ምዕራፍ ሦስት (ክፍል ሦስት)
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረውን ትምህርት ከወንጌል ላይ ልብ ብለን ብናስተውልና ብንመረምር
ለበጎ ምግባራትና በሥራ ለሚገለጥ ክርስቲያናዊ ሕይወት የሰጠውን ልዩ
ትኩረት እንገነዘባለን፡፡ ይህንን መነሻ አድርጎ ነው ቅዱስ ዮሐንስም በመልዕክቱ ስለበጎ ምግባራት ትኩረት ሰጥቶ የጻፈልን፡፡ ‘‘ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤
የሚረግሟችሁን መርቁ፤ ለሚጠሏችሁም መልካም አድርጉ፤ ስለሚበድሏችሁና ስለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ፡፡ በሰማያት ላለው አባታችሁ ልጆች
ትሆኑ ዘንድ፤ እርሱ ለክፉዎችና ለደጎች ፀሐይን ያወጣልና፣ ለጻድቃንና ለኀጥአንም ዝናምን ያዘንማልና፡፡ የሚወዷችሁን ብትወዱማ ዋጋችሁ ምንድን ነው? እንደዚህማ ቀራጮችስ ያደርጉ የለምን? ወንድሞቻችሁን ብቻ እጅ ብትነሡ
ምን ብልጫ ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ይህንኑ ያደርጉ የለምን? እንግዲህ ሰማያዊው አባታችሁ ፍጹም እንደሆነ እናንተም ፍጹማን ሁኑ፡፡’’
ማቴ 5፣44-48፡፡ ሰማያዊው አባታችን በምንድን ነው ፍጹም የሆነው? በሥራው ነው፡፡ እኛም ደግሞ ልጆቹ
እንሆን ዘንድ በሥራችንና በተቀደሰው ኑሯችን ፍጹማን ልንሆን ተጠርተናል፡፡
የተጠራንለት ክርስቲያናዊ ሕይወታችን በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል ብለን የምንተወው ብቻ ሳይሆን በዕለት ተዕለት ኑሯችን ከቀራጮችና
ከአሕዛብ የሚበልጥ የተቀደሰ ሥራን የምንሠራበት በተግባር የተፈተነ ሕይወትም ጭምር ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ በእምነት የእግዚአብሔር ልጆች እንደምንሆን እንደሚነግረን
ሁሉ (ዮሐ 1፣12) በበጎ ምግባራትም የእግዚአብሔር ልጆች እንደምንሆን ይነግረናል፡፡ (ማቴ 5፣45)፡፡ ካላመንን የእግዚአብሔር
ልጆች መሆን እንደማንችል ሁሉ በጎ ምግባራትን ገንዘብ ማድረግ ካልቻልንም የእግዚአብሔር ልጆች ልንሆን አንችልም፡፡ ክርስትና የፍጹምነት
ሕግ ነው፤ የሰማዩ አባታችንን የምንመስልበት ፍጹምነት፡፡ ይህ ፍጹምነት ደግሞ ተከፍሎ የለበትም፡፡ በእምነታችን ፍጹማን እንድንሆን
የሚጠበቅብንን ያህል በበጎ ምግባራትና በመንፈሳዊ ተግባራትም ፍጹማን
እንድንሆንም ተጠርተናል፡፡ ‘‘ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና ነቅታችሁ ኑሩ፤ ኢየሱስ ክርስቶስም ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ
አድርጉ፡፡ እንደሚታዘዙ ልጆች ባለማወቃችሁ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ክፉ ምኞት አትከተሉ፡፡ ነገር ግን የጠራችሁ ቅዱስ እንደሆነ
እንዲሁ እናንተም በአካሄዳችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፡፡ እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ የሚል ተጽፏልና፡፡ ለሰው ፊትም ሳያደላ በእያንዳንዱ
ላይ እንደ ሥራው የሚፈርድ አብን የምትጠሩት ከሆነ፣ በሕይወታችሁ ዘመን ሁሉ በፍርሐት ኑሩ፡፡’’ 1ኛ ጴጥ 1፣13-17፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረን እውነት ይህ ነው፡፡ ስለእምነት ብቻ ሳይሆን በእምነታችን
ውስጥ ስለምንኖረውም የተቀደሰ ሕይወትና ኑሮ፡፡ እግዚአብሔር ባለማመናችን
የሚፈርድብን እንደሆነ እንደሚነግረን ሁሉ በክፉ ሥራችንም ላይ እንደሚፈርድም ደግሞ ይነግረናል፡፡ ከእግዚአብሔር የምንቀበለው ብድራታችን
በእምነታችን የምንቀበለው እንደሆነ የሚነግረንን ያህል በበጎ ሥራችንና ምግባራችን እንደምንቀበልም ደግሞ ይነግረናል፡፡ ስለሆነም
በእምነት እንደምንጸድቅ ሁሉ በበጎ ምግባራችንና ሥራችንም እንጸድቃለን፡፡ “ሰው በእምነት ብቻ ሳይኾን በሥራ
እንዲጸድቅ ታያላችኹ” ያዕ 2፣24 ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት
ነው፡፡ ከዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ደግሞ ፈቀቅ ልንል ስለማይቻለን በመዳን ሕይወት ውስጥ በጎ ምግባራት ያላቸውን ድርሻ ቸል
ሳንል እናስተምራለን፣ በዚህም ደግሞ እንጸናለን፡፡
ቁ. 22-24 ‘‘ትእዛዙን እንጠብቃለንና፤ በፊቱም ደስ የሚያሰኘውን እንሠራለንና፡፡ ትእዛዙም ይህቺ ናት፤
በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናምን ዘንድ፣ ትእዛዙንም እንደሰጠን እርስ በርሳችን እንዋደድ ዘንድ፡፡ ትእዛዙን የሚጠብቅም በእርሱ
ይኖራል፤ እርሱም በእርሱ ያድራል፤ በዚህም ከእኛ ጋር እንደሚኖር ከሰጠን ከመንፈሱ እናውቃለን፡፡’’ ክርስትና በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ
ማመን አንደሆነ ሁሉ ትእዛዙን መጠበቅና በፊቱም ደስ የሚያሰኘውን መሥራትም እንደሆነ ደግሞ ተጽፎልናል፡፡ ትእዛዙን መጠበቅ በክርስቶስ
መኖር ነው፣ በጎ ምግባራትን ማድረግ በእርሱ መኖር ነው፣ በዚህም ደግሞ እርሱ በእኛ ውስጥ ይኖራል፡፡ ‘‘ትእዛዙን የሚጠብቅም በእርሱ
ይኖራል፤ እርሱም በእርሱ ያድራል፤ በዚህም ከእኛ ጋር እንደሚኖር . . . ’’ በቅዳሴያችንም ላይ እንደተገለጸው እግዚአብሔር አምላካችን ለመንገዱ ፍለጋ የለውም፡፡
ወደ ክርስቶስ ኢየሱስ የምንመጣባቸውና የምንደርስባቸው መንፈሳዊ የሚሆኑ ብዙ መንገዶች አሉልን፡፡ ከእነዚህ መንፈሳዊ ፍለጋዎች መካከል
በክርስቶስ ኢየሱስ ማመን አንደኛው ነው፡፡ ክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ፣ ስለእኛ ስለሰዎች፤ ስለመዳናችንም ሰው
እንደሆነና መከራን እንደተቀበለ ማመን ያስፈልገናል፡፡ ስለዚህም ነው ‘‘እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም’’ ሲል
ክብር ይግባውና እርሱ ራሱ በቃሉ የነገረን፡፡ ዮሐ 14፣6፡፡ በክርስቶስ ለምናምን ሁሉ ወደአብና ወደሕይወት የምንደርስበት መንገዳችን
እርሱ ነው፡፡ በክርስቶስ የማያምን ወደ አብ ሊገባና ወደ ሕይወት ሊደርስ አይቻለውምና፡፡ ‘‘በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ
ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና’’ ተበሎ
እንደተጻፈ በእግዚአብሔር ልጅ ላይ የሚኖረን እምነት ወደ መዳንና ወደ ዘለዓለም ሕይወት ከምንደርስባቸው መንገዶች መካከል አንደኛው
ነው፡፡
በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ያለን እምነት ወደ አብ የምንመጣበት መንገድ ቢሆንም
አምነን ብቻ አንቀመጥም፤ ባመንነው እንጸናለን፣ ላመንነው እንኖራለን፣ እንታዘዛለንም እንጂ፡፡ እምነት አንደኛው የመዳን መንገድ
እንደመሆኑ መጠን ይህን መንገድ የምንጠብቀውን ያህል በጎ ምግባራትም እንደእምነት ሁሉ የመዳን መንገዶች ናቸውና የእምነትን ያህል
እንዲሁ ደግሞ እንጠብቃቸዋለን፡፡ የመዳን መንገድ ሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱት መንገዶች መካከል ብንመለከት ጥምቀትንና
ቁርባንን እናገኛለን፡፡ ‘‘ዳግመኛ
ከውኃና ከመመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግስት ሊገባ አይችልም፡፡’’ ዮሐ 3፣5፡፡ እዚህ
ላይ የምናየው እምነት ወደ እግዚአብሔር መንግስት የምንገባበት መንገድ ቢሆንም አምነናል ብለን ከመጠመቅ መከልከል አለመቻላችንን
ነው፡፡ ለመዳን እምነት የሚያስፈልገውን ያህል ጥምቀትም እንዲሁ አስፈላጊ ነው፡፡ ከውኃና ከመመንፈስ ቅዱስ በጥምቀት መወለድ ካልቻልን
ወደ እግዚአብሔር መንግስት እንደማንገባ በማያሻማ ቃል ተቀምጦልናል፡፡ በሌላም በኩል ‘‘እውነት እውነት እላችኋለሁ የሰውን ልጅ(የክርስቶስን) ሥጋ ካልበላችሁ፣
ደሙንም ካልጠጣችሁ የዘለዓለም ሕይወት የላችሁም፡፡ ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው፤ እኔም በኋለኛይቱ
ቀን አስነሳዋለሁ፡፡’’ ዮሐ 6፣ 53-54፡፡ ተብሎ ስለተጻፈ ይህም ወደ ዘለዓለም ሕይወት የምንደርስበት ሌላኛው
መንገድ ነው፡፡ ያለክርስቶስ ሥጋና ደም የዘለዓለም ሕይወት እንደሌለ
ክብር ይግባውና እርሱ ራሱ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዘለዓለም ሕይወት የላችሁም ብሎ በማያሻማ ቃል አስቀምጦልናል፡፡ እኛም
ደግሞ ለቃሉ እንታዘዛለን እንጂ በቃሉ ላይ አንዳች ልናደርግ አንችልም፡፡ የዘለዓለም ሕይወት አንዲኖረን የክርስቶስን ሥጋውን እንበላለን፣
ደሙንም እንጠጣለን እንጂ ማመናችን ወይም ሌላ በጎ ምግባር ማድረጋችን በቂ ነው ብለን ራሳችንን ከክርስቶስ ሥጋና ደም አናርቅም፡፡ በ1ኛ ዮሐ 14-15 ላይ ደግሞ ‘‘እኛ ግን ከሞት ወደ ሕይወት
እንደተሻገርን እናውቃለን፣ ባልንጀራችንን እንወዳለንና፤ ባልንጀራውን የማይወድ ግን በጨለማ ይኖራል፡፡ ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ
ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳይ የሆነም ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት በእርሱ እንደማይኖር ታውቃላችሁ፡፡’’ ተብሎ ተጽፎልናል፡፡ ይህም የሚያሳየን የዘለዓለምን ሕይወት የምንወርሰው በእምነት፣
በጥምቀት፣ የክርስቶስን ሥጋና ደም በመቀበል፤ እንዲሁም ደግሞ በበጎ ምግባራትም ጭምር መሆኑን ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር
ቃል ነውና እውነት ነው፤ የተጻፈልንን ሁሉንም ደግሞ እናምናለን እንቀበላለንም፡፡ አንዱን ብቻ ነጥለን ይዘን ከሌላኛው የምናስበልጥበት
ምንም ምክንያት ሊኖረን አይችልም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ስለእምነት፣ ስለጸጋ፣ ስለጥምቀት፣ ስለ ክርስቶስ ሥጋና ደም፣ ስለ በጎ ምግባራት
. . . የተጻፉልን ሁሉ እውነተኛ የእግዚአብሔር ቃላት እንደሆኑ
እናምናለን፣ እንቀበላለንም፡፡ ሁሉም ከእግዚአብሔር የወጡ እውነተኛ ቃላት ናቸውና ለሁሉም እኩል እንገዛለን፤ እንታዘዛለንም፡፡ በፍርድ
ቀን በስሙ ስለማመናችን የምንጠየቀውን ያህል በስሙ ስለመታዘዛችንና በፊቱም ደስ የሚያሰኘውን ስለመሥራታችንም እንጠየቃለን፡፡ በሉቃ
16፣19-31 የምናነበው የድሃው አልዓዛርና የሀብታሙ ሰው ታሪክ የሚነግረን ምንድን ነው? ስለ እምነት ነውን? አይደለም፡፡ ስለበጎ
ሥራና መንፈሳዊ ምግባራት እንጂ፡፡ ሀብታሙ ሰው ስለማያምን ነው ወደ ሲዖል የተጣለው? አይደለም፡፡ ስለማመኑማ በሲዖል ወስጥ ሆኖ
አብርሃምን በሩቅ ሆኖ እንዳየውና እንደለየው፣ በእቅፉ ያለው ድሃው አልዓዛርንም ጣቱን በውሀ ነክሮ ያቀዘቅዘው ዘንድ እንዲልክለት
ለምኖታል፡፡ በእምነት ያልሆነ ሰው አብርሃምን ሊያውቀው አይችልምና፡፡ በህግና በሙሴ፣ በነቢያትም የተጻፈውን ያውቃል፣ በእስራኤልም
አምላክ በእግዚአብሔር ያምናል፡፡ ታዲያ አልዓዛር በአብርሃም እቅፍ ሲሆን ሀብታሙ ሰው እንዴት ወደ ሲዖል ሊጣል ቻለ? ስለ እምነት
ነውን? አይደለም፡፡ ስለ እምነት ሳይሆን ስለበጎ ምግባራት ነው፡፡ ሀብታሙ ሰው በጎ ምግባር ስላልነበረው፣ ከክፉ ሥራውም የተነሳ
በቅርቡ ለነበረው ድሃ ለአልዓዛር ምህረትን ሊያደርግለትና ሊራራለት ስላልቻለ ስለክፉ ሥራው ተቀጥቷል፡፡ መዳን የእምነት ጉዳይ ብቻ
አይደለም፤ ለዘለዓለም ሕይወት በሚኖረን ዝግጅት ውስጥ ግን አንደኛው አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ በእምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘትና
ወደ እርሱም መቅረብ እንደሚቻል እንደተጻፈ ሁሉ በበጎ ምግባራትና በመልካም ሥራዎቻችንም እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘትና ወደ እርሱም
መቅረብ እንደምንችል እንዲሁ ደግሞ ተጽፏል፡፡ ስለሆነም ኦርቶዶክሳዊው ትምህርት አንደኛውን አብልጦ ሌላኛውን የሚያሳንስ ሳይሆን
ሁሉንም በእኩል የሚቀበልና ሁሉንም ገንዘብ ለማድረግ በእኩል የሚተጋ ነው፡፡
. . . ይቀጥላል . . .
ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ!
No comments:
Post a Comment