ነገረ ክርስቶስ በማክሰኞ ወዳሴ ማርያም (ክፍል
አንድ)
“የመመኪያችን
ዘውድ፤ የድኅነታችን መጀመሪያ፣ የንጽኅናችንም መሠረት እኛን ስለማዳን ሰው የሆነ የእግዚአብሔርን ቃል በወለደችልን በድንግል ማርም
ተገኘልን፡፡” የሰው ልጆች ሁሉ የምንመካበትን የነፍሳችንን መመኪያ፣ የመዳናችንንም መንገድ፣
ከኀጢአታችን የነጻንበትን መድኃኒት ክርስቶስን ድንግል ማርያም ወለደቸው፡፡ ከድንግል በነሳው ሥጋው በኩል ክርስቶስ ሁላችንን ወገኖቹ
አደረገን፣ በደሙ ፈሳሽነት ታረቅንበት፣ በእርሱም የተነሳ ደግሞ ወደ አብ መግባትን አገኘን፣ ከእግዚአብሔር ርቀን የነበርን ሁላችን
በክርስቶስ ኢየሱስ ወደእግዚአብሔር ቀረብን፣ የእግዚአብሔር ጠላቶቹ የነበርንም በአንድ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት ከእግዚአብሔር
ጋር ታረቅን፡፡ “ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋራ በልጁ ሞት ከታረቅን፥
ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን” ሮሜ 5፣10፡፡
በመለኮቱ ሞት
የሌለበት እግዚአብሔር ወልድ ከድንግል ማርያም በነሳው ሥጋ ሞተልንና ሞታችንን አጠፋልን፣ መዳኛችን በሚሆን ሞቱም ከእግዚአብሔር
ጋር ታረቅን፣ ከእግዚአብሔር መንግስት እርቀን የነበርን እኛ ወደመንግሥቱ ፈለስን፡፡ “እግዚአብሔር ሙላቱ ዅሉ በእርሱ እንዲኖር፥ በእርሱም በኩል በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም
በሰማያት ያሉትን ዅሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዷልና። እናንተንም ነውርና ነቀፋ የሌላችኹና ቅዱሳን አድርጎ በእርሱ ፊት ያቀርባችኹ
ዘንድ፥ በፊት የተለያችኹትን፤ ክፉ ሥራችኹንም በማድረግ በዐሳባችኹ ጠላቶች የነበራችኹትን አኹን በሥጋው ሰውነት በሞቱ በኩል አስታረቃችኹ።” ቆላ 1፣19-22፡፡
“ሰው ከሆነ
በኋላም ፍጹም አምላክ ነው፤ ስለዚህም በድንግልና ወለደችው፡፡ ድንቅ የሆነ የመውለዷ ችሎታ የማይመረመር፤ ሊነገር የማይቻል ነው፡፡” እግዚአብሔር ወልድ ምንም እንኳን ሰው
ቢሆንም ፍጹም አምላክም ነው፡፡ መወለዱ አምላክነቱን ሊለውጠው/ሊያስቀረው አይቻለውምና፡፡ “ክርስቶስ በሥጋ መጣ፥ እርሱም ከዅሉ በላይ
ኾኖ ለዘለዓለም የተባረከ አምላክ ነው፡፡” ሮሜ 9፣5፡፡ ድንቅ የሚሆን
ይህ የጌታችን ልደቱ የእናቱን ድንግልና ሳይለውጥ በድንቅ ጥበቡ የሆነ ነውና እናቱ በድንግልና ጸንሳ በድንግልና ወልዳዋለች፡፡ አምላክ
ሰው ሆኖ በተወለደ ጊዜ አምላክነቱ እንዳልተለወጠ ሁሉ ድንግል የምትሆን እናቱም በወለደችው ጊዜ ድንግልናዋ አልተለወጠም፡፡ ይህን
ድንቅ የሚሆን የጌታችንን ልደቱን ማን ሊመረምረው ይቻለዋል? ተናግሮ ሊፈጽመው የሚቻለውስ ማን አለ? እጹብ ድንቅ ነው እንጂ!
“በእርሱ ፈቃድ፣
በአባቱ ፈቃድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ መጥቶ አዳነን፡፡” የእግዚአበሔር ፈቃዱ አንዲት ናትና
በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ፈቃድ ድኅነታችንን አግኝተናል፡፡ የአብ ፈቃዱ የወልድና የመንፈስ ቅዱስም ፈቃድ ናትና፡፡ “የእኔም የኾነ ዅሉ የአንተ ነው፤ የአንተውም የእኔ ነው” ዮሐ 17፣10 እንዲል በሦስት አካላት ያለ እግዚአብሔር አንዲት በምትሆን ፈቃዱ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት
የመዳናችንን መንገድ አበጀልን፡፡ “የላከኝን ፈቃድ
ለማድረግ ከሰማይ ወርጃለሁና” ያለ ጌታችን ፈቃዱ እንደ አባቱ አብ ፈቃድ ናትና በዚህች አንድ በምትሆን ፈቃዱ አዳነን፡፡ ዮሐ
6፣38፡፡ “በድንግልና
ፍጽምት የሆንሽ ማርያም ሆይ የድንግልናሽ ምስጋናና ክብር ታላቅ ነው፤ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ቢሆን ባለሟልነትን አግኝተሻልና፡፡” በድንግልናዋ ፍጽምት የምትሆን፣ ነውርና ነቀፌታ
ያልተገኘባት ክብርት እመቤታችንን እናደንቃታለን፣ እናከብራትማለን፡፡ ፍጥረት ሁሉ ከጸጋ በተራቆተበት ዘመን “ደስ ይበልሽ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋራ ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ” የሚል ቃልን ከመልአኩ የሰማች ናትና ስለዚህ ነገር አምላክን
የወለደች ክብርት እመቤታችንን ከፍ ከፍ እናደርጋታለን፡፡ ሉቃ 1፣28፡፡ “ያዕቆብ ከምድር እስከሰማይ ደርሳ የእግዚአብሔር መላእክት ሲወጡባት፤ ሲወርዱባት
ያያት መሰላል አንቺ ነሽ፡፡” እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ በራዕዩ የተመለከታትን ከምድር እስከ ሰማይ የተዘረጋች መሰላል ትመስላለች፡፡ ዘፍ 28፣12፡፡ በመሰላሉ ምድርና ሰማይ
እንደተገናኙ እግዚአብሔር ወልድ ከእመቤታችን በነሳው ሥጋ ምድራውያን ከሰማያውያን ጋር ህብረት ማድረግ ችለዋል፡፡ በእግዚአብሔር
ወልድ ቤዛነት ምድራውን የምንሆን እኛ ከሰማይ የሚሆን መንግሥተ እግዚአብሔርን ለመውረስ የተገባን ሆነናል፡፡ በመሳለሉ ጫፍ ላይ
እግዚአብሔር ተቀምጦ እንደነበረ ሁሉ እግዚአብሔር ወልድ ኢሱስ ክርስቶስ በእመቤታችን ማኅጸን አድሯልና በያዕቆብ መሰላል እንመስላታለን፡፡
በመሰላሉ የእግዚአብሔር መላእክት ሲወጡና ሲወርዱ እንደተመለከተ እመቤታችን ጌታችንን በወለደችው ጊዜ የምሥራቹን ለመንገር መላእክት
ወደ ምድር መውረዳቸውንና ከጌታችን ልደት የተነሳ ከሰው ልጆች ጋር ደስ መሰኘታቸቸውን ከቅዱስ መጽሐፍ እናነባለን፡፡ ሉቃ 2፣8-14፡፡
“ሙሴ በነደ
እሳት ሳትቃጠል ያያት ዕፅ አንቺ ነሽ፤ ይኸውም መጥቶ በማኅፀንሽ ያደረው የእግዚአብሔር ልጅ ነው፡፡ የመለኮቱ እሳትነት ሥጋሽን
አላቃጠለውም፡፡” እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም
ሙሴ በራዕዩ በእሳት ሳትቃጠል ያያትን ዕፅ ትመስላለች፡፡ ዘጸ 3፣2፡፡ የሚነደው እሳት ቁጥቋጦውን አንዳላቃጠለው ሁሉ እመቤታችን
ጌታችንን በጸነሰችውና በወለደችው ጊዜ የመለኮቱ እሳትነት አላቃጠላትምና ስለዚህ ነገር በእርሷ ላይ የሆነውን ታላቅ የእግዚአብሔር
ሥራ እናደንቃለን፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ብቻ ሳይሆን አባ ህርያቆስም በቅዳሴው ይህን ነገር እንዲህ ሲል ያደንቃል፡- “ድንግል ሆይ እሳተ መለኮት በሆድሽ ባደረ ጊዜ ፊቱ እሳት፤ ልብሱ እሳት፤
ቀሚሱ እሳት ነው፤ እንደምን አላቃጠለሽ፡፡ ሰባት የእሳት ነበልባል
መጋረጃ በሆድሽ ውስጥ ወዴት ተዘጋጀ፤ ወዴትስ ተጋረደ፤ ከጎንሽ በቀኝ ነውን፤ ወይስ ከጎንሽ በግራ ነውን፤ ትንሽ አካል
ስትሆኝ፡፡ የሚያንጸባርቅ ነደ እሳት የሚከበው ኪሩቤል የተሸከሙት ዙፋን በሆድሽ ውስጥ ወዴት ተዘጋጀ፤ ወዴትስ ተተከለ፤ ታናሽ ሙሽራ
ስትሆኝ፡፡”
“ዘር ያልተዘራባት
እርሻ አንቺ ነሽ፤ የሕይወት
ፍሬ ከአንቺ ወጣ፡፡” እመቤታችን
በማክሰኞ እርሻ ትመሰላለች፣ በስነ ፍጥረት ጊዜ የማክሰኞ እርሻ ያለዘር ፍሬን እንደሰጠች ሁሉ እመቤታችንም እንበለ ዘርዐ ብእሲ/ያለወንድ
ዘር ጌታችንን በድንግልና ጸንሳ በድንግልና ወልዳዋለችና ዘር ያልተዘራብሽ እርሻ አንቺ ነሽ እንላታለን፡፡ “ዮሴፍ የዋጃትና የከበረ እንቁን ያገኘባት ሣጥን
አንቺ ነሽ፤ ይኸውም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ በማኅፀንሽ አደረ፤ በዚህ ዓለምም ወለድሽው፡፡” አረጋዊ
ዮሴፍ በእርጅናው ዘመን ገንዘብ ቢያደርግሽ/ሊጠብቅሽ ቢወድ በውስጧ የከበረ እንቁን እንዳገኘ ሰው ከአንቺ የተነሳ ጌታችንን አግኝቷል
ሲል በተቆለፈች ሳጥን መስሏታል፡፡ በእርግጥም በከበረ ዕንቁ የተመሰለ መድኃኒታችን ክርስቶስን ወልዳልናለችና እመቤታችንን የከበረ
ዕንቁ የተገኘባት የተቆለፈች ሣጥን ናት እንላታለን፤ ማኅተመ ድንግልናዋ ሳይለወጥ መድኃኒታችንን ወልዳልናለችና፡፡
“የመላእክት ደስታቸው የሆነ ጌታን የወለድሽ ሆይ
ደስ ይበልሽ፡፡” መላእክት
ደስ የተሰኙበትን ታላቁን የምስራች ጌታችንን ድንግል ማርያም በማኅፀኗ ተሸከመችው፣ መላእክትም ደግሞ ስለዚህ ነገር እግዚአብሔርን
እንዳመሰገኑ ቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ ይነግረናል፡- “ድንገትም ብዙ የሰማይ ሰራዊት ከመልአኩ ጋራ ነበሩ።
እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ። ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይኹን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ።” ሉቃ 2፣13-14፡፡ “የነቢያት ዜናቸው ንጽሕት ሆይ ደስ ይበልሽ፤ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ቢሆን ባለሟልነትን አግኝተሻልና ደስ
ይበልሽ፡፡ የዓለም፤ የሰው ሁሉ ደስታ የሆነ የመልአኩን ቃል ተቀብለሻልና ደስ ይበልሽ፡፡ ዓለምን ሁሉ የፈጠረ ጌታን የወለድሽ ሆይ
ደስ ይበልሽ፡፡” የነቢያት
ዜና/ትንቢታቸው ፍጻሜውን ያገኘው ጌታችን ከእርሷ በተወለደ ጊዜ ነውና ደስ ይበልሽ አላት፤ ደስታውም ደግሞ ለሰው ሁሉ የሚሆን ታላቅ
የምስራች ነው፡፡ ሉቃ 2፣10፡፡ ይህንን ታላቅ ደስታና የምሥራች በመልአክ ብስራት የሰማና የተቀበለ ከእርሷ በቀር ከሰው ወገን
ሌላ ማንም የለምና መልአኩ ደስ ይበልሽ ብሎ አክብሮ እንደገራት ሁሉ ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬምም ደስ ይበልሽ አላት፤ ዓለምን ሁሉ የፈጠረውን
ጌታ ወልዳለችና፣ ለአምላክ እናቱ ልትሆን ተመርጣለችና፡፡
“በሚገባ የአምላክ እናት ተብለሻልና ደስ ይበልሽ፡፡” እመቤታችን ድንግል ማርያም የወለደቸው አምላክ ነውና እርሷም ደግሞ
ወላዲተ አምላክ/አምላክን የወለደች የአምላክ እናት ትባላለች፡፡ አምላክን መውለዷም ለዓለሙ ሁሉ ደስታ ነውና ስለዚህ ነገር ሊቁ
ደስ ይበልሽ ብሎ አመስግኗታል፡፡ “የሔዋን መድኃኒት ሆይ ደስ ይበልሽ፡፡ ፍጥረቱን ሁሉ የሚመግበውን እርሱን ጡትሽን አጥብተሽዋልና ደስ ይበልሽ፡፡
የኅያዋን (የጻድቃን) ሁሉ እናታቸው ደስ ይበልሽ፡፡ ትለምኚልን ዘንድ
ወደአንቺ እናንጋጥጣለን፡፡” በሔዋን አመጻና መተላለፍ የተዘጋች ገነት እመቤታችን ጌታችንን በመውለዷ
ተከፍታልናለችና እመቤታችን ለሔዋን ደስታዋ ናት፤ ከቀደሙት ወገን ከእርሷ በቀር ይህን ታላቅ ዕድል ያገኘ የለምና፤ ጌታችን በሥጋዌው
ዓለሙን ሁሉ ሊያድን በሳበ ጊዜ እንደመቤታችን የወደደውና ደስ የተሰኘበት ማንም የለምና፡፡ ፍጥረቱን ሁሉ የሚመግብ ታላቅ አምላክ
እንደ ሕጻን የድንግልን ጡቶቿን ጠብቷልና ስለዚህ ነገር ደስታ ይገባሻል አላት፡፡ በቅዳሴ ዲዮስቆሮስም እንዲህ ተጽፏል፡- “በአባቱ ፈቃድ ወረደ፤ በማርያም
ዘንድ እንግዳ ሆነ፤ እግዚአብሔር በንጹሕ ድንግልናዋ ተወለደ፡፡ በእንስሳት በረት ተጨመረ የንጉሡንም እጅ መንሻ ተቀበለ፤ ከእናቱ
ጡቶች ምግብን እየለመነ እንደ ሕፃናት አለቀሰ፡፡” አምላክን
የወለደች እመቤታችን ጌታን በመውለዷ ለኅያዋን ሁሉ እናታቸው ሆናለች፣ የወለደቸውው ልጇ የዓለሙን ሁሉ ሞት አጥፍቶታልና፤ ስለዚህም
ነገር ደግሞ በፊቱ ባለሟልነትን ያገኘች ክብርት እናቱን ለምኚልን እንላታለን፡፡
“ድንግል ሆይ፤ ቅድስት ሆይ፤ ጌታን የወለድሽ
ሆይ እኛን ለማዳን ድንቅ ምሥጢር (ተዋሕዶ) በአንቺ ቢደረግ ንጉሥን ወልደሽልናልና ፍጥረታትን በልዩ ልዩ መልክ የፈጠር የእርሱን
የገናንነቱን ነገር ፈጽመን መናገር አይቻለንምና ዝም እንበል፡፡” ስለመዳናችን እግዚአብሔር ያበጀልን መንፈሳዊ መንገድና ስለመዳናችን
ይህ አምላክ ሰው የመሆኑ ነገር እጅግ ድንቅ ነውና ስለዚህ ነገር ተናግረን እንፈጽመው ዘንድ አይቻለንምና ዝም እንላለን፡፡ እመቤታችንንም
ማክበራችን አምላክ ሰው ሊሆን በወደደ ጊዜ ከሰው ሁሉ ወገን እርሷን መርጧታልና፣ የከበረ ሥጋዋንም ተዋሕዷልና ነው፡፡ እርሱ ራሱ
እግዚአብሔር ከሰጣት ክብር የሚበልጥ እኛ የምንሰጣትና የምንጨምርላት ክብር የለንም፡፡ “ማርያም ሆይ ስለዚህ እንወድሻለን ከፍ ከፍም እናደርግሻለን፤ እውነተኛ የጽድቅ መብልንና እውነተኛ
የሕይወት መጠጥን ወልደሽልናልና፡፡” እንዳለ
አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው፡፡
“ወደ ደብረ ሲና የወረደ ለሙሴ ሕግን የሰጠ፤
የተራራውን ራስ በጽጋግ፣ በጢስ፣ በጨለማና በነፋስ የሸፈነ፤ ፈርተው የቆሙትንም በነጋሪቶች ድምጽ የገሠጸ የአብ አካላዊ ቃል ነው፡፡” በደብረ
ሲና ለሙሴ ሕግን የሰጠውና ሕገ ኦሪትን የሠራለት በአነዋወሩ ቀዳማዊ የሚሆን እግዚአብሔር ወልድ ከእመቤታችን ሥጋንና ነፍስን ነስቶ
ሰው በሆነ ጊዜ የሐዲስ ኪዳንን ሥርዐት ዳግመኛ ሠራልን፡፡ የሠራልን ይህ የሐዲስ ኪዳን ሥርዐት ደግሞ ሁላችንንም የሚያድንና ወደ
መንግሥቱ የሚያፈልሰን የቀና ሕግ ነው፡፡ ዘጸ 19፤ ሉቃ 22፣20፡፡
“በትሕትና የተናገርሽ ተራራ ሆይ ይኸውም ወደ
አንቺ የወረደው ነው፡፡ ሰውን የወደደ እርሱ ያለመለወጥ በአንቺ ሰው ሆነ፤ እንደእኛ በሚናገር ሥጋ ፍጹም ሆኖ አምላክ በመንፈስ
ቅዱስ በማኅጸኗ አደረና ፍጹም ሰው ሆነ፡፡ አዳምን ያድነው ዘንድ፣ ኀጢአቱንም ያስተሠርይለት ዘንድ፤ በሰማያት (በሰማያዊ መዐርግ)
ያኖረው ዘንድ፤ በቸርነቱና በይቅርታው ብዛት ወደ ቀድሞ ቦታው ይመልሰው ዘንድ፡፡” የእግዚአብሔር
ቃል ወደ ደብረ ሲና ወርዶ ሙሴን አንደተናገረውና ሥርዐተ ኦሪትን አንዳሳየው ሁሉ በሐዲስ ኪዳንም እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ እመቤታችንን
በተናገራት ጊዜ “ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ነው . . . ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይኾናል . . . እንሆኝ የጌታ
ባሪያ እንደ ቃልኽ ይኹንልኝ” ብላ በትሁት ቃል ተናገረች መንፈሳዊት ናት እንጂ ይገባኛል ብላ አልተጓደደችም ሉቃ
1፣29-38፡፡ ይህን ትህትናዋን የተመለከተ እግዚአብሔርም እንደእርሷ ያለ አላገኘምና አንድ ልጁን ወደእርሷ ሰደደው፤ አዳምን ያድነውና
ይቤዠው ዘንድ፡፡ ስለዚህም ነገር ደግሞ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው እንዲህ ብሏል፡- “እግዚአብሔር አብ በሰማይ ሆኖ ምሥራቅንና
ምዕራብን፤ ሰሜንንና ደቡብን፤ ዳርቻውን ሁሉ በእውነት ተመለከተ፡፡ ተነፈሰ፤ አሸተተም፤ እንደ አንቺ ያለ አላገኘም፤ የአንቺን መዓዛ ወደደ፤ ደም ግባትሽንም ወደደ፤ የሚወደውን ልጁንም ወደ አንቺ
ሰደደ፡፡”
ከዚህም በኋላ የወደቀውን አዳምን አንስቶ ወደ ቀደመ ክብሩ መለሠው፣
ፍጹም ጸጋንና ባለሟልነትንም ሰጠው፡፡
ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ!
. . . ይቀጥላል . . .
I really like it. You did great. Piease keep it up.
ReplyDeletegood i like it
ReplyDelete