Wednesday, November 9, 2016

ኃያላን ለምን ይወድቃሉ? ብርቱዎችስ ለምን ይደክማሉ?



(ክፍል ሦስት)
በአገልግሎቱ ውስጥ ክርስቶስን መስበካቸውን ትተው ራሳቸውን ሲሰብኩ፡- የኦርቶዶክሳዊው አገልግሎት ፍጻሜ ክርስቶስን ማክበርና ነፍሳትን ሁሉ ወደ ክርስቶስ እንዲደርሱ ማገዝ ነው፡፡ “እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ያስፈልጋል” ማለት የማይችል አገልጋይ በአገልግሎቱ እግዚአብሔርን ማክበር ስለማይችል ፍጻሜው እንደ ጅማሬው በመንፈሳዊነትና በጸጋ የሚፈጸም ሊሆን አይችልም፡፡ ዮሐ 3፣30፡፡ ብዙ አገልጋዮች በአገልግሎቱ ታዋቂዎች ከመሆንና ብዙ ተከታዮችን ከማፍራት ባሻገር እግዚአብሔርን መፍራትን ገንዘብ ማድረግና በትህትና መመላለስ የሚሳናቸው ከክርስቶስ ይልቅ ራሳቸውን ስለሚሰብኩና ከሰዎች የሚሆን ክብርን ስለሚሹ ነው፡፡ የአገልጋዮች ዋነኛ አጀንዳ የክርስቶስ መሰበክና ለሰዎች ሁሉ መገለጥ ነው፡፡ ሰዎችን ሁሉ የክርስቶስና አካሉ የምትሆን የቤተ ክርስቲያን እንዲሆኑ መርዳትና ማገዝ እንጂ ለራሳቸው ተከታዮችንና ደጋፊዎችን ማብዛት የእውነተኛ አገልጋዮች መገለጫ አይደለም፡፡ በዚህ ዘመን የምንመለከተው እውነታ ግን አገልጋዮችን በመደገፍና በመከተል ብዙ ምእመናን ቤተ ክርስቲያንን ሲያውኩ ነው፡፡ ከአበው ሐዋርያት፣ ከቅዱሳንም ግን እንዲህ አልተማርንም፡፡ ከሐዋርያት መካከል ክርስቶስን ከመስበክ በቀር ራሱን የሰበከ ማን ነው? ከቅዱሳን አበውስ ስለራሳቸው ክብር ሲሉ የተጣሉና የተከራከሩ እነማን ናቸው? የራሳቸውንስ ክብር የፈለጉ ወዴት አሉ? ከዚህ ይልቅ ግን በሀሰት ሲከሷቸውና ሲያሳድዷቸው ሁሉ ስለጌታችን ፍቅርና ክብር ሲሉ ተሰደዋል፤ መከራንም ተቀብለዋል እንጂ ስለራሳቸው ሲከራከሩና ደጋፊዎችን በማብዛት ክብራቸውንና እውነተኝነታቸውን ለመግለጥ ሲደክሙ አላነበብንም፡፡ ዛሬ ላይ በቤተ ክርስቲያን እየሆነ ያለው ግን እንዲህ አይደለም፡፡ አገልጋዮቻችን ክብርንና ምስጋናን ከላይ ከእግዚአብሔር ሳይሆን ከዚህች ምድር ከሰዎች ዘንድ የሚሹ ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ ደጋፊዎችንና ተከታዮችን ለራሳቸው ስለሚያደርጉ የተለያዩ አገልጋዮችን በሚደግፉና በሚከተሉ መካከል ጸብና ክርክር ሲሆን በየጊዜው እንመለከታለን፡፡ በዚህ ውስጥስ የእግዚአብሔር ክብርና መንፈሳዊነት ስፍራቸው ወዴት አለ? በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የክርስቶስ ተከታዮች እንድንሆን እንጂ ሰዎችን እንድንከተል አልተጠራንም፡፡ ለመንፈስ ቅዱስ ምክርና አሠራር እንድንታዘዝ እንጂ የምንወዳቸውን ሰዎች ፈቃድ እንድንፈጽምና እንድንታዘዝ አልተጠራንም፡፡ በዚህም የተነሳ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ክርስቶስን ሳይሆን ራሳቸውን የሚገልጡ፤ ሰዎችን የክርስቶስ ተከታዮች ሳይሆን የራሳቸው ተከታዮች የሚያደርጉ ብዙ ብርቱዎችና ኃያላን አገልጋዮች እግዚአብሔር ስለሚያዝንባቸው ይወድቃሉ፣ የመንፈሳዊነት ምሳሌ ከመሆንም ይልቅ የጸብና የክርክር መንስኤዎች ይሆናሉ፡፡         
ሌሎችን ብቻ እንጂ ራሳቸውን ማገልገል ሲተዉ፡- አገልጋዮች ለሌሎች የሚፈጽሙት አገልግሎት ለራሳቸውም እንደሚያስፈልጋቸው መዘንጋት የለባቸውም፡፡ መምህርነታቸው ለሚያስተምሯቸው ምእመናን እንጂ በጌታ ፊት እነርሱም እንደሌሎቹ እኩል ተማሪዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ለማስተማር ብቻ ብለው ሳይሆን ለራሳቸውም ለመማር ብለው ሊያጠኑና ቅዱሳት መጻሕፍትንም ቁጭ ብለው ሊማሩ ያስፈልጋቸዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ነው የሚነግረን፡- “አንተ ግን አይሁዳዊ ብትባል በሕግም ብትደገፍ በእግዚአብሔርም ብትመካ፥ ፈቃዱንም ብታውቅ ከሕግም ተምረኽ የሚሻለውን ፈትነኽ ብትወድ፤ በሕግም የዕውቀትና የእውነት መልክ ስለ አለኽ፥ የዕውሮች መሪ፥ በጨለማም ላሉ ብርሃን፥ የሰነፎችም አስተማሪ፥ የሕፃናትም መምህር እንደ ኾንኽ በራስኽ ብትታመን፤ እንግዲህ አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስኽን አታስተምርምን አትስረቅ ብለኽ የምትሰብክ ትሰርቃለኽን አታመንዝር የምትል ታመነዝራለኽን ጣዖትን የምትጸየፍ ቤተ መቅደስን ትዘርፋለኽን በሕግ የምትመካ ሕግን በመተላለፍ እግዚአብሔርን ታሳፍራለኽን በእናንተ ሰበብ የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ መካከል ይሰደባልና፥ ተብሎ እንደ ተጻፈ፡፡” ሮሜ 2፣17-24፡፡ አገልጋይነት የሰነፎች መደበቂያ ዋሻ   አይደለም፡፡ አገልጋዮች ሌሎችን እንደሚያስተምሩት ሁሉ ተቀምጠው ራሳቸውም መማር ያስፈልጋቸዋል፡፡ መማር ያቆመ አገልጋይ በአገልግሎቱ መቀጠል ስለማይቻለው መውደቁ አይቀርም፡፡
አገልግሎቱን በመንፈሳዊነት ከመፈጸም ይልቅ እንደተግባረ ሥጋ ሲቆጥሩት፡- አገልግሎት መንፈሳዊ ነው፡፡ መንፈሳዊ ሳይሆኑ መንፈሳዊውን አገልግሎት የሚፈጽሙ ሁሉ በአገልግሎቱ ውስጥ ራሳቸውን መጥቀም ስለማይችሉ ከጊዜ በኋላ አወዳደቃቸው ታላቅና የከፋ ይሆናል፡፡ አገልግሎት የሚኖሩትና የሚታዘዙት መንፈሳዊነትም ጭምር ነው እንጂ ሥራ አይደለም፡፡ “የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር” 1ኛ ቆሮ 9፣9 ስለተባለና በአገልገሎቱ የተነሳ ገንዘብ ስለምናገኝ አገልግሎት ሥራ እንደሆነ ልናስብ አይገባም፡፡ መንፈሳዊ ሳንሆን ለማገልገል ከሞከርን አገልግሎቱንም፣ በአገልግሎቱ ውስጥ የምንቀበለውንም ገንዘብ አብረን እናጣዋለን፡፡ “እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል።” ዮሐ 4፣24፡፡ እንደተባለ መንፈሳዊውን የእግዚአብሔር አገልግሎት በመንፈስና በእውነት የማይፈጽሙ አገልጋዮች ፍጻሜያቸው ውድቀት ነው፡፡ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ሊሆን የተጠራው የአስቆሮቱ ይሁዳ የተጣለው የተሰጠውን መንፈሳዊ አገልግሎትና ከክርስቶስ የተቀበለውን አደራ በመንፈሳዊነት መጠበቅ ስላልቻለ ነው፡፡ እንዲህ ባይሆንማ ኖሮ ከክርስቶስ አፍ ከመማር የሚበልጥ ምን ዕድል ነበረ? ነገር ግን ከክርስቶስ የተማረውንና ያየውን በመንፈሳዊነት መጠበቅ ስላልቻለ ይሁዳ ፍጻሜው ክፉ ሊሆን ችሏል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደሚነግረንም በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ታላላቅና ኃያላን የነበሩ ሰዎች መንፈሳዊነታቸውን መጠበቅ ባለመቻላቸውና በመንፈስ ማገልገል ስለተሳናቸው አወዳደቃቸው እንደታላቅነታቸው እንዲሁ ታላቅ ሊሆን ችሏል፡፡ ስለሆነም በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ካህን የነበረው አርዮስ፣ ጳጳሳት የነበሩት ንስጥሮስና መቅዶንዮስም ሲወድቁና ሲጣሉ ተመልክተናል፡፡ ዛሬም በዘመናችን የሃይማኖት መምህራን የነበሩ ሰዎች ከኃይማኖት መንገድ ሲወጡና ሥጋዊነት ሲያሸንፋቸው እኛ ምስክሮች ነበርን፡፡ እግዚአብሔር የሚራራልን ለመንፈሳዊነታችን እንጂ ለታላቅነታችንና ለኃያልነታችን አይደለም፡፡ የቱንም ያህል በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ የሚታይ ድርሻና አስተዋጽዖ ቢኖረን መንፈሳዊ እስካልሆንንና ለእግዚአብሔር ሐሳብ እስካልታዘዝን ድረስ ከመውደቅ የሚታደገን አይኖርም፡፡
“የእግዚአብሔር ጸጋ ለማንም እንዳይጐድለው፥ ብዙዎቹም የሚረክሱበት አንድ መራራ ሥር ወደ ላይ በቅሎ እንዳያስጨንቅ፥ ሴሰኛም የሚኾን እንዳይገኝ፥ ወይም ስለ አንድ መብል በኵርነቱን እንደ ሸጠ እንደ ዔሳው ለዚህ ዓለም የሚመች ሰው እንዳይኾን ተጠንቀቁ። ከዚያ በኋላ እንኳ በረከቱን ሊወርስ በወደደ ጊዜ እንደ ተጣለ  ታውቃላችኹና፤ በእንባ ተግቶ ምንም ቢፈልገው ለንስሓ ስፍራ አላገኘምና።” ዕብ 12፣15-17፡፡ ዛሬ ብንቆምም ነገ ደግሞ ልንወድቅ እንችላለንና ጥንቃቄን ገንዘብ ልናደርግ ይገባናል፡፡ ኃይላችን ከእግዚአብሔር የተነሳ፣ በቤቱና በአገልግሎቱ ታማኞች አድርጎ ከቆጠረንና ዕድሉን ከሰጠን ከብዙ ምህረቱና ርህራኄው የተነሳ መሆኑን መዘንጋት አይገባም፡፡ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ ታላላቆችና ኃያላን ሆነን መገለጣችን በድካማችን ውስጥ ከሚሠራውና ከሚያግዘን ከክርስቶስ ጸጋ የተነሳ ነው፡፡ ይህንን መርሳት በጀመርንበት ጊዜ ግን እንወድቃለን፣ የሰልፍ እቃ ጦራችንም ይጠፋብናል፡፡ ‘‘ኃያላን እንዴት ወደቁ! የሰልፍም ዕቃ እንዴት ጠፋ!’’ 2ኛ ሳሙ 1፣27፡፡ ኃያላን ሆይ ከኃያልነታችን እንዳንወድቅ፣ የሰልፍ ዕቃ ጦራችንም እንዳይጠፋ መንፈሳውያን እንሁን! መንፈሳዊውን አገልገሎትም በመንፈስና በእውነት እንፈጽም፡፡
ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ!

No comments:

Post a Comment