Wednesday, April 20, 2016

እንዴት እንጸልይ? (የመጨረሻ ክፍል)




አንድ ሰው ለጸሎት ሲነሳ ዝም ብሎ እንደ ውሃ ደራሽ መሆን የለበትም፡፡ ለምን? እንዴት? መቼ? እጸልያለሁ የሚሉት ጥያቄዎች ሊመለሱ ይገባል፡፡ ለምንና መቼ መጸለይ አለብን የሚለውን በክፍል አንድና ሁለት ዝግጅቶቻችን ስለተመለከትን ከዚህ ቀጥለን ደግሞ እንዴት መጸለይ እንዳለብን ለመመልከት እንሞክራለን፡፡ ስለጸሎት በምናስብበት ማናቸውም ጊዜ ልናስተወላቸው የሚያስፈልጉን ሁለት መሠረታዊ ነጥቦች አሉ፡- በእምነት መጸለይና በጥልቀት/በማስተዋል መጸለይ፡፡ እስኪ ሰፋ አድርገን እንመልከታቸው፡-
1.         በእምነት መጸለይ
እግዚአብሔር አምላካችን ስለሚያስብልንና ስለሚወደን ልመናችንን እንደሚሰማንና የሚረባንን ነገር እንደሚያደርግልን፣ የተሻለውንም ነገር እንደሚሰጠን ልናምን ያስፈልገናል፡፡ ‘‘አምናችኹም በጸሎት የምትለምኑትን ዅሉ ትቀበላላችኹ፡፡’’ ማቴ 21፣22 ተብለናልና አምላካችን እግዚአብሔር የሚያስፈልገንን ሁሉ ሳንለምነው እንደሚሰጠንም እናምናለን፡፡ ‘‘ሳትለምኑት አባታችሁ የሚያስፈልጋችሁን ያውቃልና’’ ተብሎ እንደተጻፈ እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን በለመንነው ነገር ይቅርና ባለመንነው በጎ ነገርም ላይ እርሱ ጻድቅና የታመነ ነው፡፡ (ማቴ 6፣8)፡፡ እስከ ሞት የወደደን እርሱ ደግሞ ሊሰጠን የማይወደውና የሚከለክለን ነገር እንደሌለ እናምናለን፡፡ ‘‘ለገዛ ልጁ ያልራራለት ነገር ግን ስለ ሁላችን አሳልፎ የሰጠው ያው ከእርሱ ጋር ደግሞ ሁሉን ነገር እንዲያው እንዴት አይሰጠንም?’’ ሮሜ 8፣32፡፡ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ሞት የወደደንና የታረቀን አባታችን እግዚአብሔር የበጎ ነገር ሁሉ ምንጭ፣ የመልካምነት ሁሉ መዝገብ፣ የቸርነት ሁሉ መገኛ ነውና የምንለምነውን ሁሉ ከእርሱ እንደምንቀበል አውቀን እንጸልያለን፡፡ ‘‘ለምኑ፥ ይሰጣችኹማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችኹ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፈትላችኹማል። የሚለምነው ዅሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልገውም ያገኛል፥ መዝጊያንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል። ወይስ ከእናንተ፥ ልጁ እንጀራ ቢለምነው፥ ድንጋይን የሚሰጠው ከእናንተ ማን ሰው ነው? ዓሣስ ቢለምነው እባብን ይሰጠዋልን? እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትኾኑ ለልጆቻችኹ መልካም ስጦታ መስጠትን ካወቃችኹ፥ በሰማያት ያለው አባታችኹ ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መልካም ነገርን ይሰጣቸው?’’ (ማቴ 7፣7-11)፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ለፍጥረቱ ሁሉ መጋቢ፣ የሚያዝንና የሚራራ ስለሆነ የምንለምነውን ሁሉ እንደሚሰጠንና እንደሚያደርግልን አምነን እንጸልያለን፤ ይህ እምነት እንኳን ባይኖረን ‘‘አለማመኔን እርዳው’’ ብለን ልንጸልይ ያስፈልገናል፡፡ እግዚአብሔር አምላካችንም የእምነት ሰዎች ሊያደርገንና በፊቱ የእምነት ሰዎች ሆነን እናድግ ዘንድ ሊያግዘን ይቻለዋል፡፡ (ማር 9፣24)፡፡ ሐዋርያትም በአንድ ወቅት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ‘‘እምነት ጨምርልን’’ ብለውት ነበር፡፡ ሉቃ 17፣5፡፡ እርሱም በለመኑት ነገር ሁሉ ላይ የታመነ ነውና ሐዋርያቱን በእምነት አሳድጓቸዋል፣ አጠንክሯቸዋልም፡፡
እምነት በጸሎት ሕይወታችን ውስጥ ከእግዚአብሔር ኃይልን የምንቀበልበት ታላቅ መንፈሳዊነት ነው፡፡ የቱንም ያህል እግዚአብሔር እንደረሳን ቢሰማንና የዘገየ ቢመስለንም እርሱ ሁሉን የሚያደርግበት የራሱ ጊዜ አለውና በእምነት ጸንተን እንጸልያለን፣ በእምነታችንም ወስጥ ደግሞ የእርሱን ጊዜ በትዕግስት እንጠብቃለን፡፡ ጻድቅ ኢዮብ እንዴት እንደተፈተነ እናውቃለን፤ ሆኖም ግን እግዚአብሔርን ባለማመን፣ ተስፋ በመቁረጥና የእግዚአብሔርን ጊዜ ባለመጠበቅ አልደከመም፡፡ በብዙ መከራው ውስጥ እግዚአብሔርን በመጠበቁ ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛውን እግዚአብሔር ለኢዮብ ሊባርክለት ወዷል፡፡    
2.           በጥልቀትና በማስተዋል እንጸልይ፡፡
ለጸሎት በእግዚአብሔር ፊት በምንቆምበት ጊዜ ሁሉ  ከውስጣችን የምናወጣው ማናቸውም ቃልና የምናደርገው ማንኛውም ዓይነት እንቅስቃሴ በማወቅና  በማስተዋል መሆን አለበት፡፡ ከልብ ፈንቅሎ የሚወጣ፣ ከመንፈሳዊነት ጥግ የሚመነጭ ጥልቅ ስሜት ያልተለየው፣ እውነተኛ መንፈሳዊ መሻትን የሚገልጽ እውነት እንዲኖረን ያስፈልጋል፡፡ ይህም ሲባል ጸሎታችን ኃጢአታችንን በመናዘዝና ጥፋታችንን በማመን የተደረገ (መዝ 50/ ምሳ 28፣13)፣ እግዚአብሔርን ተስፋ በማድረግና በመጠበቅ ውስጥ የሆነ (አንተ የመድኃኒቴ አምላክ ነህና በእውነትህ ምራኝ፥ አስተምረኝም ቀኑን ሁሉ አንተን ተስፋ አድርጌአለሁ መዝ 25፣5/ ሮሜ 8፣24-25)፣ በፍቅር የምንፈጽመው (1ኛ ቆሮ 13) ሊሆን ይገባል፡፡ ያለፍቅር የሚሆን ማናቸውም በጎ ነገር ሁሉ ከንቱ መሆኑ ተጽፏል፡፡ 1ኛ ዮሐ 3፣10 ላይም ወንድሙን የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም ተብሎ ተጽፏልና ጸሎታችን ጠላቶቻችንን በመውደድ፣ ለሌሎች በማዘንና በመራራት ውስጥ ሆነን የምንጸልየው ሊሆን ይገባል። በመጽናት (ኤፌ 6፣18 በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፤ በዚህም አሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ  በመጽናት ሁሉ ትጉ) እንደተባለ እግዚአብሔርን በመጽናት የምንጠብቅበትና የምንታገስበትም እንዲሆን ያስፈልገናል፡፡
በጸሎት ሕይወታችን ለማደግ ምን እናድርግ?
     ሀ. በእግዚአብሔር ፊት ለጸሎት የምንቆምበትን ሰዓት ለማርዘም ራሳችንን እናለማምድ፡፡
ጸሎት የእግዚአብሔርን ፊት መሻት ስለሆነና በእግዚአብሔርም ፊት መቆም ስለሆነ በፊቱ የምንሆንበት ጊዜ የደስታችንና የሰላማችን ጊዜ ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ፊት የሚሻ ሰው ለእግዚአብሔር የሚሆን ጊዜ አያጣም፡፡ በእርግጥ በእግዘዚአብሔር ፊት መሆን ምን ማለት እንደሆነ የሚገባንና የምንረዳው ከሆነ በእግዚአብሔር ፊት በጸሎት የምንቆምበት ጊዜ ልናጣ አንችልም፡፡ በዕለት ኑሯችን ውስጥ ለምናከናውናቸው የተለያዩ ተግባራት ጊዜ መድበን፣ መርሐ ግብር አውጥተን እንደምንተጋው ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ለመሆንና በፊቱም በጸሎት ለመቆም ጊዜ መመደብ ያስፈልገናል፡፡ ከዚህም ባሻገር በፊቱ የምንሆንበትን የጊዜ ቆይታ/ርዝማኔ ቀስ በቀስ ማሳደግም ይጠበቅብናል፡፡ ‘‘አቤቱ ሕግህን እንደምን እጅግ ወደድሁ ቀኑን ሁሉ እርሱ ትዝታዬ ነው፡፡’’ መዝ 118፡97 እንዳለ ቅዱስ ዳዊት እግዚአብሔር አምላካችን የቀን ሁሉ ትዝታችን ሊሆን ይገባል፡፡ ቅዱስ ዳዊት ንጉሥ ቢሆንና ብዙ ኃላፊነቶች የነበሩበት ቢሆንም በእግዚአብሔር ፊት የሚሆንባቸው ረጃጅም የጸሎት ጊዜያት ግን ነበሩት፡፡
      ለ. በማለዳ በመነሳት ዕለቱን በጸሎት መጀመርን እንለማመድ፡፡
‘‘ማልጄም እነሳለሁ’’ መዝ 107፣ 2 እንዳለ ቅዱስ ዳዊት በማለዳ ተነስተን ቀኑን በእግዚአብሔር ፊት በመቆምና በጸሎት ብንጀምር ቀኑ የተባረከ ይሆንልናል፣ በእግዚአብሔር ፊት መሆናችንንም ባሰብን ቁጥር ጥንካሬ ስለሚሰማን ችግሮችን የምንጋፈጥበትና የምንቋቋምበት ኃይል ይሰማናል፡፡ ቀኑን ከእግዚአብሔር ጋር በመነጋገር መጀመር እንዴት ያለ መቀደስ ነው! ከሁሉ በፊት፣ ማናቸውንም ስጋዊ ተግባራችንን ከመጀመራችን በፊት በእግዚአብሔር ፊት መቆምና የእርሱንም ፊት ማየት ታላቅ መባረክና በቀጣይ ለምናደርጋቸው ሥጋዊ ተግባራት ሁሉ መከናወን ነው፡፡
         ሐ. በየሰዓቱ መጸለይን እንለማመድ፡፡
በእርግጥ ቀኑን ሙሉ በጸሎት ማሳለፍ አይቻለንም፣ ሆኖም ግን የየቀኑን ዋና ዋና የጸሎት ጊዜያትን ተጠቅመን በእግዚአብሔር ፊት በጸሎት ማሳለፍን መለማማድ ይጠበቅብናል፡፡ ደጋግመን በእግዚአብሔር ፊት መሆን ስንችል በመንፈሳዊ ሕይወታችን የበረታንና ዕለት ዕለትም በእግዚአብሔር ጸጋ የምናድግ እንሆናለን፡፡ ‘‘ሁልጊዜ እግዚአብሔርን በፊቴ አየዋለሁ በቀኜ ነውና አልታወክም።’’ መዝ 15፣8 ተብሎ እንደተጻፈ ሁልጊዜ በየሰዓቱ እግዚአብሔርን ለማየትና በፊቱም ለመሆን ጥረት ማድረግ አለብን፡፡ በፊቱ ከምንሆንባቸው መንገዶች ዋነኛው ደግሞ ጸሎት ነው፡፡ ይህን ማድረግ ስንችል እግዚአብሔር በቀኜ ነውና አልታወክም ማለት እንችላለን፡፡ 
     መ. ባለንበት በማንኛውም ቦታ መጸለይን እንለማመድ፡፡
እግዚአብሔርን የምትሻ ነፍስ በማንኛውም ቦታና ጊዜ እርሱን ከመሻት ቸል አትልም፡፡ ‘‘ከመንፈስኽ ወዴት እኼዳለኹ ከፊትኽስ ወዴት እሸሻለኹ ወደ ሰማይ ብወጣ፥ አንተ በዚያ አለኽ። ወደ ሲኦልም ብወርድ፥ በዚያ አለኽ። እንደ ንስር የንጋትን ክንፍ ብወስድ፥ እስከባሕር መጨረሻም ብበርር፥ በዚያ እጅኽ ትመራኛለች፥ ቀኝኽም ትይዘኛለች።’’ (መዝ 138፣ 6-10) እንዲል መንፈሳዊ ሰው በማንኛውም ቦታ ቢሆን እግዚአብሔርን ማግኘት እንደሚችልና ከእርሱም ጋር መሆን እንደሚችል ያምናል፡፡ ስለሆነም ባገኘነው አጋጠሚ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት በጸሎት ለመሆን የምንጥር ከሆንን በመንፈሳዊ ሕይወታችን በቀላሉ የምናድግና የዲያብሎስንም ሽንገላ የምንቃወም መሆን እንችላለን፡፡ ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ መጸለይ እንድንችል ደግሞ በቃላችን የምንጸልያቸው/የምናስታውሳቸው የጸሎትና የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ማጥናትና መያዝ ይጠበቅብናል፡፡   
         ሠ. በጸሎታችን ስለሌሎችም መጸለይን እንማር፡፡
የእኛ ጸሎት የሚያስፈልጋቸው ብዙ ሰዎች እንዳሉ መዘንጋት የለብንም፡፡ ስለሌሎች የምንጸልይ ከሆነ እግዚአብሔር እኛ ስለራሳችን የምንደርገውን ጸሎታችንንና ልመናችንን ቶሎ ይሰማናል፡፡ ስለወዳጆቻችን ብቻ ሳይሆን ስለጠላቶቻችንም እንድንጸልይም ታዘናል፡፡ ‘‘እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሏችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፡፡’’ (ማቴ 5፣44-45) የሃይማኖታችን ራስና ፈጻሚ የሆነው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረን ጠላቶቻችንን እንድንወድ፣ የሚረግሙንን እንድንመርቅ፣  ለሚጠሉን መልካም እንድናደርግና ለሚያሳድዱንም እንድንጸልይ ነው፡፡ ይህን ማድረግ ስንችል ብቻ የሰማዩ አባታችን ልጆች እንሆናለን፤ ይህንን ማድረግ ሳንችል ግን የእግዚአብሔር ልጆች መሆን አንችልም፡፡ እግዚአብሔርን እንወዳለን እያልን የምንጠላቸው ሰዎች ሊኖሩን አይገባም፤ ስለሆነም ለጸሎት በቆምንበት ሰዓት ሁሉ ስለሌሎች ሰዎች መጸለይ አንዱ ክርስቲያናዊ ግዴታችን መሆኑን ተገንዝበን ለሌሎች መጸለይን እንማር፡፡
       ረ. በመከራችንና በችግራችን ወቅትም እንጸልይ፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን በሁሉ ላይ አምላክ እንደሆነና ሁሉን ማድረግ እንደሚችል የምናምን ከሆነ በሰላሙ ወቅት ብቻ ሳይሆን በችግራችንና በሀዘናችን ጊዜም መጸለይ አለብን፡፡ እርሱ ከችግራችን በላይ ነውና፣ በችግራችንም ላይ ሊሰለጥንበት ይቻለዋልና ከችግራችን በፊት እንደምናደርገው ሁሉ በችግራችንና በመከራችን ውስጥ ሆነን የእግዚአብሔርን ፊት በጸሎት መፈለጋችንን አንተው፡፡ በማንኛውም የሕይወታችን ጉዳይና በማንኛውም ዓይነት ርእስ ላይ መጸለይን እናዘውትር፡፡ አምላካችንን የምንሻው በነገር ሁሉ ነው እንጂ በተመረጡ ጉዳዮች ላይ ብቻ አይሁን፡፡ ኢዮብ በደስታውና በማግኘቱ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በሀዘኑና በማጣቱ ጊዜም የእግዚአብሔርን ፊት እንደፈለገ፤ ይህም እንዴት እንደጠቀመው እናውቃለን፡፡ ስለሆነም በነገሮች ሁሉ የአምላካችንን ፊት ከመሻት አንድከም፡፡
        ሰ. ስንጸልይ ማስተዋልንና ጥንቃቄን ገንዘብ እናድርግ፡፡
ጸሎት በእግዚአብሔር ፊት መቆም ስለሆነ በፊቱ መሆናችን በማስዋልና በፍርሐት፣ በመንፈሳዊ መረዳትም ሊሆን ያስፈልጋል፡፡ ጸሎት መንፈሳዊነት እንጂ ሥራ ወይም ልማድ አይደለም፡፡ ስለሆነም ዕለት ዕለት በመንፈሳዊ መረዳትና ጥንቃቄ መጸለይን መማር አለብን፡፡ ሐዋርያት ጌታችንን ‘‘ጌታ ሆይ፥ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን እንዳስተማረ እንጸልይ ዘንድ አስተምረን።’’ ያሉትና ጌታችንም ጸሎትን ያስተማራቸው፤ ጸሎት የምንማረውና ዕለት ዕለት የምናድግበት፣ በመንፈሳዊነትና በጥንቃቄ፣ በማስተዋልም የምንፈጽመው መንፈሳዊ ተግባር ስለሆነ ነው፡፡ ሉቃ 11፣1፡፡ ጸሎት በእግዚአብሔር ፊት መሆን እስከሆነ ድረስ በፊቱ በሆንንባቸው ጊዜያት ሁሉ ከእርሱ የምንማራቸው ብዙ መንፈሳዊ ትምህርቶችንና መረዳቶችን እናገኛለን፡፡
          ሸ. ኀጢአታችንን በማመንና ለሌሎች ድካም በመራራት እንጸልይ፡፡
በእግዚአብሔር ፊት ለጸሎት የምንቆመው እግዚአብሔር አምላካችን ስለማረንና ስለተቀበለን እንደሆነ መዘንጋት የለብንም፡፡ ምሕረቱን ከተቀበልን ደግሞ ኀጢአተኛነታችንን ማመንና ለንስሓ የሚገባ ፍሬ የምናፈራ፣ ለሌሎች ወገኖቻችንም የምናዝንና የምንራራ መሆን አለብን፡፡ በሉቃ 18፣10-14 እንደምናነበው ከፈሪሳዊው ጸሎት ይልቅ የቀራጩ ጸሎት መሰማቱንና ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ መመለሱን ስናስብ ጸሎት በድካማችን የራራልንን የአምላካችንን ምሕረት በማሰብና ለሌሎች ሰዎች ድካምም በመራራት የምንፈጽመው መንፈሳዊነት እንጂ በማድረጋችን የምንመፃደቅበት መንፈስ የተለየው ሥጋዊ ተግባር ብቻ አይደለም፡፡ የፈሪሳዊውን ጸሎት ብንመለከት፡- ‘‘እግዚአብሔር ሆይ፥ እንደ ሌላ ሰው ዅሉ፥ ቀማኛዎችና ዐመፀኛዎች አመንዝራዎችም፥ ወይም እንደዚህ ቀራጭ ስላልኾንኹ አመሰግንኻለኹ፤ በየሳምንቱ ኹለት ጊዜ እጦማለኹ፥ ከማገኘውም ዅሉ ዓሥራት አወጣለኹ፡፡’’ የሚል ነበር፡፡ የጸሎት ዐላማው ራስን በእግዚአብሔርና በሰዎች ዘንድ በማጽደቅ ሌሎችን መንቀፍና በድካማቸው ላይ መፍረድ አይደለም፡፡ መንፈሳዊነት ራስን በማጽደቅ ሌሎችን መኮነን ሳይሆን በብዙ ድካማችንና መተላለፋችን ውስጥ የራራልንን አምላክ ማመስገን፣ ስለበዛልን ምሕረቱና በጎነቱም ስሙን መቀደስ ነው፡፡ የእግዚአብሔር አሳቡ የወንድማችንን ጉድፍ የሚመለከት  ዓይን እንዲኖረን ሳይሆን በእኛ ዓይን ውስጥ ያለውን ምሰሶ ተመልክተን እርሱን እንድናወጣ ነው፡፡ የቀራጩ ጸሎት ግን በትሑት ሰብእናና በተሰበረ መንፈስ የተደረገ እንደነበረ እናስተውላለን፡- ‘‘ቀራጩ ግን በሩቅ ቆሞ ዐይኖቹን ወደ ሰማይ ሊያነሣ እንኳ አልወደደም፥ ነገር ግን፦አምላክ ሆይ፥ እኔን ኀጢአተኛውን ማረኝ እያለ ደረቱን ይደቃ ነበር።’’ እንደ ቀራጩ መጸለይ ስንችል ብቻ ጻድቅ ሆነን ወደ ቤታችን መመለስ እንችላለን፡፡
በጸሎት ሕይወቱ የማይደሰትና ለመጸለይ የሚሰንፍ ሰው በእግዚአሔር ፊት ሊሆንና በመንፈሳዊ ሕይወቱም ሊያድግ አይቻለውም፡፡ ጸሎት በእርግጥ በእግዚአብሐሔር ፈፊት መሆንሐሐ     ሔር ፊት መቆም እርሱንም መሻትና ከእርሱ ጋር መነጋገር መሆኑ የገባው ሰው ብቻ ነው አንዲህ ማለት የሚችለው፡- ‘‘እግዚአብሔር የርስቴ ዕድል ፈንታና ጽዋዬ ነው፥ ዕጣዬንም የምታጠና አንተ ነኽ። ገመድ ባማረ ስፍራ ወደቀችልኝ፥ ርስቴም ተዋበችልኝ። የመከረኝን እግዚአብሔርን እባርካለኹ . . . ዅልጊዜ እግዚአብሔርን በፊቴ አየዋለኹ፤ በቀኜ ነውና፥ አልታወክም። ስለዚህ፥ ልቤን ደስ አለው ምላሴም ሐሴት አደረገች፤ ሥጋዬም ደግሞ በተስፋ ታድራለች . . . የሕይወትን መንገድ አሳየኸኝ፤ ከፊትኽ ጋራ ደስታን አጠገብኸኝ፥ በቀኝኽም የዘለዓለም ፍሥሓ አለ።’’ መዝ 15፣ 5-11፡፡ የጸሎት ምንነትና ጥቅሙም ሲገባን ብቻ ምክንያት ሳናበዛ መጸለይ እንችላለን፤ በየዕለቱም የበጎነታችንን አምላክ፣ የመድኃኒታችንንም ፊት በጸሎት እንፈልጋለን፣ በፊቱም አንማልላለን፡፡ ቅዱስ ዳዊትም እንዲህ ብሏልና:- ‘‘አንተ ፊቴን ሹት ባልኽ ጊዜ፦ አቤቱ ፊትኽን እሻለኹ ልቤ አንተን አለ፡፡’’ መዝ 26፣8፡፡
የአባቶቻችን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር በፊቱ የምንሆንበትንና የምናድግበትን፣ መንፈሳዊውን የጸሎት ሕይወት ለሁላችንም ያድለን አሜን፡፡
 

No comments:

Post a Comment