(ክፍል ሁለት)
በራሳቸው ኃይልና ጥበብ ሲደገፉ፡- “እግዚአብሔር አንድ ጊዜ ተናገረ፥ እኔም ይህን ብቻ ሰማሁ ኃይል የእግዚአብሔር ነው” መዝ 61፣11፡፡ እግዚአብሔር ካልረዳንና ካላገዘን
በቀር በራሳችን ኃይልና ጥበብ ብቻ የምንፈጽመው ማናቸውም አይነት ተግባር ውጤታማ አንሆንበትም፡፡ “ያለእርሱ ፈቃድ የበላ፤
ደስ ብሎትም ተድላን የቀመሰ ማን ነው?” ይላልና፡፡ መክ 2፣25፡፡ በተለይ ደግሞ መንፈሳዊው አገልግሎት ለእግዚአብሔር ብለን
የምንፈጽመው እንደመሆኑ መጠን የእግዚአብሔርን ፈቃድና ምሪት የምንከተልበበት ሊሆን ያስፈልገዋል፡፡ ብዙ ኃያላን ታላላቅ አገልግሎቶችንና
ድንቆችን ከፈጸሙ በኋላ የሚወድቁት ከእግዚአብሔር ጥበብና ኃይል ይልቅ የራሳቸውን ሰብአዊ ኃይልና ጥበብ መደገፍ ስለሚጀምሩ ነው፡፡
በጸሎት ሕይወታቸው ሲደክሙ፡- መንፈሳዊውን ሕይወትና በመንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ የሚደረገውን አገልግሎት
ከጸሎት ሕይወት ነጥሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው፡፡ በእምነት የምንጸልየው ጸሎት በመንፈሳዊውም ሆነ ሥጋዊ ሕወታችን በጎውንና መልካሙን
ሁሉ ከእግዚአብሔር የምንቀበልበት ነው፡፡ “አምናችሁ በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ፡፡” ማቴ 21፣22፡፡ ቅዱስነታቸው
አቡነ ሺኖዳም እንዲህ ብለው ነበር፡- “ያለ ጸሎት ከሚደረግ አገልግሎት ይልቅ ያለአገልግሎት የሚደረግ ጸሎት ይሻላል፡፡” በእርግጥ
ያለጸሎት በሚደረግ አገልግሎት እግዚአብሔርን ማክበርና ደስ ማሰኘት አይቻልም፡፡ ብዙ አገልጋዮች በአገልግሎታቸው ጅማሬ ወቅት የነበራቸው
ጠንካራ የጸሎት ሕይወት አብሯቸው ስለማይዘልቅ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በአገልግሎታቸው ሲደክሙና ሲሰናከሉ ይስተዋላሉ፡፡ በጸሎት ሕይወት
የሚተጉ አገልጋዮች በአገልግሎታቸው እየበረቱና እያደጉ ሲሄዱ ከጸሎት ሕይወት የራቁት ደግሞ ከብርታታቸው እያነሱና እየጎደሉ ይመጣሉ፡፡
ከምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን መሳተፋቸውን ሲተዉት፡- ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ጋር ህብረት የምናደርግባቸውና
ኃይልን የምንቀበልባቸው መንፈሳዊ ተግባራት ናቸው፡፡ አገልጋዮች በአገልግሎታቸው ውስጥ የሚያስፈልጋቸውን ኃይልና ጸጋ መቀበል እንዲችሉ
በየጊዜው ከምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ሊሳተፉ ያስፈልጋቸዋል፡፡ “በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ። ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር ከራሱ ፍሬ ሊያፈራ እንዳይቻለው፥
እንዲሁ እናንተ ደግሞ በእኔ ባትኖሩ አትችሉም። እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችኹ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና
በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል። በእኔ የማይኖር ቢኾን እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል ይደርቅማል እነርሱንም
ሰብስበው ወደ እሳት ይጥሏቸዋል፥ ያቃጥሏቸውማል።” ዮሐ 15፣4-6፡፡ ከንስሓና ከቅዱስ ቁርባን ሕይወት የራቀ
አገልጋይ እንኳን የሚያገለግላቸውን ነፍሳት ሊጠቅም ራሱንም መጥቀም አይቻለውም፡፡ ከክርስቶስ ጋር ህብረት ስለማይኖረው ፍሬ ማፍራትና
በጸጋው ማደግ ይሳነዋል፡፡
ንስሓና ቅዱስ ቁርባን ጌታችን የሠራቸው መንፈሳዊ ሥርዐቶች ስለሆኑ ከክርስቶስ
ጋር ህብረት የምናደርግባቸውና ለመንፈስ ቅዱስ አሠራር ራሳችንን አሳልፈን የምንሰጥባቸው የተቀደሱ ምሥጢራት ናቸው፡፡ ክርስቶስ ከሠራው
ሥርዐት የሚርቁ፣ መንፈሳዊነቱንም የሚንቁና የሚያቃልሉ ሁሉ ራስ ወደሚሆን ወደ ክርስቶስ ሊደርሱ አይችሉም፡፡ አገልጋዮች በመንፈሳዊ
ምሥጢራትና ክርስቶስ በሠራቸው ሥርዐቶች ውስጥ ሱታፌ ማድረጋቸውን በተዉ ቁጥር መንፈሳዊነታቸው እየደከመ ሥጋዊነታቸው እያየለ ይመጣል፡፡
ነገሮችን በመንፈሳዊ ጥበብና በፈሪሀ እግዚአብሔር ከመፈጸም ይልቅ በሥጋዊ ሀሳብና በምድራዊ ጥበብ ለመፈጸም የሚሞክሩ አገልጋዮችን
የምናየው ራሳቸውን ከመንፈሳዊው አሠራርና ከምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ስለለዩ ነው፡፡ በአንድ ወቅት የቱንም ያህል መንፈሳዊ የነበሩ
ቢሆንም ከመንፈሳዊ ተግባራትና ከምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን የራቁ አገልጋዮች ፍጻሜያቸው የባቢሎንን አወዳደቅ የሚያህል ነው፡፡ በአገልግሎቱ
ውስጥ ለመቆየትና ለመጽናት ከመንፈሳዊነት በቀር ሌላ ዋስትና የለም፡፡ መንፈሳዊነት የሚያስፈልገው ለሚገለገሉት ምእመናን ብቻ ሳይሆን
ለአገልጋዮችም ጭምር መሆኑን የሚዘነጉ አገልጋዮች በመንፈስ ጀምረው በሥጋ የሚጨርሱ ይሆናሉ፡፡ ገላ 3፣3፡፡ ለራሳቸው መንፈሳዊ
ያልሆኑ አገልጋዮችስ እንዴት ሌሎችን መንፈሳዊ ማድረግ ይቻላቸዋል?
ይቀጥላል . . .
ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ!
No comments:
Post a Comment