Saturday, April 15, 2017

መጀመሪያይቱ የቅዱስ ዮሐንስ መልዕክት ምዕራፍ አምስት

(መዳንና በጎ ምግባራት በመጀመሪያይቱ የቅዱስ ዮሐንስ መልዕክት)
ቁ. 1-3 ‘‘ኢየሱስ መሲሕ እንደሆነ የሚያምን ሰው ሁሉ ከእግዚአብሔር ተወልዷል፡፡ ወላጁንም የሚወድ ሁሉ ከእርሱ የተወለደውን ደግሞ ይወዳል፡፡ እግዚአብሔርን ብንወደው ትእዛዙንም ብናደርግ የእግዚአብሔርን ልጅ እንደምንወደው በዚህ እናውቃለን፡፡ ትእዛዙን እንጠብቅ ዘንድ የእግዚአብሔር ፍቅሩ ይህቺ ናትና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም፡፡’’ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ የሚያምንና ቤዛነቱን የሚቀበል ሰው ሁሉ ከእግዚአብሔር ተወልዷል፡፡ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚወድ ደግሞ የላከውን አባቱንም ይወዳል፤ ልጁ ከእርሱ ዘንድ ወጥቶ መጥቷልና፡፡ እግዚአብሔርን የምንወደው ደግሞ ተእዛዛቱን በመጠበቅ ነው፤ ትእዛዛቱን የማይጠብቅ ሰው የእግዚአብሔር ፍቅር በእርሱ ዘንድ ሊኖረው አይቻለውምና፤ ትእዛዛቱ ደግሞ የፍቅር ትእዛዛት ናቸውና ከባዶች አይደሉም፡፡ በእግዘዚአብሔር ፍቅር ለመኖር እንደተጠራን ሁሉ በትእዛዛቱም ልንኖር ደግሞ ተጠርተናል፡፡ የምናደርገውን ሁሉ ስለ ፍቅሩ ብለን እናደርጋለን፤ የምንተወውንም ስለ ፍቅሩ ብለን እንተዋለን፡፡
‘‘ለዚህ ተጠርታችኋልና፤ ክርስቶስም እኮ ፍለጋውን ትከተሉ ዘንድ ምሳሌውን ሊተውላችሁ ስለእናንተ መከራን ተቀብሏል፡፡ እርሱ ኀጢአት አልሠራም፤ በአንደበቱም ሐሰት አልተገኘበትም፡፡ ሲሰድቡት አልተሳደበም፤ መከራ ሲያጸኑበትም አልተቀየመም፤ ነገር ግን እውነተኛ ፍርድን ለሚፈርደው አሳልፎ ሰጠ፡፡’’ 1ኛ ጴጥ 2፣21-23፡፡ መጠራታችን በስሙ እንድናምን ብቻ ወይም በሥራችን በማንገልጠው ፍቅር እንድንወደው አይደለም፡፡ በስሙ ማመናችንና በፍቅሩ መኖራችን ከተቀደሰው ሕይወታችንና በጎ ምግባራት ካልተለዩት ኑሯችን የሚለይ አይደለም፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኀጢአትን አንዳላደረገ እኛም ደግሞ ከኀጢአት የምንርቅና የምንጠበቅ፣ በአንደበቱም ሐሰት እንዳልተገኘበት ሁሉ ሐሰትን የምንጸየፍ፣ ሲሰድቡት እንዳልተሳደበ ሁሉ የመሰድቡንንና የሚረግሙንን የምንመርቅ ልንሆን ያስፈልገናል፡፡ ምክንያቱም ከጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተማርነውና የተቀበልነው ክርስትና በስሙ ስለማመን ብቻ ሳይሆን በስሙ መከራን ስለመቀበልና በጎ ምግባራትን ስለማድረግ፤ መንፈሳዊ ተጋድሎን ስለመጋደልም ያስተምረናልና፡፡
ቁ. 18 ‘‘ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ አንደማይበድል እናውቃለን፤ ከእግዚአብሔር የተወለደ ራሱን ይጠብቃል እንጂ ክፉ አያገኘውም፡፡’’ ክርስትና እንዲህ ነው! በክርስቶስ ማመን ብቻ ሳይሆን፣ ስለክርስቶስ ብሎ ራስን ከበደልና ከኀጢአት መጠበቅ፣ ከክፉውና ከእርኩሱ ነገር ሁሉ ራስን ማራቅ፡፡ በበደላችንና በኀጢአታችን ሙታን የነበርነውን እኛን እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ፣ በደሙ ፈሳሽነት ወደ ክብሩ መንግስት አፍልሶናል፡፡ ወደ ክብሩ መንግስት ከፈለስን ደግሞ ራሳችንን ከኀጢአት እያራቅን እስከ ሞት ድረስ የወደደንን መድኃኒታችንን ደስ በሚያሰኝ የተቀደሰ ሕይወት ልንኖር ያስፈልገናል፡፡ ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኀጢአትን አያደርግም!
ማጠቃለያ
ክርስትና አንዱን ተቀብሎ አንደኛውን መተው አይደለም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፉልን ሁሉም ቃላት ከእግዚአብሔር የወጡ እንደሆኑና የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው እንደሆኑም እናምናለን፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጸጋ ብቻ ሳይሆን ስለ እምነትና ስለ በጎ ምግባራትም ተጽፏል፡፡ ሦስቱም ከእግዚአብሔር ወጥተዋልና ሦስቱንም እኩል እናከብራቸዋለን፣ እንቀበላቸዋለን፣ እንታዘዛቸዋለንም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን መዳን በጸጋ፣ በእምነትና በበጎ ምግባራት እንደሆነ ነው፡፡ የምንድነው በሦስቱም ሕብረት እንደሆነ አንጂ ከሦስቱ በአንደኛው እንደሆነ አልተጻፈልንም፡፡ ከሦስቱ አንደኛውንና እኛ የፈለግነውንና የመረጥነውን ብቻ ወስደን መዳን በዚህ ብቻ ነው ማለት አንችልም፡፡ መዳን እኛ እንዳሰብነውና እንደገባን ሳይሆን እግዚአብሔር እንደወራልንና እንደገለጠልን፤ እኛም ደግሞ አንደታዘዝነው መጠን ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን ስለሦስቱም ስለሆነ ሦስቱንም አንቀበላለን፣ በሦስቱም እንጸናለን፡፡
መዳናችንን የፈጸመልንና የምንድንበትን መንገድ የሠራልን ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ በራሳችን መዳን ባለመቻላችንና ከአዳም አንስቶ እስከ ክርስቶስ መገለጥ ድረስ ባሉት አመታት ሞት በዓለሙ ሁሉ በመንገሱ፣ ከሰው ወገን ደግሞ አንድም ሰው እንኳን ወደ መዳን የሚያመጣውንና ወደ እግዚአብሔር የሚያደርሰውን መንገድ መሥራት ባለመቻሉ እርሱ ራሱ እግዚአብሔር በሥጋ ተገልጦና  ስለ እኛ በደል በእኛ ፈንታ ተገብቶ መከራን በመቀበል ከሞትና ከኩነኔ በደሙ ፈሳሽነት ተቤዠን፣ በራሱ ሥራ ለመዳን ዋጀን (እኛ ልንከፍለው ያልቻልነውን የበደላችንን ዕዳ ከፈለልን)፡፡ በዚህ የተነሳ ወደ እግዚአብሔር መንግስት መግባትና ከእርሱም ጋር ህብረት ማድረግ ቻልን፣ ከክርስቶስ ሥራ የተነሳ ለመንግስቱ የተገባን ሆነን ተቆጠርን፡፡ ይህ በራሱ በእግዚአብሔር የተደረገልን የመዳን መንገድ ነው እንግዲህ በመጽሐፍ ቅዱስ ጸጋ ተብሎ የተጠቀሰው፡፡ ይህም ጸጋው እንዲሁ በነጻ የተሰጠንና የተቀበልነው ስለሆነ ከእኛ የሆነ አንዳችም አስተዋጽዖ የለበትም፡፡ ይህ ጸጋው በዓለሙ ሁሉ ያሉትን የሰው ልጆች ሁሉንም ለመዳን የተገቡ አድርጓቸዋል፡፡ ከጸጋው የተነሳ ወደ መዳን የሚያደርሰው መንገድ በጸጋው በኩል ክፍት ተደርጓል፡፡ በዚህ የተከፈተ መንገድ በኩል በእምነትና በምግባር የሚጓዙ ሁሉ ወደ መዳን ይደርሳሉ፡፡ ጸጋው ወደ መዳን የሚያደርስ መንገድ እንጂ በራሱ መዳን አይደለም፡፡ ይህ ባይሆንማ ኖሮ የጸጋው ሥራና ስጦታው ለሰው ልጆች ሁሉ የተደረገ ስለሆነ ከሰው ልጆች መካከል የማይድኑ ሰዎች አይኖሩም ነበር፡፡ ምንም እንኳን ጸጋው ለዓለሙ ሁሉ የተደረገ ቢሆንም የተደረገላቸውን ይህን ነጻ ስጦታ/ጸጋ አምነው በበጎ ምግባራት የሚታዘዙትና ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት የሚቀርቡት ብቻ ይድናሉ፡፡ ጸጋው ቢሰጣቸውም የጸጋውን ስጦታ አምነው በበጎ ምግባራት መታዘዝ ያልቻሉና ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት መቅረብ ያልቻሉት ግን ጸጋው በሕይወታቸው እንዲሠራ ስላልፈቀዱ ከመዳን በአፍአ/ውጪ ይሆናሉ፡፡
ኦርቶዶክሳዊው ትምህርት እንዲህ የሚል ነው፡፡ እኛ እንደምንፈልገው ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተጻፈልን እናምናለን፣ እንቀበላለን፣ እንታዘዛለንም፡፡ መዳን በጸጋው ነውና ጸጋውን እንደገፍበታለን፤ በጸጋውም በኩል ደግሞ በእምነት እናድጋለን፤ ከክፉው እየራቅንና በጎውን ሁሉ እያደረግንና እየታዘዝን ወደ እግዚአብሔር አንደርስበታለን፤ እርሱም እውነተኛው መድኃኒት ነው፡፡ መዳን በእርሱ ብቻ ካልሆነ በቀር በሌላ የለምና፡፡ መጽሐፍም እንደሚል ‘‘መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ ከሰማይ በታች እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰው የተሰጠ ሌላ ስም ከቶ የለምና፡፡’’ ሐዋ 4፣12፡፡ መዳናችን በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ የተሠራልን ነውና የተሠራልንን ይህን መዳን ብቻ እናምናለን እንቀበላለንም እንጂ ከተሠራልን መዳን በቀር ሌላ መዳንን አናምንም፤ አንቀበልምም፤ መጸሐፍ ቅዱስ ከሚነግረንም በቀር ወደ ሌላ ፈቀቅ አንልም፡፡

ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ!

No comments:

Post a Comment