“እግዚአብሔር መንፈስ ነው ፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት
ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል።” ዮሐ4፣24
እግዚአብሔር አምላካችን
ባሕርዩ የማይመረመር፣ ከእኛ አሳብና መረዳት የራቀ፣ አኗኗሩ የማይታወቅ፣ በጊዜና በሁኔታዎች የማይወሰን፣ በጎነቱና መልካምነቱ ለሁሉ
የሚሆን … እጅግ ድንቅና ግሩም የሆነ አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን መንፈስ ነውና አሳቡና አኗኗሩ፣ ጥበቡና ምክሩ፣ መገለጡና
ምሪቱ፣ የመንገዱም ፍለጋ በመንፈሳዊነት ካልሆነ በቀር በሥጋዊ ጥበብና ምርምር ማንም ሊረዳው አይቻለውም፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን
በሚያስደንቀውና ከአእምሮአችን በላይ በሆነው ታላቅ ፍቅሩ ዓለሙን ሁሉ እንዲሁ ወዷል፡፡ “ከወደደን ከትልቅ
ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፡፡” እንዲል ኤፌ 2፣5 ፡፡ ይህ እግዚአብሔር በአንድ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ዓለሙን ሁሉ የወደደበት ታላቅ ፍቅሩ የእኛ
ሥራና የድካማችን ውጤት ሳይሆን እንዲሁ በእርሱ ፈቃድ በነጻ የሆነልን የበጎነቱ ስጦታ ነው፡፡ በሥራችንና በሕይወታችን ለአምላካችን
ወዳጆቹና ደስ የተሰኘብን አገልጋዮቹ ሆነን ሳይሆን ጠላቶቹ እንኳን ሆነን በልጁ ሞት ታርቆናል፡፡ “ጠላቶች ሳለን
ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፥ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ
በሕይወቱ እንድናለን፡፡” ተብሎ ተፅፏልና ሮሜ 5፣10፡፡ በእርግጥ የአምላካችን
የፍቅሩ ታላቅነት ለሚወዱት ብቻ ሳይሆን ሁሉንም እንዲሁ ከመውደዱ የሚመነጭና ለጠላቶቹም ሁሉ የሚተርፍ እውነተኛ ፍቅር ነው፡፡ “ስለ
ጻድቅ የሚሞት በጭንቅ ይገኛልና፤ ስለ ቸር ሰው ግን ሊሞት እንኳ የሚደፍር ምናልባት ይገኝ ይኾናል። ነገር ግን፥ ገና ኀጢአተኞች
ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቷልና፥ እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል።” ሮሜ 5፣7-8፡፡ ይህ የማይገባንን የተቀበልንበት
ታላቅ ስጦታው ደግሞ በዘመናችን ሁሉ የምንጠነቀቅለትና የምንኖርለት ታላቅ ሕይወት ነው፡፡ ክርስትናችን ለራሳችን የምንኖርበት ሳይሆን
እስከሞት ለወደደንና ወዳጆቹ አድርጎ ለተቀበለን ለእግዚአብሔር ልጅ ለኢየሱስ ክርስቶስ የምንኖረው ሕይወት ነውና የራሳችንን ሐሳብና
መሻት የምናገለግልበት ሳይሆን የመድኃኒታችንን አሳብ የምናገለግልበት ነው፡፡ ይህ አሳቡ ደግሞ ከሥጋዊ መረዳትና ጥበብ በእጅጉ የራቀ
ስለሆነ በመንፈስና በእውነት ሆነው ለማይመረምሩት ሰዎች ሊረዳቸውና ሊገነዘቡት የሚቻል አይደለም፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን
መንፈስ ስለሆነ በመንፈስ ያልሆነ ሰው ወደ እርሱ ሊደርስና ከእርሱም ጋር ኅብረት ሊያደርግ አይቻለውም፡፡ ክርስትና በሥጋዊነት ሊመዘንና
ሊመረመር አይችልም፡፡ ክርስትና መንፈሳዊነት ነውና በመንፈስ ከፍታ ላይ ያልሆኑ ሰዎች ሊደርሱበት አይቻላቸውም፡፡ “ለፍጥረታዊ ሰው
የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለሆነ ሊያውቀው አይችልም፡፡” 1ኛ ቆሮ 2፣14፡፡ የክርስቶስ በምትሆን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚደረግ ማናቸውም
ነገር መንፈሳዊ ሊሆን ይገባዋልና ሁሉም ስርዐት መንፈሳዊ ነው፡፡ ይህንን መንፈሳዊ ስርዐት ደግሞ መንፈሳዊ ያልሆኑ ሰዎች ሊረዱት፣
ሊመረምሩትና ሊኖሩት አይቻላቸውም፤ ምክንያቱም ሁሉ መንፈሳዊ ነውና፤ እኛም ደግሞ “ሕግ መንፈሳዊ እንደሆነ እናውቃለንና፡፡” ሮሜ 7፣14፡፡ ሕጉ መንፈሳዊ እስከሆነ ድረስ በሕጉ መኖር የሚችሉት መንፈሳውያን
የሆኑት ብቻ ናቸው፤ መንፈሳዊ ያልሆኑት ግን የቱንም ያክል እውቀትና መገለጥ ቢኖራቸውም የሕጉ መንፈሳዊነት ገብቷቸው በሕጉ ሊኖሩ
አይቻላቸውም፡፡
ጽድቅ/እውነት ጌታችንና
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱ ራሱ “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ” ብሏል፡፡ ዮሐ 14፣6፡፡ ይህ እውነት ግን የሚያውቁት ሳይሆን የሚኖሩት ነው፣ በመንፈሳዊነት
የሚመረምሩት እንጂ በሥጋዊነት የሚደርሱበት አይደለም፡፡ ያ ባይሆን ኖሮማ እንዲህ ተብሎ ባልተጻፈልን ነበር! “በእግዚአብሔር ጥበብ ምክንያት ዓለም እግዚአብሔርን በጥበቧ ስላላወቀች፥
በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ኾኗልና።” 1ኛ ቆሮ 1፣21፡፡ የእግዚአብሔርን ሐሳብ መረዳት የምንችለው
ከእግዚአብሔር የሆነውን ጥበብ መቀበል ስንችል ብቻ ነው፡፡ ከዓለም በሚሆን ጥበብ ወደ እግዚአብሔር ልንደርስና ሐሳቡንም ልንመረምር
አይቻለንም፡፡ ብዙ ባወቀና በመረመረ ሳይሆን የእግዚአብሔርን አሳብ ባገለገለና ለእግዚአብሔር አሳብ በተሸነፈ ነው፡፡ እንዲህ ባይሆንማ
ኖሮ ጸሓፍትና ፈሪሳውያን ወደ ክርስቶስ መምጣትና በእርሱም ማመን ቀላል በሆነላቸው ነበር፡፡ ለዚህም ነበር ጌታችንና መድኃኒታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ሲል የገሠፃቸው፡- “እናንተ በመጻሕፍት
የዘለዓለም ሕይወት እንዳላችኹ ይመስላችዃልና፥ እነርሱን ትመረምራላችኹ፤ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው፤ ነገር ግን፥ ሕይወት
እንዲኾንላችኹ ወደ እኔ ልትመጡ
አትወዱም።” ዮሐ 5፣39-40፡፡ ይህ ጌታችን ወደ እኔ መምጣት
ብሎ የተናገረው ንግግር ምንድን ነው ቢሉ መንፈሳዊነት ነው፡፡ ጸሓፍትና ፈሪሳውያን መጻሕፍትን ይመረምራሉ ነገር ግን በመንፈስ ሆነው
ስለማይመረምሩና መንፈሳዊነቱ ስለሌላቸው ወደ ክርስቶስ መምጣት ሳይችሉ ቀሩ፣ መድኃኒታቸው በመካከላቸው ሆኖ ሳለ ሳያምኑበት ቀሩ፣
እንደሚመጣ ሲጠብቁት የነበረውን የክብርን ጌታ ሰቅለው ገደሉት፡፡ ትንቢት እንደተነገረለትና ሱባኤ እንደተቆጠረለት እያወቁ፣ የሚጠብቁት
መሲሕ በመካከላቸው እየተመላለሰ ሊያውቁት አልቻሉም ነበር፡፡ የዚህ ሁሉ ምክንያቱ የእውቀታቸው ማነስ አይደለም፤ ስለክርስቶስ መምጣት
ትንቢት ስላልተነገረና ሱባዔ ስላልተቆጠረም አይደለም፤ ምክንያቱ መንፈስ የሚሆን አምላካቸውን በመንፈስና በእውነት ሊቀበሉትና ሊረዱት
ስላልወደደዱ ነው እንጂ፡፡ በመንፈስና በእውነት ሆነው ቢሆንስ ኖሮ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉት ነበር፡፡ 1ኛ ቆሮ 2፣8፡፡
ዛሬም በምድራችን
ላይ እየሆነ ያለው ነገር ይህ ነው፡፡ የክርስቶስ ነን የሚሉ ነገር ግን ከክርስቶስ አሳብ በእጅጉ የራቁ “አብያተ ክርስቲያናት”
የበዙበት፣ በክርስቶስ ስም የገዛ ፈቃዳቸውን የሚያገለግሉና ሥጋቸውን ደስ የሚያሰኙ የተጠራቀሙበት፣ “በርቶልናል” የሚሉ አሁንም
ግን በጨለማ ውስጥ ያሉና የብርሃንን ሥራ የማያደርጉ ክፉዎች የሰለጠኑበት፣ “አዲስ መገለጥና አብርሆት” ሆኖልናል የሚሉ ነገር ግን
ከትናንት ሕይወታቸው አንዲት ጋት ያህል እንኳን መለወጣቸውንና አዲስ የሚሉትን መገለጥ ፍሬ ማሳየት ያልቻሉ “ባለራዕዮች” የገነኑበት፣
በመንፈሳዊነት ስም ሥጋውያን መንፈሳዊ መስለው የሚታዩበት . . .
እውነቱ ይህ ነው፡፡ ሰዎች በእግዚአብሔር ስም የገዛ አሳባቸውንና ፈቃዳቸውን እያገለገሉ ነው፤ መንፈሳዊውን ኑሮ በሥጋዊነትና
በሰብአዊ መረዳት ለመበየን እየሞከሩ ነው፡፡ ከትናንት ይልቅ ዛሬ ብዙዎች በክርስቶስ ስም እናመልካለን ይላሉ፣ ስለክርስቶስ ያስተምራሉ፣
ስለክርስቶስ ይጽፋሉ፣ ስለክርስቶስ ይዘምራሉ፣ ብዙ ሰዎች ክርስቶስን አገኙ፣ ብዙዎችም ክርስቶስን ተቀበሉ ሲሉ እንሰማለን፣ ክርስቶስ በብዙ ቦታዎች ሲሰበክም እናስተውላለን
… በየቀኑ ብዙዎች ክርስቶስን አገኘን፣ አዲስ መገለጥና አብርሆት ሆነልን ይላሉ፣ አዲሱን ሰው እንለብስ ዘንድ አሮጌውን ሰው ከሥራው
ሁሉ ጋር አስወገድነው ይላሉ . . . ነገር ግን ዛሬም እንደትናንቱ ሥጋዊነቱ ያሸንፋቸዋል፣ በየቀኑ የሚረግሙትን
ሕይወት እነርሱ ራሳቸው ይኖሩታል፣ ሌላውን በነቀፉበት ሥጋዊነትና የጨለማ ሥራ ተይዘው ይገኛሉ፣ የጀመሩትን መፈጸም አቅቷቸው ወይ
ቀድሞ ወደነበሩበት ሕይወት አልተመለሱ ወይ ሆኖልናል በሚሉት አዲስ መገለጥ ፍሬ ማፍራት አልቻሉ ከራሳቸው አልፈው የሚመለከቷቸውን
ሁሉ ግራ ያጋባሉ፡፡
ለክርስቶስ መኖር
ማለት ምን ማለት ነው? ለክርስቶስ መኖር ማለት ራስን ደስ ማሰኘት ነው? የገዛ ፈቃድንስ ማገልገል ነው? በሌሎች ድካምስ መፍረድ ነው? የራስን መረዳት በሌሎች ላይ መጫን ነው? ነው ወይስ
መጽሐፍ ቅዱስን ማወቅና ስለመጽሐፍ ቅዱስ ማውራት ነው? “ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም
ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት
የምኖረው ነው” እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ ክርስትና ማለት የእኛ የምንለውን
ሁሉ ከክርስቶስ ጋር በመስቀል ላይ ሰቅለን፣ የእኔ የምንለውን ሁሉ ስለክርስቶስ ስንል ገድለን ስለክርስቶስ ብለን የምንኖረውና የክርስቶስ
የሆነውን ብቻ የምንፈጽምበትና የምናገለግልበት ሕይወት ነው፡፡ ገላ 2፣20፡፡ ክርስትና ስለክርስቶስ ማስተማርና መስበክ ማለት ብቻ
አይደለም፣ ክርስቶስ ኢየሱስን ማወቅ ብቻም አይደለም፣ ክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ለዓለም ሁሉ መድኃኒት ሆኖ ተገልጧል ማለት ብቻም አይደለም፣ ስለእርሱም ብዙ ማውራትና
መናገርም አይደለም … “ዳሩ ግን። እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ
ደግሞ በኑሯችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ” ተብሎ እንደተጻፈ ክርስትና ከዓለምና ከሥጋ
ርኩሰት እየራቁ በየቀኑ በኑሮአችን ሁሉ ራሳችንን ለክርስቶስ መቀደስ ነው፡፡ 1ኛ ጴጥ 1፣15-16፡፡ “እኔ ክርስቶስን
እንደምመስል እኔን ምሰሉ” እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ ክርስትና ክርስቶስን
እስክንመስለው ድረስ ነፍሳችንንና ሥጋችንን ለክርስቶስ መቀደስ ነው፡፡ 1ኛ ቆሮ 11፣1፡፡ “በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ ባለኝ በእናንተ ትምክህት እየማልሁ፥
ወንድሞች ሆይ፥ ዕለት ዕለት እሞታለሁ” እንዲል በየቀኑ ለእኛ የሆነውን
ሁሉ እየተውን ለክርስቶስ ብለን የምንኖረውና እርሱን ብቻ ደስ የምናሰኝበት ነው፡፡ 1ኛ ቆሮ 15፣31፡፡ “በሕይወትም ያሉት ስለ
እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ዅሉ ሞተ።” እንዲል ክርስትናችን ስለእኛ ለሞተውና ለተነሳው፣
የማይገባንን ብድራት ለከፈለልንና በታላቅ ፍቅር ለወደደን ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምንኖረው ኑሮ ነው እንጂ ለራሳችን የምንኖረው
አይደለም፡፡ 2ኛ ቆሮ 5፣15፡፡
ክርስትና የምናውቀው
ሳይሆን እንዳወቅን የምንኖረው ነው፣ የምንናገረው ሳይሆን እንደተናገርን የምናደርገውና የምንፈጽመው ነው፣ የምንማረው ብቻ ሳይሆን
የምንታዘዘው ነው፣ ሌሎች እንዲያደርጉት የምንጠብቀው ሳይሆን እኛ እራሳችን አድርገን ለሌሎች የምናሳየው ነው፣ አሳባዊ ሳይሆን በተግባር ተፈትኖና ተገልጦ የሚታይ ድርጊት ነው፣ በሥጋ መረዳት የምንደርስበትና
በቃል ብዛት የምንገልጠው ሳይሆን በመንፈስ የምንቃጠልበት ጥልቅ መንፈሳዊነት፤ ከሰው ጥበብና ከሥጋዊ ልማድ በእጅጉ የራቀ ጥልቅ
የመንፈስ ቅዱስ አሠራር ነው፡፡ እንግዲህ ይህንን ሕይወት ነው በአንድ ሰሞን ትጋት፣ በተወሰኑ ሰዎች ሰበካ፣ በማንበብና ከሌሎች
በመስማት ብቻ በሚሆን የአንድ ወቅት “አዲስ መገለጥ” ለመበየን የምንደክመው፡፡ ክርስትና ከእግዚአብሔር ነውና ከእግዚአብሔር ጋር
ሆኖ መምከርና ከእርሱም መማርን ይፈልጋል፡፡ ብዙ ስላወቅን አይደለም ክርስቲያኖች የምንሆነው፣ ብዙ ስለማናውቅም አይደለም በክርስትናችን
ልናድግ ያልቻልነው፡፡ “እግዚአብሔር መንፈስ ነው ፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል።” ተብሎ እንደተጻፈ
ክርስትና መንፈስ ለሚሆን አምላካችን በመንፈስና በእውነት የምንኖረው ሕይወት፣ የምናመልከው አምልኮ፣ የምንጠነቀቅበት ስርዐት እንጂ
አዳዲስ በምንላቸው ራዕዮችና መገለጦች ከእግዚአብሔር የምንርቅበት ሞኝነት አይደለም፡፡ ዮሐ4፣24፡፡
እግዚአብሔር መንፈስ
ከሆነ እንዴት በመንፈስና በእውነት እንስገድ እንዴትስ ወደ እርሱ እንቅረብ ለሚለው ጥያቄ መልሱ አንዲት፣ ቅድስት፣ ኩላዊትና ሐዋርያዊት
በሆነች ቤተክርስቲያን በኩል ነው፡፡ እርሱ ራሱ ‹‹ክብርት የሆነችን ቤተክርስቲያን›› አቅርቦልናልና መሠረቱ አንድ ጊዜ ተመሠርቷል፡፡
‹‹ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው›› (ኤፌ 5፡27)፣ (1ቆሮ 3፡11)፡፡
ዳግመኛም ‹‹በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው›› (ኤፌ 2፡20) ብሎ
ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን የነቢያትና የሐዋርያት መሠረትም በሐዋርያዊያነ አበውና በሊቃውንት ተጠብቆ እኛ ዘንድ የደረሰ በመሆኑ
ማንም ከዚህ ውጪ ከሆነ ከኢየሱስ ክርስቶስ አይደለም፡፡
የክርስትና ሕግ
መንፈሳዊ ነውና “እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ሳይኾንባት ቅድስትና ያለነውር ትኾን ዘንድ ክብርት የኾነችን
ቤተ ክርስቲያን ለራሱ እንዲያቀርብ ፈለገ።” ተብሎ እንደተጻፈ እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ባልኾነባት፤
ቅድስትና ያለነውር በሆነች ክብርት ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ ኢየሱስ የምንለይበት፣ የምንቀደስበትና ወደ እርሱም የምንቀርብበት
ጥልቅ መንፈሳዊነት ያልተለየው የመንፈስ ቅዱስ አሠራር እንጂ የአንድ ሰሞን ወረት ወይም ሥጋዊ ስሜት አይደለም፡፡ ስለሆነም እስከሞት
የወደደንን አምላካችንን በመንፈስና በእውነት ለማምለክ እስክናድግ ድረስ እንተጋለን እንጂ መንፈሳዊውን ሕግ በሥጋ ሕግና አሠራር
አንበይነውም፡፡
No comments:
Post a Comment