Wednesday, November 9, 2016

መዳንና በጎ ምግባራት በመጀመሪያይቱ የቅዱስ ዮሐንስ መልዕክት



ምዕራፍ ሦስት (ክፍል ሁለት)
ቁ. 14-15 ‘‘ እኛ ግን ከሞት ወደ ሕይወት እንደተሻገርን እናውቃለን፣ ባልንጀራችንን እንወዳለንና፤ ባልንጀራውን የማይወድ ግን በጨለማ ይኖራል፡፡ ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳይ የሆነም ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት በእርሱ እንደማይኖር ታውቃላችሁ፡፡’’ ዳግመኛም ቅዱስ ዮሐንስ ከሞት ወደ ሕይወት መሸጋገራችን የሚታወቀው ወንድሞቻችንን በመውደዳችንና ለሰው ልጆች ባለን ፍቅር እንደሆነ ይነግረናል፡፡ ወንድሙን የሚጠላ ሰው የዘለዓለም ሕይወት በእርሱ ሊኖር እንደማይችል በማያሻማ ቃል ተቀምጦልናል፡፡ ከዚህ የምንማረው ክርስትናችን/የመዳን መንገዳችን ወንድሞቻችንን በመውደድም ጭምር የምንኖረው መሆኑን ነው፡፡ በእርግጥ መዳናችን በመስቀሉ ሥራ በሆነልንና በተቀበልነው ጸጋ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ የማዳን ሥራ ላይ ባለን እምነት ቢሆንም በበጎ ምግባራትም ሁሉ የምንታዘዘውና የምንፈጽመውም ጭምር እስከሆነ ድረስ ወንድሞቻችንን በመውደድ በድርጊት የሚገለጽ ተግባራዊ ሕይወት መሆኑን ሐዋርያው አስተምሮናል፡፡ በዚህም የተነሳ በየዕለቱ የምንፈጽመውና የምናድግበት እንጂ አንድ ጊዜ ሆኖልን ተቀብለነዋል ብለን ቸል የምንለው አይደለም፡፡ በክርስቶስ ቤዛነት ላይ ያለ እምነታችን የድኅነታችን መጀመሪያ ነው፡፡ የማያምን ሰው ወደ መዳን ሊደርስ  አይቻለውምና፡፡ እምነት ወደ ድኅነት የሚያደርስ መንገድ ቢሆንም ማመናችን ብቻውን ግን ለመዳናችን ዋስትና አይደለም፡፡ ስለሆነም እንዳመንን እንዲሁ ባመንንበት ነገር መጽናትና ለአዳነን አምላክ ፈቃድ መታዘዝና ቃሉንም መፈጸም እንዳለብን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ ‘‘በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ ከሚያደርግ በቀር አቤቱ! አቤቱ! የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግስተ ሰማያት የሚገባ አይደለም፡፡ በዚያች ቀን ብዙዎች አቤቱ! አቤቱ! በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን? በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን? በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል፡፡ ያን ጊዜ ከቶ አላውቃችሁም፤ አመጽን የምታደርጉ ሁላችሁ ከእኔ ራቁ እላቸዋለሁ፡፡’’ ማቴ 7፣21-23፡፡ እዚህ ላይ የተጠቀሱት ሰዎች የእምነት ሰዎች አልነበሩምን? በትክክል የእምነት ሰዎች ነበሩ፡፡ እንዲያውም በስሙ አምነው በስሙ ትንቢትን የተናገሩ፣ በስሙ አጋንንትን ያወጡ፣ በስሙ ብዙ ተአምራትን ያደረጉ ሰዎች ነበሩ፡፡ ታዲያ እንዴት ወደመንግስተ ሰማያት የማይገቡ ሊሆኑ ቻሉ? በምግባራቸውና በኑሮ ፍሬያቸው እግዚአብሔርን ደስ ስላላሰኙት ነው፡፡ ስለሆነም ለመዳን እምነት አስፈላጊ ቢሆንም በበጎ ምግባራትና በመንፈሳዊ ተጋድሎ መጽናትም የእምነትን ያህል አስፈላጊ ነው፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በእምነታችን ጸንተን በተግባር የተገለጠና በበጎ ምግባራት የተደገፈ ክርስትና ሊኖረን እንደሚያስፈልግ እንዲህ ሲል ጽፎልናል፡- ‘‘ ወንድሞቻችን ሆይ አባቶቻችን ሁሉ ደመና እንደጋረዳቸው ሁሉም በባህር መካከል አልፈው እንደ ሄዱ ልታውቁ እወዳለሁ፡፡ ሁሉንም ሙሴ በደመናና በባሕር አጠመቃቸው፡፡ ሁሉም ያንን መንፈሳዊ ምግብ ተመገቡ፡፡ ሁሉም ያንን መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፤ ይኸውም በኋላቸው ከሚሄደው ከመንፈሳዊ ዐለት የጠጡት ነው፤ ያም ዐለት ክርስቶስ ነበረ፡፡ እግዚአብሔር ግን ከእነርሱ በሁሉም ደስ አላለውም፤ ብዙዎቹ በምድረ በዳ ወድቀዋልና፡፡ እነርሱ እንደተመኙ እኛ ደግሞ ክፉ እንዳንመኝ እነርሱ ለእኛ ምሳሌ ሆኑልን፡፡ . . . እነርሱን ያገኛቸው ይህ ሁሉ ነገር በኋላ ዘመን  ለምንነሣው ለእኛ ትምህርትና ምክር ሊሆነን ምሳሌ ሊሆን ተጻፈ፡፡’’ 1ኛ ቆሮ 10፣1-11፡፡ እግዚአብሔር ከግብጽ ባወጣቸው በህዝቡ ደስ ያልተሰኘው ስለምን ነበር? ቃሉን ስላላመኑት ነበርን? ችግራቸው የእምነት አልነበረም፡፡ ስላመኑትማ በተአምራቱ ከግብጽ አውጥቶ ተስፋ ያደረገልንን ከነዓንን ያወርሰናል ብለው በእምነት ከግብጽ ወጥተዋል፡፡ በእምነት ቢወጡም በመንገዳቸው ለአምላካቸው ሐሳብ፣ ለቃሉና ለፈቃዱ ሊታዘዙ ስላልቻሉ እግዚአብሔር አምላካቸው ደስ አልተሰኘባቸውም፤ በዚህም የተነሳ ቃል የገባላቸውን ከነዓንን ሳያወርሳቸው ቀርቷል፡፡ ‘‘ እነርሱን ያገኛቸው ይህ ሁሉ ነገር በኋላ ዘመን  ለምንነሣው ለእኛ ትምህርትና ምክር ሊሆነን ምሳሌ ሊሆን ተጻፈ፡፡’’ እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ እኛም በክርስቶስ ደም በተዋጀንበት ቤዛነቱ መንግስቱን እንደምንወርስ እናምናለን፤ ስላመንን ብቻ ግን መንግስቱን ልንወርስ ስለማንችል ላመንነውና ቤዛነትን ላገኘንበት ለጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፈቃድ፣ ለቃሉም መታዘዝ እንዳለብን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ መታዘዝን እንቢ ካልን ግን እምነታችን ብቻውን መንግስቱን አያወርሰንም፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ ዝቅ ብሎ በቁ. 12 ላይ ‘‘አሁንም ያ ቆሜያለሁ ብሎ በራሱ የሚታመን ሰው እርሱ እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ’’ ያለው፡፡ በእርግጥ በክርስቶስ ላይ ያለን እምነት ነው የሚያቆመን፤ ነገር ግን ቆሜያለሁ ስንል ምናልባት ወድቀን እንዳንገኝ በእምነታችን ወስጥ ሆነን የምንፈጽመውን መታዘዝና የምናደርጋቸውን በጎ ምግባራት ማስተዋልና ራሳችንንም መፈተሽ ይጠበቅብናል፡፡ ያለ በጎ ምግባራት የምንኖረው ክርስትና የለንምና፡፡
በስሙ እናምን ዘንድ የጠራን አምላካችን የተወልን ምሳሌው በስሙ እንድናምን ብቻ ሳይሆን እርሱ እንዳደረገ እንድናደርግና ፍለጋውንም እንድንከተለው ነው፡፡ ‘‘ለዚህ ተጠርታቸኋልና ክርስቶስም እኮ ፍለጋውን ትከተሉ ዘንድ ምሳሌውን ሊተውላችሁ ስለእናንተ መከራን ተቀብሏል፡፡’’ 2ኛ ጴጥ 2፣21፡፡ ከዚህ የምንማረው ምንድን ነው? ክርስትና በክርስቶስ ማመን ብቻ ሳይሆን የክርስቶስን ፍለጋ መከተል፤ እርሱ እንደተመላለሰም መመላለስ መሆኑን ነው፡፡ ትክክለኛው የክርስትና ትምህርት ሰዎች ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ እንዲያምኑ ብቻ የሚያስተምር ሳይሆን ከክርስቶስ ኢየሱስ እንዳዩትና እንደተማሩት እንዲኖሩ የሚያስተምርም ነው፡፡ ‘‘ . . . ሥራችሁ ለክርስቶስ መንግስት እንደሚገባ ይሁን፡፡ . . . ይህንንም ጸጋ እግዚአብሔር ሰጥቷችኋል፤ ነገር ግን ስለእርሱ መከራ ልትቀበሉም ነው እንጂ ልታምኑበት ብቻ አይደለም፡፡’’             ፊል 1፣27-29፡፡ እውነተኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ይህ ነው፣ እንድናምን ብቻ ሳይሆን ባመንነው ጸንተን በሥራ እንድንታዘዝ፣ ኑሯችንና ሥራችን ሁሉ ለክርስቶስ መንግስት እንደሚገባ እንዲሆን፣ በስሙ እንድናምን ብቻ ሳይሆን ስለስሙ መከራን እንድንቀበል፡፡ የምንቀበለው መከራ የሚጀምረው ደግሞ ከገዛ ማንነታችን፣ ከራሳችን ፈቃድና ከሥጋችን ሐሳብ ነው፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳለን፡-‘‘ መንፈስ ይሻልና ሥጋ ግን ደካማ ነው፡፡’’ ማቴ 26፣41፡፡ ክርስትና ሥጋን ማሸነፍ፣ የመንፈስንም ፈቃድ መፈጸም ነው፡፡ ክርስትና ይህን ሁሉ የሚያካትት ሰፊ ትምህርት ነው እንጂ አንዱን ብቻ ነጥለን ወስደን ሌላውን የምንተወው አይደለም፡፡ ስለእምነት እንደምናስተምር ሁሉ ስለ በጎ ምግባራትም እናስተምራለን፤ ስለ እግዚአብሔር ጸጋ የምናስተምረውን ያህል ስለ ሰው ልጆች ድርሻና ሱታፌም እናስተምራለን፡፡
. . . ይቀጥላል . . .
ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ!

No comments:

Post a Comment