Tuesday, December 6, 2016

ነገረ ክርስቶስ በውዳሴ ማርያም



የጌታችንና መድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የመንግሥቱ ወንጌል/የምሥራቹ በአራት ወንጌላውያን ተጽፎ በሐዲስ ኪዳን ውስጥ ታላቅ ስፍራን ይዞ እናገኘዋለን፡፡ ወንጌል ማለት የምስራች ማለት ሲሆን የአምላክ ሰውን መውደድና ሰዎችን ሁሉ ለመንግሥቱ የተገቡ ይሆኑ ዘንድ ሰዎችን በሚመስል ማንነት በደካማ ሥጋ ውስጥ ራሱን መግለጡንና ሰዎችን ሁሉ በእውነተኛ ፍቅርና መውደድ መፈለጉን ለሰዎች ሁሉ የሚነግር ታላቅ ዜና ነው፡፡ ይህ ታላቅ ዜና የጌታችንና መድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደቱን፣ ስደቱን፣ ዕድገቱን፣ ትምህርቱን፣ ገቢረ ተአምራቱን፣ ለሰዎች ያደረገውን ርህራሄና ቸርነቱን፣ የተቀደሰ ኑሮውንና አርዓያነቱን፣ መከራውንና ስቅለቱን፣ ሞቱንና ትንሣኤውን፣ ዕርገቱንና ዳግም ምጽዓቱን . . . ይነግረናል፡፡ የጌታችን ወንጌል በአራት ወንጌላውያን ቢጻፍም የሚያወራው ግን ሰው ሆኖ ስለተገለጠው አምላክ ስለቤዛችን፤ መሲህ ሆኖ ሊያድነን ስለመጣውና በምድር ላይ ስለተመላለሰው ስለናዝሬቱ ኢየሱስ ነው፡፡ ምንም እንኳን ወንጌሉ በአራት ወንጌላውያን ቢጻፍና ስለጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቢያወራም በጸሐፊዎቹ ስም የማቴዎስ፣ የማርቆስ፣ የሉቃስና የዮሐንስ ወንጌል ተብሎ ይጠራል፡፡ ክርስትና የቅዱሳንን ተጋድሎና ሱታፌ ያከብራልና ታሪኩና ትምህርቱ የጌታችንና መድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቢሆንም መታሰቢያነቱን ግን ለጸሐፊዎቹ ሰጥቷል፤ ጸሐፊዎቹ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከታሪኩ ጋር የተቀደሰ ግንኙነት/ሱታፌ ነበራቸውና፡፡ በውዳሴ ማርያም ውስጥም ተመሳሳይ ሁኔታን እናስተውላለን፤ አብዛኛው የምስጋናው ክፍል የጌታችንና መድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋዌ/ሰው መሆን የሚያነሳና የሚያመሰግን ቢሆንም መታሰቢያነቱ ግን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ለሆነባትና የተቀደሰ ሥጋዋን ወስዶ ማደሪያው ላደረጋት ለተቀደሰች እናቱ ለእመቤታችን ለድንግል ማርያም እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ውዳሴ ማርያም የእመቤታችን መታሰቢያ ቢሆንም የክርስቶስ የሥጋዌው ምስጋና ነው፡፡ የጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆንና ዓለሙን ሁሉ መውደድ፣ የተቀደሰ ፍለጋውና ቤዛነቱ በሚገርም ጥበብ፣ በድንቅ ምሥጢር፣ በመንፈሳዊ ቃላት በውዳሴ ማርያም ውስጥ ተገልጾ እናነበዋለን፡፡ 
የሰኞ ውዳሴ ማርያም
ጌታ ልቡ ያዘነና የተከዘ አዳምን ነፃ ያወጣውና ወደ ቀድሞ ቦታው ይመልሰው ዘንድ ወደደ፡፡
አዳም ከእግዚአብሔር ህብረት፣ ከእረፍት ስፍራው ከገነት ተለይቷልና በልቡ አዝኗል፤ ተክዟልም፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ተገልጦ መርገሙን እስከሚሽርለትና በደሙ ቤዛነት እዳውን ከፍሎ ነጻ እስከሚያወጣው ድረስ በሲዖል ውስጥ በስቃይ ኖሯል፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላ ግን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምንና ልጆቹን ወደቀደመ ሥፍራችን ወደ ክብሩ መንግስት ሊያፈልሰን ፈቃዱ ሆኗል፡፡ እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኀጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን። እንዲል ቆላ 113-14፡፡
ከድንግል ያለወንድ ዘር በሥጋ ተወለደና አዳነን፡፡ ከይሲ ዲያብሎስ ያሳታት ሔዋንን እግዚአብር ምጥሽንና ጻርሽን አበዛዋለሁ ብሎ ፈረደባት፣ ሰውን ወደደና ነጻ አደረጋት፡፡
የአዳምን ዕዳ ከፍሎ ከፍርድ የሚያወጣውና የሚታደገው ወገን/አካል ስላልነበረ እራሱ እግዚአብሔር አዳምን ሊያድነውና ቤዛ ሊሆነው ወደደ፡፡ አዳም ከበደሉ የተነሳ እግዚአብሔርን ቢያሳዝነውም የተበደለው እግዚአብሔር ለአዳም ካሳውን እራሱ ከፍሎለት እራሱ ታረቀው፡፡ ይኸውም ደግሞ ከራሱ ከእግዚአብሔር ምህረትና ርህራሄ የተነሳ እንጂ ከአዳም ከሆነው በጎነትና መልካምነት የተነሳ አይደለም፡፡ ነገር ግን፥ የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደዱ በተገለጠ ጊዜ፥ እንደ ምሕረቱ መጠን ለዐዲስ ልደት በሚኾነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም፡፡ ቲቶ 3፣4-5፡፡ በዲያብሎስ ክፉ ምክር ያጣነውን የእግዚአብሔር መንግስት ዳግመኛ እንገባበት ዘንድ እርሱ እግዚአብሔር ባወቀ፤ እንደምክሩ ታላቅነት መጠን ነጻ አደረገን፡፡ ሔዋንን የዲያብሎስ ምክር ቢጎዳትም በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሆነው የእግዚአብሔር ምክር ግን ለዘለዓለም ጠቀማት፡፡ እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥ በሕይወታቸውም ዅሉ ስለሞት ፍርሀት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ዅሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ።ዕብ 2፣14-15፡፡
ነቢዩ ኢሳይያስ በመንፈስ ቅዱስ የአማኑኤልን ምስጢር አየ ስለዚህም ሕፃን ተወለደልን ወልድም ተሰጠን ብሎ አሰምቶ ተናገረ፡፡
ሕፃን ተወልዶልናልና፣ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፣ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘለዓለም አባት፣ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል፡፡ኢሳ 9፣6-7፡፡ ኢሳይያስ የጌታችንን መወለድ በመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ ትንቢት ተናግሯል፡፡ የሚወለደው ህፃን ደግሞ ዓለሙን ሁሉ የሚዋጅ ብርቱ መድኃኒት ነው፡፡ ኢሳይያስም ብቻ ሳይሆን ካህኑ ዘካርያስም እንዲህ ሲል ስለጌታችን ቤዛነት ትንቢት ተናግሯል፡- የእስራኤል ጌታ አምላክ ይባረክ፥ ጐብኝቶ ለሕዝቡ ቤዛ አድርጓልና፤ ከጥንት ዠምሮ በነበሩት በቅዱሳን ነቢያት አፍ እንደ ተናገረ፥ በብላቴናው በዳዊት ቤት የመዳን ቀንድን አስነሥቶልናል፤ ማዳኑም ከወደረኛዎቻችንና ከሚጠሉን ዅሉ እጅ ነው፤ እንደዚህ ለአባቶቻችን ምሕረት አደረገ፤ ለአባታችን ለአብርሃምም የማለውን መሐላውን ቅዱሱን ኪዳን ዐሰበ፤ በእርሱም ከጠላቶቻችን እጅ ድነን በዘመናችን ዅሉ ያለፍርሐት በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ እንድናገለግለው ሰጠን።ሉቃ 1፣68-75፡፡

ሰው ሆይ ፈጽመህ ደስ ይበልህ እግዚአብሔር ዓለሙን ወዶታልና አንድ ልጁንም የሚያምንበት ሁሉ እስከ ዘለዓለም ፈጽሞ ይድን ዘንድ አሳልፎ ሰጥቶናልና ልዑል ክንዱን ሰደደልን፡፡
እግዚአብሔር ዓለሙ ሁሉ ይድን ዘንድ አንድያ ልጁን ቤዛና መድኃኒት አድርጎ ሰጥቷል፡፡ በእርሱ የሚያምን ዅሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና።
ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና።ዮሐ 3፣16-17፡፡ አሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ለዓለም ሁሉ መዳን ሆኗል፤ ከእርሱ በቀር እንድንበት ዘንድ የሚቻለን ሌላ የመዳን መንገድ የለንም፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን የሚሆነው የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለዋጋ ለሰው ሁሉ ቀርቧልና፡- መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና። ሐዋ 4፣12፡፡ መዳናችንም በሕግ ሥራ ወይም ከሰው ወገን በሚገኝ በጎነት የሚሆን ሳይሆን በጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ ፈሳሽነት የሚሆን መዳንና ጽድቅ ነው፡፡ አኹን ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለሕግ ተገልጧል፥ እርሱም፥ ለሚያምኑ ዅሉ የኾነ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው፡፡ሮሜ 3፣21-22፡፡

የነበረው የሚኖረው፤ የመጣው ዳግመኛም የሚመጣው ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ያለመለወጥ ፍጹም ሰው ሆነ፡፡ አንዱ ወልድ በሥራው ሁሉ አልተለየም እግዚአብሔር ቃል መለኮት አንድ ነው እንጂ፡፡
እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ሰው ሆኖ በሥጋ ተገልጧል፡፡ ዮሐ 1፣14፡፡ የእግዚአብሔር ማዳኑ አንዲት ናትና የዳንንባት የወልድ ማዳኑ የአብና የመንፈስ ቅዱስም ናት፡፡ አብ እንዲሠራ እንዲሁ ደግሞ ወልድም ይሠራልና፡፡ አባቴ እስከዛሬ ይሠራል፤ እኔም ደግሞ እሠራለሁ እንዲል ዮሐ 5፣17፡፡ አብ ከወልድ የተለየ ማዳን እንደሌለው ሁሉ ወልድም ከአብ የለየ ማዳን የለውም፡፡ ወልድ አዳነን ስንል አብና መንፈስ ቅዱስም አዳነን እንላለንና፣ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ እግዚአብሔር ብለን እናምናለንና እግዚአብሔር በአንድነቱ አዳነን፡፡ አንዱ ወልድ በሥራው ሁሉ አልተለየም እግዚአብሔር ቃል መለኮት አንድ ነውና የሚለው ይህንን ነው፡፡ በእኔ የሚኖረው አብ እርሱ ሥራውን ይሠራል፡፡ ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ ዮሐ 14፣10፡፡   

የነቢያት ሐገራቸው ቤተልሔም ሆይ ደስ ይበልሽ፤ ሁለተኛው አዳም ክርስቶስ በአንቺ ዘንድ ተወልዷልና፤ የቀድሞውን ሰው አዳምን ከምድር (ከሲኦል) ወደ ገነት ይመልሰው ዘንድ፤ አዳም ሆይ መሬት ነበርክና ወደ መሬት ትመለሳለህ ብሎ የፈረደበትንም የሞት ፍርድ ያጠፋለት ዘንድ፤ ብዙ ኃጢአት ባለችበት የእግዚአብሔር ጸጋ ትበዛለች፡፡
ቤተልሔም የደስታ ማደሪያ ናት መድኅን ክርስቶስ ተወልዶባታልና፤ ይኸውም ደግሞ ለዓለሙ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ ነው፡፡ አንቺም ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ፥ አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትኾኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ፤ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ዠምሮ ከዘለዓለም የኾነ፥ በእስራኤልም ላይ ገዢ የሚኾን ይወጣልኛል። ሚክ 5፣2፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ቤተ ልሔም ትባላለች፤ ለዓለሙ ሁሉ ደስታ የሚሆን መድኅን ክርስቶስ በማኅጸኗ አድሯልና፡፡ አንድም ደግሞ ቤተ ልሔም የእንጀራ ቤት ማለት ነው፤ እመቤታችንም የሕይወት እንጀራ የሚሆን የኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ ናትና ቤተ ልሔም ትባላለች፡፡ ዮሐ 6፣48፡፡ ሞት በአዳም በኩል ወደ ዓለም ቢገባም በክርስቶስ በኩል ደግሞ ለዓለሙ ሁሉ ሕይወትና መዳን ሆኗል፡፡ የአዳም መተላለፍ በክርስቶስ መታዘዝ ተሽሯልና፡፡ ነገር ግን፥ በአዳም መተላለፍ ምሳሌ ኀጢአትን ባልሠሩት ላይ እንኳ፥ ከአዳም ዠምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ሞት ነገሠ፤ አዳም ይመጣ ዘንድ ላለው ለእርሱ አምሳሉ ነውና። ነገር ግን፥ ስጦታው እንደ በደሉ መጠን እንደዚያው አይደለም፤ ባንድ ሰው በደል ብዙዎቹ ሞተዋልና፥ ነገር ግን፥የእግዚአብሔር ጸጋና በአንድ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የኾነው ስጦታ ከዚያ ይልቅ ለብዙዎች በዛ። አንድ ሰውም ኀጢአትን በማድረጉ እንደኾነው መጠን እንደዚያው ስጦታው አይደለም፤ ፍርድ ከአንድ ሰው ለኵነኔ መጥቷልና፥ ስጦታው ግን በብዙ በደል ለማጽደቅ መጣ።ሮሜ 5፣14-16፡፡ ብዙ ኃጢአት ባለበት ዓለም ውስጥ የእግዚአብሔር ጽድቁ ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለሙ ሁሉ ጸጋውን አበዛ፡፡ ከጸጋው ብዛት የተነሳም ወደ እግዚአብሔር መንግስት ቀረብን፡፡ የጸጋው ኃይልና ታላቅነት ከአዳም በደል የበለጠና የበረታ ስለሆነ ቅዱስ ኤፍሬም ብዙ ኃጢአት ባለችበት የእግዚአብሔር ጸጋ ትበዛለች፡፡ብሎ ገለጸው፡፡ ዳሩ ግን ኀጢአት በበዛበት፥ ኀጢአት በሞት እንደነገሠ፥ እንዲሁ ደግሞ ጸጋ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተነሣ በጽድቅ ምክንያት ለዘለዓለም ሕይወት ይነግሥ ዘንድ፥ ጸጋ ከመጠን ይልቅ በለጠ።ሮሜ 5፣20-21፡፡

የሰው ሁሉ ሰውነት ፈጽሞ ደስ ይላታል፡፡ በሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በምድርም ሰላም ለሰውም እርሱ በሚፈቅደው እያሉ አሰምተው ንጉስ ክርስቶስን ከመላእክት ጋር ያመሰግኑታል፡፡ የቀድሞውን እርግማን አጥፍቷልና፤የጠላትን ምክሩን አፈረሰበት ለአዳምና ለሔዋን የእዳ ደብዳቤአቸውን ቀደደላቸው፡፡ በዳዊት ሀገር የተወለደ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምንና ሄዋንን ነጻ አደረጋቸው፡፡
የጌታችን ልደት ለዓለሙ ሁሉ ደስታ ነውና መላእክቱ ከእረኞቹ ጋራ በደስታ እግዚአብሔርን አመስግነውታል፡፡ ሉቃ 2፣8-15፡፡ እውነተኛው ደስታችን ከክርስቶስ ሥራ፣ ከማዳኑም ኃይል የተገኘ ነውና፡፡ የቀድሞውን እርግማን ያጠፋ ዘንድም ክርስቶስ ራሱን ለመስቀል ሞት አሳልፎ ሰጥቶልናል፡፡ ክርስቶስ ስለእኛ እርግማን ኾኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን፡፡   ገላ 3፣13፡፡ ይህም ደግሞ የሆነው በራሱ በእግዚአብሔር ሐሳብ ነው፡፡ ሐሳቡም የጠላት ዲያብሎስን ምክርና ክፉ ሐሳቡን አፍርሶታል፣ ሽሮታልም፤ የምንከሰስበትን የዕዳችንንም ክስ አጥፍቶልናል፡፡ በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው፡፡እንዲል ቆላ 2፣14፡፡ የክርስቶስ ቤዛነት፣ የመስቀሉ ሥራ አዳምንና ልጆቹን ሁሉ ነጻ አወጣን፡፡ በዚህም የተነሳ ከምንከሰስበት የአዳም መተላለፍና ዕዳ ነጻ ሆነናል፡፡ በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን፡፡ተብሎ ተጽፏልና ገላ 5፣1፡፡

በዚህ ዓለም ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ የምታበራ እውነተኛ ብርሃን ስለ ሰው ፍቅር ወደ ዓለም የመጣህ ፍጥረት ሁሉ በመምጣትህ ደስ አለው አዳምን ከስህተት አድነኸዋልና ሄዋንንም ከሞት ጻዕረኝነት ነጻ አድርገሃታልና የምንወለድበትን መንፈስ (ረቂቁን ልደት) ሰጠኸን ከመላእክት ጋርም አመሰገንህ፡፡
ለሰው ዅሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር። በዓለም ነበረ፥ ዓለሙም በእርሱ ኾነ፥ ዓለሙም አላወቀውም። የእርሱ ወደኾነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ዅሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይኾኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፡፡ዮሐ 1፣9-12፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የነፍሳችን ጨለማ የራቀበት እውነተኛ ብርሃን ነው፣ ከብርሃኑም የተነሳ ደስ ይለናል፤ ሐሴትም እናደርጋለን፣ የተቀበልነው፣ በስሙ የምናምን እኛ ከእግዚአብሔር ተወልደናልና፤ የእግዚአብሔርም ልጆች ሆነናልና፡፡ ከማይጠፋ ዘር ዳግመኛ ተወልደናልና የእግዚአብሔር ወራሾቹ ሆነናል፤ እንደባለጠግነቱ መጠንም ጸጋውንና ክብሩን እንወርሳለን፡፡ 1ኛ ጴጥ 1፣23 ሮሜ 8፣17፡፡

. . . ይቀጥላል . . .
ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ!





No comments:

Post a Comment