Saturday, April 15, 2017

ትምህርተ ንስሓ (ክፍል ሁለት)


እለውስተ ንስሓ ሀለውክሙ አትኅቱ ርዕስክሙ/ በንስሓ ውስጥ ያላችሁ ራሳችሁን ዝቅ አድርጉሥርዐተ ቅዳሴ

በሥርዐተ ቅዳሴያችን ከእግዚኦታ በኋላ ዲያቆኑ እለውስተ ንስሓ ሀለውክሙ አትኅቱ ርዕስክሙ/ በንስሓ ውስጥ ያላችሁ ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ ብሎ ሲያውጅ ካህኑ ደግሞ አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ በንስሐ ወስጥ ወዳሉት ወገኖች ተመልከት፣ እንደ ይቅርታህም ብዛት ይቅር በላቸው፣ እንደቸርነትህም ብዛት በደላቸውን አጥፋላቸው፤ ከክፉ ነገርም ሁሉ ጠብቃቸው፤ ሰውራቸውም፡፡ የቀደመ ሥራቸውን ይቅር ብለህ በሰላም ነፍሳቸውን አድን፤ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያንህ አንድ አድርጋቸው፡፡ ተቀዳሚ ተከታይ በሌለው በአንድ ልጅህ በጌታችንና በአምላካችን በመድኃኒታችንም በኢየሱስ ክርስቶስ በይቅርታውና በምህረቱ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያንህ ጨምራቸው፡፡ብሎ ይጸልይላቸዋል፡፡ ንስሓ ራሳችንን ዝቅ አድርገን የአምላካችንን ምህረትና ይቅርታ የምንጠይቅበት መንፈሳዊ መንገድ ነው፡፡ የንስሓ ሰው ይገባኛል ብሎ የሚጓደድ ሳይሆን ባይገባኝም ከምህረትህና ከበጎነትህ የምመጸወት ድሃ ነኝ በማለት በአትኅቶ ርዕስ/ራስን ዝቅ በማድረግ የሚቀርብ ነው፡፡  

በንስሓ ወቅት መሬት ላይ መተኛት፣ የምንመገበውን የምግብ መጠን መቀነስ፣ ከዓለማዊ ነገሮችና ለመንፈሳዊ ሕይወት ከማይመቹ ጓደኞች/ግንኙነቶች መራቅ ያስፈልጋል ። በንስሓ ጊዜ እንዳናደርግ ከታዘዝነው ነገር ራሳችንን በመግዛት መቆጠብ አለብን፤ እግዚአብሔር በቸርነቱ ወደ ድኅነት ከጠራን በኋላ እንደገና ተመልሰን ወደተውነው ድካማችን መመለስ የለብንም ። የጊዜውን ሳይሆን የመጨረሻውን ማሰብ አለብን ። 2 ጢሞ 4 ፥ 10 ። መዝ 6፥ 6። እንግዲህ ተነሳሒው በእውነት ኀጢአቱን አውቆ በካህኑ ፊት በስውር ለሚያየውና ለሚሰማው ለእግዚአብሔር ከተናዘዘ በኋላ ከካህኑ ሁለት ነገሮችን ይቀበላል። እነርሱም ቀኖናና ፍትሐት ናቸው። ምንም እንኳን ተነሳሒው በመጸጸቱና ከቀደመ ክፋቱ በመመለሱ ከዘለዓለም የሞት ቅጣት ቢድንም ዓይነቱና መጠኑ የተለያየ ጊዜያዊ ቅጣት መቀበል ይገባዋል። ይህም የንስሓ ቀኖና ይባላል። ጊዜያዊ ቅጣት ወይም ቀኖና ያስፈለገበት ምክንያት ኀጢአትን መሥራት ምን ያህል ክፉ እንደሆነ ለተነሳሒው ለማሳሰብና ዳግመኛ እንዳይበድል ለማስጠንቀቅ እንዲሁም ደግሞ ሥጋን በመገሰጽ ለነፍሱ የጽድቅንና የደኅንነትን ጎዳና ለማስተማር ነው። ምንጊዜም ፍቅሩና ምሕረቱ ከእኛ ጋር ቢሆንም እግዚአብሔር በአባትነቱ ላጠፋነው ጥፋት በጊዜያዊ ቅጣት ይቀጣናል። መልካም አባት ልጁን እንደሚገስጽና እንደሚቀጣ ዓይነት ይቀጣናል። ዕብ 12፥5-11። እንግዲህ ያልተገራ ልቦና ካለን ለእግዚአብሔር በማስገዛት የኀጢአታችንንም ቅጣት በደስታ በመቀበል የበለጠ ጸጋና ረድኤትን እናገኛለን። በዚያን ጊዜ ያልተገረዘው ልባቸው ቢዋረድ፣ የኀጢአታቸውንም ቅጣት ቢቀበሉ እኔ ለያዕቆብ የማልኩትን ቃልኪዳኔን አስባለሁ … ምድሪቱንም አስባለሁ። ተብሎ ተጽፏልና ዘሌ 26፥41-42። በካህኑ የታዘዘልንን ቀኖና መፈጸማችን ኀጢአትን ሁሉ ይቅር በሚልና በሚያስተሠርይ አምላክ ማመናችንን የምናረጋግጥበት ነው፡፡ በእምነታችን ውስጥ በሚሆነው መታዘዛችን ምህረቱ ብዙ ከሚሆን አምላካችን የበደል ሥርየትንና ይቅርታን እንቀበላለን፡፡

ከቀኖና ቀጥለን የምናገኘው ሌላኛው ሥርዐተ ንስሓ ፍትሐት ነው፡፡ ፍትሐት የምንለው ከኀጢአት እስራት ተፈትተን ለበደላችን የቅርታን፣ ለኀጢአታችን ደግሞ ሥርየትን አግኝተን ንጹሐን የምንሆንበትን የንስሓ ሂደት ነው። ቀኖና የምንለው ተነሳሒው ለኀጢአቱ ምክርና ተግሳጽ የሚያገኝበትን፣ በንስሐ ቅጣት የሚቀበልበትን፣ ካሳ መቀጫ የሚከፍልበትን ሥርዐተ ንስሓ ሲሆን ፍትሐት የምንለው ደግሞ ካህኑ የንስሓውን ጸሎት ከፈጸመ በኋላ በተሰጠው የክህነት ሥልጣን እግዚአብሔር ይፍታህባለው ጊዜ ተነሳሒው የኀጢአት ሥርየትንና የበደል ይቅርታን የሚያገኝበትን ሥርዐት ነው፡፡ ንስሓ የገባው ሰው ከኀጢአቱ ተፈትቶ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቁ ታላቅ ጸጋ ነው። ለኀጢአታችን ሥርየት እንደዚህ ዓይነቱን ቀላል መንገድ ስላዘጋጀልን ክርስቶስን ማመስገን ይገባናል። ብዙ ሳንደክም ወንድማችንና አባታችን ለሆነው ካህን በመናዘዝና ምክሩንና ቀኖናውን በመቀበል በኀጢአት ከሚመጣብን የዘለዓለም ቅጣት መዳናችን እጅግ ደስ የሚያሰኝ ነው። ይህንንም ሥልጣን ለካህናት የሰጣቸው እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ እናነባለን፡፡ ማቴ 16፣19 ማቴ 18፣18፡፡ እንግዲህ ፍትሐት የተቀበለ ተነሳሒ ሁሉ ኀጢአቱ የተሰረየለትና በደሉም የተደመሰሰለት ስለሆነ ከዘለዓለም የሞት ቅጣትና ከበደል ቅጣት ሁሉ ነጻ ይሆናል።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በዝሙት የተከሰሰውን የቆሮንቶሱን ሰው በሥጋው እንዲቀጣ ፈርዶበታል። እንደዚህ በሠራው ላይ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሁን ፈርጄበታለሁ . . . መንፈሱ በጌታ በኢየሱስ ቀን ትድን ዘንድ እንደዚህ ያለው ሰው ለሥጋው ጥፋት ለሰይጣን እንዲሰጥ ፍርዴ ነው። 1ኛ ቆሮ 5፥1-5። ይኸው ሐዋርያ ለሁለተኛ ጊዜ በጻፈው መልዕክቱ ከላይ የተጠቀሰው የቆሮንቶስ ሰው ቅጣቱ የሚበቃው ስለሆነ ማኅበረ ክርስቲያኑ ይቅርታ እንዲያደርጉለት ጠይቋል። እንደዚህ ላለ ሰው ይህ ከእናንተ የምትበዙት የቀጣችሁት ቅጣት ይበቃዋልና እንደዚህ ያለው ከልክ በሚበዛ ኀዘን እንዳይዋጥ ይልቅ ተመልሳችሁ ይቅር ማለትና ማጽናናት ይገባችኋል። ስለዚህ ፍቅርን እንድታጸኑ እለምናችኋለሁ፤ ስለዚህ ደግሞ ጽፌ ነበርና . . . 2ኛ ቆሮ 2፥6-11። እንግዲህ የሐዋርያውን ምክር ሰምተን ዛሬ በሕይወተ ሥጋ የምንገኝ ክርስቲያኖችም በበደላችን ምክንያት ካህኑ የሚሰጠንን ምክርና ተግሳጽ አዳምጠን የንስሐውንም ቅጣት ማለትም ቀኖናውን ተቀብለን በደስታ ብንፈጽመው መንፈሳዊ ደህንነታችን ይጠበቃል። መንፈሳዊ ግዴታችንንም እንወጣለን። በቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና የሚሰጠው እንደተነሳሒው የኀጢአት ዓይነትና እንዳለበት የመንፈሳዊ ሁኔታ ታይቶ ነው። ካህኑ የተነሳሒውን የኑሮ ሁኔታና ያጋጠመውን ፈተና በማስመልከት ምክርና ትምህርት ይሰጠዋል። እንደመልካም የነፍስ ሐኪምም እንደበሽታው ሁኔታ ካህኑ አስፈላጊውን የነፍስ መድኃኒት ይሰጠዋል። የቀኖና አሰጣጥ መንገዱና ዓይነቱ ብዙ ነው። ለአንዳንዱ ተነሳሒ የቃል ምክርና ተግሳጽ ብቻ የሚበቃው አለ። ለሌላው ጾም ብቻ ወይም ከስግደት ጋር ቀኖና ይሰጠዋል። ልዩ የንስሐ ጸሎት፣ ምጽዋት፣ ለተበደለው ወገን ካሳ መክፈል፣ ለችግረኞች አገልግሎት መስጠት አስፈላጊም ከሆነ ለተወሰነ ጊዜ ከቁርባን ሕይወት መለየት ወይም ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ተግባራትን  መፈጸም ወይም ለቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ኑሮ የሚጠቅሙ የጉልበትም ሆነ የአእምሮ ሥራዎችን መሥራትና የመሳሰሉት ሁሉ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ይቆጠራሉ። ንስሓ ማለት መታጠብ፣ ከዕድፍ/ከኀጢአት መንጻት ማለት ሲሆን፤ ድኅነት የሚገኘው ደግሞ በንስሓ ሕይወት ውስጥ በመመላለስ  የዘለዓለም ሕይወት የሚሰጠውን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን በመቀበል ነው። ዮሐ 6 ፥ 33። ብዙ ሰዎች የቅዱስ ቁርባን ሕይወትን እንደ ትርፍ ነገርና በዕድሜ የተገደበ (ለአረጋውያን ወይም ለሕጻናት ብቻ የተተወ) አድርገው ስለሚቆጥሩት የክርስቶስን ሥጋና ደም ለመቀበል ሲዘጋጁ አይታዩም ። ነገር ግን ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በቅዱስ ቁርባን ሕይወት ውስጥ መመላለስ የግድ ያስፈልገዋል። ቀኖና የተቀበልንበት በደላችን የሚሠረይበት ሥርዐተ ንስሓ ፍጹም የሚሆነውና በጀመርነው የንስሓ ሕይወት ውስጥ መቀጠልና ፍሬ ማፍራት የምንችለው የጌታችንን ሥጋውን ስንበላና ደሙንም ስንጠጠጣ ነው፡፡ በመሆኑም በንስሓ ሕይወታችን ውስጥ ስለሚሰጠን ቀኖናና ከቀኖናው በኋላ ስለሚደረግልን የኀጢአት ፍትሐት የምንጠነቀቀውን ያህል ከንስሓ በኋላ ስለሚኖረን የቅዱስ ቁርባን ሕይወትም ልንጠነቀቅና ተገቢውን ትኩረት ልንሰጠው ይገባል፡፡  

ሌላው ልናስተውለው  የሚባን ጉዳይ ደግሞ ንስሓ ከገባንና ከቆርብን በኋላ እንደገና በኀጢአት ልንወድቅ እንችላለን ብለን ከንስሓ ሕይወት መራቅ እንደሌለብን ነው። አምላካችን ለምን ንስሐ አልገባህም እንጂ ለምን ኀጢአት ሠራህ?” አይልምና ሁለተኛ ስንበድል ኀፍረት ሳይሰማንና ከኃጢአት መላቀቅ ካልቻልሁ በየጊዜው የንስሓ አባቴን ከማስቸግር አርፌ ብቀመጥ ይሻለኛል ሳንል በየጊዜው በንስሓ ሕይወታችን እያደግንና እየጠነከርን ለመሄድ ጥረት ማድረግ አለብን፡፡ ከንስሓ በኋላ ሰይጣን በደጊመ ኀጢአት ሊፈትነንና በንስሓ ሕይወታችን እንዳንደሰት በተስፋ መቁረጥ ሊያቆየን ጥረት ማድረጉን አይተውም፤ ሁሉንም እርግፍ አድርገን እንድንተወውና ከንስሓም በኋላ መልሰን ያንንኑ በደላችንን ደግመን ማድረጋችንን እያስታወሰ  ክፉውን ሐሳብ በአእምሯችን ውስጥ በማግባት ሊፈታተነን ይችላል። ነገር ግን ከንስሓ በኋላ እንደ መላእክት በቅድስና ብቻ እንኖራለን ማለት ሳይሆን ጻድቅ ሰባት ጊዜ ይወድቃል፤ ሰባት ጊዜም ይነሳል። ምሳ 24 ፥ 16። እንደተባለ አምላካችን ብንወድቅ ሊያነሳን ፤ ብንጠፋ ሊፈልገን፤ ብንርቅ ሊያቀርበን፤ በኀጢአት ብንረክስ ሊቀድሰን (እንደ ባዘቶ ሊያጠራን) የታመነ አምላክ ስለሆነ ተስፋ ሳንቆርጥ፤ በኃጢአታችን ሳንደበቅ፤ ዘወትር ለንስሓ መዘጋጀት አለብን ። ኢሳ 1 ፥ 18 ።

የንስሓ ጊዜ መቼ ነው?

ሰው በሕይወተ ሥጋ ካለ ክፉውንና በጎውን መለየት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ንስሐ መግባት አለበት። ጠቢቡ ሰሎሞን ቀኑን ሙሉ እግዚአብሔርን በመፍራት ኑርእንዲል (ምሳ 23፥17)፤ የንስሓ ጊዜ ዛሬ፣ ከዛሬም ደግሞ አሁን ነው። ብዙ ሰዎች የንስሓ ጊዜን ከሚያዘገዩባቸው ምክንያቶች ውስጥ ዳግም እበድላለሁ ብሎ ማሰብ ዋናው ነው። ነገር ግን እንኳን ስለነገዋ ስለዛሬዋም የማናውቅ ነንና ዛሬ ልናደርገው የሚገባንን ብቻ በማድረግ የነገውን ለእግዚአብሔር እንተውለት። ያዕ 4፥13-16፡፡ ጌታችንም ደግሞ እንዲህ ሲል ነግሮናል፡- ነገ ለራሱ ይጨነቃልና፥ ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል።ማቴ 6፣34፡፡ ነገ ሌላ ንስሓ የምንገባበት በደል ስለሚኖር ዛሬን በንስሓ ማሳለፍ ተገቢ ነው፡፡ ሌሎች ሰዎች ደግሞ ንስሓ መታሰር ነው ብለው ያስባሉ፡፡ ንስሓ ገባንም አልገባንም ኀጢአትን ማድረግ ለማንም አልተፈቀደም፡፡ ኀጢአትን አድርጎ ያለንስሓ ከመሆን ግን ስለበደሉት ኀጢአት ንስሓ መግባት የተሻለ ነው፡፡ በእርግጥ ንስሓ ለፈቃደ እግዚአብሔርና ለፍቅሩ፣ ለቃሉና ለዘለዓለማዊ ሐሳቡ  ራሳችንን የምንለይበትና የምንሰጥበት ሕይወት ነው፡፡ ሕዝ 20፥ 37፤  ኤፌ 4 ፥1፤ ሮሜ 12፥9-13፡፡ ስለሆነም ስለበደላችን በመጸጸት እግዚአብሔርን ብንሻው ፈልጉ ታገኛላችሁ ያለን አምላክ ወደራሱ ያቀርበናል እንጂ ከፍቅሩና ከበጎነቱ በአፍአ አይተወንም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የራሴ የሆነ ንብረትና ትዳር ሳይኖረኝ፣ ለቁም ነገር ሳልደርስ እንዴት ንስሓ እገባለሁ የሚሉም አሉ። እግዚአብሔር ግን ሀብታችንን ወይም ያለንበትን የኑሮ ደረጃ አይደለም የሚፈልገው፡፡ ለቅዱሳን አባቶቻችን አንዳች ሳይኖራቸው የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ያልነሳቸው አምላካችን በእኛም ሕይወት ውስጥ የተሻለውን ነገር ሊያደርግልን የታመነ ነው፡፡ ስለዚህም አስቀድመን ጽድቁንና መንግሥቱን በመሻት በንስሓ ሕይወታችን ውስጥ ለምንቀበለው የእግዚአብሔር በረከት ልንተጋ ያስፈልገናል፤ የቅዱሳን አምላክ በረከቱ ብዙ ነውና! ዘፍ 18፥1-19፤ ጥበ 10፥10፤ ዘፍ 32፥ 10፡፡
የሰው ልጅ እግዚአብሔር በወሰነለት ዕድሜ የሚንቀሳቀስ ደካማ ፍጡር እንደመሆኑ መጠን አብዛኛው የኑሮው ሁኔታ በዕለትና በሰዓት የተወሰነ ስለሆነ ከንስሓ መራቅና ለነገ ብሎ ማሰብ በእሳት እንደመጫወት ነው፡፡ ቀናትና ሰዐታት የእግዚአብሔር ስጦታዎች መሆናቸውን ተረድቶ እናደርገው ዘንድ የሚጠበቅብንን ነገር በተገቢው ወቅትና ሰዓት ማድረግ በክርስትና ሕይወት ውስጥ እጅግ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ በወንጌል እንደምናነበው የተሰጣቸውን ጊዜ በአግባቡ መጠቀም ያልቻሉትና ጊዜያቸውን በከንቱ ያሳለፉ ሰዎች መጨረሻቸው የማይረባ ጸጸትና ለቅሶ ነው፡፡ ማቴ 25፡፡

ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ!

No comments:

Post a Comment