Thursday, July 28, 2016

‘‘ኃያላን እንዴት ወደቁ! የሰልፍም ዕቃ እንዴት ጠፋ!’’ 2ኛ ሳሙ 1፣27፡፡



(ክፍል አንድ)
መጽሐፍ ቅዱስ ከሚነግረን እውነት ውስጥ አንደኛው ኃያላን የነበሩ ሰዎች እንዴት እንደወደቁና በሰልፍ የበረቱትም እንዴት እንደተሸነፉ ነው፡፡ ኃያላን የሚባሉት በሰማያዊው ሀብትና ጸጋ የበረቱትና ብዙ ድንቆችን የፈጸሙት፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሱት ሰዎች ሲሆኑ ሰልፍ ተብሎ የተጠቀሰውም የሚያመለክተው የሰው ልጅ በምድር ላይ ሲኖር የሚያልፍባቸውን የሕይወት ምዕራፎች ነው፡፡ ‘‘በምድር ላይ የሰው ሕይወት ብርቱ ሰልፍ አይደለምን?’’ እንዲል፡፡ ኢዮ 7፣1፡፡ ክርስቲያኖች ሆነን በዚህች ምድር ላይ ስንኖር በመንፈሳዊውም ሆነ ሥጋዊ ኑሯችን የሚገጥሙን የተለያዩ ተግዳሮቶች ስላሉ እነዚህ ተግዳሮቶች ራሳችንን ለእግዚአብሔር ፈቃድና ሃሳብ የምንለይባቸውና የምንታገልባቸው (የምንዋጋባቸው) ሰልፎች ናቸው፡፡ እነዚህን ሰልፎች በድል የምንወጣባቸውን የሰልፍ ዕቃዎች ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ይነግረናል፡- ‘‘የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችኹ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ዅሉ ልበሱ። መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋራ አይደለምና፥ ከአለቃዎችና ከሥልጣናት ጋራ ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዢዎች ጋራ፥ በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሰራዊት ጋራ ነው እንጂ። ስለዚህ፥ በክፉው ቀን ለመቃወም፥ ዅሉንም ፈጽማችኹ ለመቆም እንድትችሉ፥ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ዅሉ አንሡ። እንግዲህ ወገባችኹን በእውነት ታጥቃችኹ፥ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችኹ፥ በሰላም ወንጌልም በመዘጋጀት እግሮቻችኹ ተጫምተው ቁሙ፤ በዅሉም ላይ ጨምራችኹ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ዅሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤ የመዳንንም ራስ ቍር የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው።’’ ኤፌ 6፣11-17፡፡ በሰልፍ ውስጥ መውደቅና መሸነፍ የምንለው ከእግዚአብሔር ምክርና ፈቃድ ውጪ መጓዝና ፈቃዱን መፈጸም አለመቻል፣ እንደቃሉ አለመኖር፣ በምድራዊ ሐሳብና በስጋዊ ምኞት መሸነፍ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ራስን ደስ ማሰኘት . . .    እንደሆነ ታሪካቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ከተመዘገበ የተለያዩ ሰዎች ሕይወት እንማራለን፡፡ ቅዱሳን የምንላቸው በኑሯቸው ሁሉ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኙና ፈቃዱን ያገለገሉ ሰዎች እንደሁኑ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ ‘‘ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ፥ እግዚአብሔርም ስለ ወሰደው አልተገኘም፡፡ ሳይወሰድ እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘ ተመስክሮለታልና’’ ዕብ 11፣5፡፡ ሄኖክ ሞትን እንዳያይ የተወሰደው በኑሮው ሁሉ እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘቱ ስለተመሰከረለት ነው፡፡ እግዚአብሔርን በኑሯችን ሁሉ ደስ ማሰኘት ካልቻልን በሰልፉ ውስጥ ተሸናፊዎች እንሆናለን፡፡
በእርግጥ ብዙ ኃያላንና ብርቱዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ላይ እናገኛለን፡፡ ብዙ ብርቱዎችና ኃያላን እግዚአብሔር ስላገዛቸውና ስለረዳቸው ብዙ ድንቆችንና ተአምራትን በእግዚአብሔር ስም እንዳደረጉም እናነባለን፡፡ ታናሹ ብላቴና ዳዊት የጦሩን ሰው ጎልያድን በወንጭፍ እንዳሸነፈው (1ኛ ሳሙ 17)፣ ጌድዮን ሦስት መቶ ሰዎችን ብቻ ይዞ ብዛታቸው እንደ አንበጣ የኾነ ምድያማውያንና ዐማሌቃውያንን፣ የምሥራቅንም ሰዎች እንዳሸነፈ (መሳ 7)፣ ቅዱስ ጴጥሮስ በአንዲት ቀን ስብከት ሦስት ሺህ ነፍሳትን ወደ ክርስቶስ መንግስት እንዳፈለሰ ( ሐዋ 2)፣ ቅዱስ ጳውሎስ በልብሱ ጨርቅ እንኳን ሳይቀር ብዙ ድንቆችንና ተአምራትን ያደርግ እንደነበር (ሐዋ 19) . . . ይነግረናል፡፡ እንደኛ ሰዎች ቢሆኑም ነገር ግን አካሄዳቸው እግዚአብሔርን ደስ ስላሰኘው በእጃቸው ብዙ ድንቅና ተአምራት ሊደረግ እንደቻለ እናነባለን፡፡ ከሐዋርያትም በኋላ የተነሱ የቤተ ክርስቲያን አባቶችና ሊቃውንት ሕይወታቸውንና ፈቃዳቸውን ሁሉ ለእግዚአብሔር መስጠት ስለቻሉ እግዚአብሔር አምላካችን ብዙ ተአምራትንና ድንቆችን በእነርሱም ላይ አድሮ ፈጽሟል፡፡ በቅርቡ ዘመን ታሪክም ራሳቸውን ለእግዚአብሔር የለዩና ፈቃዳቸውን ለፈቃዱ መተው የቻሉት ቅዱሳን አባቶቻችንና እናቶቻችንም ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ አድርገው ብዙ ተአምራትን እንደፈጸሙ እናነባለን፡፡ በእኛው ማህበረሰብ ውስጥ የተፈጠሩ ኢትዮጵያውያን ቅዱሳን ከእግዚአብሔርና ከተቀደሰ ሕይወታቸው የተነሳ ብዙ ድንቆችን እንዳደረጉ ታሪክ እንኳን ሳይቀር ይመሰክርልናል፡፡
ተአምራትና ድንቅ ለእግዚአብሔር የባህርይ ገንዘቦቹ ናቸው፡፡ እርሱ ሁሉን ይችላልና፣ የሚሳነውም ነገር የለምና በቅዱሳኑ እያደረ ኃይሉንና ተአምራቱን ይገልጣል፡፡ ቅዱሳኑ በሕይወታቸው ደስ አሰኝተውታልና፤ በኑሯቸውም ሁሉ ፈቃዱንና ሐሳቡን ተከትለው የራሳቸውን ፈቃድና ሐሳብ መተው ችለዋልና እግዚአብሔር አምላካቸው ተብሎ በእነርሱ ሊጠራ አያፍርባቸውም፡፡ ዕብ 11፣16፡፡ በዚህም የተነሳ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደምናነበው፣ ከቤተ ክርስቲያን ታሪክም አንደምንረዳው ብዙ ቅዱሳን ሰዎች የእግዚአብሔርን ክብር መግለጥ ችለዋል፣ ብዙዎችን ወደ መዳን መንገድ መርተዋል፣ በተአምራትና በድንቅ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሰብከውታል፡፡ በዚህ ሁሉ ወስጥ ግን ‘‘የኃይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳይሆን’’ እያሉ ክብሩን ሁሉ ለአምላካቸው ስለተዉ ከጅማሬያቸው የሚልቅን ፍጻሜ ሊቀበሉ ችለዋል፡፡ 2ኛ ቆሮ 2፣7፡፡ ‘‘ስለዚህም በመገለጥ ታላቅነት እንዳልታበይ የሥጋዬ መውጊያ፥ እርሱም የሚጎስመኝ የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ፤ ይኸውም እንዳልታበይ ነው’’ እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ በእጃቸው የተደረገው ድንቅና ተአምር ሁሉ ከእግዚአብሔር መሆኑን ተረድተው እግዚአብሔርን ብቻ እንጂ ራሳቸውን ስላላከበሩ ቢወድቁ እንኳን እየተነሱ በኋላ ዘመን ለምንነሳ ክርስቲያኖች ሁሉ ሳይቀር አርአያና ምሳሌ ሆኑልን፡፡ 2ኛ ቆሮ 12፣7፡፡
እውነተኛው የክርስትና ትምህርት እንዲህ ያለ ነው፡፡ በነገር ሁሉ እስከ ሞት የወደደንን መድኃኒታችንን ደስ ማሰኘት፤ የእርሱንም ፈቃድ ብቻ መፈጸምና ማገልገል፡፡ ክርስትና የሚፈልገው ራስን ማክበር ሳይሆን ‘‘እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ያስፈልጋል’’ ማለትን ነው፡፡ ዮሐ 3፣30፡፡ እስኪ በዘመናችን ካሉ ክርስቲያኖችና አገልጋዮች መካከል ‘‘እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ያስፈልጋል’’ የሚል ማን ነው? በአገልግሎትና በወንጌል ሽፋን የራሱን ፈቃድ ለማቆም የማይሞክር ማን ነው? በዚህ ዘመን እየሆነና እኛም እያየነው ያለነው ስለክርስቶስና ስለወንጌል ሲሉ ለመተውና ለመሸነፍ የተዘጋጁ አገልጋዮችንና ክርስቲያኖችን ሳይሆን ማሸነፋቸውን በክርስቶስ ስምና በመንፈሳዊነት ሽፋን ለማጽደቅ የሚሞክሩትን ነው፡፡ ከክርስቶስ ግን እንዲህ አልተማርንም ክብር የሚገባው እርሱ፤ ክብርም ደግሞ የባሕርይ ገንዘቡ የሆነ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከልዑል ቦታው ወርዶ በበረት ሲያድር፣ በግርግም ሲተኛ፣ አምላከ ሆኖ ሳለ ሰው ሲሆንና በምድር ላይ በደካማ ማንነት ሲገለጥ መዳናችንን በዝምታ ነው የሰራልን፡፡ መጽሐፍ ‘‘አፉን አልከፈተም’’ እንዲል በጎውን ከማድረግ ባለፈ በአንደበቱ ሀሰት አልተገኘበትም፣ በከሳሾቹም ፊት አንዳች አልተናገረም፡፡ እርሱ ዝም ብሎ ነበር ሥራውን ይሰራ የነበረው፡፡ ኢሳ 53፣7፤ ሐዋ 8፣32፡፡ እኛ ግን ስለራሳችንና ስለታላቅነታችን አውርተን አንጠግብም፣ እግዚአብሔር በእኛ ውስጥ ስለሰራው ሥራ እርሱን ሳይሆን ራሳችንን ልናከብር እንወዳለን፡፡ እርሱ ግን እጅግ ታላቅ ሲሆን ራሱን አላከበረም፡፡ ‘‘እኔ ራሴን ባከብር ክብሬ ከንቱ ነው፤ የሚያከብረኝ እናንተ አምላካችን የምትሉት አባቴ ነው’’ እንዳለ ክብርን ከላይ ከአባቱ ዘንድ እንጂ ከምድር አልፈለገም ነበር፡፡ ዮሐ 8፣54፡፡ ከክርስቶስ የተማርነው ይህንን ነው፤ ዝም ብሎ የሰማዩን አባታችንን ፈቃድ መፈጸም፣ የእርሱን ሃሳብ ማገልገል፡፡ እኛ እንደምንፈልገው ሳይሆን እርሱ እንደሚፈልገው ማድረግ፤ እኛ እንዳሰብንና እንደፈቀድን ሳይሆን እርሱ እንዳሰበና እንደፈቀደ መፈጸም፤ በእሺታ መንፈስ መታዘዝ፡፡ ይህ በሚሆንበት ጸብና ክርክር፣ ቁጣና አድመኝነት፣ ጥልና መለያየት፣ ራስን ማክበርና ደስ ማሰኘትስ ከወዴት ይመጣሉ?
እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ‘‘ነገር ግን ሩጫዬንና ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን አገልግሎት እርሱም የእግዚአብሔርን ጸጋ ወንጌልን መመስከር እፈጽም ዘንድ ነፍሴን በእኔ ዘንድ እንደማትከብር እንደ ከንቱ ነገር እቆጥራለሁ፡፡’’ ማለት ካልቻልን እውነተኞች የእግዚአብሔር መንግስት ሰራተኞች ልንሆን አይቻለንም፡፡ ሐዋ 20፣24፡፡ መንፈሳዊነት ለእግዚአብሔር ሐሳብ መሸነፍ ነው፣ የእግዚአብሔርንም ሥራ በመንፈስና በትህትና መሥራት ነው፡፡ በስጋዊነት፣ በስሜትና በስጋዊ ጥበብ መድከም፤ በዚህም ለማሸነፍ መጣር አይደለም፡፡ ‘‘አዎን፥ በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ እውቀት ነገር ሁሉ ጉዳት እንዲሆን እቆጥራለሁ፤ ስለ እርሱ ሁሉን ተጐዳሁ፥ ክርስቶስንም አገኝ ዘንድ፥ በክርስቶስም በማመን ያለው ጽድቅ ማለት በእምነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ያለው ጽድቅ እንጂ ከሕግ ለእኔ ያለው ጽድቅ ሳይሆንልኝ፥ በእርሱ እገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጕድፍ እቆጥራለሁ፡፡’’ ይህ ነው እንግዲህ ክርስትና፡- ከእኛና ከዚህች ምድር የሆነውን ሁሉ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታችን እውቀት ብለን ጉዳት እንደሆነ መቁጠር፣ በእምነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ያለውን፤ በመንፈስ ከምናመልከው አምላካችን የሚደረግልንን ጽድቅ መጠበቅ፣ በእርሱ እንገኝ ዘንድ ሁሉን እንደጉድፍ መቁጠር፡፡ ፊል 3፣8-9፡፡ እንዲህ የሚያደርጉ መንፈሳውያን ባሉበት ጸብና ክርክር፣ ጥልና መለያየት፣ ነቀፌታና ፈራጅነት፣ ወንድምን መርታትና ማሸነፍ ከወዴት ይመጣሉ? በእርግጥም ላይኛይቱ ጥበብ መንፈሳዊትና ፍጽምትም ናት፣ ከስጋዊ ሐሳብና ምክርም በእጅጉ የራቀች ናት፣ ወንድምን የምትወድና ደስ የምታሰኝም ናት፡፡ ‘‘ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፥ በኋላም ታራቂ፥ ገር፥ እሺ ባይ ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባት፥ ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት፡፡’’ ያዕ 3፣17፡፡
አሁን ባለንበት በዚህ ዘመን የእግዚአብሔር አገልጋዮችና የወንጌል ሰባኪዎች ነን ብለን ራሳችንን የገለጥን አንዳንድ ሰዎች አለን፡- ቃሉን ስናስተምር ደስ እናሰኝ የነበርን፣ ብዙዎችን ወደ መንጋው የቀላቀልን፣ ለክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን የደከምን፣ ስለ ፍቅር ያስተማርን፣ ስለ ይቅርታ የሰበክን፣ ስለ አንድነት የመከርን፣ በእምነት ስለመጽናት የተናገርን፣ እንደዋኖች ሆነን ራሳችንን የገለጥን . . . ከዚህ ሁሉ በኋላ ግን ለሌሎች ባስተማርነው ቃል መጽናት ተስኖን የወደቅን፣ ፍቅርን እንዳላስተማርን በጥላቻ ውስጥ ሆነን የተገኘን፣ ስለ ይቅርታ እንዳልሰበክን ይቅርታ ለማድረግ የሰነፍን፣ ስለ አንድነት እንዳልመከርን መለያየትን ስንዘራ የተደረሰብን፣ በእምነት ስለመጽናት እንዳልተናገርን ከእምነት መንገድ ወጥተን የሚያስነቅፍ ነገር የተገኘብን . . . ብዙ ታላላቆችና ኃያላን ዛሬ ላይ እንደትናንቱ ሆነን አልተገኘንም፡፡ ትናንት የነበረን በጎነት፣ ቅንነት፣ መንፈሳዊ ቅድስና፣ ትህትና፣ እግዚአብሔርን መፍራት . . . ዛሬ ላይ አልተገኘብንም፡፡ ስለ ሃይማኖት ሰውነታችን ብዙዎች እንዳልተከራከሩልን ዛሬ ላይ ለብዙዎች የመሰናክል ደንጊያ ሆነን የሃማኖታችንን ፍሬ ለሌሎች ማሳየት ያቃተን፤ ግን ደግሞ አሁንም ራሳችንን የሃይማኖት አገልጋዮች አድረገን የምንቆጥር አለን፡፡ በእርግጥ ግን ከትናንት ኃያልነታችን ዛሬ እንዴት ልንወድቅ ቻልን? መንፈሳዊነታችንስ እንዴት ሊጠፋ ቻለ?
ይቀጥላል . . .

No comments:

Post a Comment