Wednesday, April 6, 2016

የተነሳሒው ጸሎት

 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ዱ አምላክ አሜን!
በሰማይና በምድር ከፍ ከፍ ያልህ፣ ክብርህ ከሰማያት በላይ የሆነ ታላቅነትህ በዓለሙ ሁሉ የሞላ፣ ፍጥረቱን ሁሉ የምትገዛ፣ አጋእዝትና ኃይላት፣ ሊቃናትና መኳንንት፣ መናብርትና ስልጣናት በፍርሃት የሚገዙልህ፣ ፍጥረትን ሁሉ ፈጥረህ የምትገዛ፣ ሁሉን የያዝህ፣ ሁሉን የምታውቅ፣ ሁሉን የምታደርግ፣ ሁሉን የምታኖር አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ሆይ ከምስጋና ሁሉ በሚበልጥ ምስጋና አንተን አመሰግናለሁ፣ ከክብርም ሁሉ በሚበልጥ ክብር አንተን ብቻ አከብራለሁ፣ ከከፍታም ሁሉ በሚበልጥ ከፍታ አንተን ብቻ ከፍ በል እላለሁ፡፡ እንደ ሥራዬስ ከፊትህ ለመቆም የተገባሁ አይደለሁም፣ ለቅጣትና ለሞት፣ ለጥፋትም የተገባሁ ነኝ እንጂ፡፡ አባት ሆይ አንተ ሰው እንደሚያውቀኝ አይደለም የምታውቀኝ፣ አንተ ነውሬን ሁሉ ታውቃለህና፡፡ ከሰዎች ተሸሽጌ፣ ጨለማን ተገን አድርጌ፣ መዝጊያን ዘግቼ፣ ልብስ ተከናንቤ የበደልኩትን በደልና የፈጸምኩትን ርኩሰቴንና ነገሬን ሁሉ አይተሃልና ከፊትህ አልተሰወርኩም፡፡
የዘላላም አምላክ ሆይ ከፊትህ ስቆም እጅግ እየፈራሁና እየተንቀጠቀጥሁ ነው፡፡ ተጥዬ ከነበርኩበት አመድና ትቢያ ላይ አንስተህ ለታላቅ ክብር፣ ለጸጋ ጠርተኸኝ ነበር፡፡ የቀደመ ክፋቴንና በደሌን ረስተህ እንደ እጆቼ ሥራ ሳትከፍለኝ ብዙዎች ሲፈርዱብኝ አንተ ግን ሳትፈርድብኝ በፍቅር ተቀብለህ ዳግም አትበድል ብለህ በይቅርታ አልፈኸኝ ነበር፡፡ ጌታ ሆይ እኔ ግን ለሠጠኸኝ ክብርለጸጋህ መታመን አቅቶኝ ዳግመኛ ሳጠፋ ተገኘሁ፡፡ ቃልህን ተላልፌ እንደ ቀድሞው በኃጢአት ዳግመኛ ወደቅሁ፡፡ በፊትህ ቅንነትና በጎነት አልተገኘብኝም፡፡ በፊትህ ብዙ ክፋትን አድርጌያለሁና፡፡ ከየት አምጥተህ የት እንዳሰቀመጥከኝ ሳስብየሰጠኸኝን፣ ያደረክልኝን ነገር ሳስተውል እራሴን ክፉኛ እረግመዋለሁ፡፡ እኔን ፍለጋ የተጓዝክበትን መንገድ ባስታወስሁ ቁጥር ደግሞ ውስጤ በሐዘን ይደማል፡፡ አንዳች በጎ ነገር ሳታገኝብኝ፣ ምንም ላልረባህና ላልጠቅምህ ከልዑል ቦታ ከዙፋንህ ወርደህ እራስህን የምታስጠጋበት አጥተህ በበረት ስታድር፣ እንደ ድሀ በግርግም ስትተኛ፣ በአንተ ድህነት እኔን ባለጠጋ ልታደርገኝ ድሀ ሆነህ የምትለብሰው ስታጣ፣ በጨርቅ ስትጠቀለል፣… ይህን ሁሉ ሳስብ እራሴን እጠላለሁ፡፡ እንደሸክላ በእጅህ የሠራኸውን ሰውነቴን ተዋሕደህ፣ ዝምድናዬ እንዳይርቅህ፣ ከእኔ መዛመድን ፈልገህ፣ የአዳምን ሥጋና ሰውነቱን ገንዘብ አድርገህ ዝቅ ብለህ ስትታይ፣ በትሕትናህ በዓለም ስትገለጥ፣ ጌታ ሆይ አንድም ሰውአንተን በጎ አሳብ አለማወቁ፣ ሊያውቅህም አለመፍቀዱ በእጅጉ የሚያሳዝን ነገር ነው፡፡ እኔ እራሴ አንተን አለማወቄ፣ አውቄህ ለፈቃድህ አለመገዛቴ፣ ለቃልህ አለመታዘዜ ለምን እንደሆነ አላውቅም፡፡ ለሞትክልኝ ላንተ በሞትህ ልመስልህ ባይቻለኝ መኖር እንኳን አለመቻሌን ሳስብ ራሴን እንቀዋለሁ፣ ማንነቴን እታዘበዋለሁ፡፡
የሰው ልጆችን ዝምድና ሽተህ በእኛ ሥጋ ስትገለጥ እጅግ አድርገን ናቅንህ፣ በኀጢአታችን ሳትፈርድ ብትቀበለን፣ ክፋታችንንና በደላችንን ብትተውልን የኀጢአተኞች፣ የቀራጮችና የአመንዝሮች ወዳጅ ብለን ተቃወምንህ፡፡ በታላቅነትህ፣ በእጆችህ ሥራ እያስደነቅህ፣ በኃይለኝነትህ ደዌአችንንና ሕማማችንን ሁሉ በማራቅህ፣ የታመሙትን ፈውሰህ፣ የሞቱትን በማስነሳትህ በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል ብለን አማንህ፡፡ ጌታ ሆይ አንተ ግን እስከዚህ ድረስ እንደታገስኸን ነው፡፡ በአንድ ሰውስ እንኳን ለመፍረድ አለመፈለግህ በእጅጉ ያስደንቀኛል፡፡ መምህራችን አንተ የእኛን የተማሪዎችህን እግር ልታጥብ ዝቅ ብለህ፣ የቆሸሹ እግሮቻችንን ስትይዝ፣ ሠማይና ምድርን በሠራህባቸው እጆችህ እግሮቻችንን ስትነካ፣ ንፁሓን እጆችህ ጨብጠውን ስመለከት፣ ማበሻ ጨርቅ ወስደህ እግራችንን አጥበህ ስታደርቅልን ይህ ሁሉ ትሕትናና ፍለጋህ ያስለቅሰኛል፡፡ ፍቅርህ ይህን ያህል መሆኑ፣ የእኔ ልብ ግን ዛሬም ይበልጥ መጠንከሩ ያሰጨንቀኛል፡፡ ብዙ ነገር ይቆጨኛል፣ ለፍቅርህ አለመታመኔ፣ ፍቅርህን መበደሌ ይጸጽተኛል፡፡ እንዲሁ ያለ ዋጋ እኔን መውደድህ፣ ብዙ ዘመንና ብዙ ጊዜ ለእኔ ይቅርታና ምሕረት ማድረግህ ነገር ግን ለይቅርታህና ለፍቅርህ የሚስማማ ጥቂት  በጎ ሥራ በእኔ ሕይወት አለመኖሩ ያስጨንቀኛል፡፡
ሰንበትን ይሽራል፣ የሙሴንም ሕግ ይቃወማል፣ ለቄሣር ግብር እንዳይገባ ህዝቡን ሲያሳምፅና ሲያሳድም አይተናል፣ ቤተ መቅደሱንም አፈርሰዋለሁ ብሏል ብለን በሐሰት ለምን እንደከሰስንህ ባሰብኩ ቁጥር በገዛ ስራዬ ያለመጠን እጸጸታለሁ፡፡ በእውነት የምትፈርድ አንተ በጲላጦስ ፊት በአደባባይ ለፍርድ መቆምህ ሲታሰበኝ፣ ጲላጦስ ሲመረምርህና ሲያሳጣህ ምንም ልትመልስለት ሳትወድ ዝምታን እንደመረጥህ፣ ጲላጦስ ወደ ሄሮድስ ሲልክህ፣ በሄሮድስ ፊት ደግሞ ዳግመኛ ለፍርድ ስትቆም፣ ሄሮድስ በንቀት ሲመለከትህ፣ ለመዘበት ጌጠኛ ልብስ ሲያለብስህ በትዕግሥት ችለህ ዝም ማለትህን ሳስበው ይደንቀኛል፡፡ ሄሮድስ ተሳልቆ ዳግመኛ ወደ ጲላጦስ ሲልክህ፣ በቁጣም ሲጎትቱህ አንተ ግን በይቅርታ ትከተላቸው ነበር፡፡ ሄሮድስ ሲያስገርፍህ በእሺታ ጀርባህን ለገራፊዎች መስጠትህ ዛሬም ድረስ ይገርመኛል፡፡  ጌታዬ ሆይ መልክህ ጠፍቶ ጀርባህ እስከሚላጥ ድረስ የተገረፍከውና የቆሰልከው  ለእኔ እንደሆነ አውቄያለሁ፡፡ መስቀል ተሸክመህ የቀራንዮን ተራራ በትዕግሥት የወጣኸው፣ ብዙ ጊዜ ወድቀህ በእርጥብ እንጨት የተቀጠቀጥከው ለእኔ ፍቅር እንደሆነ ገብቶኛል፡፡ እጆችህና እግሮችህ በችንካር የተመቱት፣ እንደ ብራና በመስቀል ላይ ተወጥረህ ደምህን ያፈሰስከው፣ ልብሶችህን ተገፈህ እርቃንህን የሆንከው ለእኔ ስትል፣ እኔን ለማልበስ እንደሆነ ተረድቻለሁ፡፡ ሆምጣጤና ሐሞት የጠጣኸው፣ ጎንህን በጦር የተወጋኸው . . . አዎን ጌታዬ ሆይ ይህ ሁሉ ስለእኔ ነው፣ ስለፍቅርህና መውደድህ ብለህ ነው፣ እምናለሁ ጌታዬ እንዲህ የደከምክልኝ ወደ ቀድሞ ክብሬ ልትመልሰኝ ነው፡፡ በሐዲስ ተፈጥሮ ልታከብረኝ፣ ርስት፣ መንግሥት ልታወርሰኝ እንደሆነም ተገንዝቤያለሁ፡፡ ይህን በሚያኽል ፍቅር ወደኸኝ፣ በእንዲህ ዓይነት መስዋዕትነት ፈለግኸኝ፣ እኔ ግን ዛሬም በኀጢአት መኖሬ፣ ካንተ ርቄ ውዬ ማደሬ በእጅጉ የሚገርም ነው፡፡ ሆኖም ግን ጌታዬ ሆይ ለእኔ ያለህ ፍቅር ዛሬም ያው መሆኑ፣ አሁንም ይቅር ልትለኝ መፍቀድህ ይበልጥ እንድወድህ አደረገኝ፡፡ እያወቅሁ ባጠፋም፣ ብዙ ጊዜ ደጋግሜ ብበደልም መልስህ ‘‘አልፈርድብህም ደግመህ ኀጢአትን አታድርግ፡፡’’ የሚል አንድ ብቻ ነው፡፡ ቃልህን ሰምቼ፣ ደግሜ ስበድልህም ቃልህ ያው ነው፣ አይለወጥም፡፡ ‘‘አልፈርድብህም ደግመህ ኀጢአትን አታድርግ፡፡’’ ትለኛለህ፡፡ እግዚአብሔር ሆይ ከእንግዲህ ግን ሁለተኛ . . . ሁለተኛ አላጠፋም፡፡ የዛሬን ብቻ ይቅር በለኝ እንጂ ዳግመኛ አልበድልህም፡፡ እኔን የወደድክበት ፍቅርህ እንድወድህ አድርጎኛል፡፡ ለምንም ላልጠቅም፣ ምንም ላልሠራልህ፣ የማልረባና የማልበጅ  እኔን ‘‘ፈትታችሁ አምጡልኝ ለጌታው ያስፈልጋል’’ (ማቴ 213) ብለህ ስለላክህብኝ በጣም ተገርሜያለሁ፡፡ እኔ ላንተ የማስፈልግ ሆኜ መገኘቴ በእጅጉ አስደንቆኛል፡፡ በፊትህ በጎነት እንዳላደረግሁ እያወቅሁት የሚረባና የሚጠቅም አድርግህ እንደቆጠርከኝ ሳስብ አሁንም ድረስ እገረማለሁ፣ ለኅሊናዬ የረቀቀብኝን በጎነትህን፣ ብዙ ፍቅርህን፣ ታላቁን መውደድህን፣ የተቀበለኝ ይቅርታህን፣ በደሌን የተውክበትን ቅንነትህንና ተቀባይነትህን፣ ያለፍርድ የጠበቀኝን ትዕግሥትህን፣ ያለቅጣት የተወኝ አባትነትህን፣ ያለመጸጸት የሆነልኝን ይቅርታህን . . . ዝም ብዬ አስበዋለሁ . . . አስበዋለሁ . . . አሁንም ዝም ብዬ አስበዋለሁ . . . ካሰብኩትም በኋላ አንደገና እያሰብሁ እገረማለሁ፣ እደነቃለሁ፣ ቃላት በማይገልጹት ጥልቅ ስሜት ውስጥ እሰጥማለሁ፣ አስቤው ይገባኝና እረዳው ዘንድ ሐሳቤ ታናሽ ይሆንብኛል፣ በቃላት እገልጸው ዘንድ ስሞክር የማውቃቸውን ቃላት ሁሉ ሰነፎች ሆነው አገኛቸዋለሁ፡፡ የበጎነቴ አምላክ ሆይ ስለዚህ ነገር ዝም ከማለት በቀር ምን ማለት እችላለሁ? . . . አዎን ሐሳቤ እጅግ ታናሽ ነው፣ ብዙ ቃላትም እንኳን ቢሆኑ ታናሽ ናቸው፣ እናም በቃ ዝም ብቻ እላለሁ፣ በዝምታዬ ውስጥ ምሥጢር የሆነብኝን ይህን ታላቅ ነገር እፈልጋለሁ፣ በዝምታዬ ውስጥ የምሰማውን ላደምጥ ወደ አንተ ዘንበል እላለሁ፡፡
አቤቱ ጌታዬ ሆይ የማልጠቅምና የማልረባ ሆኜ ሳለሁ እንደሚረባና እንደሚጠቅም አድርገህ ስለቆጠርከኝ፣ ወደ አንተ መምጣቴን ስለፈለግኸው፣ በፊትህ መሆኔን ስለምትወድ፣ መመለሴንም ስለምትናፍቅ ከዚህ ፍቅር ፈቀቅ እል ዘንድ እንዴት ይቻለኛል? . . . ጌታ ሆይ  አንተ ስለተናገርህ፣  አንተ የምትፈልገኝ ስለሆነ፣ የትናንት ክፋቴን ስለረሳህልኝ ዳግም ላልመለስ፣ ወደመጣሁበት ላላይ፣ ከፊትህም ላልጠፋ ቃል ገብቼ አንተን ብቻ እያየሁ፣ አንተን ብቻ እየሰማሁ ካንተ ጋር ውዬ አድራለሁ፡፡ ጌታ ሆይ እኔ ግን ከፊትህ ለመቆም፣ በአንተም ዘንድ ውሎ ለማደር ሰውነቴን እንደሚገባ ባልቆጥረውም ምሕረት ስላደረግኽልኝ፣ ዳግመኛም ዕድል ስለሰጠኸኝ . . . ወደ ቀደመ መንገዴ ላልመለስ፣ የተውኩትን ነገር ላላደረግ፣ የጣልኩትንም ላላነሳ፣ ወደወጣሁበት ላልመለከት ቃል እገባለሁ፡፡ ስላደረግህልኝ በጎነት፣ ስለበዛልኝ ምሕረትህ እያመሰገንኩህ፣ እኔን የወደድክበትን ፍቅር እያሰብኩ፣ አስከምመለስ የጠበቀኝን ትዕግሥትህን እያሰላሰልሁ፣ ስለመመለሴ መደሰትህን እያደነቅሁ፣ እኔን ፍለጋ የተጓዝክበትን መንገድ እያስታወስሁ እስከ ዘመኔ መጨረሻ አብሬህ እኖራለሁ፡፡

2 comments:

  1. እግዚአብሔር አገልግሎታችሁን ይባርክላችሁ፡፡ በርቱ ከዚህ የበለጠ ሥራ እንጠብቃለን፡፡

    ReplyDelete
  2. አለን ከእናንተ ጋር ነን፡፡ እየተከተልናችሁ ስለሆነ በርቱ፡፡ እየተከተልናችሁ መሆኑን እረስታችሁ ሥራችሁን ከመስራት ወደ ኋላ እንዳትሉ፡፡ ገና ብዙ ነገር ነው ከእናንተ የምንጠብቀው፡፡

    ReplyDelete