(ክፍል ሁለት)
- ክፋት የሌለበት ቸር፣ በቀል የሌለበት የዋህ፣ ቁጣ የሌለበት ትዕግስተኛ፣ ኀጢአት የሌለበት ጻድቅ፣ እድፍ የሌለበት ንጹህ፣ ጠማምነት የሌለበት ቅን ነው፡፡
- ያለ መከልከል ሰጪ፣ ያለ መንፈግ ለጋስ፣ ያለ ቂምና ያለ ቅናት ኀጢአትን የሚያስተሠርይ ነው፡፡
- ለሚጠሩት ሰዎች የቀረበ ነው፣ ለሚፈሩትም በጎውን ነገር የሚያደርግ ነው፣ ለሚመቱት ሰዎች የተከፈተ በር ነው፡፡ ያለ መሰናክል ጥርጊያ ጎዳና፣ እሾህ የሌለበት ንጹህ ፍለጋ ነው፡፡
- የአማልክት አምላክ የአጋዕዝት ጌታ እግዚአብሔር እርሱ ብቻ ነው፡፡
- ከዚህ በኋላ ከአቤል ደም ጀምሮ እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ የቅዱሳን ነቢያት ደም ዓለምን ለማዳን አንዳልጠቀመ ባየ ጊዜ ቤዛ መድኃኒት የሚሆን ልጁን ሰደደልን፣ ፈጽሞ ያድን ዘንድ፣ በፊቱ የሕያዋንንና የሙታንን መታሰቢያም ያገባ ዘንድ፡፡
- በወዲያ ሳለ መጣ፣ በወዲህም ሳይሰማ ተላከ፡፡
- ከዙፋኑ ሳይነቃነቅ፣ ከቦታውም ሳይናወጥ ወረደ፡፡
- በሁሉ ምሉዕ ሲሆን በማኅፀን ተፀነሰ፣ ማኅተመ ድንግልና ሳይከፍት ተወለደ፡፡
- እንደ ሕፃን አደገ፣ በሰው መጠን እስኪጎለምስ ድረስ በየጥቂቱ አደገ፡፡
- በሠላሳ ዘመን በዮርዳኖስ ተጠመቀ፣ በሁለተኛ ልደት መታጠብ ከኀጢአት ያነጻን ዘንድ፡፡
- ከዲያብሎስ ዘንድ ተፈተነ፣ ተራበ ተጠማም፣ የሰማይ መንግሥት ወንጌልን እያስተማረ ታይቶ ተመላለሰ፡፡
- ከዚህ በኋላ ለሕማም በዕፀ መስቀል ላይ እጁን ዘረጋ፣ በደሙ መረጨት የሕሙማንን ቁስል ያድን ዘንድ፡፡
- በፊት እንደነበረ ለዘለዓለሙ ለልጅ ልጅ ይኖራል፡፡
- የጥበብ ሀገሯ ወዴት ነው? ማደሪያዋስ ወዴት ነው? ቦታዋ ወዴት ነው? የጎዳናዋስ ፍለጋ በወዴት ተገኘ?
- ባሕሩን ተሻግሮ በቀይ ወርቅ የገዛት ማነው? ከደመናትስ በላይ ወጥቶ ያወረዳት ማን ነው? መዋቲ ጎዳናዋን አያውቃትም፤በሰውም ዘንድ የለችም፡፡
- ከሰው ሁሉ ተዘነጋች፣ ከሰማይ አዕዋፍም ሁሉ ተሰወረች፣ እርሷን የገዙ ከእግዚአብሔር ጋራ ተወዳጁ፣ እርሷን የሚጠሏት ሞትን ይወዳሉና፡፡ ከፀሐይ ይልቅ ታምራለች፣ ከከዋክብትም አኗኗር፡፡ እርሷ ቀዳማዊት እንደመሆኗ ከብርሃን ጋራ ስትነጻጸር ትገኛለች፡፡
- በእርጅና ሳለች ሁሉን ታድሳለች፣ በየትውልዱም በጻድቃን ሰውነት ትፋለሳለች፡፡
- ከከበረ እንቁ እርሷ ትበልጣለች፣ ክብርም ሁሉ መጠኗ አይደለም፣ ምክር እውቀት አላት፣ ጽንዕ አእምሮም አላት፣ ነገሥታቱም በእርሷ ይነግሳሉ፣ ኃያላንም በእርሷ ዕውነትን ይጽፋሉ፡፡
- ደጋጎች በእርሷ ይከበራሉ፣ መኳንንትም በእርሷ ምድርን ይይዛሉ፣ የሚወዷትን ትወዳለች፣ ሕጓን የሚጠብቁትንም ትጠብቃለች፣ እርሷንም የሚሹ ባለሟልነትን ያገኛሉ፡፡
- በእውነት መንገዶች ትመላለሳለች፣ በእውነት ፍለጋም ትመላለሳለች፣ ለሚያውቋት ሰዎች ብዕልን ትሰጣቸው ዘንድ መዝገባቸውንም ተድላን ትመላ ዘንድ፡፡
- ሁሉን የሚያውቅ እርሱ ያውቃታል፡፡ ሁሉን የሚረዳ እርሱ ጎዳናዋን አሳመረ፣ እርሱ ለባለሟሉ ለያዕቆብ ለቅዱሱም ለእስራኤል ሰጠው፡፡ ከዚህ በኋላ በምድር ላይ ታየች እንደ ሰውም ተመላለሰች፡፡
- እነሆ ቤትን ሠራች፣ ሰባት አዕማድንም አቆመች፣ የእርሷን እርድ አረደች፣ በማድጋዋም የእርሷን ወይን ጨመረች፣ የእርሷንም ማዕድ አዘጋጀች፡፡
- ባሮቿን ላከች፣ በረጅም ስብከት ሰነፍ የሆነ ሰው ወደኔ ይምጣ እያለች፡፡ እውቀት ያነሳቸውንም ትጠራለች፣ ኑ የኔን ኅብስት ብሉ፣ የኔን ወይንም ጠጡ፣ ስንፍናንም ትታችሁ ኑሩ እያለች፡፡
- ጥበብ ግን መድኃኒታችን ነው፣ በሥጋው መስዋዕትነት ያዳነን፣ በደሙም ፈሳሽነት የተወዳጀን፣ ለመንግሥቱም የመረጠን ለዘለዓለሙ፡፡
- የብርሃናት አምላክ እግዚአብሔር፣ የሥልጣናት ጌታ እግዚአብሔር፣ የሊቃነ መላእክት ጌታ እግዚአብሔር፣ በሞት ታስራ የነበረች ነፍስን ፈታህ፡፡ በጨለማ የተቸነከረውንም በአንድ ልጅህ በመስቀል ላይ መቸንከር አበራህ፡፡
- የኛን ሕማማት የፈታ፣ ሸክማችንንም ሁሉ ያራቀ፣ የኀጢአታችንን ማሠሪያነት ሁሉ የፈታ፣ አቤቱ የእኛን መከራ መቀጥቀጥ ወስደህ ያዳንኸን፣ የሕይወት ቦታ ጎዳና የሆንህልን፣ ከጥፋት ወደማይጠፋ ጽድቅ የመለስከን፡፡
- አቤቱ አምላካችን ሁሉን የያዝህ የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት መጋረጃው ብርሃን፣ ፊቱ እሳት፣ የጌትነቱም ዙፋን የማይመረመር፣ ለቅዱሳን ያዘጋጀው የተድላው ማረፊያም የማይነገር፣ ልብሱ የብርሃን መዝገብ የሚሆን፡፡
- ቅዱሳን መላእክትንም ትጠብቃለህ፣ ሁሉ እየተንቀጠቀጠ በማየት የሚያመሰግንህ፡፡ ተራራዎቹን ያቀልጣቸዋል፣ ስሙም በተነገረ ጊዜ ጭንጫው ይሰነጠቃል፡፡
- ሰማያትን በእጅ ሰብስበህ ያለበስህ፣ ምድር የምትንቀጠቀጥልህ ቀላያትም በአንድነት፡፡
- በእርሱ የጠላት ሰራዊት ሁሉ የተቸገሩ፣ ዲያብሎስ ወደቀ፣ አርዌ ተረገጠ፣ ከይሲም ጠፋ፡፡
- በአንተ ያመኑ አሕዛብ በርሱ ብርሃን የሆኑ፣ አቤቱ በአንተም የጸኑ፣ ሕይወት በአንተ የተገለጸ፣ ተስፋም የጸና፣ ወንጌልም የተሰበከ፣ በርሱ ጥፋት የጠፋ፣ የማይጠፋውም የጸና፡፡
- አዎን አቤቱ የሁሉ አምላክ ነህ፡፡
- አዎን አቤቱ የሁሉ ንጉሥ ነህ፡፡
- አዎን አቤቱ ሁሉን የያዝህ ነህ፡፡
- አዎን አቤቱ ሁሉን የምትገዛ ነህ፡፡
- አዎን አቤቱ ሁሉን የምታድን ነህ፡፡
- አዎን አቤቱ በእውነት የሁሉ ገዢ ነህ፡፡
- አዎን አቤቱ የሁሉ መድኃኒት ነህ፡፡
- አዎን አቤቱ ሁሉን የምትጠብቅ ነህ፡፡
- አዎን አቤቱ ሁሉን የምትመግብ ነህ፡፡
- የልጅህን ሥጋ ከኛ ሥጋ ጋራ አንድ እንዳደረግህ፣ የመሲሕህንም ደም ከእኛ ደም ጋራ አንድ እንዳደረግህ፣ እንዲሁ አንተን መፍራትን በልቦናችን፣ በጎ አምልኮትህንም በኅሊናችን ጨምር፡፡
- ሥጋውያን የምንሆን እኛ ግን የሥጋን ሕግ እናስባለን፣ የሥጋንም ሥራ እንሠራለን፣ በሥጋ መንገድም እንሄዳለን፣ አንተ ግን የመንፈስን ሥራ አስተምረን፣ የመንፈስንም ሕግ አንተ አስረዳን፣ የመንፈስን መንገድ ምራን፡፡
- እኛን ኃጥአንን ብትምረን ያንጊዜ መሐሪ ትባላለህና፣ ጻድቃንን ግን ከሥራቸው የተነሳ ትምራቸዋለህ፣ እንደ ጽድቃቸውም ትሰጣቸዋለህ፡፡
- የቀደመ በደላችንን አታስብብን፣ አቤቱ ይቅርታህ ፈጥኖ ይደረግልን፡፡
- ወደ አንተ እንጮሃለን፣ ወደ አንተ እናለቅሳለን፣ ወደ አንተ እንማለላለን ለዘለዓለሙ፡፡
ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ!
No comments:
Post a Comment