Wednesday, March 16, 2016

ጸሎት ለመንፈሳዊ ሕይወት ዕድገት (ክፍል ሁለት)




እንዴት መጸለይ ይገባናል?
በአንድ ወቅት ሐዋርያት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጸልይ ዘንድ አስተምረን ብለውት ነበር፡፡ ሉቃ 11፣1 ፡፡ በእርግጥ መጸለይ እንዳለብን ብቻ ሳይሆን እንዴት መጸለይ እንዳለብንም ልናውቅ ያስፈልገናል፡፡ ጸሎት ሁሉ ተቀባይነት የለውም፡፡ ራሱን በማጽደቅ የጸለየው ፈሪሳዊ ጸሎቱ በእግዚአብሔር ፊት አለመወደዱን ስናስብ ስለጸለይን ብቻ እንደማንሰማ እንገነዘባለን ፡፡ሉቃ 18፣14 ፡፡ በሌላም በኩል ‘‘እጃችሁንም ወደ እኔ ብትዘረጉ ዓይኔን ከእናንተ እሰውራለሁ፥ ልመናንም ብታበዙ አልሰማችሁም እጆቻችሁ ደም ተሞልተዋል፡፡’’ የሚለውን ቃል ስናነብ አምላካችን ወዶና ፈቅዶ የሚቀበለውና ደስ የሚሰኝበት ልመናና ጸሎት የትኛው ነው ብለን እንጠይቃለን፡፡ ኢሳ 1፣15፡፡
‘‘አንተ ግን ስትጸልይ፥ ወደ እልፍኝህ ግባ መዝጊያህንም ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ ጸልይ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል።’’ እንዲል እግዚአብሔር ደስ የሚሰኝበት ጸሎት በእምነት የምንጸልየውና በስውር የለመንነውን በግልጥ የምንከፈልበትም ነው፡፡ ማቴ 6፣6፡፡ ወደ እግዚአብሔር የምንደርስበት ጸሎት በእምነት ሆነን በፊቱ የምንቆምበት እንጂ ለሰዎች የምንታይበትና ራሳችንን የምንገልጥበት አይደለም፡፡ ‘‘ስትጸልዩም እንደ ግብዞች አትኹኑ፤ ለሰው ይታዩ፡ ዘንድ በምኵራብና በመንገድ ማእዘን ቆመው መጸለይን ይወዳሉና፤ እውነት እላችዃለኹ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል።’’ ማቴ 6፣5፡፡ ‘‘አሕዛብም በመናገራቸው ብዛት እንዲሰሙ ይመስላቸዋልና፥ ስትጸልዩ እንደ እነርሱ በከንቱ አትድገሙ።’’ እንደተባልን እውነተኛው ጸሎት በእግዚአብሔር ላይ ያለን እምነትና መደገፍ እንጂ በፊቱ የምናበዛው የቃላት ጥርቅም አይደለም፡፡ ማቴ 6፣7፡፡ ‘‘አንተ ፊቴን እሹት ባልህ ጊዜ። አቤቱ፥ ፊትህን እሻለሁ ልቤ አንተን አለ።’’ ተብሎ እንደተፃፈ ጸሎት የእግዚአብሔርን ፊት የምንሻበትና የምናይበትም እንጂ ከአምላካችን ጋር ሕብረት ሳናደርግበት ዝም ብለን የምንናገረው የቃላት ህግ ወይም በልማድ የምናደርገው ንግግር አይደለም፡፡ መዝ 26፣8፡፡ ጸሎት የእግዚአብሔርን ፊት መሻት፣ ማየትና በፊቱም መሆን ነውና ቃላት ከአፋችን ሳይወጡ እርሱ መሻታችንን ያያል፣ የውስጣችንን ይሰማልናል፣ የሚያስፈልገንንም ያደርግልናል፡፡ ‘‘ሳትለምኑት አባታችኹ የሚያስፈልጋችኹን ያውቃልና።’’ ማቴ 6፣8፡፡ በእምነትና በመንፈስ የምንጸልየው ጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር የምንሆንበትና ሕብረት የምናደርግበት ስለሆነ እጅግ ደስ እንሰኝበታለን፡፡ ‘‘እኔ ግን በጽድቅ ፊትህን አያለሁ ክብርህን ሳይ እጠግባለሁ።’’ መዝ 16፣15፡፡
መቼ ነው መጸለይ ያለብን?       
እንግዲህ ጸሎት የእግዚአብሔርን ፊት መሻትና ማየት ከሆነ በቀን ውስጥ በምንችልበት ጊዜና አጋጣሚ ሁሉ ፊቱን መሻትና በፊቱ መሆን የተገባ ነው፡፡ ጸሎታችን እንዴትም ያለ ይሁን (ረጅምም ሆነ አጭር) በምንችለው አቅም ሁሉ በጸሎት የአምላካችንን ፊት መሻትና ማየት ክርስቲያናዊ ግዴታችን ነው፡፡ በአገኘነው አጋጣሚና ጊዜ ሁሉ በአምላካችን ፊት ለጸሎት መቆም እጅግ ደስ የሚያሰኝና የሚጠቅም ተግባር ነው፤ ሆኖም ግን ሰዎች በተለያየ ምክንያት ልንደክምና ልንዘነጋ ስለምንችል በቀን ሰባት ጊዜ ያህል እንድንጸልይ ስርዐተ ቤተ ክርስቲያን ተሰርቶልናል፡፡ በማናቸውም ቦታና በምንም አይነት ሁኔታ ውስጥ ብንሆን ልንጸልይና የእግዚአብሔርን ፊት ልንሻ ያስፈልገናል፡፡ በእርግጥ በተለያዩ ምክንያቶች ለቀኑ የተሰሩልንን የጸሎት ስርዐቶች መፈፀም ባንችል እንኳን ለየቀኑ ክፍለ ጊዜያት የተሰሩልንና የተመደቡልንን የጸሎት ክፍለ ምንባባት አስቦ መዋሉ የተገባ ነው፡፡
1. ጸሎተ ነግህ/የጠዋት ጸሎት፡- በዚህ የጸሎት ጊዜ የአዝማናትን ጌታ፣ ብርሀንንና ጨለማን የፈጠረ፣ ጊዜን በእድሜያችን ላይ የሚጨምር፣ ጨለማን የሚያነጋ፣ ከጨለማ ክፉ ስራ የሚሰውር፣ አዲስ ቀንን የሚሰጥ … እግዚአብሔርን እናመሰግናለን፡፡ ይህ ክፍለ ሰዓት አዳም የተፈጠረበትና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጲላጦስ ፊት ለፍርድ የቆመበትም ስለሆነ ይህንን እያሰብን እንጸልያለን፡፡ እርሱ ንጹህ ሲሆን ስለ እኛ ሲል ተከሶልናልና፣ ሰማያዊው ዳኛ ምንም በደል ሳይኖርበት ስለበደላችንና ስለመተላለፋችን ተፈርዶበታልና ይህን እያሰብን እንጸልያለን፡፡ በዚህ ሰዓት መዝ 5 እና መዝ 62 ይጸለያል፡፡
2. ጸሎተ ሰለስት/የሦስት ሰዓት ጸሎት፡- በዚህ የጸሎት ክፍለ ጊዜ ሦስት ነገሮችን እያሰብን እንጸልያለን ይኸውም፡- የሔዋንን ከአዳም ጎን መገኘት፣ የእመቤታችንን ሐዲስ ብሥራትና የጌታችንን በጲላጦስ ፊት ቀርቦ መገረፍ ነው፡፡ በዚህም ውስጥ የእግዚአብሔርን ድንቅ ስራና ፍለጋውንም እናደንቃለን፡፡ ምንም በደል ሳይኖርበት እርሱ ስለእኛ ተገርፎ በመገረፉ ቁስል ፈውሶናልና የመድኃኒታችንን ታላቅ ፍቅሩንና መውደዱን እያሰብን እንጸልያለን፡፡ በዚህ ሰዓት መዝ 129 ይጸለያል፡፡
3. ጸሎተ ጊዜ ስድስቱ ሰዓት/የእኩለ ቀን ጸሎት፡- በዚህ የጸሎት ክፍለ ጊዜ የጌታችንንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን በቀራንዮ አደባባይ ስለዓለሙ ሁሉ ፍቅር እርቃኑን መሰቀሉን እያሰብን እንጸልያለን፡፡ እንዲህ ባለ ታላቅ ፍቅር የወደደንን የአምላካችንን ብዙ ፍቅር እናደንቃለን፡፡ በዚህ ሰዓት መዝ 53 ይጸለያል፡፡
4. ጸሎተ ጊዜ ተሰዐቱ ሰዓት/የዘጠኝ ሰዓት ጸሎት፡- በዚህ የጸሎት ክፍለ ጊዜ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሆኖ ነፍሱን ስለሁላችን መዳን ቤዛ አድረጎ መስጠቱን እያሰብን እንጸልያለን፡፡ ጌታችን በተሰቀለበት ዕለት ልክ ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ስጋው በሥልጣኑ ለይቷልና፡፡ በሞቱ የሆነልንን ሕይወት እናስተውላለን፤ ይህንንም ታላቅ ሕይወት በጥንቃቄ እንጠብቀዋለን፡፡ በዚህ ሰዓት መዝ 89 ይጸለያል፡፡
5. ጸሎተ ሰርክ/ የምሽት ጸሎት፡- በዚህ የጸሎት ክፍለ ጊዜ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመስቀሉ መከራ በኋላ ወደ መቃብር መውረዱን እያሰብን እንጸልያለን፡፡ ሞትንና መቃብርን ሊያጠፋ መሞቱንና ወደ መቃብር መወረዱን በዚህም ወደ ሕይወት መመለሳችንን እናስባለን፡፡ በዚህ ሰዓት መዝ 140 ይጸለያል፡፡
6. ጸሎተ ንዋም/የመኝታ ጸሎት፡- በዚህ የጸሎት ክፍለ ጊዜ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለመከራ ተላልፎ በተሰጠባት ምሽት በጌቴ ሰማኒ ባለ የአትክልት ስፍራ ሆኖ መጸለዩንና ጭንቀታችንንና የሞታችንን ጣእር ማጥፋቱን እናስባለን፡፡ በዚህ ሰዓት መዝ 142 ይጸለያል፡፡
7. ጸሎተ መንፈቀ ሌሊት/ የእኩለ ሌሊት ጸሎት፡- በዚህ የጸሎት ክፍለ ጊዜ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትንና የሞትን ጣእር አጥፍቶ በእኩለ ሌሊት ከሙታን በኩር ሆኖ መነሳቱንና በትንሣኤው የሆነልንን ትንሣኤ እያሰብን እንጸልያለን፡፡  በዚህ ሰዓት መዝ 118 ዛይ እና ሔት ይጸለያል፡፡
ከነዚህም በተጨማሪም ጊዜ ያልተወሰነባቸው ጸሎቶች የማዕድ ጸሎት፣ የመንገድ ጸሎት፣ መከራን ለማራቅ የፈቃድ ጸሎት፣ የንስሓ ጸሎት፣ ፈቃድ የሚፈጸምበት (ልጅን፣ ጥበብን እንደመሻት ያለ) ጸሎቶች ናቸው፡፡ (በፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 14)፡፡
ፍትሐ ነገሥት ‹‹…በጸሎት ጊዜ የሚያነቡት በወንጌልና በመጽሐፍ የተጻፈ ነው፡፡ አባታችን ሆይ ብላችሁ ጸልዩ፡፡ እንዲሁም በጸሎት መጨረሻ ሁሉ ጸሎተ ሃይማኖት በሉ›› ይላል፡፡ በተጨማሪም ‹‹በቀንና በሌሊት የሚጸለየው ጸሎት ከዳዊት መዝሙር ይሁን በውስጡ ምስጋና፣ መማለድ፣ የፈጣሪን አንድነቱን መናገር፣ ኃጢአትን ማመን ስላለበት›› በማለት ይደነግጋል፡፡
… ይቀጥላል …

No comments:

Post a Comment