Wednesday, April 13, 2016

ጸጋና መዳን በኦርቶዶክሳዊው አስተምህሮ (ክፍል ሁለት)


ነጻ ፈቃድና ጸጋ
ነጻ ፈቃድም ይሁን መዳን ሁለቱም የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸው፡፡ የእግዚአብሔር ስጦታዎች ደግሞ እርስ በርሳቸው የሚጣሉና የሚጠፋፉ አይደሉም፡፡ ስለሆነም በውስጣችን የሚሆነው የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ነጻ ፈቃዳችንን የሚያስቀር አይደለም፡፡ ነጻ ፈቃዳችንን ተጠቅመን ለሥራው ምላሽ እንሰጣለን፣ በእርሱ ውስጥ እኛም አብረነው እንሠራለን፣ እርሱም በመንገዳችን ሁሉ ይመራናል ያግዘናልም፡፡ በውስጣችን የሚሆን ሥራውን ልናስቆምና ልንቃወምም ደግሞ እንችላለን፡፡ ‘‘እናንተ ዐንገተ ደንዳናዎች፥ ልባችኹና ዦሯችኹም ያልተገረዘ፥ እናንተ ዅልጊዜ መንፈስ ቅዱስን ትቃወማላችኹ፤ አባቶቻችኹ እንደ ተቃወሙት እናንተ ደግሞ።’’ ሐዋ 7፣51 51  ብሎ እንደተጻፈ ለመንፈስ ቅዱስ አሠራር የሚታዘዙ ያሉትን ያህል የመንፈስ ቅዱስን ሥራ የማይታዘዙና የሚቃወሙ ሰዎች መኖራቸውን መዘንጋት የለብንም፡፡ ጸጋው ሁልጊዜም አብሮን ሊሆንና በእኛም ውስጥ ሊሠራ የተዘጋጀ ቢሆንም ለጸጋው ሥራ እሺ ብለን መታዘዝ ካልቻልን ጸጋው በእኛ ውስጥ ሊሠራ አይችልም፡፡ እኛ ራሳችን ለጸጋው ሥራ ራሳችንን መስጠት ካልቻልን ጸጋው ብቻውን በእኛ ውስጥ ሊሠራና መዳናችንን ሊፈጽምልን አይችልም፡፡ ‘‘ለቤዛም ቀን የታተማችኹበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ።’’ ተብሎ እንደተጻፈ በውስጣችን የሚሠራውን መንፈስ ቅዱስን የማንታዘዝና ደስ ማሰኘት የማንችል ከሆንን ጸጋው ብቻውን በውስጣችን የሚሠራው ሥራ አይኖርም፡፡ ኤፌ 4፣30፡፡ ስለሆነም መዳን የእግዚአብር ጸጋና የሰው ልጆች ሱታፌ ውጤት እንጂ የጸጋው ውሳኔ ብቻ አይደለም፡፡ ‘‘መንፈስን አታጥፉ’’ ተብሎ እንደተጻፈ 2ኛ ተሰ 5፣19 በጸጋው የተደረገልንን ነጻ ስጦታና ከስጦታውም የተነሳ በሕይወታችን ሊሆንልን ያለውን የመንፈስ አሠራር የምናከብርና የምንታዘዝ እንጂ የምናሳዝንና የምናጠፋ መሆን የለብንም፡፡ በእርግጥ የእግዚአብሔር ጸጋ ቢያግዘንም እገዛውን ለመቀበል ወይም ለመቃወም ግን ምርጫው አለን፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ሥራ ውስጥ አብረን ብንሳተፍ ጸጋው ይረዳናል እኛም ወደ ፍጹም ሙላቱ እስክንደርስ ድረስ እናድጋለን፡፡ መንፈስ ቅዱስን ብንቃወም ግን አያስገድደንም፡፡ ጸጋው ሊያድነን፣ ሊረዳንና ሊያግዘን ሁል ጊዜም የቀረበ ቢሆንም ፈቃዳችንን ግን ይፈልጋል፡፡ ጌታም ደግሞ ሁልጊዜ ይጠይቀናል ‘‘ልትድን ትወዳለኽን ? ’’ ዮሐ 5፣6፡፡ ያለ ፈቃዳችንና መታዘዛችን ጸጋው ብቻውን ሊያድነን አይችልም፡፡ ጸጋውም ሆነ ነጻ ፈቃዳችን ሁለቱም የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸውና እርስ በርሳቸው አይቀዋወሙም፡፡ ነጻ ፈቃዳቸውን ተጠቅመው ለጸጋው የሚታዘዙ ይድናሉ፤ ነጻ ፈቃዳቸውን ተጠቅመው ከጸጋው ፈቀቅ የሚሉ ደግሞ አይድኑም፡፡
ጸጋና መንፈሳዊ ተጋድሎ
ክርስትና የጸጋ ሕይወት ብቻ ሳይሆን የመንፈሳዊ ተጋድሎም ጭምር ነው፡፡ ‘‘የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችኹ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ዅሉ ልበሱ።’’ ኤፌ 6፣11፡፡ እንደሚል የእግዚአብሔር ዕቃ ጦር የተባለው የእግዚአብሔር ጸጋ የማሸነፊያችን ምክንያት ቢሆንም ካልተጠቀምንበት ግን ልናሸንፍበት አንችልም፡፡ ጸጋው በመንፈሳዊው ተጋድሎ ውስጥ የሚረዳንና የሚያግዘን፣ ወደ መዳንም የሚያደርሰን መንገድ ነው፡፡ መጋደላችን ከጸጋው የተነሳ ነው፡፡ ጸጋው የሚያግዘን ባይሆን ኖሮ ለተጋድሎ መነሳት እንችልም ነበር፤ ምክንያቱም መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፡፡ ኤፌ 6፣12፡፡ ‘‘በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችኹ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤ በዓለም ያሉት  ወንድሞቻችኹ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችኹ በእምነት ጸንታችኹ ተቃወሙት።’’ እንደተባለ ዲያብሎስን እንዋጋዋለን፣ እንቃወመዋለንም ነገር ግን በራሳችን ኃይል አይደለም፡፡ ጠላትን እንዋጋለን እንታገላለን፣ በእግዚአብሔርና በጸጋውም እንታመናለን፡፡ 1ኛ ጴጥ 5፣8-9፡፡ ስለዚህ ክርስትና የጸጋ ሕይወት ብቻ አይደለም ማለት ነው፤ በጸጋው ውስጥ የሚሆን ተጋድሎም ጭምር እንጂ፡፡
ቆላ 1፣29 ‘‘ለዚህም ነገር ደግሞ፥ በእኔ በኀይል እንደሚሠራ እንደ አሠራሩ እየተጋደልኹ፥ እደክማለኹ።’’ ተብሎ እንደተጻፈ በክርስትና ውስጥ እስከሚደክሙ ድረስ የሚደረግ መጋደል አለ፤ ይህም መጋደል ደምን እስከማፍሰስ የሚደርስ ነው፡፡ ‘‘ከኀጢአት ጋራ እየተጋደላችኹ ገና ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችኹም’’ ይላልና ዕብ 12፣4፡፡ ከገዛ ሥጋችንና ፈቃዳችን ጋር እየተጋደልን እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት እንጥራለን፣ የሚረዳንን ጸጋውንም ደግሞ እንደገፋለን እንጂ በጸጋው ድነናል ብለን ጸጋውን የስንፍናችን ምክንያት በማድረግ መንፈሳዊ ተጋድሏችንን ከመፈጸም ወደ ኋላ አንልም፡፡ ደግሞም የእግዚአብሔር ጸጋ ኃይልን የምንቀበልበት ብቻ ሳይሆን የምንደክምበትም ሊሆን ይችላል፡፡ 2ኛ ቆሮ 12፣5-10 ‘‘እንደዚህ ስለ አለው እመካለኹ፥ ስለ ራሴ ግን ከድካሜ በቀር አልመካም። ልመካ ብወድስ ሞኝ አልኾንም፥ እውነትን እላለኹና፤ ነገር ግን፥ ማንም ከሚያይ ከእኔም ከሚሰማ የምበልጥ አድርጎ እንዳይቈጥረኝ  ትቻለኹ። ስለዚህም በመገለጥ ታላቅነት እንዳልታበይ የሥጋዬ መውጊያ፥ ርሱም የሚጐስመኝ የሰይጣን መልእክተኛ  ተሰጠኝ፤ ይኸውም እንዳልታበይ ነው። ስለዚህ ነገር ከእኔ እንዲለይ ሦስት ጊዜ ጌታን ለመንኹ። ርሱም፦ ጸጋዬ ይበቃኻል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና፥ አለኝ። እንግዲህ የክርስቶስ ኀይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለኹ። ስለዚህ ስለ ክርስቶስ በድካም፣ በመንገላታትም በችግርም፣ በስደትም፣ በጭንቀትም ደስ ይለኛል፤ ስደክም ያን ጊዜ ኀይለኛ ነኝና።’’ የእግዚአብሔር የጸጋው ኃይልና ብርታት በድካማችን ውስጥም የሚገለጥ ነው፡፡ ስለሆነም ዲያብሎስን በሙሉ ኃይላችን እንቃወመዋለን ሆኖም የእግዚአብሔርን ጸጋ ግን አንተውም/ቸል አንልም፡፡
በሌላም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አንዲህ የሚል ተጽፏል፡- ‘‘እግዚአብሔርም ጌዴዎንን፦ ከአንተ ጋራ ያለው ሕዝብ በዝቷል፤ ስለዚህ፥ እስራኤል፦ እጄ አዳነኝ ብሎ እንዳይታበይብኝ እኔ ምድያምን በእጃቸው አሳልፌ አልሰጣቸውም።’’ አለው፡፡ መሳ 7፣2፡፡  ይህም በጥቂቷ ጥረታችንና እንቅስቃሴያችን ውስጥ ጸጋው ታላቅ ነገርን እንደሚያደርግልን እንደሚያግዘንም ያስረዳል፡፡ እንዲያግዘንና እንዲሰራልን ግን እኛ ወደ  ሰልፉ መውጣት አለብን፡፡ ወደ ሰልፉ ሳንወጣ ዝም ብለን ብንቀመጥ ጸጋው ወደ ሰልፍ ወጥቶ ስለ እኛ አይዋጋልንም፡፡ ጸጋው በሰልፉ ውስጥ እንዲረዳንና እንዲያግዘን እኛ በሰልፉ ውስጥ መገኘት አለብን፡፡ በእጃችን ብንሠራም ኃይሉ ግን ከሚያግዘን ከእግዚአብሔር ጸጋ የተነሳ ነው፡፡ ጸጋውን ጥለን ብቻችንን አንሠራም፤ ጸጋው ይሠራልናል ብለንም ሁሉን ትተን አንቀመጥም፡፡ ክርስትና በጸጋው መደገፍ እንደሆነ ሁሉ በጸጋው ውስጥ መሥራትም ነው፡፡ ‘‘ነገር ግን፥ የኀይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳይኾን ይህ መዝገብ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን’’ 2ኛ ቆሮ 4፣7 ተብሎ እደተጻፈ የኃይሉ ታላቅነት ከጸጋው የተነሳ ነው፤ ሆኖም ግን በድካማችን ወስጥ የሚሆነው የኃይሉ ታላቅነት ይገለጥ ዘንድ በጸጋው ተደግፈን እንሰራለን፣ እንጋደላለንም፡፡
ታዲያ ቅዱስ ጳውሎስ ለምን “እንግዲህ ምሕረት ለወደደ ወይም ለሮጠ አይደለም፥ ከሚምር ከእግዚአብሔር ነው እንጂ። ’’ አለ ? ሮሜ 9፣16፡፡ የሰው ልጆች ፈቃድና ድካም በመዳናቸው ውስጥ ምንም ድርሻ የለውም ማለቱ ይሆን? አይደለም፤ ምክንያቱም እርሱ ራሱ እንዲህ ብሏልና፡- “ሩጫዬን ጨርሻለሁ’’ 2ኛ ጢሞ 4፣7፡፡ መዳን በጸጋ ብቻ ቢሆንና የሰው ልጆች ድርሻና ሱታፌ ባያስፈልግ ኖሮ የቅዱስ ጳውሎስ ሩጫ አያስፈልግም ነበር፡፡ የሰው ልጆች ሱታፌ በመዳን ውስጥ አስፈላጊ በመሆኑ ግን ቅዱስ ጳውሎስ ሩጫውን እስከሚጨርስ ድረስ በትዕግስት ሮጧል፡፡ በፊል 3፣13-14 ላይም እንዲህ ሲል ጽፎልናል፡- “ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ገና እንዳልያዝኹት እቈጥራለኹ፤ ነገር ግን፥ አንድ ነገር አደርጋለኹ፤ በዃላዬ ያለውን እየረሳኹ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለኹ በክርስቶስ ኢየሱስ ከፍ ከፍ ያለውን የእግዚአብሔርን መጥራት ዋጋ እንዳገኝ ምልክትን እፈጥናለኹ።’’ ከዚህ የምንማረው ዐቢይ ቁም ነገር ክርስትና አንድ ጊዜ ድነናል ብለን የምንተወው፣ ጸጋውን ሰበብ አድርገን መንፈሳዊውን ተጋድሎ ቸል የምንልበትና የምንተውበት ሳይሆን በየዕለቱ ወደ እግዚአብሔር ለመድረስ የምናድግበት ከፍታ መሆኑን ነው፡፡
“በእሽቅድምድም ስፍራ የሚሮጡት፥ ዅሉ እንዲሮጡ፥ ነገር ግን፥ አንዱ ብቻ ዋጋውን እንዲቀበል አታውቁምን እንዲሁም ታገኙ ዘንድ ሩጡ።’’ 1ኛ ቆሮ 9፣24፡፡ ጸጋው ወደ በለጠው ዋጋ ለመድረስ የምንሮጥበት ዋጋውን የመቀበላችን ዋስትና ነው እንጂ ላለመሮጥና ላለመድከም የምንሰንፍበት ምክንያት አይደለም፡፡ በሮጥንበት ልክና መጠን እንዲሁ ዋጋችንን እንቀበላለን፡፡ በሩጫችን ውስጥ ስንደክም ግን ጸጋው ያግዘናል፣ ያበረታናልም፡፡ ሩጫ የሌለበት የክርስትና ሕይወት የለም፡፡ ተጀምሮ እስከሚፈጸም ድረስ ክርስትናችን በሩጫ የተሞላ ስለሆነ ይህንን ሩጫ በትእግስት እንድንሮጥ ታዘናል፡፡ “እኛ ደግሞ ሸክምን ዅሉ ቶሎም የሚከበንን ኀጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን  ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ’’ ዕብ 12፣1-2፡፡ ጸጋው ላለመሮጥና ላለመጋደል ምክንያት እንደሚሆን ማሰብ ከስሕተት ላይ ይጥላል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን በጸጋው የሚያምኑና የሚደገፉ ከጸጋው የተነሳ ለመንፈሳዊ ተጋድሎና ለበጎ ምግባራት ሲፋጠኑና ሲተጉ እንጂ ጸጋውን ሰበብ አድረገው ከመንፈሳዊው ተጋድሎና ከበጎ ምግባራት ራሳቸውን ሲያሸሹ አይደለም፡፡ “ስለዚህ፥ እኔ ያለዐሳብ እንደሚሮጥ ዅሉ፥ እንዲሁ አልሮጥም፤ ነፋስን እንደሚጐስም ዅሉ እንዲሁ አልጋደልም’’ ተብሎ እንደተጻፈ እንዴት መሮጥ እንዳለብን ማስተዋል ግን የእኛ ድርሻ ነው፡፡ እንሮጣለን/እንጋደላለን፤ ግን ደግሞ የእግዚአብሔርን ጸጋ፣ የበጎነቱንም ሥራ እንለምናለን፡፡ ሩጫችን ብቻውን የምንፈልገውን ወጤት ስለማያስገኝልን ጸጋውን እንደገፋለን፡፡ 1ኛ ቆሮ 9፣26፡፡
“ነገር ግን፥ በእግዚአብሔር ጸጋ የኾንኹ እኔ ነኝ፤ ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋው ከንቱ አልነበረም ከዅላቸው ይልቅ ግን ደከምኹ፥ ዳሩ ግን ከእኔ ጋራ ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው እንጂ እኔ አይደለኹም።’’ 1ኛ ቆሮ 15፣10፡፡ እንዲህ እናምናለን፡- ክርስቲያኖች ልንሆን የተጠራነውና የእግዚአብሔር ልጆቹ ተብለን ልንጠራ ስልጣንን የተቀበልነው በጸጋው ነው፡፡ የሆንነውን ሁሉ የሆንነው ከጸጋው ስጦታ የተነሳ ነው፣ ይህም ጸጋው መንግስቱን የምንወርስበት እንደሆነም እናምናለን፤ ግን ደግሞ በጸጋው ተደግፈን አብዝተን እንደክማለን፣ ለፈቃዱና ለሐሳቡም እንታዘዛለን፣ ደምን እስከማፍሰስ ደርሰን ከኀጢት ጋር እንጋደላለን፡፡ በእርግጥ ምሕረት ለወደደ ወይም ለሮጠ አይደለም፡፡ ሆኖም ምሕረቱን ለማይሹና ለማይሮጡም የእግዚአብሔር ጸጋ አያግዛቸውምና ምህረቱን ሊቀበሉ አይችሉም፡፡ የክርስትና ትምህርት ጽንፍ አይደለም፡፡ ጽንፍ መያዝ በክርስትናችን ውስጥ የለም፡፡ “መዳን በጸጋው ብቻ፣ መዳን በእምነት ብቻ፣ መዳን በበጎ ምግባራት ብቻ’’ የሚሉ ትምህርቶች ከክርስትና የወጡ/ያፈነገጡ ጽንፎች ናቸው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም እንዲህ አይደለም የሚያስተምረን፡፡ እውነተኛው የክርስትና ትምህርትና ከመጽሐፍ ቅዱስ የምናነበውም መዳን በጸጋ፣ በእምነትና በበጎ ምግባራት እንደሆነ ነው፡፡ መዳን በዚህ ብቻ ነው ብሎ አንደኛውን ብቻ ነጥሎ መውሰድ እግዚአብሔር የሰራልንን መዳን በራሳችን ፈቃድና አቅም መወሰንና መበየን ነው፡፡ ክርስትና ግን እንዲህ አይደለም፤ ለእኛ የሚመችና የሚሻል መስሎ የታየንን መንገድ የመዳን መንገድ ነው ብሎ መከተል ሳይሆን እግዚአብሔር አምላካችን እንደሰራልንና እርሱ ራሱ እንዳበጀልን በዚያ በተሰራልን መንገድ በእሺታ መጓዝ ነው፡፡ በዚያ መንገድ መጓዝ ከባድ ሆኖ ብናገኘው ግን ወደሚረዳንና ወደሚያግዘን ጸጋው በእምነት እንቀርባለን እንጂ አምላክ የሰራልንን የመዳን መንገድ ትተን የራሳችንን የመዳን መንገድ አናቆምም፡፡ 
1ኛ ቆሮ 3፣7-8 “እንግዲያስ የሚያሳድግ እግዚአብሔር እንጂ የሚተክል ቢኾን ወይም የሚያጠጣ ቢኾን አንዳች አይደለም። የሚተክልና የሚያጠጣ አንድ ናቸው፥ ነገር ግን፥ እያንዳንዱ እንደ ራሱ ድካም መጠን የራሱን ደመወዝ ይቀበላል።’’ የሚተክልም ሆነ የሚያጠጣ እግዚአብሔር ካላሳደገ በራሳቸው ምንም መለወጥ አይችሉም፡፡ የተከሉትንና ያጠጡትን የሚያሳድገው እግዚአብሔር ነውና፡፡ ሆኖም ግን የተከሉትንና ያጠጡትን እግዚአብሔር ሊያሳድግላቸው የሚችለው መጀመሪያ መትከልና ማጠጣት ሲችሉ መሆኑን አንዘነጋውም፡፡ ስለ ጸጋም ያለው እውነተኛው አስተምህሮ ይህ ነው፡፡ ያለ እግዚአብሔር ጸጋ አንድንም፣ በራሳችንም ጥረት አንዳችም ማድረግ አይቻለንም፤ ስለዚህም በጸጋው እንደገፋለን፣ በጸጋው ተደግፈን ግን እንተክላለን እናጠጣለንም፣ ጸጋው ደግሞ ያሳድግልናል፡፡ ጸጋው ያሳድግልናል ብለን መትከላችንንና ማጠጣታችንን እንተውም፣ የእኛ ድካም ያለጸጋው ከንቱ ድካም ብቻ ነውና፡፡ ጸጋውን ብቻ ታምነን ደግሞ መትከላችንንና ማጠጣታችንን እንተውም፡፡ እያንዳንዱ እንደ ራሱ ድካም መጠን የራሱን ደመወዝ ይቀበላል።’’ እንደተባለ ለመትከልና ለማጠጣት እንደ ደከምንበት መጠንና ልክ እንደ ጸጋው መጠን እርሱ ለእያንዳንዳችን ብድራታችንን ይከፍለናል፡፡ ጸጋው የነጻ ስጦታው ቢሆንም በጸጋው ተደግፈው ለጸጋው እንደሚገባ መኖር ያልቻሉ ጸጋው ብቻውን ሊያድናቸው አይችልም፡፡ ያለጸጋውም ደግሞ በጥረታቸውና በድካማቸው እንደሚድኑ የሚያስቡም ያለጸጋው እርዳታ ድካማቸው ብቻውን ሊያድናቸው አይችልም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረን ይህንን ነው፡፡ መዳናችን በጸጋው እንደሆነ ቢነግረንም በጸጋው ብቻ ግን አላለም፤ በጸጋው ውስጥ ሆነን እብረን የምናደርገው ሱታፌ እንዳለም ይነግረናል፡፡ በሥራችን ብቻ እንደማንድን የሚነግረንን ያህል በጸጋውም ብቻ እንደማንድን ይነግረናል፡፡ “ነፋስን የሚጠባበቅ አይዘራም፥ ደመናንም የሚመለከት አያጭድም።’’ መክ 11፣4 እንደተባለ መዳን በጸጋው ብቻ ነው የሚል በጎውን ከማድረግና የእግዚአብሔርን ፈቃድ ከመታዘዝ ይሰንፋል፣ መዳን በበጎ ምግባርና በመንፈሳዊ ተጋድሎ ብቻ ነው የሚልም ከእግዚአብሔር ጸጋና እገዛ ስለሚርቅ ፍጻሜው ከንቱ ልፋትና ተስፋ መቁረጥ ብቻ ይሆናል፡፡ እንግዲያው ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ የትኛው ነው? መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን በጸጋው እንድንደገፍም በመንፈሳዊ ተግባራት እንድንጠመድም ነው፡፡ በጸጋው እንደገፋለን፣ በጎውን ለማድረግም እንተጋለን፡፡ በጸጋው ብቻ ወይም በመንፈሳዊ ምግባራትም ብቻ የሚል ትምህርት የለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን ስለ ሁለቱም ነው፡- ስለ ጸጋም፤ ስለ መንፈሳዊ ምግባራትም፡፡ ክርስትና እንዲህ ነው፡- መትከልና ማጠጣት፣ ከተከሉና ካጠጡ በኋላ ግን የሚያሳድገውን እግዚአብሔርን መጠበቅ/ጸጋውን  መታመን፡፡ ስለሆነም ምንም እንኳን ምሕረት ለሮጠ ወይም ለወደደ ባይሆን ወደሚምረው እግዚአብሔር መሮጥ ግን ተገቢ ነው፡፡ እንደክማለን፣ እንሮጣለንም ምሕረቱንና ጸጋውን ግን ከእግዚአብሔር እንጠባበቃለን፤ እርሱም ሊምረንና ሊያድነን የታመነ ነው፡፡

ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ!

No comments:

Post a Comment