Tuesday, December 6, 2016

ቅዳሴ ቄርሎስ (ክፍል አንድ)



የአማልክት አምላክ፤ የአጋዕዝት ጌታ አቤቱ ወደአንተ አነዋወሩ የማይፈጸም ኅቡእ አምላክ፤ ከሁሉ ይልቅ ልዑል ነው፤ አነዋወሩ የማይገኝ ነው፡፡
የሚያቃጥል እሳት፣ የሚያድንም እሳት፣ የአማልክት አምላክ፣ የጌቶችም ጌታ ነው፡፡ ዙፋኑ ከሰማያት በላይ፤ የእግሩም መመላለሻ ምድር  ነው፡፡ በብርሃን የሚኖር ልዑል ምጡቅ ነው፡፡
በሰማይ ያለ ማደሪያው ሥውር ልዑል ነው፡፡ የእሳት መጐናፀፊያ የሚጐናፀፍ በነደ እሳትም ያጌጠ ነው፡፡ ዙፋኑ ከእሳት አለቆች በላይ የሚሆን፤ መመላለሻው በማይዳሰስ በአየር ላይ፣ ጠፈሩም በልዑል ሰማይ፣ መንኰራኩሩ ደመና፣ ጎዳናውም በባሕር ማዕበል ላይ፣ በሚላኩት በእሳት አለቆችም ነው፡፡
የሚያቃጥል እሳት እንዳያቃጥላቸው በሁለቱ የእሳት ክንፋቸው ፊታቸውን ይሸፍናሉ፡፡ ግሩም የሚሆን ብርሃኑ (ነበልባሉ) እንዳይመታቸው በሁለት የብርሃን ክንፋቸው እግራቸውን ይሸፍናሉ፡፡ እረቂቅ በሚሆን ሁለት ክንፋቸው እስከዓለም ዳርቻ ይወጣሉ፡፡
ሱራፌል በአለቆቻቸው፤ ኪሩቤልም በምስጋናቸው፤ መላእክትም በየሥርዓታቸው፤ ትጉሃንም በየሠራዊታቸው፤ የትጉሃንም አለቆች በየወገናቸው፤ እሳትነት ያላቸው መላእክት በብርሃናቸው፤ መንፈሳውያን በአነዋወራቸው ግሩም በሚሆን ቃል ያመሰግናሉ፡፡
ይቀድሳሉ ከፍ ባለና በታላቅ ቃል ይጮሃሉ፤ ሲያመሰግኑም እንዲህ ይላሉ፤ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ፍጹም አሸናፊ እግዚአብሔር የጌትነትህ ምስጋና በሰማይና በምድር የመላ ነው፡፡
እኛም ከእነርሱ ጋር በአንድነት የጌታችንና የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አባት አንተ ቅዱስ ነህ፤ የጌትነትህም ምስጋና ግሩም ነው እንላለን፡፡ ይኸውም ብቻውን በእውነት ልጅህ ነው፤ አንተም ብቻህን በእውነት አባቱ ነህ፡፡
ከአንተ መወለዱ አይገኝም፤ ለአነዋወርህ ጥንት እንደሌለው ለእርሱም ለልጅህ ጥንት የለውም፣ ፍጻሜም የለውም፤ ለዘመንህም ጥንት እንደሌለው ለዘመኑ ጥንት የለውም፡፡
ከአንተ ከተወለደ ከልጅህ በቀር በቀኝህ የሚቀመጥ የለም፤ በዙፋንህም ላይ የሚቀመጥ የለም፤ እንደ አንተ ያለ አርዐያህና አምሳልህ ነው እንጂ፡፡
ይኸውም ልጅህ የምክርህ አበጋዝ ነው፡፡ ከአንተ የተገኘ ወዳጅህ አምሳልህና መልክህ፤ ኅሊናህና ኃይልህ፤ ጥበብህና ምክርህ፤ ቀኝህና ክንድህ፤ ከእውነተኛ ባሕርይህ የተወለደ እውነተኛ አምላክ ወልድ ዋሕድ ነው፡፡
በሁሉ ፍጹም የሚሆን ቃል ከባሕርይህ ወጣ፡፡ ከአንተ የተወለደ አርዐያህ ከአንተ ጋራ የሚተካከል ከአንተ ጋራ ልዑል ግሩም የሚሆን ፡፡
መላእክትና የመላእክት አለቆች ይሰግዱለታል፤ ሰውን በመውደድህ ወደእኛ ሰደድኸው ወደኸናልና፡፡
እርሱ ራሱን አዋርዶ አዳነን ፤ ከአንተ የተወለደ እንደአንተ የሆነው በእኛ አምሳል ከእኛ ተወለደ፤ ይኸውም የሚመስልህ ነው፡፡
ይህ በእኛ አምሳል በመካከላችን ተመላለሰ፡፡ ፍጹምነቱ ከአንተ ጋራ የሚተካከል የሚመስልህና  እንደአንተ ያለ እርሱ ነው፡፡
የአነዋወርህን ነገር እርሱ ነገረን እንደ እኛ ሥጋ ሆነ፡፡ ዳግመኛም በአርያም ሱራፌልን የሚያስደነግጣቸው እርሱ በፈቃዱ  ታመመ፡፡
ዐይተን አቃለልነው፡፡ በአንተ ዘንድ ገናና እንደመሆኑ መጠን በእኛ ዘንድ ጌታ የተመሰገነ ነው፤ ከትጉሃንም የተሠወረ ነው፤ በእኛ ባሕርይ ተወልዶ በእውነት ተገልጦ ታየ፡፡
በመልክ በብርሃን አንተን ይመስላል፤ ሰው ሆኖ ሥጋችንን መሰለ በእኛም  አምሳል ከእኛ ዘንድ ኖረ፤ እንደአንተም የተመሰገነ ነው፡፡
ወጣ፣ ወደ አኛም ወረደ እንደ እኛ ተሰደበ ፡፡ ወጣ ወደ አንተም ዐረገ እንደአንተም የከበረ ነው ፡፡
ትጉሃን በሰማያት የሚያመሰግኑት እርሱ የእሾህ ዘውድ ደፋ፤ ከወንበዴዎችም ጋራ በዕፀ መስቀል ላይ ተሰቀለ፤ ልዑላኑ እየፈሩ በፊቱ እራሳቸውን የሚያዋርዱለት እርሱ በሚሰቅሉት ፊት ለሕማም እራሱን አዋረደ፡፡
ሰማይንና ምድርን የተሸከመውን በዕፀ መስቀል ላይ ደካማ እንጨት ተሸክመው፤ ሰማይና ምድር የሚንቀጠቀጡለትን ጠባብ መቃብር በተቀበረበት ጊዜ ወሰነው፡፡
የዓለምን ዳርቻ በመኻል እጁ የሰበሰበውን፤ የዓለምንም ባሕር በእፍኙ የዘገነውን በበፍታ ገንዘው በሦስት ክንድ ከስንዝር መቃበር ቀበሩት፡፡ ክቡር ራሱን ዘረጋ፤ ከእርሱም የተነሣ መቃብር ተመላ ፡፡
በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ወዳሉበት ደጅ ተዘግቶ ሳለ ገባ፡፡ ከደቀ መዛሙርቱም ተለይቶ ወጣ፡፡
በዚያም ሳለ ጌትነቱ ሰማያትን መላ፡፡ ወደ ሰማይም ዐረገ፤ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ ሰማይ ዙፋኑ ሆነ ምድርም የእግሩ መመላለሻ፡፡
ዳግመኛም ሕያዋንንና ሙታንን ይገዛ ዘንድ ይመጣል፡፡ ከላይ ነጐድጓዱ ይሰማል፤ ቃሉም የምድርን መሠረት ያናውጣል፡፡ ሙታንም ከመቃብራቸው ወደ እርሱ ይወጣሉ፡፡ ከአባቱ፣ ከመንፈስ ቅዱስም ጋራ ክብር ምስጋና ለዘለዓለሙ የርሱ የሚሆን ፡፡
አቤቱ በእውነት በቃልህ፤ ሁሉን በሞትህ ያስነሣሃቸው፤ ሙታንንም የምታስነሣ አንተ ነህ፡፡ ከከሃድያንም ወገን በመስቀልህ ያመኑብህ፤ ከስሑታንም ወገን በሞትህ የተመለሱ፣ በኃጢአት ከተዳደፉት ወገን በመከራህ የተቀደሱ፤ ከሙታንም ወገን በትንሣኤህ ያስነሳሃቸው፤ በአንተ ለመፍረድ ከተሰበሰቡ ወገን ያመኑብህ፡፡
የብረትን መዝጊያ ከፍተህ ሥጋቸው በመቃብር የጠፋውን ታስነሣቸዋለህ፡፡ በሕይወታቸው ያንቀላፉትን ታነቃቸዋለህ፤ በመሬት የተኙትንም ታስነሣቸዋለህ፡፡ ኃጥአን ባሮችን ነፃ ታደርጋቸዋለህ፡፡ የተዳደፉትን በምህረትህ ታከብራቸዋለህ፡፡
በይቅርታህ ዐላውያንን አንድ ታደርጋቸዋለህ (ታስማማቸዋለህ)፤ የተመለሱትን በቃልህ ታጸናቸዋለህ፡፡ በጎዳናህ ይሄዱ ዘንድ አላውያንን ትመልሳቸዋለህ፤ ወደቦታህ ይገቡ ዘንድ የተበተኑትን ትሰበስባቸዋለህ፡፡
ከወገኖችህ የበደሉትን አንተን ወደ ማመን ትመልሳቸዋለህ፡፡
የመንፈስ ደካሞችን አቤቱ አንተ ታጸናቸዋለህ፡፡ በምድር የሚኖሩ ሁሉ አንተ አምላክ እንደሆንህ ያውቁህ ዘንድ፤ ከአንተ የተወለደው የምትወደው ልጅህና ወዳጅህ የላክኸው ኢየሱስ ክርስቶስንም፤ ከእርሱ ጋራ ክብር ያለህ፤ ሥውር ከሚሆን መንፈስ ቅዱስም ጋራ ለዘለዓለሙ፡፡

ነገረ ክርስቶስ በውዳሴ ማርያም



የጌታችንና መድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የመንግሥቱ ወንጌል/የምሥራቹ በአራት ወንጌላውያን ተጽፎ በሐዲስ ኪዳን ውስጥ ታላቅ ስፍራን ይዞ እናገኘዋለን፡፡ ወንጌል ማለት የምስራች ማለት ሲሆን የአምላክ ሰውን መውደድና ሰዎችን ሁሉ ለመንግሥቱ የተገቡ ይሆኑ ዘንድ ሰዎችን በሚመስል ማንነት በደካማ ሥጋ ውስጥ ራሱን መግለጡንና ሰዎችን ሁሉ በእውነተኛ ፍቅርና መውደድ መፈለጉን ለሰዎች ሁሉ የሚነግር ታላቅ ዜና ነው፡፡ ይህ ታላቅ ዜና የጌታችንና መድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደቱን፣ ስደቱን፣ ዕድገቱን፣ ትምህርቱን፣ ገቢረ ተአምራቱን፣ ለሰዎች ያደረገውን ርህራሄና ቸርነቱን፣ የተቀደሰ ኑሮውንና አርዓያነቱን፣ መከራውንና ስቅለቱን፣ ሞቱንና ትንሣኤውን፣ ዕርገቱንና ዳግም ምጽዓቱን . . . ይነግረናል፡፡ የጌታችን ወንጌል በአራት ወንጌላውያን ቢጻፍም የሚያወራው ግን ሰው ሆኖ ስለተገለጠው አምላክ ስለቤዛችን፤ መሲህ ሆኖ ሊያድነን ስለመጣውና በምድር ላይ ስለተመላለሰው ስለናዝሬቱ ኢየሱስ ነው፡፡ ምንም እንኳን ወንጌሉ በአራት ወንጌላውያን ቢጻፍና ስለጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቢያወራም በጸሐፊዎቹ ስም የማቴዎስ፣ የማርቆስ፣ የሉቃስና የዮሐንስ ወንጌል ተብሎ ይጠራል፡፡ ክርስትና የቅዱሳንን ተጋድሎና ሱታፌ ያከብራልና ታሪኩና ትምህርቱ የጌታችንና መድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቢሆንም መታሰቢያነቱን ግን ለጸሐፊዎቹ ሰጥቷል፤ ጸሐፊዎቹ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከታሪኩ ጋር የተቀደሰ ግንኙነት/ሱታፌ ነበራቸውና፡፡ በውዳሴ ማርያም ውስጥም ተመሳሳይ ሁኔታን እናስተውላለን፤ አብዛኛው የምስጋናው ክፍል የጌታችንና መድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋዌ/ሰው መሆን የሚያነሳና የሚያመሰግን ቢሆንም መታሰቢያነቱ ግን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ለሆነባትና የተቀደሰ ሥጋዋን ወስዶ ማደሪያው ላደረጋት ለተቀደሰች እናቱ ለእመቤታችን ለድንግል ማርያም እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ውዳሴ ማርያም የእመቤታችን መታሰቢያ ቢሆንም የክርስቶስ የሥጋዌው ምስጋና ነው፡፡ የጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆንና ዓለሙን ሁሉ መውደድ፣ የተቀደሰ ፍለጋውና ቤዛነቱ በሚገርም ጥበብ፣ በድንቅ ምሥጢር፣ በመንፈሳዊ ቃላት በውዳሴ ማርያም ውስጥ ተገልጾ እናነበዋለን፡፡ 
የሰኞ ውዳሴ ማርያም
ጌታ ልቡ ያዘነና የተከዘ አዳምን ነፃ ያወጣውና ወደ ቀድሞ ቦታው ይመልሰው ዘንድ ወደደ፡፡
አዳም ከእግዚአብሔር ህብረት፣ ከእረፍት ስፍራው ከገነት ተለይቷልና በልቡ አዝኗል፤ ተክዟልም፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ተገልጦ መርገሙን እስከሚሽርለትና በደሙ ቤዛነት እዳውን ከፍሎ ነጻ እስከሚያወጣው ድረስ በሲዖል ውስጥ በስቃይ ኖሯል፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላ ግን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምንና ልጆቹን ወደቀደመ ሥፍራችን ወደ ክብሩ መንግስት ሊያፈልሰን ፈቃዱ ሆኗል፡፡ እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኀጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን። እንዲል ቆላ 113-14፡፡
ከድንግል ያለወንድ ዘር በሥጋ ተወለደና አዳነን፡፡ ከይሲ ዲያብሎስ ያሳታት ሔዋንን እግዚአብር ምጥሽንና ጻርሽን አበዛዋለሁ ብሎ ፈረደባት፣ ሰውን ወደደና ነጻ አደረጋት፡፡
የአዳምን ዕዳ ከፍሎ ከፍርድ የሚያወጣውና የሚታደገው ወገን/አካል ስላልነበረ እራሱ እግዚአብሔር አዳምን ሊያድነውና ቤዛ ሊሆነው ወደደ፡፡ አዳም ከበደሉ የተነሳ እግዚአብሔርን ቢያሳዝነውም የተበደለው እግዚአብሔር ለአዳም ካሳውን እራሱ ከፍሎለት እራሱ ታረቀው፡፡ ይኸውም ደግሞ ከራሱ ከእግዚአብሔር ምህረትና ርህራሄ የተነሳ እንጂ ከአዳም ከሆነው በጎነትና መልካምነት የተነሳ አይደለም፡፡ ነገር ግን፥ የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደዱ በተገለጠ ጊዜ፥ እንደ ምሕረቱ መጠን ለዐዲስ ልደት በሚኾነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም፡፡ ቲቶ 3፣4-5፡፡ በዲያብሎስ ክፉ ምክር ያጣነውን የእግዚአብሔር መንግስት ዳግመኛ እንገባበት ዘንድ እርሱ እግዚአብሔር ባወቀ፤ እንደምክሩ ታላቅነት መጠን ነጻ አደረገን፡፡ ሔዋንን የዲያብሎስ ምክር ቢጎዳትም በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሆነው የእግዚአብሔር ምክር ግን ለዘለዓለም ጠቀማት፡፡ እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥ በሕይወታቸውም ዅሉ ስለሞት ፍርሀት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ዅሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ።ዕብ 2፣14-15፡፡
ነቢዩ ኢሳይያስ በመንፈስ ቅዱስ የአማኑኤልን ምስጢር አየ ስለዚህም ሕፃን ተወለደልን ወልድም ተሰጠን ብሎ አሰምቶ ተናገረ፡፡
ሕፃን ተወልዶልናልና፣ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፣ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘለዓለም አባት፣ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል፡፡ኢሳ 9፣6-7፡፡ ኢሳይያስ የጌታችንን መወለድ በመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ ትንቢት ተናግሯል፡፡ የሚወለደው ህፃን ደግሞ ዓለሙን ሁሉ የሚዋጅ ብርቱ መድኃኒት ነው፡፡ ኢሳይያስም ብቻ ሳይሆን ካህኑ ዘካርያስም እንዲህ ሲል ስለጌታችን ቤዛነት ትንቢት ተናግሯል፡- የእስራኤል ጌታ አምላክ ይባረክ፥ ጐብኝቶ ለሕዝቡ ቤዛ አድርጓልና፤ ከጥንት ዠምሮ በነበሩት በቅዱሳን ነቢያት አፍ እንደ ተናገረ፥ በብላቴናው በዳዊት ቤት የመዳን ቀንድን አስነሥቶልናል፤ ማዳኑም ከወደረኛዎቻችንና ከሚጠሉን ዅሉ እጅ ነው፤ እንደዚህ ለአባቶቻችን ምሕረት አደረገ፤ ለአባታችን ለአብርሃምም የማለውን መሐላውን ቅዱሱን ኪዳን ዐሰበ፤ በእርሱም ከጠላቶቻችን እጅ ድነን በዘመናችን ዅሉ ያለፍርሐት በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ እንድናገለግለው ሰጠን።ሉቃ 1፣68-75፡፡

ሰው ሆይ ፈጽመህ ደስ ይበልህ እግዚአብሔር ዓለሙን ወዶታልና አንድ ልጁንም የሚያምንበት ሁሉ እስከ ዘለዓለም ፈጽሞ ይድን ዘንድ አሳልፎ ሰጥቶናልና ልዑል ክንዱን ሰደደልን፡፡
እግዚአብሔር ዓለሙ ሁሉ ይድን ዘንድ አንድያ ልጁን ቤዛና መድኃኒት አድርጎ ሰጥቷል፡፡ በእርሱ የሚያምን ዅሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና።
ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና።ዮሐ 3፣16-17፡፡ አሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ለዓለም ሁሉ መዳን ሆኗል፤ ከእርሱ በቀር እንድንበት ዘንድ የሚቻለን ሌላ የመዳን መንገድ የለንም፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን የሚሆነው የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለዋጋ ለሰው ሁሉ ቀርቧልና፡- መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና። ሐዋ 4፣12፡፡ መዳናችንም በሕግ ሥራ ወይም ከሰው ወገን በሚገኝ በጎነት የሚሆን ሳይሆን በጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ ፈሳሽነት የሚሆን መዳንና ጽድቅ ነው፡፡ አኹን ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለሕግ ተገልጧል፥ እርሱም፥ ለሚያምኑ ዅሉ የኾነ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው፡፡ሮሜ 3፣21-22፡፡

የነበረው የሚኖረው፤ የመጣው ዳግመኛም የሚመጣው ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ያለመለወጥ ፍጹም ሰው ሆነ፡፡ አንዱ ወልድ በሥራው ሁሉ አልተለየም እግዚአብሔር ቃል መለኮት አንድ ነው እንጂ፡፡
እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ሰው ሆኖ በሥጋ ተገልጧል፡፡ ዮሐ 1፣14፡፡ የእግዚአብሔር ማዳኑ አንዲት ናትና የዳንንባት የወልድ ማዳኑ የአብና የመንፈስ ቅዱስም ናት፡፡ አብ እንዲሠራ እንዲሁ ደግሞ ወልድም ይሠራልና፡፡ አባቴ እስከዛሬ ይሠራል፤ እኔም ደግሞ እሠራለሁ እንዲል ዮሐ 5፣17፡፡ አብ ከወልድ የተለየ ማዳን እንደሌለው ሁሉ ወልድም ከአብ የለየ ማዳን የለውም፡፡ ወልድ አዳነን ስንል አብና መንፈስ ቅዱስም አዳነን እንላለንና፣ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ እግዚአብሔር ብለን እናምናለንና እግዚአብሔር በአንድነቱ አዳነን፡፡ አንዱ ወልድ በሥራው ሁሉ አልተለየም እግዚአብሔር ቃል መለኮት አንድ ነውና የሚለው ይህንን ነው፡፡ በእኔ የሚኖረው አብ እርሱ ሥራውን ይሠራል፡፡ ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ ዮሐ 14፣10፡፡   

የነቢያት ሐገራቸው ቤተልሔም ሆይ ደስ ይበልሽ፤ ሁለተኛው አዳም ክርስቶስ በአንቺ ዘንድ ተወልዷልና፤ የቀድሞውን ሰው አዳምን ከምድር (ከሲኦል) ወደ ገነት ይመልሰው ዘንድ፤ አዳም ሆይ መሬት ነበርክና ወደ መሬት ትመለሳለህ ብሎ የፈረደበትንም የሞት ፍርድ ያጠፋለት ዘንድ፤ ብዙ ኃጢአት ባለችበት የእግዚአብሔር ጸጋ ትበዛለች፡፡
ቤተልሔም የደስታ ማደሪያ ናት መድኅን ክርስቶስ ተወልዶባታልና፤ ይኸውም ደግሞ ለዓለሙ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ ነው፡፡ አንቺም ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ፥ አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትኾኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ፤ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ዠምሮ ከዘለዓለም የኾነ፥ በእስራኤልም ላይ ገዢ የሚኾን ይወጣልኛል። ሚክ 5፣2፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ቤተ ልሔም ትባላለች፤ ለዓለሙ ሁሉ ደስታ የሚሆን መድኅን ክርስቶስ በማኅጸኗ አድሯልና፡፡ አንድም ደግሞ ቤተ ልሔም የእንጀራ ቤት ማለት ነው፤ እመቤታችንም የሕይወት እንጀራ የሚሆን የኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ ናትና ቤተ ልሔም ትባላለች፡፡ ዮሐ 6፣48፡፡ ሞት በአዳም በኩል ወደ ዓለም ቢገባም በክርስቶስ በኩል ደግሞ ለዓለሙ ሁሉ ሕይወትና መዳን ሆኗል፡፡ የአዳም መተላለፍ በክርስቶስ መታዘዝ ተሽሯልና፡፡ ነገር ግን፥ በአዳም መተላለፍ ምሳሌ ኀጢአትን ባልሠሩት ላይ እንኳ፥ ከአዳም ዠምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ሞት ነገሠ፤ አዳም ይመጣ ዘንድ ላለው ለእርሱ አምሳሉ ነውና። ነገር ግን፥ ስጦታው እንደ በደሉ መጠን እንደዚያው አይደለም፤ ባንድ ሰው በደል ብዙዎቹ ሞተዋልና፥ ነገር ግን፥የእግዚአብሔር ጸጋና በአንድ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የኾነው ስጦታ ከዚያ ይልቅ ለብዙዎች በዛ። አንድ ሰውም ኀጢአትን በማድረጉ እንደኾነው መጠን እንደዚያው ስጦታው አይደለም፤ ፍርድ ከአንድ ሰው ለኵነኔ መጥቷልና፥ ስጦታው ግን በብዙ በደል ለማጽደቅ መጣ።ሮሜ 5፣14-16፡፡ ብዙ ኃጢአት ባለበት ዓለም ውስጥ የእግዚአብሔር ጽድቁ ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለሙ ሁሉ ጸጋውን አበዛ፡፡ ከጸጋው ብዛት የተነሳም ወደ እግዚአብሔር መንግስት ቀረብን፡፡ የጸጋው ኃይልና ታላቅነት ከአዳም በደል የበለጠና የበረታ ስለሆነ ቅዱስ ኤፍሬም ብዙ ኃጢአት ባለችበት የእግዚአብሔር ጸጋ ትበዛለች፡፡ብሎ ገለጸው፡፡ ዳሩ ግን ኀጢአት በበዛበት፥ ኀጢአት በሞት እንደነገሠ፥ እንዲሁ ደግሞ ጸጋ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተነሣ በጽድቅ ምክንያት ለዘለዓለም ሕይወት ይነግሥ ዘንድ፥ ጸጋ ከመጠን ይልቅ በለጠ።ሮሜ 5፣20-21፡፡

የሰው ሁሉ ሰውነት ፈጽሞ ደስ ይላታል፡፡ በሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በምድርም ሰላም ለሰውም እርሱ በሚፈቅደው እያሉ አሰምተው ንጉስ ክርስቶስን ከመላእክት ጋር ያመሰግኑታል፡፡ የቀድሞውን እርግማን አጥፍቷልና፤የጠላትን ምክሩን አፈረሰበት ለአዳምና ለሔዋን የእዳ ደብዳቤአቸውን ቀደደላቸው፡፡ በዳዊት ሀገር የተወለደ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምንና ሄዋንን ነጻ አደረጋቸው፡፡
የጌታችን ልደት ለዓለሙ ሁሉ ደስታ ነውና መላእክቱ ከእረኞቹ ጋራ በደስታ እግዚአብሔርን አመስግነውታል፡፡ ሉቃ 2፣8-15፡፡ እውነተኛው ደስታችን ከክርስቶስ ሥራ፣ ከማዳኑም ኃይል የተገኘ ነውና፡፡ የቀድሞውን እርግማን ያጠፋ ዘንድም ክርስቶስ ራሱን ለመስቀል ሞት አሳልፎ ሰጥቶልናል፡፡ ክርስቶስ ስለእኛ እርግማን ኾኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን፡፡   ገላ 3፣13፡፡ ይህም ደግሞ የሆነው በራሱ በእግዚአብሔር ሐሳብ ነው፡፡ ሐሳቡም የጠላት ዲያብሎስን ምክርና ክፉ ሐሳቡን አፍርሶታል፣ ሽሮታልም፤ የምንከሰስበትን የዕዳችንንም ክስ አጥፍቶልናል፡፡ በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው፡፡እንዲል ቆላ 2፣14፡፡ የክርስቶስ ቤዛነት፣ የመስቀሉ ሥራ አዳምንና ልጆቹን ሁሉ ነጻ አወጣን፡፡ በዚህም የተነሳ ከምንከሰስበት የአዳም መተላለፍና ዕዳ ነጻ ሆነናል፡፡ በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን፡፡ተብሎ ተጽፏልና ገላ 5፣1፡፡

በዚህ ዓለም ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ የምታበራ እውነተኛ ብርሃን ስለ ሰው ፍቅር ወደ ዓለም የመጣህ ፍጥረት ሁሉ በመምጣትህ ደስ አለው አዳምን ከስህተት አድነኸዋልና ሄዋንንም ከሞት ጻዕረኝነት ነጻ አድርገሃታልና የምንወለድበትን መንፈስ (ረቂቁን ልደት) ሰጠኸን ከመላእክት ጋርም አመሰገንህ፡፡
ለሰው ዅሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር። በዓለም ነበረ፥ ዓለሙም በእርሱ ኾነ፥ ዓለሙም አላወቀውም። የእርሱ ወደኾነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ዅሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይኾኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፡፡ዮሐ 1፣9-12፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የነፍሳችን ጨለማ የራቀበት እውነተኛ ብርሃን ነው፣ ከብርሃኑም የተነሳ ደስ ይለናል፤ ሐሴትም እናደርጋለን፣ የተቀበልነው፣ በስሙ የምናምን እኛ ከእግዚአብሔር ተወልደናልና፤ የእግዚአብሔርም ልጆች ሆነናልና፡፡ ከማይጠፋ ዘር ዳግመኛ ተወልደናልና የእግዚአብሔር ወራሾቹ ሆነናል፤ እንደባለጠግነቱ መጠንም ጸጋውንና ክብሩን እንወርሳለን፡፡ 1ኛ ጴጥ 1፣23 ሮሜ 8፣17፡፡

. . . ይቀጥላል . . .
ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ!





መዳንና በጎ ምግባራት በመጀመሪያይቱ የቅዱስ ዮሐንስ መልዕክት



ምዕራፍ ሦስት (ክፍል ሦስት)
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረውን ትምህርት ከወንጌል ላይ ልብ ብለን ብናስተውልና ብንመረምር ለበጎ ምግባራትና  በሥራ ለሚገለጥ ክርስቲያናዊ ሕይወት የሰጠውን ልዩ ትኩረት እንገነዘባለን፡፡ ይህንን መነሻ አድርጎ ነው ቅዱስ ዮሐንስም በመልዕክቱ ስለበጎ ምግባራት ትኩረት ሰጥቶ የጻፈልን፡፡ ‘‘ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ የሚረግሟችሁን መርቁ፤ ለሚጠሏችሁም መልካም አድርጉ፤ ስለሚበድሏችሁና ስለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ፡፡ በሰማያት ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ፤ እርሱ ለክፉዎችና ለደጎች ፀሐይን ያወጣልና፣ ለጻድቃንና ለኀጥአንም ዝናምን ያዘንማልና፡፡ የሚወዷችሁን ብትወዱማ ዋጋችሁ ምንድን ነው? እንደዚህማ ቀራጮችስ ያደርጉ የለምን? ወንድሞቻችሁን ብቻ እጅ ብትነሡ ምን ብልጫ ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ይህንኑ ያደርጉ የለምን? እንግዲህ ሰማያዊው አባታችሁ ፍጹም እንደሆነ እናንተም ፍጹማን ሁኑ፡፡’’ ማቴ 5፣44-48፡፡ ሰማያዊው አባታችን በምንድን ነው ፍጹም የሆነው? በሥራው ነው፡፡ እኛም ደግሞ ልጆቹ እንሆን ዘንድ በሥራችንና  በተቀደሰው ኑሯችን ፍጹማን ልንሆን ተጠርተናል፡፡ የተጠራንለት ክርስቲያናዊ ሕይወታችን በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል ብለን የምንተወው ብቻ ሳይሆን በዕለት ተዕለት ኑሯችን ከቀራጮችና ከአሕዛብ የሚበልጥ የተቀደሰ ሥራን የምንሠራበት በተግባር የተፈተነ ሕይወትም ጭምር ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ በእምነት የእግዚአብሔር ልጆች እንደምንሆን እንደሚነግረን ሁሉ (ዮሐ 1፣12) በበጎ ምግባራትም የእግዚአብሔር ልጆች እንደምንሆን ይነግረናል፡፡ (ማቴ 5፣45)፡፡ ካላመንን የእግዚአብሔር ልጆች መሆን እንደማንችል ሁሉ በጎ ምግባራትን ገንዘብ ማድረግ ካልቻልንም የእግዚአብሔር ልጆች ልንሆን አንችልም፡፡ ክርስትና የፍጹምነት ሕግ ነው፤ የሰማዩ አባታችንን የምንመስልበት ፍጹምነት፡፡ ይህ ፍጹምነት ደግሞ ተከፍሎ የለበትም፡፡ በእምነታችን ፍጹማን እንድንሆን የሚጠበቅብንን ያህል በበጎ ምግባራትና  በመንፈሳዊ ተግባራትም ፍጹማን እንድንሆንም ተጠርተናል፡፡ ‘‘ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና ነቅታችሁ ኑሩ፤ ኢየሱስ ክርስቶስም ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ፡፡ እንደሚታዘዙ ልጆች ባለማወቃችሁ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ክፉ ምኞት አትከተሉ፡፡ ነገር ግን የጠራችሁ ቅዱስ እንደሆነ እንዲሁ እናንተም በአካሄዳችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፡፡ እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ የሚል ተጽፏልና፡፡ ለሰው ፊትም ሳያደላ በእያንዳንዱ ላይ እንደ ሥራው የሚፈርድ አብን የምትጠሩት ከሆነ፣ በሕይወታችሁ ዘመን ሁሉ በፍርሐት ኑሩ፡፡’’ 1ኛ ጴጥ 1፣13-17፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረን እውነት ይህ ነው፡፡ ስለእምነት ብቻ ሳይሆን በእምነታችን ውስጥ ስለምንኖረውም የተቀደሰ ሕይወትና ኑሮ፡፡ እግዚአብሔር  ባለማመናችን የሚፈርድብን እንደሆነ እንደሚነግረን ሁሉ በክፉ ሥራችንም ላይ እንደሚፈርድም ደግሞ ይነግረናል፡፡ ከእግዚአብሔር የምንቀበለው ብድራታችን በእምነታችን የምንቀበለው እንደሆነ የሚነግረንን ያህል በበጎ ሥራችንና ምግባራችን እንደምንቀበልም ደግሞ ይነግረናል፡፡ ስለሆነም በእምነት እንደምንጸድቅ ሁሉ በበጎ ምግባራችንና ሥራችንም እንጸድቃለን፡፡ ሰው በእምነት ብቻ ሳይኾን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችኹያዕ 2፣24 ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ነው፡፡ ከዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ደግሞ ፈቀቅ ልንል ስለማይቻለን በመዳን ሕይወት ውስጥ በጎ ምግባራት ያላቸውን ድርሻ ቸል ሳንል እናስተምራለን፣ በዚህም ደግሞ እንጸናለን፡፡
ቁ. 22-24 ‘‘ትእዛዙን እንጠብቃለንና፤ በፊቱም ደስ የሚያሰኘውን እንሠራለንና፡፡ ትእዛዙም ይህቺ ናት፤ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናምን ዘንድ፣ ትእዛዙንም እንደሰጠን እርስ በርሳችን እንዋደድ ዘንድ፡፡ ትእዛዙን የሚጠብቅም በእርሱ ይኖራል፤ እርሱም በእርሱ ያድራል፤ በዚህም ከእኛ ጋር እንደሚኖር ከሰጠን ከመንፈሱ እናውቃለን፡፡’’ ክርስትና በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን አንደሆነ ሁሉ ትእዛዙን መጠበቅና በፊቱም ደስ የሚያሰኘውን መሥራትም እንደሆነ ደግሞ ተጽፎልናል፡፡ ትእዛዙን መጠበቅ በክርስቶስ መኖር ነው፣ በጎ ምግባራትን ማድረግ በእርሱ መኖር ነው፣ በዚህም ደግሞ እርሱ በእኛ ውስጥ ይኖራል፡፡ ‘‘ትእዛዙን የሚጠብቅም በእርሱ ይኖራል፤ እርሱም በእርሱ ያድራል፤ በዚህም ከእኛ ጋር እንደሚኖር . . . ’’ በቅዳሴያችንም ላይ እንደተገለጸው እግዚአብሔር አምላካችን ለመንገዱ ፍለጋ የለውም፡፡ ወደ ክርስቶስ ኢየሱስ የምንመጣባቸውና የምንደርስባቸው መንፈሳዊ የሚሆኑ ብዙ መንገዶች አሉልን፡፡ ከእነዚህ መንፈሳዊ ፍለጋዎች መካከል በክርስቶስ ኢየሱስ ማመን አንደኛው ነው፡፡ ክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ፣ ስለእኛ ስለሰዎች፤ ስለመዳናችንም ሰው እንደሆነና መከራን እንደተቀበለ ማመን ያስፈልገናል፡፡ ስለዚህም ነው ‘‘እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም’’ ሲል ክብር ይግባውና እርሱ ራሱ በቃሉ የነገረን፡፡ ዮሐ 14፣6፡፡ በክርስቶስ ለምናምን ሁሉ ወደአብና ወደሕይወት የምንደርስበት መንገዳችን እርሱ ነው፡፡ በክርስቶስ የማያምን ወደ አብ ሊገባና ወደ ሕይወት ሊደርስ አይቻለውምና፡፡  ‘‘በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና’’ ተበሎ እንደተጻፈ በእግዚአብሔር ልጅ ላይ የሚኖረን እምነት ወደ መዳንና ወደ ዘለዓለም ሕይወት ከምንደርስባቸው መንገዶች መካከል አንደኛው ነው፡፡
በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ያለን እምነት ወደ አብ የምንመጣበት መንገድ ቢሆንም አምነን ብቻ አንቀመጥም፤ ባመንነው እንጸናለን፣ ላመንነው እንኖራለን፣ እንታዘዛለንም እንጂ፡፡ እምነት አንደኛው የመዳን መንገድ እንደመሆኑ መጠን ይህን መንገድ የምንጠብቀውን ያህል በጎ ምግባራትም እንደእምነት ሁሉ የመዳን መንገዶች ናቸውና የእምነትን ያህል እንዲሁ ደግሞ እንጠብቃቸዋለን፡፡ የመዳን መንገድ ሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱት መንገዶች መካከል ብንመለከት ጥምቀትንና ቁርባንን እናገኛለን፡፡ ‘‘ዳግመኛ ከውኃና ከመመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግስት ሊገባ አይችልም፡፡’’ ዮሐ 3፣5፡፡ እዚህ ላይ የምናየው እምነት ወደ እግዚአብሔር መንግስት የምንገባበት መንገድ ቢሆንም አምነናል ብለን ከመጠመቅ መከልከል አለመቻላችንን ነው፡፡ ለመዳን እምነት የሚያስፈልገውን ያህል ጥምቀትም እንዲሁ አስፈላጊ ነው፡፡ ከውኃና ከመመንፈስ ቅዱስ በጥምቀት መወለድ ካልቻልን ወደ እግዚአብሔር መንግስት እንደማንገባ በማያሻማ ቃል ተቀምጦልናል፡፡ በሌላም በኩል ‘‘እውነት እውነት እላችኋለሁ የሰውን ልጅ(የክርስቶስን) ሥጋ ካልበላችሁ፣ ደሙንም ካልጠጣችሁ የዘለዓለም ሕይወት የላችሁም፡፡ ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው፤ እኔም በኋለኛይቱ ቀን አስነሳዋለሁ፡፡’’ ዮሐ 6፣ 53-54፡፡ ተብሎ ስለተጻፈ ይህም ወደ ዘለዓለም ሕይወት የምንደርስበት ሌላኛው መንገድ ነው፡፡ ያለክርስቶስ ሥጋና ደም የዘለዓለም  ሕይወት እንደሌለ ክብር ይግባውና እርሱ ራሱ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዘለዓለም ሕይወት የላችሁም ብሎ በማያሻማ ቃል አስቀምጦልናል፡፡ እኛም ደግሞ ለቃሉ እንታዘዛለን እንጂ በቃሉ ላይ አንዳች ልናደርግ አንችልም፡፡ የዘለዓለም ሕይወት አንዲኖረን የክርስቶስን ሥጋውን እንበላለን፣ ደሙንም እንጠጣለን እንጂ ማመናችን ወይም ሌላ በጎ ምግባር ማድረጋችን በቂ ነው ብለን ራሳችንን ከክርስቶስ ሥጋና ደም  አናርቅም፡፡ በ1ኛ ዮሐ 14-15 ላይ ደግሞ ‘‘እኛ ግን ከሞት ወደ ሕይወት እንደተሻገርን እናውቃለን፣ ባልንጀራችንን እንወዳለንና፤ ባልንጀራውን የማይወድ ግን በጨለማ ይኖራል፡፡ ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳይ የሆነም ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት በእርሱ እንደማይኖር ታውቃላችሁ፡፡’’ ተብሎ ተጽፎልናል፡፡ ይህም የሚያሳየን የዘለዓለምን ሕይወት የምንወርሰው በእምነት፣ በጥምቀት፣ የክርስቶስን ሥጋና ደም በመቀበል፤ እንዲሁም ደግሞ በበጎ ምግባራትም ጭምር መሆኑን ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ነውና እውነት ነው፤ የተጻፈልንን ሁሉንም ደግሞ እናምናለን እንቀበላለንም፡፡ አንዱን ብቻ ነጥለን ይዘን ከሌላኛው የምናስበልጥበት ምንም ምክንያት ሊኖረን አይችልም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ስለእምነት፣ ስለጸጋ፣ ስለጥምቀት፣ ስለ ክርስቶስ ሥጋና ደም፣ ስለ በጎ ምግባራት . . . የተጻፉልን  ሁሉ እውነተኛ የእግዚአብሔር ቃላት እንደሆኑ እናምናለን፣ እንቀበላለንም፡፡ ሁሉም ከእግዚአብሔር የወጡ እውነተኛ ቃላት ናቸውና ለሁሉም እኩል እንገዛለን፤ እንታዘዛለንም፡፡ በፍርድ ቀን በስሙ ስለማመናችን የምንጠየቀውን ያህል በስሙ ስለመታዘዛችንና በፊቱም ደስ የሚያሰኘውን ስለመሥራታችንም እንጠየቃለን፡፡ በሉቃ 16፣19-31 የምናነበው የድሃው አልዓዛርና የሀብታሙ ሰው ታሪክ የሚነግረን ምንድን ነው? ስለ እምነት ነውን? አይደለም፡፡ ስለበጎ ሥራና መንፈሳዊ ምግባራት እንጂ፡፡ ሀብታሙ ሰው ስለማያምን ነው ወደ ሲዖል የተጣለው? አይደለም፡፡ ስለማመኑማ በሲዖል ወስጥ ሆኖ አብርሃምን በሩቅ ሆኖ እንዳየውና እንደለየው፣ በእቅፉ ያለው ድሃው አልዓዛርንም ጣቱን በውሀ ነክሮ ያቀዘቅዘው ዘንድ እንዲልክለት ለምኖታል፡፡ በእምነት ያልሆነ ሰው አብርሃምን ሊያውቀው አይችልምና፡፡ በህግና በሙሴ፣ በነቢያትም የተጻፈውን ያውቃል፣ በእስራኤልም አምላክ በእግዚአብሔር ያምናል፡፡ ታዲያ አልዓዛር በአብርሃም እቅፍ ሲሆን ሀብታሙ ሰው እንዴት ወደ ሲዖል ሊጣል ቻለ? ስለ እምነት ነውን? አይደለም፡፡ ስለ እምነት ሳይሆን ስለበጎ ምግባራት ነው፡፡ ሀብታሙ ሰው በጎ ምግባር ስላልነበረው፣ ከክፉ ሥራውም የተነሳ በቅርቡ ለነበረው ድሃ ለአልዓዛር ምህረትን ሊያደርግለትና ሊራራለት ስላልቻለ ስለክፉ ሥራው ተቀጥቷል፡፡ መዳን የእምነት ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ ለዘለዓለም ሕይወት በሚኖረን ዝግጅት ውስጥ ግን አንደኛው አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ በእምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘትና ወደ እርሱም መቅረብ እንደሚቻል እንደተጻፈ ሁሉ በበጎ ምግባራትና በመልካም ሥራዎቻችንም እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘትና ወደ እርሱም መቅረብ እንደምንችል እንዲሁ ደግሞ ተጽፏል፡፡ ስለሆነም ኦርቶዶክሳዊው ትምህርት አንደኛውን አብልጦ ሌላኛውን የሚያሳንስ ሳይሆን ሁሉንም በእኩል የሚቀበልና ሁሉንም ገንዘብ ለማድረግ በእኩል የሚተጋ ነው፡፡ሐሔር ሐ
. . . ይቀጥላል . . .
ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ!