Wednesday, April 6, 2016

ጸጋና መዳን በኦርቶዶክሳዊው አስተምህሮ (ክፍል አንድ)


ጸጋ የሚለውን ቃል የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዘገበ ቃላት እንዲህ ይፈታዋል፡- ሀብት፣ መልካም ስጦታ ፣ ዕድል ፈንታ፣ ስርየት፣ ይቅርታ፣ ሞገስ፣ የቸርነት ሥራ፣ አለዋጋ የሚሰጥና የሚደረግ፡፡ በመዳን ትምህርት ጸጋ የምንለው እግዚአብሔር አምላክ በአንድ ልጁ በጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ዓለሙን ሁሉ የታረቀበትንና ከሰው በሆነ ሥራ ሳይሆን እርሱ ራሱ እግዚአብሔር በአንድ ልጁ በሠራው ሥራ በኩል ወደ እግዚአብሔር መንግስት መግባት የቻልንበትን በጎ ስጦታውን ነው፡፡ ከእኛ በሆነው ሥራ ከበደላችን የተነሳ ሁላችንም ሞተንና ከእግዚአብሔር መንግስት ርቀን እንኖር ነበርን፡፡ ለበደላችን የሚሆን በቂ ካሳ መክፈል የማንችል ስለሆንንና፣ ከእኛ በሆነ ሥራ ለመዳን ባለመቻላችን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመዳናችን መንገድ ሆነ፣ እርሱ እንዳሰበ የመዳናችንን መንገድ በራሱ አበጀልን፡፡ በእርሱም በኩል ወደ አብ መግባት ቻልን፡፡ ‘‘በእርሱ ሥራ ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለንና።’’ ኤፌ 2፣18፡፡ ይህ የመዳናችን መንገድ በእኛ ጥረትና ድካም የተሠራ ሳይሆን በእግዚአብሔር ሐሳብና በበጎ ፈቃዱ እንዲሁ በነጻ፣ ያለዋጋ የተደረገልንና የተቀበልነው ስለሆነ ጸጋ ይባላል፡፡ ምክንያቱም ከእግዚአብሔር የተቀበልነው ነጻ ስጦታ ነውና፡፡ ይህም የጸጋው ስጦታ ለተቀበሉትና በስሙም ለሚያምኑት ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች የሚሆኑበት ታላቅ ስልጣን ነው፡፡ ዮሐ 1፣12፡፡ ይህ ታላቅ ስጦታው በበደላችን ሙታን የሆንነውን በሕይወት እንድንኖር ያደረገበትና በአዳም በኩል የሆነውን የሰው ልጆች ኀጢአተኝነት እግዚአብሔር በአንድ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ይቅር ያለበትና የተወበት ነው፡፡ ስለሆነም ይህ የመዳናችን ነገር በጌታችንና አምላካችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ በነጻ የተደረገልን ነውና ጸጋ እንለዋለን፡፡ ምክንያቱም ያለእርሱ ሥራ ከእኛ በሆነ ሥራና ጥረት ልንድን አልቻልንምና፡፡  ‘‘በጸጋ ከኾነ ግን ከሥራ መኾኑ ቀርቷል፤ ጸጋ ያለዚያ ጸጋ መኾኑ ቀርቷል።’’ እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ መዳናችን ከእግዚአብሔር የተቀበልነው የፍቅሩ ነጻ ስጦታ ነው እንጂ በጥረታችንና በድካማችን ያመጣነውና የደረስንበት አይደለም፡፡ ሮሜ 11፣6፡፡
የዓለሙ ሁሉ መዳን እግዚአብሔር አምላካችን በአንድ ልጁ በጌታችንና አምላካችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ባደረገልን እርቅ የተፈጸመ ነው፡፡ እርሱ ሊሞትልን ባይፈቅድ ኖሮ እስከ ዛሬ ድረስ ልንድንበት የምንችልበት  ምንም መንገድ አልነበረም፡፡ አዳም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በማፍረሱ በፈቃዱ ሞትን አምጥቷል፡፡ በፈቃዱ ያመጣውን ሞት ግን የሚያጠፋበትና የሚያርቅበት አቅምም ሆነ ሌላ መንገድ አልነበረውም፡፡ ምክንያቱም በበላህ ጊዜ ትሞታለህ ስለተባለ ዕፀ በለስን በልቶ ሞቷል፡፡ የእግዚአብሔር ፍርድ ደግሞ መፈጸም ስለነበረበት አዳም መዋቲ/የሚሞት ሆኗል፡፡ ይህን መዋቲ ሰውነት ከሞት የሚያወጣና የሚታደግ ደግሞ ከራሱ ከእግዚአብሔር በቀር ሌላ ማንም አልነበረምና ራሱ እግዚአብሔር ሰው ሆኖ በሰውነቱ የአዳምን ቅጣት ተቀብሎ፣ በአምላክነቱ ደግሞ የአዳምን በደል ቀጥቶ አዳነን፡፡ ይህን ነው እንግዲህ ጸጋ የምንለው፡፡ በእኛ ጥረትና በሥራችን ሳይሆን በእግዚአብሔር ሐሳብና ጥበብ ወደ እርሱ የቀረብንበትና ወደ መንግስቱ የፈለስንበት የመዳናችን መንገድ፡፡ መዳናችን በእግዚአብሔር የሆነልንና የተደረገልን ነው እንጂ እኛ በደከምነው ድካምና በብዙ ጥረታችን ያመጣነው አይደለም፡ ‘‘ያዳነን በቅዱስም አጠራር የጠራን እግዚአብሔር ነውና፥ ይህም እንደ ራሱ ዐሳብና ጸጋ መጠን ነው እንጂ እንደ  ሥራችን መጠን አይደለም፤ ይህም ጸጋ ከዘለዓለም ዘመናት በፊት በክርስቶስ ኢየሱስ ተሰጠን ’’ 2ኛ ጢሞ 1፣9፡፡
መዳናችን በእግዚአብሔር ጸጋ፣ ያለዋጋ እንዲሁ በነጻ በተቀበልነው ስጦታው ከሆነ ከእኛ ምን ይጠበቃል? በመጀመሪያ መዳናችን ከእኛ በሆነው ድካም ሳይሆን በመስቀሉ ደም በመዋጀታችን መሆኑን ማመን ይጠበቅብናል፡፡ ይህንን ካመንን በኋለ ደግሞ ላመንነው እምነታችንና ለተቀበልነው የጸጋው ስጦታ መታመንና እንደሚገባ መኖር ያስፈልጋል፡፡ ‘‘በበጎ ሥራ ዅሉ ፍሬ እያፈራችኹ በእግዚአብሔርም ዕውቀት እያደጋችኹ፥ ከደስታም ጋራ በዅሉ ለመጽናትና ለመታገሥ እንደ ክብሩ ጕልበት መጠን በኀይል ዅሉ እየበረታችኹ፥ በቅዱሳንም ርስት በብርሃን እንድንካፈል ያበቃንን አብን እያመሰገናችኹ፥ በነገር ዅሉ ደስ ልታሠኙ ለጌታ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እንለምናለን።’’ ተብለናልና ጸጋው የምንጠነቀቅለትና እግዚአብሔርን ደስ በማሰኘት የምንኖርበት እንጂ መዳናችን በጸጋው ስለሆነ ብለን ቸል የምንለውና የምንሰንፍበት አይደለም፡፡ ቆላ 1፣ 10-12፡፡ ጸጋው የመዳናችን ዋስትናና ጅማሬ ነው እንጂ ፍጻሜው አይደለም፡፡ ለሆነልንና ለተቀበልነው የጸጋው ስጦታ መታመን ካልቻልንና እንደሚገባ ካልኖርን፣ በክርስቲያናዊ ኑሯችን ውስጥ በሥራ የተገለጠ መታዘዝ ከሌለን በጸጋው የሆነልን መዳን ብቻውን ወደ መዳን አያመጣንም፡፡ ‘‘ለሰው ፊትም ሳያደላ በያንዳንዱ ላይ እንደ ሥራው የሚፈርደውን አባት ብላችኹ ብትጠሩ  በእንግድነታችኹ ዘመን በፍርሀት ኑሩ።’’ የተባልነው ጸጋው ወደ መዳን የሚያደርሰን የቸርነቱ ውጤት ቢሆንም በስራ በተገለጠ ክርስቲያናዊ ሕይወት ካልታዘዝነውና እግዚአብሔር ደስ የሚሰኝበትን ሥራ ካልሠራንበት ጸጋውን የሰጠን አምላክ ራሱ በክፉ ሥራችን ስለሚፈርድብን ነው፡፡ 1ኛ ጴጥ 1፣17፡፡ 
ጸጋ እንደ እግዚአብሔር ስጦታ
ጸጋ የእግዚአብሔር ነጻ ስጦታ ነው ካልን ስጦታውም ደግሞ ልዩ ልዩ ነው፡፡ እርሱ እንዳሰበና እንደ ወደደ መጠን ለእያንዳንዳችን የጸጋውን ስጦታ ያካፍለናል፡፡ ላካፈለን ጸጋው ግን እንደሚገባ የምንኖርና የምንታመን መሆን ክርስቲያናዊ ግዴታችን ነው፡፡ ጸጋውን መቀበላችን ብቻውን የመዳናችን ፍጻሜ ሊሆን አይችልም፡፡ ለተቀበልነው ጸጋ መታዘዝና እንደሚገባው መኖር ካልቻልን ፍፃሜያችን ጥፋት ነው የሚሆነው፡፡ ጸጋ በሥራ የምንታዘዘው ነው እንጂ በጸጋው ስለዳንን ከእኛ የሚፈለግ ምንም ድርሻ የለም ብለን የምንሰንፍበት ምክንያት አይደለም፡፡ ‘‘ነገር ግን፥ በእግዚአብሔር ጸጋ የኾንኹ እኔ ነኝ፤ ለኔም የተሰጠኝ ጸጋው ከንቱ አልነበረም ከዅላቸው ይልቅ ግን ደከምኹ፥ ዳሩ ግን ከእኔ ጋራ ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው እንጂ እኔ አይደለኹም።’’ 1ኛ ቆሮ 15፣10፡፡ የቅዱስ ጳውሎስ መጠራትና ሐዋርያነቱ በእግዚአብሔር ጸጋ የሆነ ነው፣ ነገር ግን በጸጋው ውስጥ ደግሞ እንደሚገባ ደክሟል/ አገልግሏል፡፡ ሁሉ ከጸጋው የተነሳ ቢሆንለትም ጸጋው እንደረዳው መጠን ከመድከምና ከመጋደል ግን ወደ ኋላ አላለም፡፡ ‘‘ለኔም የተሰጠኝ ጸጋው ከንቱ አልነበረም’’ ሲል የጻፈው በተሰጠው ጸጋና በበዛለት የእግዚአብሔር ነጻ ስጦታ ውስጥ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ይጥርና በሥራ የተገለጠ መንፈሳዊ ሕይወት ለመኖር ይደክም ስለነበረ ነው፡፡ ይህን ማድረግ ባይችል ኖሮ በእርግጥም ጸጋው ከንቱ በሆነ ነበር (ወደ መዳን ባላመጣው ነበር፡፡) ደቀ መዝሙሩ ጢሞቴዎስንም እንዲህ ብሎት ነበር፡- ‘‘የተሰጠኽን፥ ባንተ ያለውን የጸጋ ስጦታ ቸል አትበል።’’ 1ኛ ጢሞ 4፣14፡፡ ከእግዚአብሔር የሆነልንና የተቀበልነው የጸጋው ስጦታ በቸልተኝነት የምንይዘው ሳይሆን ዕለት ዕለት የምንጠነቀቅለትና በታላቅ መንፈሳዊነትና ጥንቃቄ ውስጥ ሆነን የምንታዘዘውም ጭምር ነው፡፡
በሉቃ 10፣17-19 ላይ እንዲህ የሚል ቃል አለ፡- ‘‘ሰብዓውም በደስታ ተመልሰው፦ ጌታ ሆይ፥ አጋንንት ስንኳ በስምኽ ተገዝተውልናል አሉት። እንዲህም አላቸው  ሰይጣንን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየኹ። እንሆ፥ እባቡንና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ፥ በጠላትም ኀይል ዅሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችዃለኹ፥ የሚጐዳችኹም ምንም የለም።’’ እንግዲህ ከእግዚአብሔር ከምንቀበላቸው የጸጋ ስጦታዎች መካከል በስሙ አጋንንትን ማውጣትና ታላታቅ ድንቆችንና ተአምራትን ማድረግ ይገኙበታል፡፡ በማቴ 17፣19-21 ላይ ደግሞ እንዲህ ተጽፏል፡-  ‘‘ከዚህ በዃላ ደቀ መዛሙርቱ ብቻቸውን ወደ ኢየሱስ ቀረቡና፦ እኛ ልናወጣው ያልቻልን ስለ ምን ነው አሉት። ኢየሱስም፦ ስለእምነታችኹ ማነስ ነው፤ እውነት እላችዃለኹ፥ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያኽል እምነት ቢኖራችኹ፥ ይህን ተራራ፦ ከዚህ ወደዚያ ዕለፍ ብትሉት ያልፋል፤ የሚሳናችኹም ነገር የለም። ይህ ዐይነት ግን ከጸሎትና ከጦም በቀር አይወጣም አላቸው።’’ አጋንንትን ማውጣት የእግዚአብሔር ጸጋ/ስጦታ ነው? ወይስ የሰዎች ልጆች ጸሎትና መንፈሳዊ ተጋድሎ ውጤት? በእርግጥ የእግዚአብሔር ጸጋ/ስጦታ መሆኑ ባያጠራጥርም ስጦታው ግን አብረን ከእግዚአብሔር ጋር የምንሠራበት ነው፡፡ 1ኛ ቆሮ 3፣9፡፡ ‘‘አብረንም እየሠራን የእግዚአብሔርን ጸጋ በከንቱ እንዳትቀበሉ ደግሞ እንለምናለን’’ 2ኛ ቆሮ 6፣1፡፡ የእግዚአብሔርን ጸጋ በከንቱ መቀበል የተባለው እንዴት ያለ መቀበል ነው? ይህ ከንቱ መቀበል ለተቀበልነው ጸጋ እንደሚገባ አለመኖርና ክርስትናችንን ለእግዚአብሔር አለመቀደስ ነው፡፡
በሌላም ቦታ ‘‘የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከዅላችኹ ጋራ ይኹን።’’ ተብሎ እንደተጻፈ ይህ ጸጋ ሰው ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ጋር በህብረት የሚሠራበት ነው፡፡ 2ኛ ቆሮ 13፣14 ፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ህብረት የማናደርግበትና በመንፈሳዊነት የማንመላለስበትና የማንጠነቀቅበት ጸጋ ወደ መዳን ሊመራን አይችልም፡፡ በ1ኛ ቆሮ 3፣9-10  ላይም እንዲህ ተጸፏል፡- ‘‘የእግዚአብሔር እርሻ ናችኹ፤ የእግዚአብሔር ሕንጻ ናችኹ፤ ከርሱ ጋራ ዐብረን የምንሠራ ነንና። የእግዚአብሔር ጸጋ እንደተሰጠኝ መጠን እንደ ብልኀተኛ የአናጺ አለቃ መሠረትን መሠረትኹ፥ ሌላውም በላዩ ያንጻል። እያንዳንዱ ግን በርሱ ላይ እንዴት እንዲያንጽ ይጠንቀቅ።’’ በእርግጥም ከእግዚአብሔር የምንቀበለው ጸጋ እንደ ብልህ አናጺ በተቀበልነው  ላይ እንዴት እንደምናንጽ/ እንደምንታዘዘው የምንጠነቀቅበትን መንፈሳዊነት ይሻል፡፡ የሰው ልጅ ነጻ ፈቃድ ለእግዚአብሔር ጸጋ ምላሽ እስካልሰጠ ድረስ ሊድን አይችልም፡፡ ጸጋው ወደ መዳን የምንመጣበት መንገድ ቢሆንም በዚህ መንገድ መጓዝና ወደ መዳን መድረስ የሰው ልጆች ድርሻ ነው፡፡ ‘‘ዛሬ ድምፁን ብትሰሙት፥ አባቶቻችኹ እኔን የፈተኑበት፣ የመረመሩበትም፥ አርባ ዓመትም ሥራዬን ያዩበት፥ በምድረ በዳ፣ በፈተና ቀን በማስመረር እንደ ኾነ፥ ልባችኹን እልከኛ አታድርጉ።’’ ዕብ 3፣8-9፡፡ እስራኤል አርባ ዓመታት ሙሉ ለእግዚአብሔር ባለመታዘዛቸውና ፈቃዱንና ሀሳቡን ቸል በማለታቸው ወደ እረፍቱ ለመግባት ቢወጡም ወደ እረፍቱ ሳይገቡ ቀርተዋል፡፡ በሀዲስ ኪዳንም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እረፍቱ ሊያስገባን አስቀድሞ እርሱ በራሱ ብቻውን እረፍታችንን ሰርቶልናል፡፡ በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰራልን እረፍት ነው እንግዲህ ጸጋ የሚባለው፡፡ ወደ እረፍቱ ሊያስገባን ጸጋው ቢሰጠንም ወደ እረፍቱ እንድንገባ ለጸጋው ካልታዘዝን ጸጋው ብቻውን እረፍት የተባለች መንግስቱን አያወርሰንም፡፡ ‘‘እንግዲህ ወደ እረፍቱ ለመግባት ተስፋ ገና ቀርቶልን ከሆነ፥ ምናልባት ከእናንተ ማንም የማይበቃ መስሎ እንዳይታይ እንፍራ’’ ተብሎ እንደተጻፈ ጸጋው ለእረፍቱ የተገባን አድርጎ ከቆጠረንና ወደ እረፍቱ የሚያገባን መንገዳችን ከሆነ ምናልባት ለእረፍቱ የማንበቃና ያልተገባን ሆነን እንዳንገኝ ለጸጋው እንደሚገባ መኖርና መታዘዝ ይጠበቅብናል፡፡ ዕብ 4፣1፡፡ ይህ ማለት ግን ያለ እግዚአብሔር ጸጋ ሥራችን ብቻውን ያድነናል ማለት አይደለም፡፡ መንፈስ ቅዱስ ሊያድነንና ሊቤዠን ቢችልም ብቻውን ግን አይሠራም፡፡ መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን ውስጥ በሚሠራው ሥራ ውስጥ ሱታፌ እንዲኖረን ይሻል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ብቻውን የሚሠራና እኛም ድርሻ ከሌለን የሚኮነኑ ሰዎች አይኖሩም ማለት ነው፡፡ በእርግጥ መዳን በጸጋ ብቻ ከሆነ አንድም ኀጢአተኛ በምድር ላይ ሊኖር አይችልም፡፡ በምድር ላይ ወደ እግዚአብሔር ለመመለስና ለመታዘዝ የማይወዱ ሰዎች መኖር ጸጋ ብቻውን የማያድን መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡
‘‘ሙሴም ኢያሱን፦ ጎልማሳዎችን ምረጥልን፥ ወጥተኽም ከዐማሌቅ ጋራ ተዋጋ፤ እኔ ነገ የእግዚአብሔርን በትር በእጄ ይዤ በኰረብታው ራስ ላይ እቆማለኹ አለው። ኢያሱም ሙሴ እንዳለው አደረገ፥ ከዐማሌቅም ጋራ ተዋጋ፤ ሙሴና አሮንም ሖርም ወደ ኰረብታው ራስ ወጡ። እንዲህም ኾነ፤ ሙሴ እጁን ባነሣ ጊዜ እስራኤል ድል ያደርግ ነበር፤ እጁንም ባወረደ ጊዜ ዐማሌቅ ድል ያደርግ ነበር። የሙሴ እጆች ግን ከብደው ነበር፤ ድንጋይም ወሰዱ፥ በበታቹም አኖሩ፥ ርሱም ተቀመጠበት፤ አሮንና ሖርም አንዱ በዚህ አንዱ በዚያ ኾነው እጆቹን ይደግፉ ነበር፤ ፀሓይም እስክትገባ ድረስ እጆቹ ጠነከሩ። ኢያሱም ዐማሌቅንና ሕዝቡን በሰይፍ ስለት አሸነፈ።’’ ዘጸ 17፣9-13፡፡ ድሉ ከኢያሱ ሰራዊት ብርታት የተነሳ ነው ወይስ ከሙሴ ጸሎት? የአንዱን ድርሻ ከሌላው ለይቶ ማየት ከስሕተት ላይ ይጥላል፡፡ ኢያሱ የቱንም ያህል በብርታት ቢዋጋ ያለ ሙሴ ጸሎት (ያለ እግዚአብሔር ጸጋ) ድል ማድረግ አይችልም ነበር፡፡ ኢያሱም ለሰልፍ ባይወጣ ኖሮ የሙሴ ጸሎት ብቻውን ሰልፉን አይተካም ነበር፡፡ የሰው ሥራና የእግዚአብሔር ጸጋ የሚነጣጠሉ ሳይሆን አብረው የሚሄዱ ናቸው፡፡ ያለጸጋው ብቻችንን ምንም ማድረግ አንችልም፣ ጸጋውም ደግሞ ያለእኛ ሱታፌ ብቻውን አያድነንም፡፡ ጸጋ ከእግዚአብሔር ነው፣ ለጸጋው መታዘዝና እንደሚገባ መኖር ደግሞ ከእኛ ነው፡፡
ዳዊትስ ጎልያድን እንዴት አሸነፈው ? 1ኛ ሳሙ 17፣45-47፡፡ ‘‘ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን አለው፦ አንተ ሰይፍና ጦር ጭሬም ይዘኽ ትመጣብኛለኽ፤ እኔ ግን ዛሬ በተገዳደርኸው በእስራኤል ጭፍራዎች አምላክ ስም በሰራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም እመጣብኻለኹ። እግዚአብሔር ዛሬ አንተን በእጄ አሳልፎ ይሰጣል፤ እመታኽማለኹ፥ ራስኽንም ከአንተ አነሣዋለኹ፤ የፍልስጥኤማውያንንም ሰራዊት ሬሶች ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት ዛሬ እሰጣለኹ። ይኸውም ምድር ዅሉ በእስራኤል ዘንድ አምላክ እንዳለ ታውቅ ዘንድ፤ ይህም ጉባኤ ዅሉ እግዚአብሔር በሰይፍና በጦር የሚያድን እንዳይደል ያውቅ ዘንድ ነው። ሰልፉ ለእግዚአብሔር ነውና፤ እናንተንም በእጃችን አሳልፎ ይሰጣል።’’ እግዚአብሔር የረዳው ባይሆን ኖሮ ዳዊት ብቻውን ጎልያድን ማሸነፍ አይችልም ነበር፤ ዳዊትም ወደ ሰልፉ ባይወጣ ኖሮ የእግዚአብሔር ክንዱና ማዳኑ አይገለጥም ነበር፡፡ በሀዲስ ኪዳንም እንዲሁ ነው፤ ጸጋው የመዳናችን መንገድ ሆኖ ተሰጥቶናል፤ ያለጸጋው መዳን አይቻለንምና፡፡ ጸጋው ቢሠጠንና ለመዳን የተገባን ቢያደርገንም ለጸጋው መታዘዝና እንደሚገባ መኖር የእኛ ድርሻ ነው፡፡ ጸጋው ድካማችንን ያግዛል እንጂ የእኛን ድርሻ አይፈጽምልንም፡፡ ጸጋው የእግዚአብሔር ድርሻ ሲሆን በጸጋው አምኖ በበጎ ምግባራት መጽናት ደግሞ የእኛ ድርሻ ነው፡፡ ጸጋ፣ እምነትና በጎ ምግባራት አብረው የሚኖሩና የማይነጣጠሉ ናቸው፡፡ መዳን እነዚህ ሦስቱ ተባብረው ሲገኙ ነው አንጂ ከሦስቱ አንደኛው በጎደለበት ዘንድ መዳን የለም፡፡ ከጎልያድና ከዳዊት አንደምንማረው ምንም እንኳን ድል ከእግዚአብሔር ቢሆንም ለሰልፍ መውጣት ግን ከሰው ነው፡፡ እግዚአብሔር ድልን የሚሰጠው ወደ ሰልፉ ለወጡት ብቻ ነውና፡፡ በጸጋው መጠቀምና መዳን የምንችለው ለጸጋው ስጦታ መታዘዝና ለዚህም የሚገባ ክርስቲያናዊ ሕይወት ሲኖረን ብቻ ነው፡፡ ወደ ጸጋው በእምነትና በመታዘዝ የሚመጡትን ሁሉ እግዚአብሔር ይቀበላቸዋል፣ ይረዳቸዋል፣ ያግዛቸዋል፣ ወደ መዳንም ያመጣቸዋል፡፡ ጸጋው አድኖናል ብለው ለጸጋው የማይታዘዙትና ድርሻቸውን ከማድረግ የሚሰንፉትን ደግሞ ጸጋው ብቻውን ሊረዳቸውና ሊሠራባቸው አይቻለውም፡፡

    ይቀጥላል . . .

4 comments:

  1. በከመዝ ነአምን/እንዲህ እናምናለን ዓምድ ስር የሚወጡት ትምህርቶች መሰረታዊ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርቶች የያዙ ስለሆኑ በጣም ጥሩ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ፡፡ ከዚህ በበለጠ አጠናክራችሁ እንደምትገፉበትና ለኦርቶዶክሳዊው ትምህርት መገለጥና መስፋፋት የበኩላችሁን አስተዋጽዖ እንደምታበረክቱ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ የቤተ ክርስቲያን አምላክ የሚበልጠውን ጸጋ ያብዛላችሁ፡፡

    ReplyDelete
  2. አለን ከእናንተ ጋር ነን፡፡ እየተከተልናችሁ ስለሆነ በርቱ፡፡ እየተከተልናችሁ መሆኑን እረስታችሁ ሥራችሁን ከመስራት ወደ ኋላ እንዳትሉ፡፡ ገና ብዙ ነገር ነው ከእናንተ የምንጠብቀው፡፡

    ReplyDelete
  3. ጥሩ ጅምር ነው፡፡ እኛስ ምን ልንረዳችሁ እንችላለን? የምንረዳችሁ ነገር ካለ የምንችለውን ለማድረግ ዝግጁ ነን፡፡

    ReplyDelete
  4. I really your work. Please go on this way to teach us the Orthodox perspectives of salvation. May God bless all the group members who have part on this work.

    ReplyDelete