(ክፍል አንድ)
- እግዚአብሔር በገናንነቱ ገናና ነው፤ በቅድስናው የተቀደሰ ነው፤ በምስጋናው የተመሰገነ ነው፤ በክብሩም የከበረ ነው፡፡
- ከመቼ ወዲህ የማይሉት ቀዳማዊ ነው፤ እስከዛሬ የማይሉት ማእከላዊ ነው፣ እስከዚህ የማይሉትም ደኃራዊ ነው፡፡
- ለአነዋወሩ ጥንት የለውም፤ ለአኳኋኑም ፍጻሜ የለውም፤ ለዘመኑ ቁጥር የለውም፤ ለውርዝውናውም ማርጀት የለበትም፤ ለኃይሉም ጽናት ድካም የለበትም፤ ለመልኩ ጥፋት የለበትም፡፡ ለፊቱ ብርሃንም ጨለማ የለበትም፡፡
- ለጥበቡ ባሕር ድንበር የለውም፤ ለትእዛዙም ይቅርታ መስፈርት የለውም፤ ለመንግሥቱ ስፋት ዐቅም ልክ የለውም፣ ለአገዛዙም ስፋት ወሰን የለውም፡፡
- በኅሊና የማያገኙት ሥውር ነው፤ በልቡናም የማይረዱት ምጡቅ ነው፤ አንሥርት የማይደርሱበት ረጅም ነው፤ ዓሣዎች የማይዋኙበት ጥልቅ ነው፡፡
- ከተራሮች ራስ ይልቅ ከፍ ያለ ነው፤ ከባሕር ጥልቅነት ይልቅ ጥልቅ ነው፤ ነገሥታት የማይነሳሱበት ጽኑ ነው፤ መኳንንት የማይቃወሙት አሸናፊ ነው፡፡
- የጥበበኞችን ምክር የሚያጠፋ ጥበበበኛ ነው፤ የሚመክሩትን ሰዎች አሳባቸውን የሚያስረሳ ዐዋቂ ነው፤ የጸኑ ልጓሞችን የሚፈታ ኃያል ነው፤ የኃጥአንን ጥርሶች የሚያደቅ፣ የትእቢተኞችንም ክንድ የሚቀጠቅጥ ብርቱ ነው፡፡
- የግብዞችን ፊት የሚያዋርድ ክቡር ነው፤ የዝንጉዎችን ብርሃን የሚያርቅ ከሃሊ ነው፡፡
- ባልንጀራ የሌለው አንድ ነው፤ ዘመድ የሌለው ሥሉጥ ነው፤ ሰማያት ይጠፋሉ፤ የብስም ትጠፋለች፤ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃል፡፡ እርሱ ግን እስከ ዘለዓለሙ እርሱ ነው፡፡
- የባሕር መመላለሷ ድንቅ ነው፤ ድንቅስ በልዕልናው እግዚአብሔር ነው፤ የሚመስለው የለም፤ ከፍጥረትም ሁሉ ከአማልክትም ልጆች ሁሉ የሚተካከለው የለም፡፡ እርሱ ብቻ አምላክ ነው፤ እርሱም ብቻ ጌታ ነው፤ ፈጣሪም እርሱ ብቻ ነው፤ ሠሪም እርሱ ብቻ ነው፡፡
- ስላሰበው ጥበብ እረዳት አይሻም፤ ስለ ወደደውም ሥራ መካር አይሻም፡፡ ሳይሆን ቀድሞ እንደ ሆነ አድርጎ፤ ያልተደረገውንም እንደ ተደረገ አድርጎ ሁሉን ያውቃል፡፡
- ሳይጠይቅ ኅሊናን ይመረምራል፤ ሳይመረምር ልቡናን ይፈትናል፤ ያለመብራት በጨለማ ያለውን ያያል፡፡
- ጻድቁን ጽድቅን ሳይሠራ ያውቀዋል፤ ኃጥኡንም ኃጢአት ሳይሠራ ያውቀዋል፤ ልበኞችን ከአባታቸው ወገብ (አብራክ) ሳይወጡ ያውቃቸዋል፤ ኃጥአንንም ከእናታቸው ማኅጸን ያውቃቸዋል፡፡
- የሚሸሸገው የለም የሚሰወረውም የለም፤ ከእርሱም የሚሰወር የለም፤ ሁሉ በእርሱ ዘንድ የተገለጸ ነው፤ በዓይኖቹም ፊት ሁሉ የተዘረጋ ነው፡፡ ሁሉ በመጽሐፉ የተጻፈ ነው፤ በኅሊናውም ሁሉ የተጠራ ነው፡፡
- ቁጥር የሌላቸው ታላላቆችን፣ መመርመር የሌለባቸውን የተደነቁ፣ የከበሩ ሥራዎችን ይሠራል:: ሥራው ካየነው ይልቅ እጹብ ነው፤ ኃይሉም ከሰማነው ይልቅ ድንቅ ነው፤ ጌትነቱም ከነገሩን ይልቅ ድንቅ ነው፡፡
- ከጨለማ ለይቶ ብርሃንን ፈጠረ፣ ደመናውን መለየት ያውቃል፡፡ ውኃውን እንደወደደ ይከፍለዋል፤ የተመረጡትን በደመና ይሠውራል፡፡
- ምድርን ፈጠራት መጠኗንም አዘጋጀ፤ ፍጻሜዋንም እንደምንም ተከለ፤ ማዕዘኗንም አጸና፡፡
- ባሕርን ከእናቷ ሆድ በወጣች ጊዜ በበሮች አጠራት፡፡ ልብሷንም ደመና አደረገላት፤ በጉም ጠቀለላት፤ ወሰን አደረገላት፤ በውስጧም መዝጊያዎችንና ቁልፎችን አደረገላት፡፡ ‘‘እስከዚህ ድረሺ፤ ከወሰንሽም አትተላለፊ፤ ማዕበልሽ በውስጥሽ ይመላለስ (ይነቃነቅ) እንጂ’’ አላት፡፡
- በበላይዋ ላይ የንጋት ብርሃን ተዘጋጀ፤ የአጥቢያ ኮከብም ትእዛዙን ዐወቀ፡፡ እርሱ ከምድር ጭቃን ነሥቶ ሕያው የሆነውን ፈጠረ፡፡ በምድርም ላይ እንዲነጋገር አደረገው፡፡
- እርሱ እስከ ዓለም ዳርቻ ደረሰ፡፡ በጥልቅ ፍለጋም ተመላለሰ፡፡
- ከግርማው የተነሳ የሞት ደጆች ይከፈታሉ፤ የሲኦል በሮችም ባዩት ጊዜ ይደነግጣሉ፡፡ ከሰማይ በታች ያለውን ስፋቱን፣ ከሰማይ በላይ የሚሆነውንም እርሱ ያውቀዋል፡፡
- በእርሱ ትእዛዝ ዋግ ከመዝገቡ ይወጣል፡፡ ከሰማይ በታች ያለ አዜብ (ነፋስ ) ይመላለሳል፡፡ ዝናምን በምድረበዳ ያጸናዋል፣ ሰው በሌለበትና የሰው ልጅ በማይኖርበት ይዘንም ዘንድ፡፡
- እርሱ የውኃውን መፍሰሻ ወሰነ፤ ክረምትንም በያመቱ ይከፍታል፤ በጋውንም ኋላ በጊዜው ጊዜ ያመጣዋል፡፡ደመናውንም በቃሉ ይጠራዋል ውኃም እየተንቀጠቀጠ ይመልስለታል፡፡
- ብልጭልጭታውንም እርሱ ይልከዋል፤ እርሱም ይሄዳል፤ ‘‘ምንድር ነው?’’ እያለ ይመልስለታል፡፡ እርሱ ደመናን በጥበቡ ይቆጥረዋል፡፡ ሰማይን (ጠፈርን ) ወደ ምድር ያዘነብለዋል፡፡
- እርሱ ብቻ የአርያምን ኃይል ለበሰ፤ በምስጋናና በክብር ተጌጠ፡፡
- እሳታውያን ኪሩቤል፣ ብርሃን የለበሱ ሱራፌልም እርሱን ያመሰግናሉ፡፡ በማያርፍ ቃል፣ ዝም በማይል፣ በማይደክምም አንደበት ሁሉም ተባብረው ተሰጥዎ ባለበት ባንድ ቃል ‘‘የጌትነትህ ምስጋና በሰማይ በምድር የመላ ፍጹም አሸናፊ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር’’ ይላሉ፡፡
- ፍጹም አሸናፊ እግዚአብሔር የጌትነትህ ምስጋና በሰማይና በምድር የመላ ነው፡፡
- ሁሉ ከእርሱ ነው፣ ሁሉም ስለእርሱ ነው፣ ሁሉም የእርሱ ነው፣ ሰማይ በእርሱ ነው፣ ከሰማያት በላይ ያለ ሰማይም የእርሱ ነው፣ የአርያም ስፋት የክብሩ ዙፋን ነው፣ የምድርም ስፋት የእግሩ መመላለሻ ናት፡፡
- ፀሐይ የእርሱ ነው፣ ጨረቃም ከእርሱ ነው፣ ከዋክብትም የእጁ ሥራ ናቸው፣ ደመናት መልክተኞቹ፣ ነፋሳትም ሠረገላዎቹ ናቸው፣ እሳትም የቤቱ ግርግዳ ነው፡፡
- የቤቱ ጠፈር ውኃ ነው፣ የዙርያውም ጸፍጸፍ የበረድ ሰሌዳ ነው፣ ድንኳኖቹ ብርሃናት ናቸው፡፡ የመሰወሪያ መጋረጃውም የብርሃን መብረቅ ነው፤ መመላለሻውም በአየር ነው ::
- የመናገሩ ድምፅ በብልጭልጭታ ያለ ነው፡፡ የነጎድጓዱ ቃል በሠረገላዎች አለ፡፡ ባሕር ባሪያው ናት፣ የወንዝ ፈሳሾች ተገዥዎቹ ናቸው፡፡ ቁር አስሐትያም ፈቃዱን የሚሠሩ ናቸው፡፡
- ከምድር ዳርቻ ደመናውን ያወጣል፣ መብረቅንም በዝናም ጊዜ አደረገ፣ ዝናምንም እንደ መሽረብ ነጠብጣብ ያፈሳል፣ ጉምን እንደ አመድ ይበትነዋል፣ በረድንም እያጠቃቀነ ያወርዳል፣ ለእንስሳም ሣሩን ያለመልማል፡፡
- እንዳሰበ ያደርጋል፣ እንደ ጀመረም የጀመረውን ይፈጽማል፣ እንደወደደም ያከናውናል፡፡ ያሳዝናል፣ ደስ ያሰኛል፤ ያደኸያል፣ ባለጸጋም ያደርጋል፡፡ ያዋርዳል፣ ያከብራል፤ ይገድላል፣ ያድናልም፤ ድውይ ያደርጋል፣ ይፈውሳልም፤ ይኮንናል፣ ያጸድቃልም፡፡
- የወደደውን ይምራል፣ ሊያስጨንቀው የወደደውን ያስጨንቃል፣ የሚምረውን ይምረዋል፡፡ ይቅር የሚለውን ይቅር ይለዋል፡፡
No comments:
Post a Comment