንደርስበትና የምንገባበት የክርስቶስ ትንሣኤ ይሆናል፡፡ 
የእረፍታችን መጀመሪያ የሆነውን የክርስቶስን ትንሣኤ ስናከብር ሥጋችንንና ነፍሳችንን ለዚህ ሰማያዊ ስጦታና መንፈሳዊ ዓለም ማዘጋጀት ይጠበቅብናል፡፡ የክርስቶስን ትንሣኤ በልዩ መንፈሳዊነት፣ በጠለቀ መረዳትና ተመስጦ ሆነን፤ በሰማያት ካሉ ቅዱሳኑና እነርሱንም ካከበረ ከመድኃኒታችን ህብረት ውስጥ ሆነን ልናከብር ስለሚገባን በምድርም ያለው ሥርዐት መንፈሳዊ ሆኖ ተሠርቶልናል፡፡ በሁሉም የጾሙ ሳምንታት በተለይም ደግሞ በሰሙነ ህማማት ወስጥ የምንደርስበት ከፍ ያለ መንፈሳዊነትና ተመስጦ ነገረ ትንሣኤውን በጥልቀት እንድንረዳውና ከጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መንፈሳዊ ህብረትና አንድነት እንዲኖረን ያግዘናል፡፡ የትንሣኤውን ነገር በመንፈስ ሆነን መረዳት ስንችል ደግሞ በትንሣኤው የሆነልንንና የተሠራልንን እረፍት፣ የተቀበልነውንም ጸጋ እናስባለን፤ በዚህም ውስጥ በምድር ላይ ሆነን ትንሣኤውን እያከበርን ከመንፈሳዊው ዓለምና ከሰማያዊው ህብረት ጋር አንድ መሆንና መተባበር እንችላለን፤ በክርስቶስ ትንሣኤ ያገኘነውን መጻኢ እረፍትና የክብሩንም መንግሥት አጥብቀን እንናፍቃለን፡፡
በጾማችንና በሌሎችም መንፈሳዊ ተግባሮቻችን የተሠሩልን ሥርዐቶች ሁሉ ዋናኛ ዓላማቸው እኛን ወደተሻለው መንፈሳዊ መረዳትና ከፍታ ማድረስ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ስለ ሕግ ሳይሆን ስለመንፈሳዊነትና ከፍ ስላለው የእግዚአብሔር እውቀትና መረዳት ስንል የተሠሩልንን መንፈሳዊ ሥርዐቶች እንፈጽማለን፡፡ በዓለ ትንሣኤ የክርስቶስን ማዳን፣ የፍቅሩንም ፍለጋ የምናስብበት እንደመሆኑ መጠን የክርስቶስን ሐሳብና ፈቃድ የምናገለግልበት፣ እንደቃሉ የምንመላለስበት እንጂ ከመንፈሳዊ ተግባር ርቀን ፈቃዳችንን የምናገለግልበትና ሥጋችንን ደስ የምናሰኝበት አይደለም፡፡ በምድር ላይ የምንኖረው ሕይወት የክርስቶስ እንደሆነ ስለምናምን ትንሣኤን ስናከብር ክርስቶስን በማሰብና እርሱንም በመፈለግ ደስ እንሰኛለን እንጂ በመብልና በመጠጥ እራሳችንን ደስ አናሰኝም፡፡
ከክርስቶስ ጋራ ተሰቅያለኹ፤ እኔም አኹን ሕያው ኾኜ አልኖርም፥ ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አኹንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ እራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው።ገላ 2፣20፡፡ ክርስትናችን ከክርስቶስ ጋር የተሰቀልንበት ነውና ክርስቶስን ደስ ከማሰኘት ዳግመኛ ሥጋን ደስ ወደ ማሰኘት ፈቀቅ አንልም፡፡ ይህ ሕይወታችን እኛ ሕያዋን ሆነን የምንኖርበት ሳይሆን ክርስቶስ በእኛ የሚኖርበት ነውና በዓለ ትንሣኤውን ክርስቶስ ደስ በሚሰኝባቸው ተግባራት እንጠመድበታለን እንጂ ከመንፈሳዊነት በራቀና ሥጋዊነት በተጫነው ሁኔታ አናከብረውም፡፡ የክርስቶስን ሥጋና ደም የምንቀበልበት እንጂ በዶሮና በበግ ሥጋ የምናሳልፈው ትንሣኤ የክርስቶስ ሊሆን አይችልም፡፡
እኛ ደግሞ ሸክምን ዅሉ ቶሎም የሚከበንን ኀጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስለ አለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጧልና። ዕብ 12፣1-2፡፡ ተብሎ እንደተጻፈ ጌታችንና መደኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለእረፍታችን መድከሙንና መከራን መታገሱን እያሰብን እኛም እንደ እርሱ ሁሉ በፊታችን ያለውን ነውር ሁሉ በመናቅና ሥጋችንን ደስ ከማሰኘት በመጠበቅ ከሁሉ የሚበልጠውን የትንሣኤውን ደስታና ብርሃን እንጠብቃለን እንጂ በመብልና በመጠጥ፣ በዘፈንና በጭፈራ እራሳችንን አናረክስም፡፡ ክርስቶስ መከራን የተቀበለው፣ የሞተው፣ ትንሣኤውንም የሰጠን ለመንፈሳዊ ሐሳብና አላማ እንጂ ለሥጋዊነትና ለዓለማዊነት አይደለም፡፡ ስለሆነም የጌታችንን ትንሣኤ የምናከብረው በመንፈሳዊነት እንጂ በዓለማዊነት አይደለም፣ በነፍስ ደስታ እንጂ በሥጋዊነት አይደለም፣ በዝማሬና ክርስቶስን በማመስገን እንጂ በዘፈንና በጭፈራ አይደለም፣ እራስን በመግዛት እንጂ ብዙ በመብላትና በመጠጣትም አይደለም፡፡
እንደ እግዚአብሔር ሐሳብና ፈቃድ በመንፈሳዊነት የሚደረግ በዓለ ትንሣኤና በዓለ ሃምሳ ይሁንልን!

ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ!

ትምህርተ ንስሓ (ክፍል ሁለት)


እለውስተ ንስሓ ሀለውክሙ አትኅቱ ርዕስክሙ/ በንስሓ ውስጥ ያላችሁ ራሳችሁን ዝቅ አድርጉሥርዐተ ቅዳሴ

በሥርዐተ ቅዳሴያችን ከእግዚኦታ በኋላ ዲያቆኑ እለውስተ ንስሓ ሀለውክሙ አትኅቱ ርዕስክሙ/ በንስሓ ውስጥ ያላችሁ ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ ብሎ ሲያውጅ ካህኑ ደግሞ አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ በንስሐ ወስጥ ወዳሉት ወገኖች ተመልከት፣ እንደ ይቅርታህም ብዛት ይቅር በላቸው፣ እንደቸርነትህም ብዛት በደላቸውን አጥፋላቸው፤ ከክፉ ነገርም ሁሉ ጠብቃቸው፤ ሰውራቸውም፡፡ የቀደመ ሥራቸውን ይቅር ብለህ በሰላም ነፍሳቸውን አድን፤ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያንህ አንድ አድርጋቸው፡፡ ተቀዳሚ ተከታይ በሌለው በአንድ ልጅህ በጌታችንና በአምላካችን በመድኃኒታችንም በኢየሱስ ክርስቶስ በይቅርታውና በምህረቱ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያንህ ጨምራቸው፡፡ብሎ ይጸልይላቸዋል፡፡ ንስሓ ራሳችንን ዝቅ አድርገን የአምላካችንን ምህረትና ይቅርታ የምንጠይቅበት መንፈሳዊ መንገድ ነው፡፡ የንስሓ ሰው ይገባኛል ብሎ የሚጓደድ ሳይሆን ባይገባኝም ከምህረትህና ከበጎነትህ የምመጸወት ድሃ ነኝ በማለት በአትኅቶ ርዕስ/ራስን ዝቅ በማድረግ የሚቀርብ ነው፡፡  

በንስሓ ወቅት መሬት ላይ መተኛት፣ የምንመገበውን የምግብ መጠን መቀነስ፣ ከዓለማዊ ነገሮችና ለመንፈሳዊ ሕይወት ከማይመቹ ጓደኞች/ግንኙነቶች መራቅ ያስፈልጋል ። በንስሓ ጊዜ እንዳናደርግ ከታዘዝነው ነገር ራሳችንን በመግዛት መቆጠብ አለብን፤ እግዚአብሔር በቸርነቱ ወደ ድኅነት ከጠራን በኋላ እንደገና ተመልሰን ወደተውነው ድካማችን መመለስ የለብንም ። የጊዜውን ሳይሆን የመጨረሻውን ማሰብ አለብን ። 2 ጢሞ 4 ፥ 10 ። መዝ 6፥ 6። እንግዲህ ተነሳሒው በእውነት ኀጢአቱን አውቆ በካህኑ ፊት በስውር ለሚያየውና ለሚሰማው ለእግዚአብሔር ከተናዘዘ በኋላ ከካህኑ ሁለት ነገሮችን ይቀበላል። እነርሱም ቀኖናና ፍትሐት ናቸው። ምንም እንኳን ተነሳሒው በመጸጸቱና ከቀደመ ክፋቱ በመመለሱ ከዘለዓለም የሞት ቅጣት ቢድንም ዓይነቱና መጠኑ የተለያየ ጊዜያዊ ቅጣት መቀበል ይገባዋል። ይህም የንስሓ ቀኖና ይባላል። ጊዜያዊ ቅጣት ወይም ቀኖና ያስፈለገበት ምክንያት ኀጢአትን መሥራት ምን ያህል ክፉ እንደሆነ ለተነሳሒው ለማሳሰብና ዳግመኛ እንዳይበድል ለማስጠንቀቅ እንዲሁም ደግሞ ሥጋን በመገሰጽ ለነፍሱ የጽድቅንና የደኅንነትን ጎዳና ለማስተማር ነው። ምንጊዜም ፍቅሩና ምሕረቱ ከእኛ ጋር ቢሆንም እግዚአብሔር በአባትነቱ ላጠፋነው ጥፋት በጊዜያዊ ቅጣት ይቀጣናል። መልካም አባት ልጁን እንደሚገስጽና እንደሚቀጣ ዓይነት ይቀጣናል። ዕብ 12፥5-11። እንግዲህ ያልተገራ ልቦና ካለን ለእግዚአብሔር በማስገዛት የኀጢአታችንንም ቅጣት በደስታ በመቀበል የበለጠ ጸጋና ረድኤትን እናገኛለን። በዚያን ጊዜ ያልተገረዘው ልባቸው ቢዋረድ፣ የኀጢአታቸውንም ቅጣት ቢቀበሉ እኔ ለያዕቆብ የማልኩትን ቃልኪዳኔን አስባለሁ … ምድሪቱንም አስባለሁ። ተብሎ ተጽፏልና ዘሌ 26፥41-42። በካህኑ የታዘዘልንን ቀኖና መፈጸማችን ኀጢአትን ሁሉ ይቅር በሚልና በሚያስተሠርይ አምላክ ማመናችንን የምናረጋግጥበት ነው፡፡ በእምነታችን ውስጥ በሚሆነው መታዘዛችን ምህረቱ ብዙ ከሚሆን አምላካችን የበደል ሥርየትንና ይቅርታን እንቀበላለን፡፡

ከቀኖና ቀጥለን የምናገኘው ሌላኛው ሥርዐተ ንስሓ ፍትሐት ነው፡፡ ፍትሐት የምንለው ከኀጢአት እስራት ተፈትተን ለበደላችን የቅርታን፣ ለኀጢአታችን ደግሞ ሥርየትን አግኝተን ንጹሐን የምንሆንበትን የንስሓ ሂደት ነው። ቀኖና የምንለው ተነሳሒው ለኀጢአቱ ምክርና ተግሳጽ የሚያገኝበትን፣ በንስሐ ቅጣት የሚቀበልበትን፣ ካሳ መቀጫ የሚከፍልበትን ሥርዐተ ንስሓ ሲሆን ፍትሐት የምንለው ደግሞ ካህኑ የንስሓውን ጸሎት ከፈጸመ በኋላ በተሰጠው የክህነት ሥልጣን እግዚአብሔር ይፍታህባለው ጊዜ ተነሳሒው የኀጢአት ሥርየትንና የበደል ይቅርታን የሚያገኝበትን ሥርዐት ነው፡፡ ንስሓ የገባው ሰው ከኀጢአቱ ተፈትቶ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቁ ታላቅ ጸጋ ነው። ለኀጢአታችን ሥርየት እንደዚህ ዓይነቱን ቀላል መንገድ ስላዘጋጀልን ክርስቶስን ማመስገን ይገባናል። ብዙ ሳንደክም ወንድማችንና አባታችን ለሆነው ካህን በመናዘዝና ምክሩንና ቀኖናውን በመቀበል በኀጢአት ከሚመጣብን የዘለዓለም ቅጣት መዳናችን እጅግ ደስ የሚያሰኝ ነው። ይህንንም ሥልጣን ለካህናት የሰጣቸው እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ እናነባለን፡፡ ማቴ 16፣19 ማቴ 18፣18፡፡ እንግዲህ ፍትሐት የተቀበለ ተነሳሒ ሁሉ ኀጢአቱ የተሰረየለትና በደሉም የተደመሰሰለት ስለሆነ ከዘለዓለም የሞት ቅጣትና ከበደል ቅጣት ሁሉ ነጻ ይሆናል።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በዝሙት የተከሰሰውን የቆሮንቶሱን ሰው በሥጋው እንዲቀጣ ፈርዶበታል። እንደዚህ በሠራው ላይ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሁን ፈርጄበታለሁ . . . መንፈሱ በጌታ በኢየሱስ ቀን ትድን ዘንድ እንደዚህ ያለው ሰው ለሥጋው ጥፋት ለሰይጣን እንዲሰጥ ፍርዴ ነው። 1ኛ ቆሮ 5፥1-5። ይኸው ሐዋርያ ለሁለተኛ ጊዜ በጻፈው መልዕክቱ ከላይ የተጠቀሰው የቆሮንቶስ ሰው ቅጣቱ የሚበቃው ስለሆነ ማኅበረ ክርስቲያኑ ይቅርታ እንዲያደርጉለት ጠይቋል። እንደዚህ ላለ ሰው ይህ ከእናንተ የምትበዙት የቀጣችሁት ቅጣት ይበቃዋልና እንደዚህ ያለው ከልክ በሚበዛ ኀዘን እንዳይዋጥ ይልቅ ተመልሳችሁ ይቅር ማለትና ማጽናናት ይገባችኋል። ስለዚህ ፍቅርን እንድታጸኑ እለምናችኋለሁ፤ ስለዚህ ደግሞ ጽፌ ነበርና . . . 2ኛ ቆሮ 2፥6-11። እንግዲህ የሐዋርያውን ምክር ሰምተን ዛሬ በሕይወተ ሥጋ የምንገኝ ክርስቲያኖችም በበደላችን ምክንያት ካህኑ የሚሰጠንን ምክርና ተግሳጽ አዳምጠን የንስሐውንም ቅጣት ማለትም ቀኖናውን ተቀብለን በደስታ ብንፈጽመው መንፈሳዊ ደህንነታችን ይጠበቃል። መንፈሳዊ ግዴታችንንም እንወጣለን። በቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና የሚሰጠው እንደተነሳሒው የኀጢአት ዓይነትና እንዳለበት የመንፈሳዊ ሁኔታ ታይቶ ነው። ካህኑ የተነሳሒውን የኑሮ ሁኔታና ያጋጠመውን ፈተና በማስመልከት ምክርና ትምህርት ይሰጠዋል። እንደመልካም የነፍስ ሐኪምም እንደበሽታው ሁኔታ ካህኑ አስፈላጊውን የነፍስ መድኃኒት ይሰጠዋል። የቀኖና አሰጣጥ መንገዱና ዓይነቱ ብዙ ነው። ለአንዳንዱ ተነሳሒ የቃል ምክርና ተግሳጽ ብቻ የሚበቃው አለ። ለሌላው ጾም ብቻ ወይም ከስግደት ጋር ቀኖና ይሰጠዋል። ልዩ የንስሐ ጸሎት፣ ምጽዋት፣ ለተበደለው ወገን ካሳ መክፈል፣ ለችግረኞች አገልግሎት መስጠት አስፈላጊም ከሆነ ለተወሰነ ጊዜ ከቁርባን ሕይወት መለየት ወይም ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ተግባራትን  መፈጸም ወይም ለቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ኑሮ የሚጠቅሙ የጉልበትም ሆነ የአእምሮ ሥራዎችን መሥራትና የመሳሰሉት ሁሉ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ይቆጠራሉ። ንስሓ ማለት መታጠብ፣ ከዕድፍ/ከኀጢአት መንጻት ማለት ሲሆን፤ ድኅነት የሚገኘው ደግሞ በንስሓ ሕይወት ውስጥ በመመላለስ  የዘለዓለም ሕይወት የሚሰጠውን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን በመቀበል ነው። ዮሐ 6 ፥ 33። ብዙ ሰዎች የቅዱስ ቁርባን ሕይወትን እንደ ትርፍ ነገርና በዕድሜ የተገደበ (ለአረጋውያን ወይም ለሕጻናት ብቻ የተተወ) አድርገው ስለሚቆጥሩት የክርስቶስን ሥጋና ደም ለመቀበል ሲዘጋጁ አይታዩም ። ነገር ግን ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በቅዱስ ቁርባን ሕይወት ውስጥ መመላለስ የግድ ያስፈልገዋል። ቀኖና የተቀበልንበት በደላችን የሚሠረይበት ሥርዐተ ንስሓ ፍጹም የሚሆነውና በጀመርነው የንስሓ ሕይወት ውስጥ መቀጠልና ፍሬ ማፍራት የምንችለው የጌታችንን ሥጋውን ስንበላና ደሙንም ስንጠጠጣ ነው፡፡ በመሆኑም በንስሓ ሕይወታችን ውስጥ ስለሚሰጠን ቀኖናና ከቀኖናው በኋላ ስለሚደረግልን የኀጢአት ፍትሐት የምንጠነቀቀውን ያህል ከንስሓ በኋላ ስለሚኖረን የቅዱስ ቁርባን ሕይወትም ልንጠነቀቅና ተገቢውን ትኩረት ልንሰጠው ይገባል፡፡  

ሌላው ልናስተውለው  የሚባን ጉዳይ ደግሞ ንስሓ ከገባንና ከቆርብን በኋላ እንደገና በኀጢአት ልንወድቅ እንችላለን ብለን ከንስሓ ሕይወት መራቅ እንደሌለብን ነው። አምላካችን ለምን ንስሐ አልገባህም እንጂ ለምን ኀጢአት ሠራህ?” አይልምና ሁለተኛ ስንበድል ኀፍረት ሳይሰማንና ከኃጢአት መላቀቅ ካልቻልሁ በየጊዜው የንስሓ አባቴን ከማስቸግር አርፌ ብቀመጥ ይሻለኛል ሳንል በየጊዜው በንስሓ ሕይወታችን እያደግንና እየጠነከርን ለመሄድ ጥረት ማድረግ አለብን፡፡ ከንስሓ በኋላ ሰይጣን በደጊመ ኀጢአት ሊፈትነንና በንስሓ ሕይወታችን እንዳንደሰት በተስፋ መቁረጥ ሊያቆየን ጥረት ማድረጉን አይተውም፤ ሁሉንም እርግፍ አድርገን እንድንተወውና ከንስሓም በኋላ መልሰን ያንንኑ በደላችንን ደግመን ማድረጋችንን እያስታወሰ  ክፉውን ሐሳብ በአእምሯችን ውስጥ በማግባት ሊፈታተነን ይችላል። ነገር ግን ከንስሓ በኋላ እንደ መላእክት በቅድስና ብቻ እንኖራለን ማለት ሳይሆን ጻድቅ ሰባት ጊዜ ይወድቃል፤ ሰባት ጊዜም ይነሳል። ምሳ 24 ፥ 16። እንደተባለ አምላካችን ብንወድቅ ሊያነሳን ፤ ብንጠፋ ሊፈልገን፤ ብንርቅ ሊያቀርበን፤ በኀጢአት ብንረክስ ሊቀድሰን (እንደ ባዘቶ ሊያጠራን) የታመነ አምላክ ስለሆነ ተስፋ ሳንቆርጥ፤ በኃጢአታችን ሳንደበቅ፤ ዘወትር ለንስሓ መዘጋጀት አለብን ። ኢሳ 1 ፥ 18 ።

የንስሓ ጊዜ መቼ ነው?

ሰው በሕይወተ ሥጋ ካለ ክፉውንና በጎውን መለየት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ንስሐ መግባት አለበት። ጠቢቡ ሰሎሞን ቀኑን ሙሉ እግዚአብሔርን በመፍራት ኑርእንዲል (ምሳ 23፥17)፤ የንስሓ ጊዜ ዛሬ፣ ከዛሬም ደግሞ አሁን ነው። ብዙ ሰዎች የንስሓ ጊዜን ከሚያዘገዩባቸው ምክንያቶች ውስጥ ዳግም እበድላለሁ ብሎ ማሰብ ዋናው ነው። ነገር ግን እንኳን ስለነገዋ ስለዛሬዋም የማናውቅ ነንና ዛሬ ልናደርገው የሚገባንን ብቻ በማድረግ የነገውን ለእግዚአብሔር እንተውለት። ያዕ 4፥13-16፡፡ ጌታችንም ደግሞ እንዲህ ሲል ነግሮናል፡- ነገ ለራሱ ይጨነቃልና፥ ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል።ማቴ 6፣34፡፡ ነገ ሌላ ንስሓ የምንገባበት በደል ስለሚኖር ዛሬን በንስሓ ማሳለፍ ተገቢ ነው፡፡ ሌሎች ሰዎች ደግሞ ንስሓ መታሰር ነው ብለው ያስባሉ፡፡ ንስሓ ገባንም አልገባንም ኀጢአትን ማድረግ ለማንም አልተፈቀደም፡፡ ኀጢአትን አድርጎ ያለንስሓ ከመሆን ግን ስለበደሉት ኀጢአት ንስሓ መግባት የተሻለ ነው፡፡ በእርግጥ ንስሓ ለፈቃደ እግዚአብሔርና ለፍቅሩ፣ ለቃሉና ለዘለዓለማዊ ሐሳቡ  ራሳችንን የምንለይበትና የምንሰጥበት ሕይወት ነው፡፡ ሕዝ 20፥ 37፤  ኤፌ 4 ፥1፤ ሮሜ 12፥9-13፡፡ ስለሆነም ስለበደላችን በመጸጸት እግዚአብሔርን ብንሻው ፈልጉ ታገኛላችሁ ያለን አምላክ ወደራሱ ያቀርበናል እንጂ ከፍቅሩና ከበጎነቱ በአፍአ አይተወንም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የራሴ የሆነ ንብረትና ትዳር ሳይኖረኝ፣ ለቁም ነገር ሳልደርስ እንዴት ንስሓ እገባለሁ የሚሉም አሉ። እግዚአብሔር ግን ሀብታችንን ወይም ያለንበትን የኑሮ ደረጃ አይደለም የሚፈልገው፡፡ ለቅዱሳን አባቶቻችን አንዳች ሳይኖራቸው የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ያልነሳቸው አምላካችን በእኛም ሕይወት ውስጥ የተሻለውን ነገር ሊያደርግልን የታመነ ነው፡፡ ስለዚህም አስቀድመን ጽድቁንና መንግሥቱን በመሻት በንስሓ ሕይወታችን ውስጥ ለምንቀበለው የእግዚአብሔር በረከት ልንተጋ ያስፈልገናል፤ የቅዱሳን አምላክ በረከቱ ብዙ ነውና! ዘፍ 18፥1-19፤ ጥበ 10፥10፤ ዘፍ 32፥ 10፡፡
የሰው ልጅ እግዚአብሔር በወሰነለት ዕድሜ የሚንቀሳቀስ ደካማ ፍጡር እንደመሆኑ መጠን አብዛኛው የኑሮው ሁኔታ በዕለትና በሰዓት የተወሰነ ስለሆነ ከንስሓ መራቅና ለነገ ብሎ ማሰብ በእሳት እንደመጫወት ነው፡፡ ቀናትና ሰዐታት የእግዚአብሔር ስጦታዎች መሆናቸውን ተረድቶ እናደርገው ዘንድ የሚጠበቅብንን ነገር በተገቢው ወቅትና ሰዓት ማድረግ በክርስትና ሕይወት ውስጥ እጅግ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ በወንጌል እንደምናነበው የተሰጣቸውን ጊዜ በአግባቡ መጠቀም ያልቻሉትና ጊዜያቸውን በከንቱ ያሳለፉ ሰዎች መጨረሻቸው የማይረባ ጸጸትና ለቅሶ ነው፡፡ ማቴ 25፡፡

ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ!

መጀመሪያይቱ የቅዱስ ዮሐንስ መልዕክት ምዕራፍ አምስት

(መዳንና በጎ ምግባራት በመጀመሪያይቱ የቅዱስ ዮሐንስ መልዕክት)
ቁ. 1-3 ‘‘ኢየሱስ መሲሕ እንደሆነ የሚያምን ሰው ሁሉ ከእግዚአብሔር ተወልዷል፡፡ ወላጁንም የሚወድ ሁሉ ከእርሱ የተወለደውን ደግሞ ይወዳል፡፡ እግዚአብሔርን ብንወደው ትእዛዙንም ብናደርግ የእግዚአብሔርን ልጅ እንደምንወደው በዚህ እናውቃለን፡፡ ትእዛዙን እንጠብቅ ዘንድ የእግዚአብሔር ፍቅሩ ይህቺ ናትና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም፡፡’’ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ የሚያምንና ቤዛነቱን የሚቀበል ሰው ሁሉ ከእግዚአብሔር ተወልዷል፡፡ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚወድ ደግሞ የላከውን አባቱንም ይወዳል፤ ልጁ ከእርሱ ዘንድ ወጥቶ መጥቷልና፡፡ እግዚአብሔርን የምንወደው ደግሞ ተእዛዛቱን በመጠበቅ ነው፤ ትእዛዛቱን የማይጠብቅ ሰው የእግዚአብሔር ፍቅር በእርሱ ዘንድ ሊኖረው አይቻለውምና፤ ትእዛዛቱ ደግሞ የፍቅር ትእዛዛት ናቸውና ከባዶች አይደሉም፡፡ በእግዘዚአብሔር ፍቅር ለመኖር እንደተጠራን ሁሉ በትእዛዛቱም ልንኖር ደግሞ ተጠርተናል፡፡ የምናደርገውን ሁሉ ስለ ፍቅሩ ብለን እናደርጋለን፤ የምንተወውንም ስለ ፍቅሩ ብለን እንተዋለን፡፡
‘‘ለዚህ ተጠርታችኋልና፤ ክርስቶስም እኮ ፍለጋውን ትከተሉ ዘንድ ምሳሌውን ሊተውላችሁ ስለእናንተ መከራን ተቀብሏል፡፡ እርሱ ኀጢአት አልሠራም፤ በአንደበቱም ሐሰት አልተገኘበትም፡፡ ሲሰድቡት አልተሳደበም፤ መከራ ሲያጸኑበትም አልተቀየመም፤ ነገር ግን እውነተኛ ፍርድን ለሚፈርደው አሳልፎ ሰጠ፡፡’’ 1ኛ ጴጥ 2፣21-23፡፡ መጠራታችን በስሙ እንድናምን ብቻ ወይም በሥራችን በማንገልጠው ፍቅር እንድንወደው አይደለም፡፡ በስሙ ማመናችንና በፍቅሩ መኖራችን ከተቀደሰው ሕይወታችንና በጎ ምግባራት ካልተለዩት ኑሯችን የሚለይ አይደለም፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኀጢአትን አንዳላደረገ እኛም ደግሞ ከኀጢአት የምንርቅና የምንጠበቅ፣ በአንደበቱም ሐሰት እንዳልተገኘበት ሁሉ ሐሰትን የምንጸየፍ፣ ሲሰድቡት እንዳልተሳደበ ሁሉ የመሰድቡንንና የሚረግሙንን የምንመርቅ ልንሆን ያስፈልገናል፡፡ ምክንያቱም ከጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተማርነውና የተቀበልነው ክርስትና በስሙ ስለማመን ብቻ ሳይሆን በስሙ መከራን ስለመቀበልና በጎ ምግባራትን ስለማድረግ፤ መንፈሳዊ ተጋድሎን ስለመጋደልም ያስተምረናልና፡፡
ቁ. 18 ‘‘ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ አንደማይበድል እናውቃለን፤ ከእግዚአብሔር የተወለደ ራሱን ይጠብቃል እንጂ ክፉ አያገኘውም፡፡’’ ክርስትና እንዲህ ነው! በክርስቶስ ማመን ብቻ ሳይሆን፣ ስለክርስቶስ ብሎ ራስን ከበደልና ከኀጢአት መጠበቅ፣ ከክፉውና ከእርኩሱ ነገር ሁሉ ራስን ማራቅ፡፡ በበደላችንና በኀጢአታችን ሙታን የነበርነውን እኛን እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ፣ በደሙ ፈሳሽነት ወደ ክብሩ መንግስት አፍልሶናል፡፡ ወደ ክብሩ መንግስት ከፈለስን ደግሞ ራሳችንን ከኀጢአት እያራቅን እስከ ሞት ድረስ የወደደንን መድኃኒታችንን ደስ በሚያሰኝ የተቀደሰ ሕይወት ልንኖር ያስፈልገናል፡፡ ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኀጢአትን አያደርግም!
ማጠቃለያ
ክርስትና አንዱን ተቀብሎ አንደኛውን መተው አይደለም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፉልን ሁሉም ቃላት ከእግዚአብሔር የወጡ እንደሆኑና የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው እንደሆኑም እናምናለን፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጸጋ ብቻ ሳይሆን ስለ እምነትና ስለ በጎ ምግባራትም ተጽፏል፡፡ ሦስቱም ከእግዚአብሔር ወጥተዋልና ሦስቱንም እኩል እናከብራቸዋለን፣ እንቀበላቸዋለን፣ እንታዘዛቸዋለንም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን መዳን በጸጋ፣ በእምነትና በበጎ ምግባራት እንደሆነ ነው፡፡ የምንድነው በሦስቱም ሕብረት እንደሆነ አንጂ ከሦስቱ በአንደኛው እንደሆነ አልተጻፈልንም፡፡ ከሦስቱ አንደኛውንና እኛ የፈለግነውንና የመረጥነውን ብቻ ወስደን መዳን በዚህ ብቻ ነው ማለት አንችልም፡፡ መዳን እኛ እንዳሰብነውና እንደገባን ሳይሆን እግዚአብሔር እንደወራልንና እንደገለጠልን፤ እኛም ደግሞ አንደታዘዝነው መጠን ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን ስለሦስቱም ስለሆነ ሦስቱንም አንቀበላለን፣ በሦስቱም እንጸናለን፡፡
መዳናችንን የፈጸመልንና የምንድንበትን መንገድ የሠራልን ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ በራሳችን መዳን ባለመቻላችንና ከአዳም አንስቶ እስከ ክርስቶስ መገለጥ ድረስ ባሉት አመታት ሞት በዓለሙ ሁሉ በመንገሱ፣ ከሰው ወገን ደግሞ አንድም ሰው እንኳን ወደ መዳን የሚያመጣውንና ወደ እግዚአብሔር የሚያደርሰውን መንገድ መሥራት ባለመቻሉ እርሱ ራሱ እግዚአብሔር በሥጋ ተገልጦና  ስለ እኛ በደል በእኛ ፈንታ ተገብቶ መከራን በመቀበል ከሞትና ከኩነኔ በደሙ ፈሳሽነት ተቤዠን፣ በራሱ ሥራ ለመዳን ዋጀን (እኛ ልንከፍለው ያልቻልነውን የበደላችንን ዕዳ ከፈለልን)፡፡ በዚህ የተነሳ ወደ እግዚአብሔር መንግስት መግባትና ከእርሱም ጋር ህብረት ማድረግ ቻልን፣ ከክርስቶስ ሥራ የተነሳ ለመንግስቱ የተገባን ሆነን ተቆጠርን፡፡ ይህ በራሱ በእግዚአብሔር የተደረገልን የመዳን መንገድ ነው እንግዲህ በመጽሐፍ ቅዱስ ጸጋ ተብሎ የተጠቀሰው፡፡ ይህም ጸጋው እንዲሁ በነጻ የተሰጠንና የተቀበልነው ስለሆነ ከእኛ የሆነ አንዳችም አስተዋጽዖ የለበትም፡፡ ይህ ጸጋው በዓለሙ ሁሉ ያሉትን የሰው ልጆች ሁሉንም ለመዳን የተገቡ አድርጓቸዋል፡፡ ከጸጋው የተነሳ ወደ መዳን የሚያደርሰው መንገድ በጸጋው በኩል ክፍት ተደርጓል፡፡ በዚህ የተከፈተ መንገድ በኩል በእምነትና በምግባር የሚጓዙ ሁሉ ወደ መዳን ይደርሳሉ፡፡ ጸጋው ወደ መዳን የሚያደርስ መንገድ እንጂ በራሱ መዳን አይደለም፡፡ ይህ ባይሆንማ ኖሮ የጸጋው ሥራና ስጦታው ለሰው ልጆች ሁሉ የተደረገ ስለሆነ ከሰው ልጆች መካከል የማይድኑ ሰዎች አይኖሩም ነበር፡፡ ምንም እንኳን ጸጋው ለዓለሙ ሁሉ የተደረገ ቢሆንም የተደረገላቸውን ይህን ነጻ ስጦታ/ጸጋ አምነው በበጎ ምግባራት የሚታዘዙትና ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት የሚቀርቡት ብቻ ይድናሉ፡፡ ጸጋው ቢሰጣቸውም የጸጋውን ስጦታ አምነው በበጎ ምግባራት መታዘዝ ያልቻሉና ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት መቅረብ ያልቻሉት ግን ጸጋው በሕይወታቸው እንዲሠራ ስላልፈቀዱ ከመዳን በአፍአ/ውጪ ይሆናሉ፡፡
ኦርቶዶክሳዊው ትምህርት እንዲህ የሚል ነው፡፡ እኛ እንደምንፈልገው ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተጻፈልን እናምናለን፣ እንቀበላለን፣ እንታዘዛለንም፡፡ መዳን በጸጋው ነውና ጸጋውን እንደገፍበታለን፤ በጸጋውም በኩል ደግሞ በእምነት እናድጋለን፤ ከክፉው እየራቅንና በጎውን ሁሉ እያደረግንና እየታዘዝን ወደ እግዚአብሔር አንደርስበታለን፤ እርሱም እውነተኛው መድኃኒት ነው፡፡ መዳን በእርሱ ብቻ ካልሆነ በቀር በሌላ የለምና፡፡ መጽሐፍም እንደሚል ‘‘መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ ከሰማይ በታች እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰው የተሰጠ ሌላ ስም ከቶ የለምና፡፡’’ ሐዋ 4፣12፡፡ መዳናችን በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ የተሠራልን ነውና የተሠራልንን ይህን መዳን ብቻ እናምናለን እንቀበላለንም እንጂ ከተሠራልን መዳን በቀር ሌላ መዳንን አናምንም፤ አንቀበልምም፤ መጸሐፍ ቅዱስ ከሚነግረንም በቀር ወደ ሌላ ፈቀቅ አንልም፡፡

ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ!

Tuesday, January 31, 2017

መጀመሪያይቱ የቅዱስ ዮሐንስ መልዕክት ምዕራፍ አራት



መጀመሪያይቱ የቅዱስ ዮሐንስ መልዕክት ምዕራፍ አራት
(መዳንና በጎ ምግባራት በመጀመሪያይቱ የቅዱስ ዮሐንስ መልዕክት)
ቁ. 4 ልጆች ሆይ እናንተ ግን ከእግዚአብሔር ናችሁ፣ ክፉውንም አሸንፋችሁታል፡፡ ከእግዚአብሔር የሆኑ ሁሉ ክፉውን ያሸንፋሉ፤ ክፉውን ማሸነፍ የምንከተለው የክርስቶስ ፍለጋ ነውና፡፡ በዓለም ግን መከራን ትቀበላላችሁ፤ ነገር ግን ጽኑ፤ እኔ ዓለሙን ድል ነስቼዋለሁና፡፡ ዮሐ 16፣33፡፡ ተብሎ እንደተጻፈ ጽኑ የተባልንበት ይህ መጽናት እንዴት ያለ ነው? መጠራታችን ክርስቶስ ለኖረው ሕይወት ነው፣ የክርስቶስ ሕይወቱ ደግሞ በዘመነ ሥጋዌው በምድር ላይ የተመላለሰው የተቀደሰ መመላለሱ ነው፡፡ እኔ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርኹኽ ዮሐ 17፣4 ተብሎ እንደተጻፈ የክርስቶስን ፍለጋ እንከተላለን ስንል እርሱ የአባቱን ፈቃድ እንደፈጸመ እኛም እስከሞት የወደደንን የአምላካችንን ፈቃድ እንከተላለን እንፈጽማለንም ማለታችን ነው፡፡ ከእርሱ ፈቃድ የተለየ ፈቃድ ካለን እንዴት የእርሱ ልንሆን እንችላለን? መጠራታችን በስሙ ልናምን ብቻ ሳይሆን በስሙ መከራንም ልንቀበል ነውና ክርስትና በስሙ ማመን ብቻ ሳይሆን በስሙ መጋደልና መከራ መቀበልም ነው፡፡ ፊልጵ 1፣29፡፡ ስለሆነም እውነተኛው የክርስትና አስተምህሮ በክርስቶስ ስም ስለማመን እንደሚያስተምረው ሁሉ ለክርስቶስ መኖርን፣ ለእርሱ ብሎ ማድረግንና መጋደልንም ያስተምራል፡፡
የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን እንከተለው እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሶ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጧልና፡፡ በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ ከኃጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን እስኪ አስቡት፡፡ ገና አልጸናችሁምና፣ ደማችሁን ለማፍሰስ እስክትደርሱ ኀጢአትን ተጋደሏት፣ አሸንፏትም፡፡ ዕብ 12፣2-4፡፡ ክርስቶስ የናቀው ነውር ምንድን ነው? በጎውን ማድረግ የመዳን መንገድ ባይሆን ኖሮ ክርስቶስ በምድር ላይ ለሠላሳ ሦስት ዓመታት መመላለስ ሳያስፈልገው ደሙን ብቻ ሊያፈስልን ይቻለው ነበር፡፡ በእነዚህ ሁሉ አመታት ግን ያሳየንና የተወልን የምንከተለው ፍለጋ አለን፡፡ ክርስትና በክርስቶስ ደም፣ በቤዛነቱ ማመን እንደሆነ ሁሉ የክርስቶስ ፍለጋውን መከተልም ነው፡፡ በክርስቶስ ባለን እምነት ለማደግ የምንተጋውን ያህል እንዲሁ ደግሞ ፍለጋውን ለመከተልና በተግባር የተፈተነውን ክርስትና ለመኖርና ለማድረግም እንተጋለን፤ በክርስቶስ እናምናለን የምንል ከሆነ የእምነታችን ራስና ፈጻሚ የሆነውን እርሱን መከተልና እርሱ እንደተመላለሰም ልንመላለስ ያስፈልገናልና፡፡
እንመላለስበት እግዚአብሔር አስቀድሞ ላዘጋጀው በጎ ሥራ በኢየሱስ ክርስቶስ የፈጠረን ፍጥረቱ ነንና፡፡ ኤፌ 2፣10፡፡እንግዲህ ምን እንላለን? እግዚአብሔር የፈጠረን በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ እንድናምን ብቻ ሳይሆን እንመላለስበት ዘንድ አስቀድሞ ላዘጋጀው በጎ ሥራውም ጭምር ስለሆነ በስሙ እንደምናምን ሁሉ ስለ ስሙ ብለን በጎውን ማድረግና በተቀደሱ ተግባራት መመላለስንም አንተውም፡፡ ይህን ብቻ አድረጉ (እምነትን ብቻ) የሚል የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የለምና! እውነተኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የሚነግረንና የሚያስተምረን በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ፣ እግዚአብሔርንም በማወቅ እያደጋችሁ በሁሉ ደስ ታሰኙት ዘንድ፡፡ በፍጹም ኃይል፣ በክብሩ ጽናት፣ በፍጹም ትዕግስት፣ በተስፋና በደስታም ጸንታችሁ፡፡ ብሎ ነው፡፡ ቆላ 1፣10-11፡፡ በእምነት እንድንጸና፣ በክርስቶስ ላይ ባለን እምነት እንድንደገፍ እንደሚነግረን ሁሉ በበጎ ሥራ፣ በፍጹም ትዕግስትና በተስፋ እንድንጸናም ይነግረናል፡፡ በፍጹም ትዕግስት የተባልነው ክርስትና አንድ ጊዜ አምነን የምንተወው ብቻ ሳይሆን በእምነታችን ውስጥ የምንታዘዘው በድርጊት የሚገለጥ ሕይወትና የምንታገሰው መከራም ጭምር ስለሆነ ነው፡፡
ቁ. 7-8 ወንድሞቻችን ሆይ እርስበርሳችን እንፋቀር፤ ፍቅር እግዚአብሔር ነውና፤ የሚፋቀርም ሁሉ እርሱ ከእግዚአብሔር ተወለደ፤ እግዚአብሔርንም ያውቀዋል፡፡ ወንድሙን የማያፈቅር እግዚአብሔርን አያውቅም፤ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና፡፡ክርስትና እምነት ብቻ ሳይሆን በእምነት ውስጥ የሚሆን በተግባር የሚገለጥ በጎ ምግባርም ነውና በእምነት የእግዚአብሔር ልጆች ሆነን እንደምንወለደው ሁሉ በበጎ ምግባራትና በተቀደሰ ክርስቲያናዊ ኑሯችንም ከእግዚአብሔር እንወለዳለን፡፡   በዮሐንስ ወንጌል ላይ ደግሞ እንዲህ ተጽፏል፡- ለተቀበሉት ሁሉ በስሙ ለሚያምኑ የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑ ሥልጣንን ሰጣቸው፡፡ ዮሐ 1፣12፡፡ በእምነታችን የእግዚአብሔር ልጆች እንደምንሆን ሁሉ በበጎ ምግባራችንም የእግዚአብሔር ልጆች እንሆናለን፡፡ ስለሆነም በክርስትናችን ውስጥ ለበጎ ምግባራት ያለን ቦታ ለእምነት ከሚኖረን ቦታ እንዲያንስ አንፈቅድም፡፡ በእምነት ለማደግ የምንተጋውን ያህል በበጎ ምግባራት ለማደግም እንዲሁ ደግሞ በእጅጉ እንተጋለን፡፡ ከቅዱስ መጽሐፍና ከቅዱሳን አባቶቻችን እንዲህ ተምረናልና! ግን እላችኋለሁ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ የሚረግሟችሁን መርቁ፣ ለሚጠሏችሁ መልካም አድርጉ፤ ስለሚበድሏችሁና ስለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ፡፡ በሰማያት ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ፡፡ ማቴ 5፣44-45፡፡ ይህ ከሆነ የእግዚአብሔር ልጆች የምንሆነው በእምነታችን ብቻ ሳይሆን በበጎ ምግባራችንም ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህም በእምነታችን ብቻ ወይም በበጎ ምግባራችንም ብቻ አንድንም ማለት ነው፡፡ ታዲያ እውነተኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የትኛው ነው?
እውነተኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ስለመዳን የሚነግረን መዳናችንን እግዚአብሔር በራሱ በነጻ እንደሰጠን ይህም ደግሞ ጸጋው እንደሆነ፤ ይህም በነጻ የሆነልንን ጸጋውን ደግሞ ልናምን እንደሚያስፈልገን ነው፡፡ ጸጋው በዓለሙ ሁሉ በሙላት መሆኑና መደረጉ ብቻውን ዓለሙ ይህንን ጸጋ እስካላመነና እስካልተቀበለ ድረስ ሊድን አይቻለውምና ይህንን ጸጋ ማመን ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ጸጋ ከታመንን በኋለ ደግሞ እንዳመንን እንዲሁ ደግሞ ጸጋውን በሥራችን የምንታዘዝ ልንሆን ያስፈልገናል፡፡ ጸጋው በእምነት አድኖናል ብለን በጎውን ከማድረግ ብንሰንፍ ጸጋው ብቻውን ሊያድነን አይችልምና፡፡ ወንድሞቻችን አሁንም በሥጋችን ሳለን በሥጋ ፈቃድ እንኖር ዘንድ አይገባም፡፡ እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞታላችሁ፤ ነገር ግን በመንፈሳዊ  ሥራ የሥጋችሁን ፈቃድ ብትገድሉ ለዘለዓለም በሕይወት ትኖራለችሁ፡፡ በእግዚአብሔር መንፈስ የሚሠሩ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው፡፡ሮሜ 8፣12-14፡፡ እንግዲህ መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን እንዲህ ነው! ስለ ጸጋ፣ ስለ እምነትና ስለ በጎ ምግባራት ይነግረናል፡፡ በጸጋ ስለ መዳን፣ በእምነት ስለ መዳንና በበጎ ምግባራት ስለ መዳንም ይነግረናል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ግን አንደኛውን ብቻ ነጥሎ መዳን በጸጋ ብቻ፣ ወይም በእምነት ብቻ፣ ወይም በበጎ ምግባራት ብቻ ነው ብሎ ግን አይነግረንም፡፡ በዚህም የተነሳ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን መዳን በጸጋው፣ በጸጋው ላይ ባለን እምነትና ከእምነታችን የተነሳ በምናደርጋቸው በጎ ምግባራት እንደሆነ ታስተምራለች፡፡
ቁ 16-17 እኛስ የእግዚአብሔር ፍቅር ከእኛ ጋር እንዳለ አውቀን አምነናል፤ እግዚአብሔር ፍቅር ነው፤ በፍቅር የሚኖርም ከእግዚአብሔር ጋር በፍቅር ይኖራል፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ይኖራል፡፡ በዚህም በፍርድ ቀን በእርሱ ዘንድ መወደድን እናገኝ ዘንድ ከእኛ ጋር ያለችው የእግዚአብሔር ፍቅር ትፈጸማለች፡፡  እግዚአብሔር እርሱ ራሱ አስቀድሞ እንደወደደንና ስለመዳናችን አንድ ልጁን ቤዛ አድርጎ እንደሰጠልን እናምናለን፡፡ በዚህ እምነታችንም ደግሞ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘትና ልጆቹም ለመሆን ስንል ወንድሞቻችንን እንወዳለን፡፡ ክርስቶስ የሁሉ ራስ ነውና፤ እኛም ሁላችን ደግሞ ራስ የሚሆን የክርስቶስ የአካሉ ብልቶች ነንና፡፡ በአካሉ ወስጥ ያለውን አንደኛውን ብልት ወንድማችንን ብንጠላ ራስ ወደሚሆነው ክርስቶስ ልንደርስ አንችልምና ወንድሞቻችንን ሁሉ እንወዳለን፡፡ እናምናለን፤ ባመንነው ደግሞ ጸንተን ላመንነው እንታዘዛለን፤ ባመንነው እንኖራለን እንዳመንን እንዲሁ ደግሞ እናደርጋለን፡፡ ከዚህ የወጣ ሁሉ ከክርስትና የወጣ ነው፡፡ ክርስትና ጸጋ ብቻ፣ ወይም እምነት ብቻ፣ ወይም በጎ ምግባራት ብቻ አይደለምና፡፡ ክርስትና ጸጋ፣ እምነትና በጎ ምግባራት በአንድ ላይ ነው እንጂ፡፡
ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ!
 . . . ይቀጥላል . . .


ቅዳሴ ቄርሎስ (ክፍል ሁለት)



ቅዳሴ ቄርሎስ (ክፍል ሁለት)
ይህን ንጹሕ ቅዱስ መስዋዕት በፊትህ እናቀርባለን፤ ስለ አቤልና ስለ ሴት፤ ስለ ሄኖክ፤ ስለ መልከ ጼዴቅም፡፡ ስለአብርሃም፣ ስለ ይስሐቅና ስለ ያዕቆብ፤ ስለ ሙሴና ስለአሮን፤ ስለ ነቢያትም ሁሉ፡፡ 
ስለ ስምዖን ጴጥሮስ፤ ስለ ዮሐንስ መጥምቅም፤ ስለ ሐዋርያትም ሁሉ፡፡
ስለ ዳዊትና ሕዝቅያስ፤ ስለ ኢዮስያስና ስለ ንጉስ ቆስጠንጢኖስ፤ በቀናች ሃይማኖት ስለሞቱት ነገሥታት ሁሉ፡፡
ስለ ኤጲስ ቆጶሳት፤ ስለ ቀሳውስትና ስለ ዲያቆናት፤ ስለ ንፍቀ ዲያቆናትና ስለ አናጉንስጢሳውያን፤ ስለ ወራዙትና ስለ ደናግልም ሁሉ፡፡
መንፈስ ቅዱስ በላይዋ ስላደረባትና የሕይወት መንፈስ ስለ ተፈጸመላት ነፍስ፡፡ በምትወደው በልጅህና በወዳጅህ፤ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምሳል ስለ ተቀረጸች መልክ ሁሉ፡፡
ይህ ቁርባን ስለ ተደረገላቸው፤ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንህ ስላገቧቸውና ደገኛ ቅዱስ ወደሚሆን ወደ መሠውያህ ፊት ስላቀረቧቸው ቅዱሳንም ሁሉ፡፡
በቀናች ሃይማኖት በምድር ላይ ሁሉ ስለሚኖሩ ስለ መንገደኞችና ስለ ስደተኞችም ሁሉ፤ ከዚህ ዓለም የወጡ፡፡
በምትወደው በልጅህና በወዳጅህ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስም ስላመኑ አፍና አንደበት ሁሉ፡፡ ከርሱ ጋራ ክብር ያለው ሥውር ከሚሆን ከመንፈስ ቅዱስም ጋራ፤ ለዘለዓለሙ፡፡
ለእነርሱም ለሁሉም፤ ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ቤተ ክርስቲያንህ ትሰግድልሃለች፣ ሙሽራህም ከፍ ከፍ ታደርግሃለች፡፡ በልዑላን ጥቅም፤ በሱራፌል ቅዳሴና በኪሩቤል ውዳሴ፤ በመላእክትም ምስጋና፤ በትጉሃን ልመና፤ በቅዱሳንም ፍጹምነት፡፡
በአዳም ንጽሕና፤ በኖኅም መሥዋዕት፤ በአብርሃም እንግዳ ተቀባይነት፤ በይስሐቅ ቸርነት፤ በያዕቆብ መገለጽ፡፡
በዮሴፍ እስራት፤ በኢዮብ ትዕግሥት፤ በሙሴም የዋህነት፤ በኤልያስም ምስጋና፡፡
በሐዋርያትም ማፍቀር፤ በቅዱሳንም ልመና፤ በተሰደዱ ሰዎች ድካም፤ ባልበደሉ ሰዎች ጽድቅ፤ ንጽሕናን ባገኙ ሰዎች ትሕትና፡፡
በንጹሓን ገድል፤ ከምግብ በተለዩ ሰዎች ትህርምት፤ ፍጹማን ስለሆኑ ቅዱሳን ጽድቅ ፡፡
በምድር ዳርቻ ርቀት፤ በባሕር አዝዋሪ ጥልቅነት፤ በመባርቅት ብልጭታ፤ በደመናትም መውጣት ፡፡
በመላእክት ምስጋና፤ በቅዱሳንም ምስጋና፤ በትጉሃን ንጽሕና በልዑላንም መስማማት፤ በመንፈሳውያን ብርሃን ፡፡
በካህናት ቀኝ፤ በሰማዕታት መሞት፤ በምዕመናንም ደም፤ በብርሃናውያን መላእክትም ገናንነት ፡፡
በልጅህ መመታት (ተጸፍኦ)፤ በአንድ ልጅህ ሕማማት፤ ሁሉን በያዘ ሥልጣንህም ፡፡
ወደ ጌታችንና ወደ መድኃኒታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ አባት በምታርግ ጸሎት ፡፡
እርሱን በሚያሲዙባት በዚያች ሌሊት ፡፡
ክቡራትና ብፁዓት በሚሆኑ እድፍ በሌለባቸው እጆቹ ኅብስቱን ያዘ፤ ወደ አንተ ወደ አባቱ ወደ ሰማይ አቅንቶ አየ፡፡
አመሰገነ ባረከ ቆረሰ ፡፡ አላቸውም ንሡ ብሉ ይህ ኅብስት እማሬ ኃጢአት በሚሠረይ ገንዘብ ለዓለሙ ሁሉ ቤዛ ስለእናንተ የሚፈተት ሥጋዬ ነው፡፡
ዳግመኛም ራታቸውን ከበሉ በኋላ ጽዋውን ይዞ አመሰገነ፤ ባረከ፤ አከበረም፡፡ ደቀመዛሙርቱንም አላቸው ንሡ ጠጡ ይህ ጽዋ፤ እማሬ ኃጢአትን ለማስተሥረይ ስለእናንተ የሚፈስና ለዓለሙ ሁሉ ቤዛ የሚሰጥ ሐዲስ ሥርዓት የሚሆን ደሜ ነው፡፡
የሚነድ የእሳት ሰይፍ ሜሎስ (መንፈስ ቅዱስ) ይገለጽ፤ ሰማየ ሰማያትም በቸርነትህ ይከፈት፤ በፈቃድህም ሕያውና ቅዱስ መንፈስህ ይላክ፤ ይውረድ፤ ይምጣም። በዚህም ኅብስትና ጽዋ ላይ ይረፍ ይባርከው ይቀድሰውም፤ ከአንድ ልጅህ ከጌታችንና ከአምላካችን ከመድኃኒታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋና ደም ጋራ አንድ ይሆን  ዘንድ። ለሚቀርቡት የበደል ማስተሥረያለሚቀበሉትም የኃጢአት ይቅርታ ይሆን ዘንድ ።
በቀናች ሃይማኖት አን ሆነው ከርሱ ለሚቀበሉ ሰዎች ሁሉ ለይቅርታና ለምሕረት ለደኅንነትና ለረድኤት፤ ለነፍስና ለሥጋ ሕይወት ይሁንላቸው፡፡ ለበደል ማስተሥረያ፤ ለኃጢአት ይቅርታ፤ ለትንሣኤ ሙታንና ለሐዲስም ሕይወት ይሁንላቸው፤ ለዘለዓለሙ።
ግመኛም ሁሉን የሚይዝ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አባት እግዚአብሔርን እንማልዳለን። አቤቱ የመንፈስ ቅዱስን መውረድ እየተመኘን ዐይኖቻችንን ወደአንተ እንሰቅላለን። በአብራከ ልቡናችንም እንሰግድልሃለን የኅሊናችንንና የመንፈሳችንን ራስ እናዋርድልሃለን ።
አቤቱ በቅድስናህ ቀድሰን በምሕረትህም አንጻን፤ ቅዱስ ምስጢርህንም ለመቀበል የተገባንና አንድ የሆን አድርገን ።  
በቅዱስ መሠውያህ በፊትህ ያኖርነው ይህ የእሳት ፍሕም የሚከሰን አይሁን። የፈተትነው ይህ የአምልኮ ኅብስት ለበቀል አይሁንብን ነፍችንንና ሥጋችንን ስላላነን ።
የሚያቃጥል እሳትን ለመብላት የጋለ ፍሕምንም ለመዋጥ ከንፈርን መክፈት የሚያስፈራ ነው። ነፍስ ውስጥዋን ከሽንገላ ካላነጻች ።
በድንኳኑ ውስጥ የንጹሕ ሙሽራን መሠዋቱን ማየት የሚያስፈራ ነው ።
ሕያው የሚሆን የአምላክን ልጅ በሰማያዊ አባቱ ፊት መሠዋቱን ማየት  የሚያስፈራ ነው ።
የመለኮትን ብልጭታ መቅረብ፤ የጌትነት ብርሃንንም (መብረቅመንካት የሚያስፈራ ነው ።
ለመያዙ ራሳችንን እናንጻ ለመቀበሉ ነፍሳችንን እንቀድስ ንጹሕ መግዝዐ ላህም ሆኖ ይሠዋ ዘንድ ለወደደ አብ ምስጋና ይገባዋል እንበል ።
ለወልድም ምስጋና ይገባዋል፤ ይውም ንጹሕ የሚሆን መግዝዐ ላህም ነው፡፡ ይህን ኅብስት ንጹሕ የሚሆን የመግዝዐ ላህም ሥጋ ላደረገው ለመንፈስ ቅዱስም ምስጋና ይገባዋል ።
ሦስት ስም አንድ እግዚአብሔር ነው፤ ሦስት ገጽ አንድ መልክ፤ ሦስት አካል አንድ ባሕርይ ነው ።
በትጉሃን መላእክት አፍ መመስገን ይገባዋል፤ በነቢያትና በሐዋርያትም አፍ መመስገን ቅዱስ መባል ይገባዋል ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለሙ እስከ ሁለተኛ ጉባኤ ድረስ ።
አብ ከልጁ ጋራ ከመንፈስ ቅዱስም ጋራ ከሰዓትና ከዕለት ከአውራኅና ከዓመታት አስቀድሞ የነበረ ነው ።
በአነዋወር ለአንዱ ከሁለተኛው፤ ለሁለተኛውም ከሦስተኛው መቅደም የለም። የመባርቅት ፍጥነታቸው ምን ያህል ነው። የንሥር ክንፎች ፍጥነት ምን ያህል ነው።
ባለመለያት አንድ ናቸው፤ ባለመቀላቀልም አንድ ናቸው፤ በሦስትነት ይኖራሉ፤ ባንድነት የተያያዙ ናቸው፤ በአካል የተካከሉ ናቸው፤ በብርሃንና በፀዳል የተመሳሰሉ ናቸው ፡፡
አብ ልጁን ዓለም ሳይፈጠር የወለደው በሥራ ሊረዳው አይደለም፡፡ የመንፈስ ቅዱስም ባሕርይ የተገኘ ብልሃትና ሥራ ለማወጣጣት አይደለም፡፡
ከእግዚአብሔር አብ ብቻ መወለዱን እንናገር፤ ያን ጊዜ እናት አልነበረችውም፤ የፍጡራን አነዋወር ገና አልታየም ነበርና፤ ዳግመኛም ምድራዊ አባት ሳይኖረው የአምላክ ልጅ ብቻውን ከዳዊት ልጅ ከድንግል ብቻ መወለዱን እንናገር፤ እናውራ ፡፡
በዘር ለመወለድ አባት ስላልነበረው የሰውነት ሥራ አልጎደለበትም፤ ከድንግል ብቻ ፈጽሞ ሰው ሆነ እንጂ፡፡
ከአዳም ጎን አጥንት በተፈጠረች ጊዜ እናት ስላልነበረቻት ሔዋን የሴቶች ባሕርይ እንዳልጎደለባት፤ እንዲሁ የአዳምን አባት በሥጋ በወለደችው ጊዜ የማርያም ማኅተመ  ድንግልናዋ አልጎደለም ፡፡
አዳምን የጎኑ አጥንት በተነቀለ ጊዜ እንዳላሳመመው እንደዚሁ የገሊላ ወገን የምትሆን የአምላክን እናት ሕማመ ወሊድ አላገኛትም ።
እንዲህ እናምናለን እንዲህም እንታመናለን ይህ የምንፈትተው ኅብስት ከዕብራውያን ልጅ የነሣው የክርስቶስ ሥጋ እንደ ሆነ ።
ዳግመኛም ይህ ጽዋ የእግዚአብሔር በግ ከሚሆን የፈሰሰ ደመ መለኮት እንደሆነ እናምናለን፤ ዳግመኛም ይህ ትእምርተ መስቀል በሕማማቱ ጊዜ የተዘረጋ የክርስቶስ የመስቀሉ ምሳሌ እንደ ሆነ እናምናለን ።
ደምን የተረጨች ልብስን ለለበሰ ለርሱ በመሠዊያው ፊት እንሰግዳለን ደምን ለተረጨች ለዚያችም ልብስ ለዘለዓለሙ ።
ያን ጊዜ ከዚህ ከማይጠፋ ምሥጢር የተቀበልን የእኛ አፋችን ደስታን ተመላ አንደበታችንም ደስ አለው ።
አቤቱ ዓይን ያላየውን ጆሮ ያልሰማውን በሰው ልቦናም ያልታሰበውን ቅዱስ ስምህን ለሚወዱ ሰዎች ያዘጋጅህ አምላክ ምን ትደነቅ። በቅድስት ቤተ ክርስቲያንህ ላለን ለታናናሾች ሕፃናት ለእኛ ገለጽህ፤ አብ ሆይ ይህ ፈቃድህ በፊትህ የሆነው አምላካችን እግዚአብሔር አንተ ይቅር ባይ ስለ ሆንህ ነውና።
ለአንተም እስከ አርያም ድረስ ምስጋናን ክብርንም ለአብና ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስም እናቀርባለን ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ ።
የጠራኸንንና የቀደስኸንን እኛን አቤቱ በአጠራርህ ዐድለን፤ በፍቅርህ ጠብቀን በምስጋናህም አጽናን ።
ከክፉ ነገር ሁሉ ጠብቀን በዘለዓለም መንግሥትህ በልጅህ በክርስቶስ በቀኝህ አድነን፡፡ ርሱ ያለ ክብር ጽንዕ ለአንተ ይገባል ርሱ ጋራ ከመንፈስ ቅዱስም ጋራ ዛሬም ዘወትርም፤ ለዘለዓለሙ ።