Tuesday, December 15, 2015

ነገረ ክርስቶስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን



በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
ነገረ ክርስቶስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
   እንዲህ እናምናለን፤ እንዲህም እናስተምራለን፡፡ (ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ)፡፡
ነገረ ክርስቶስ ማለት ስለ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምናምነውን እምነት የምናስተምረውን ትምህርት የሚያጠቃልል ነው፡፡ ይህ ክፍለ ትምህርት በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን ስለ ጌታችን መድኃኒታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚታመነው፣ የሚነገረው፣ የምንመራበት ምንድነው የሚለውን በሚገባ ለመረዳት በቅዱሳት መጻሕፍት፣ በሊቃውንት፣ በትውፊት የተላለፈውን አስተምህሮ የምናቀርብበት ነው፡፡
   አግዚአብሔር አምላካችን የሚታየውን ዓለም ከማስገኘቱ በፊት እስከ ዘላለም ድረስ በአንድነቱና በሦስትነቱ፣ በመለኮቱ፣ በመንግሥቱ አለ፡፡ ከጎሕና ከጽባሕ በፊት፣ ከመዓልትና ከሌሊት በፊት፣ መላእክት ሳይፈጠሩ እግዚአብሔር አለ፡፡ ሰማያት ሳይዘረጉ፣ የየብስም ፊት ሳይታይ፣ ሐመልማላት ሳይበቅሉ እግዚአብሔር በመንግሥቱ ነበረ፡፡ ከሚንቀሳቀስ እንስሳ በፊት ከሚበሩም አዕዋፍ በፊት፣ ከባሕር አራዊት በፊት፣ እግዚአብሔር በመንግስቱ ነበረ፡፡ አዳምን በእርሱ አምሳልና አርአያ ሳይፈጥረው፣ ትእዛዙንም ሳያፈርስ እግዚአብሔር በመንግሥቱ ነበረ (ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ)፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው ወወልደ ማርያም ሥግው ከአምላክ የተገኘ አምላክ፣ ከብርሃን የተገኘ ብርሃን፣ ከባሕርይ የተገኘ ባሕርይ፣ ከሕይወት የተገኘ አዳኝ ከመድኃኒት የተገኘ መድኅን፣ ከገዥ የተገኘ ገዢ፣ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንድ ህላዌ እንደሆነ እናምናለን (መዝገበ ሃይማኖት)፡፡
ከአብ መወለዱም በዚህ ዘመን፣ በዚህ ወቅት፣ በዚህ ሰዓት ተብሎ ዘመን አይቆጠርለትም፤ በሰውና በመላእክት አእምሮም ሊመረመር አይችልም፡፡ ሰውንም ስለማዳን በአባቱ ፈቃድ በእርሱም ፈቃድ በመንፈስ ቅዱስም ፈቃድ ከቅድስት ድንግል ማርያም ያለ ወንድ ዘር በድንግልና ተወለደ፡፡ ከወለደችውም በኋላ ድንግልናዋ አልተለወጠም፡፡ በሚያስደንቅ ትሕትና ሰው ሆነ፤ በሚያስደንቅ ዙፋኑ ለደቀመዛሙርቱ ሲያገለግል ባዩት ጊዜ አገልጋዮች መላእክት ደነገጡ፡፡ ትሕትና ወዳለበት ፍቅር የአሕዛብን እግረ ልቡና ያቀና ዘንድ ግሩም እሳት በትሕትና መገለጡን ባዩ ጊዜ መላእክት ደነገጡ (ሃይማኖተ አበው ዘያዕቆብ ዘስሩግ)፡፡ ፍጥረቱን ሁሉ ሰብስቦ የያዘና ፍጥረቱን ሁሉ የሚመግብ ጌታቸው በብብቷ (በክንዷ) ተቀምጦ ጡቷን ሲጠባ ባዩ ጊዜ በአርያም ፈለጉና በዚህ ዓለም እንደ ቀድሞው ከአባቱና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አገኙት፡፡ የጌታን ትሕትና ባዩ ጊዜም ዓይኖቻቸውን ወደ ላይ ወደ አርያም ከፍ ከፍ አደረጉ ክንፋቸውንም ዘርግተው ለሁሉ ጌታ ለአንተ ምስጋና ይገባሃል እያሉ ጌታቸውን አመሰገኑ፡፡ (አንቀጸ ብርሃን)
አዳምን ካልታረሰች መሬት የፈጠረው ሔዋንንም ከአዳም ያለእናት የፈጠራት እርሱ ከንጽሕት ድንግል ያለ ወንድ ዘር ተወለደ፡፡ ያለ እናት ሔዋን ተገኝታ ነበርና ስለዚህ የአዳምን ብድራት ትከፍለው ዘንድ አዳም ያለ እናት ሔዋንን ስላስገኘ እንዳይመካ ድንግል ያለ አባት ክርስቶስን ወለደች ይህም ድንቅ በሚሆን አንድነት የፍጥረት ሁሉ እኩልነት ይታወቅ ዘንድ ነው፡፡ (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)፡፡
ዳግመኛም ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ‹‹ከአዳም አጥንት ጎድን ሲነሳ ምንም አካል እንዳልጎደለው እንዲሁ ከድንግል የምትናገር ነፍስን ሲነሳ ማኅተመ ድንግልናዋ አልተለወጠም፡፡ አዳም የጎድን አጥንት ከእርሱ ከተነሳ በኋላ አካል ሳይጎድለው ፍጹም ሆኖ እንደኖረ እንዲሁ ድንግልም ሕጻን ክርስቶስ ከእርሷ ከተወለደ በኋላ በድንግልና ጸንታ ኖረች›› አለ፡፡ ሕዝ 44፤1-3፣ መኃ 4፤12
ነቢያት ስለእርሱ ሰው መሆን ተነበዩ፡፡ ኢሳይያስ ‹‹እነሆ ድንግል ትጸንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ይሉታል ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሆነ ማለት ነው›› አለ፡፡ ዳግመኛም ‹‹ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል። ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም ድረስ በፍርድና በጽድቅ ያጸናውና ይደግፈው ዘንድ በዳዊት ዙፋንና በመንግሥቱ ላይ አለቅነቱ ይበዛል፥ ለሰላሙም ፍፃሜ የለውም። የእግዚአብሔር ቅንዓት ይህን ያደርጋል።›› በማለት ትንቢት ተናገረ፡፡ ዳግመኛም ‹‹ሕፃኑ አባቱንና እናቱን መጥራት ሳያውቅ የደማስቆን ሀብትና የሰማርያን ምርኮ በአሦር ንጉሥ ፊት ይወስዳልና ስሙን፦ ምርኮ ፈጠነ፥ ብዝበዛ ቸኰለ ብለህ ጥራው አለኝ›› አለ፡፡  (ኢሳ 14 ፣ 9፤6፣ 8፤4)፡፡ ጌታችን በመወለዱ በዲያብሎስ የተያዙትን ማርኳል፣ ሲኦልን በዝብዟልና ስሙ ‹‹ምርኮ ፈጠነ ብዝበዛም ቸኮለ›› ተብሎ ተጠራ፡፡    
የማይደፈር ግሩም ነው፤ በእኛ ዘንድ ግን ትሑት ነው፡፡ የማይደረስበት ልዑል ነው፤ በእኛ ዘንድ ግን የባርያውን መልክ ነሳ፡፡ የማይዳሰስ እሳት ነው፡፡ እኛ ግን አየነው፣ ዳሰስነው፣ ከእርሱም ጋር በላን ጠጣንም (ቅዳሴ ማርያም)፡፡ ሁሉ በእርሱ የተፈጠረና ሁሉን ሚመግብ ሁሉ በእጁ የተያዘ መላእክት የሚታዘዙለትና የሚያገለግሉት፣ እኔ ግን በመካከላችሁ እንደሚያገለግል ነኝ አለ (ሉቃ 22፤27)፡፡
በአዳም ምክንያት የጨለመውን ልቡናችንን ለማብራትና በእርሱ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር ብርሃን ሆኖ የመጣ (ዮሐ 12፤16)፡፡ ጨለማን ያስወገደ ብርሃን የሃይማኖትና የጽድቅ ጣሪያዋ (ጠፈሯ)፣ ሃይማኖትም ወንጌልም፣ በብዙ ድካም እርሱን ደስ ያሰኙት የሚወርሱት፣ የሃይማኖት ገንዘብን ይዘው በሠርክ የሚገቡበት መንግስተ ሰማያት እርሱ ነው (ሉቃ 17፤21 ፣ መልክአ ኢየሱስ)፡፡
ክብርና ምስጋና ይግባውና የእኛን ሞት ሞቶ የእርሱን ሕይወት የሰጠን፡፡ ድዳ ለነበሩት ቃል፣ ለተሰበሩት ምርጉዝ፣ ለዕውራን ብርሃን፣ለሐንካሶች መሄጃ፣ ለለምጻሞች የሚያነጻቸው ሆነ፡፡ በዴዌ የተያዙትን አዳነ፣ ደንቆሮዎችን ፈወሰ፣ ሞትን ዘለፈው ጨለማንም አሰቃየው፡፡ ብርሃን ኅልፈት የሌለበት፣ ፀሐይ፣ የማይጠፋ ፋኖስ፣ በቅዱሳን ላይ ዘወትር የሚያበራ ፀሐይ፣ በተወሰነ በቁርጥ ፈቃድ ለዓለም ጌጥ ሁሉን የፈጠረ፣ ሰውን ለማዳን ለሁሉ የተገለጠ፣ ነፍሳችንን የመለሳት እርሱ ነው (ኪዳን ዘነግህ)፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ‹‹ምንስ እላለሁ ምንስ እናገራለሁ ከዘመን በፊት የነበረ እርሱ ትንሽ ሕጻን ሆኗልና ፈጽሜ አደንቃለሁ፡፡ ከሰማየ ሰማያት በላይ የሚሆን በዘለዓለማዊ ዙፋን የሚኖር እርሱ በበረት ተጣለ›› በማለት የጌታን ትሕትና አደነቀ፡፡  ነፋሳት የሚታዘዙለት፣ መላእክት የሚላላኩት እርሱ ለእናቱና ለዘመዶቹ እየታዘዘ አደገ፡፡ ሁሉን አዋቂ ሲሆን አልአዓዛርን የት ቀበራችሁት ብሎ ጠየቀ፤ እርሱ የሕይወት ውሃ ሲሆን ከሳምራዊት ሴት ውሃ ለመነ፡፡ ምራቅ ከጭቃ ጋር ለውሶ እውር ያበራ እርሱን አይሁድ ምራቅ ተፉበት፡፡
ጠባቂ አጥተው ለባዘኑት መልካም እረኛ ሆኖ መጣ ስለበጎቹም ነፍሱን ሰጠ፡፡ (ዮሐ 1፤11) ቅዱስ ያሬድ ‹‹ኖላዊ ኄር ኖላዊሆሙ ለእስራኤል ዘመጽአ ውስተ ዓለም ተአዛዚ ከዊኖ ክርስቶስ ለአሕዛብ፡፡ ኦሆ ብሂሎ ተአዛዚ ከዊኖ ወረደ ወመጽአ ለአድኅኖ… ከመ ይቤዙ ወያድኅን ዓለመ፡፡ ቸር እረኛ እስራኤልን የሚጠብቃቸው ታዛዥ ሆነ ክርስቶስ ለአሕዛብ የመጣ፡፡ እሺ ብሎ ታዛዥ ሆኖ ዓለምን ይቤዥና ያድን ዘንድ ከሰማይ ወረደ፤ መጣ፡፡›› (ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ ገጽ )*)፡፡ በማለት ሁሉን የሚገዛ አምላክ ዓለሙን ሊቤዥና ሊያድን እሺ ብሎ በፈቃዱ መምጣቱን መሰከረ፡፡
ሁሉን የሚመግብ፣ የሕይወት እንጀራንና የሕይወት መጠጥን የሚሰጥ ጌታ ወደ ሰርግ ተጠራ፡፡ ለፍጥረቱ ማዕድን የሚያዘጋጅ ጌታ በፈሪሳዊው ስምዖን ቤት ለግብዣ ተጠራ፡፡ ዮሐ 2፤2፣ ሉቃ ፤36-37፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም በፈሪሳዊው ማዕድ ላይ የቀረበው የጌታ ማዕድ በሚለው ስብከቱ ‹‹ ንስሓ ስለምትገባው ስለዚያች ኃጢአተኛ ሴት ሲል ከግብዣው ቤት ተገኘ፤ ጌታ ርሀቡ ሥጋዊው ምግብ ሳይሆን የዚያች ኃጢአተኛ እንባ እንጂ… ወደ ፈሪሳዊው ስምዖን ቤት የሄደው በምግብና በመጠጥ ለመዝናናት አልነበረም ሕይወት መድኃኒት የሆነውን ትምህርቱን በማዕዱ ለማቅረብ በመሻቱ ነበር እንጂ፡፡ … ክፉ የተባለው ሰይጣን በመብል ምክንያት አዳምና ሔዋንን ሞትን የሚያመጣ ምክርን እንደመከራቸው እንዲሁ ቸሩ ጌታችን ደግሞ በማዕድ ቦታ ተገኝቶ ሕይወት ሰጪ የሆነ ትምህርቱን ለአዳም ልጆች በማዕዱ አቀረበ፡፡ እርሱ ጌታችን የጠፉትን ነፍሳት ለማጥመድ አሳ አስጋሪ ነበር፡፡ ቀራጮችና አመንዝሮች ወደ ስካርና ሥርዐት አልበኝነት ሲፋጠኑ ተመለከታቸው፤ ሥጋንም ከሚያወፍር የማዕድ ቦታ እነርሱን በማስገር ነፍስን ወደሚያወፍር ጾም ሊያሻግራቸው የቃሉን መረብ በማዕዱ ውቅያኖስ ላይ ጣለው፡፡›› በማለት ገለጸው፡፡ (ስብከት ወተግሳጽ ዘቅዱስ ኤፍሬም)፡፡
ይቀጥላል….

4 comments:

  1. Really it is good work. We expect you to do more. May God bless you.

    ReplyDelete
  2. ቃለ ህይወት ያሠማልን፡፡

    ReplyDelete
  3. እናመስግናለን። በርቱልን።

    ReplyDelete
  4. ቃለ ህይወት ያሰማልን

    ReplyDelete